Saturday, 27 February 2021 00:00

የአድዋ ድል ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የሥነ ልቡና ልዕልና የተገኘ ነው።

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ
‹‹ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም።… በአፍሪካ በኩል ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሣቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምጽና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል። የኛ ዓለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። አሁን የኹሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው…››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ ገጽ ፻፶፱)። ይህንን የተናገረው ቤርክሊይ የተባለ ጸሐፊ ነው። (Berkeley, George; The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik)። ከአድዋ ጦርነት በኋላ ይህና እንዲህ ዓይነቱ የአድናቆት ምስክርነት ከዓለም ዙሪያ ለኢትዮጵያውያን መበርከቱን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። የአድዋ ድል የዓለም ፖለቲካዊ አካሔድ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው። እንዲያውም የዚያን ዘመኑን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ብሎ መክፈልና ማጥናት ይቻላል። በዓለም ላይ ከታዩ እጅግ አስገራሚና ወሳኝ ክስተቶች እንደ አንዱም መመደብ የሚችል ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በጊዜው አሉ የተባሉትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀችና ከጊዜው ኃያላን አንዷ የሆነች አንዲት አውሮፓዊት ሥልጡን ሀገር፣ እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣኔ በሌላትና እንደ አውሮፓውያኑ የምታመርተው ቀርቶ የምትገዛውና በእርዳታ የምታገኘው የጦር መሣሪያ እንኳን በቁጥር ውሱንና እጅግ ኋላ ቀር በሆነ፣ ዘመናዊ የጦርነት ስልትን እንደ ሌሎቹ ያልተራቀቀችበት፣ ጦርና ጋሻን በያዙ ዜጎቿ የምትዋጋ እንጂ የወታደሮቿ ቍጥር ጥቂት በሆነባት፣ በአንዲት አፍሪካዊት ሀገር መሸነፏ ነበር።

 

ጦርነቱ በሁለት አውሮፓውያን ወይም በሁለት አፍሪካውያን ሀገራት መካከል የተደረገ ቢሆን ኖሮ፡ ጥቂትም ቢሆን የኃይል መመጣጠን ስለሚኖር ይህን ያክል አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን በጉልበተኞች ጽንፍ ባለች በአንዲት ሀገርና በምስኪኖች ጽንፍ ባለች በሌላ ሀገር ምክንያት የተደረገ በመሆኑና ውጤቱም ሥጋ ለባሽ ከሚጠብቀው አመክንዮአዊ ውጤት እጅግ የተለየ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ ጳውሎስ ኞኞና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ገለጹት ‹‹ሁሉም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምታሸንፋት›› ያስቡ የነበረው ይህን አለመመጣጠን በሰውኛ መነጽር በማየት ነበር። ታዲያ ድሉ እንዴት ተገኘ?

የድሉ ዋና መሠረት የሥነ ልቡናና አስተሳሰብ ሚዛን ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውና በውጊያ አቅማቸው ክፉኛ ተማምነውና መተማመናቸውም ወደ ትዕቢት ከፍ ብሎ ነበር። ‹‹…በቅርብ ቀን ምኒልክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…›› ይል የነበረው የኢጣሊያ የጦር መሪ፡ የጄኔራል ባራቲዬሪ ንግግርም ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ሕዝቡም ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ‹‹ድል አድራጊው›› እያሉ እርሱን መጥራታቸው የዚህ ሌላው ማሳያ ነበር። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፷፫)።

በኢትዮጵያውያን በኩል ምንም እንኳን የኢጣሊያ ዐቅም እጅግ እንደሚልቅ ቢረዱትም፡ ከንጉሡ አዋጅ ጀምሮ ካላቸው የጦር ቁስ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መተማመናቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡-

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም።

‹‹አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቶአል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለሚሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፮-፻፶፱)።

በዚህ አዋጅ ላይ ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ የሚያኖረው እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ ርትዕንና ፍትሕን እስከ ያዙ ድረስ በእግዚአብሔር እርዳታ አለመጠራጠር፣ ጠላትን በጠላትነት የመፈረጁ ነገር የመጣው ሀገር የሚያጠፋና ሃይማኖት የሚለውጥ በመሆኑ እንደ ሆነ፣ በእግዚአብሔር ረዳትነት እንደሚዋጉት፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በውጊያና በጉልበት ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖት ሲባል በማዘንም ማገዝ እንደሚቻል ማመን እንደሚገባ ተገልጾአል። ጦርነትን በውጊያ ብቻ ሳይሆን ‹‹የሚያዝኑ ብፁዐን ናቸው›› እንደ ተባለ በማዘንና ወደ እግዚአብሔር በማልቀስ ድል መንሣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ምን ዓይነት መንፈሳዊ የሥነ ልቡና ልዕልና ነው? (ማቴ. ፭፡፬)። ኢጣሊያኖች የጎደላቸው ይህ ዓይነቱ ‹‹መሣሪያ›› ነበር።

የኢጣሊያ መልእክተኞች ሁሉ ለጦርነት መቋመጣቸውንና በጉልበታቸው ክፉኛ መመካታቸውን ያዩት እቴጌ ጣይቱም ‹‹የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ይህን ግፍ ተመልከት። በመድፋቸውና በጠብ መንጃቸው ተመክተው የፈቀዳቸውን ተናገሩ፤ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን አላወቁም። እኛም በክርስቶስ ኃይል አንፈራቸውም›› ማለታቸው ያነሣነውን ጉዳይ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የአድዋ ጦርነት እጅግ የተለያየ የኑሮና የፍልስፍና ሐሳብ (Paradigm) ባላቸው ሁለት ተቃራኒ ሀገራት መካከል የተደረገ ጦርነት ነው። አንደኛዋ ሀገር ቅኝ ገዢና ወራሪ፣ ብዙ ሀገራትን አስቀድማም የወረረች፣ አሉ ከተባሉ ሥልጡን ሀገራት አንዷ፣ ባለኝ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የወታደር ኃይል አሸንፋለሁ ብላ የምታስብና የምትወጋትን ሀገር እጅግ የናቀች፣ ጥቁር የነጭ ባሪያ መሆንና በነጭ ሥር መተዳደር አለበት ብላ የምታምን፣ የሌላ ሀገርን ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ የመጣች፣ የወታደሮቿ የመጨረሻ ግብ ቅኝ ገዝተው ጀግና ተብለው መሞገስና የተሻለ ሀብትንና ዝናን እንደ ሀገርም እንደ ግልም ማካበት የሆነባት…ወዘተ ነበረች። ሁለተኛዋ ደግሞ በተቃራኒው ቅኝ ገዝታም ተገዝታም የማታውቅ፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብንም ‹አግባብ አይደለም› ብላ የምትጠየፍ፣ ከሥልጣኔ አንጻር እጅግ ኋላ ቀር የምትባል፣ ከጉልበት ይልቅ በእግዚአብሔር የሚያምኑ ዜጎች የሞሉባትና የቱንም ሀገር ስለ ድህነቱ የማትንቅ፡ ስለ ብልጽግናውም ክባ የማትፈራ፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረና እኩል እንጂ ማንም የማንም ባሪያ እንዳልሆነ የምታምን፣ የሌላን የማትነካ የራሷንም የማታስነካ፣ የዜጎቿ (የወታደሮቿ) የመጨረሻ ግብ ሀገርንና ሃይማኖትን ማዳንና ለዚህም ሲባል በመሠዋት ሰማያዊ ክብርን ማግኘት … ወዘተ ነበር።

በዚህ የእሳቤ መሠረት የተነሣ ኢትዮጵያውያን ወኔያቸው ልዩ ነበር። ይህ ወኔ ‹‹የቆምኩትና የምዋጋው ለእውነት ነው፤ ምድራውያን ብቻ ሳይሆኑ እግዚአብሔርና በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ሁሉ አብረውኝ አሉ፤ ብሞት እንኳን ሞቴ የከበረ ነው›› የሚል ግዙፍ አስተሳሰብ የፈጠረው ፍርሃትን የሚያርቅ ወኔ ነው። በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች ወደሚሞቱበት ቦታ ሲወሰዱ እንደ ሌሎች ከመፍራትና ከመለማመጥ ይልቅ በፈገግታና ወደ ሰርጉ እንደሚሔድ ሙሽራ በደስታ እንደ ነበረው ሁሉ፡ ኢትዮጵያውያንም ይህ ዓይነቱ አሳብ በልባቸው የተሰነቀ ነበር። ስለዚህ ምንም መሣሪያን ያልያዙት፣ እንኳን መሣሪያን ሊይዙ ይቅርና ለእግራቸው ጫማ ያላደረጉትም ቢሆኑ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጸጉሩ የታጠቀ የኢጣልያ ወታደር ፊት ሲቆሙ በጥብዐትና በጀግንነት ነበር።

በአንጻሩ ደግሞ የኢጣልያ ተዋጊዎች የኃይል ሚዛኑ በጥቂቱም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያውያን ባደላበት ጊዜ ሁሉ ፍርሃት የሚወራቸው ዓይነት ነበሩ። የአምባላጌን በመሰሉት ውጊያዎች ላይ የኢትዮጵያውያኑን ድል ካዩ በኋላ አስጨናቂ የፍርሃት ዝግጅትን ያደርጉ የነበረው ለዚሁ ነበር። የመቀሌው ምሽግ እዚህ ላይ ሁነኛ ማስረጃ ይሆነናል፤

ጳውሎስ ኞኞ (፻፸፪-፻፸፭) እንደ ተረከው በመቀሌው ምሽግ የኢጣሊያ ወታደሮች በቅድሚያ ፫ ሜትር ስፋት ያለው ግንብ ገነቡ። ይህ አልበቃ ብሏቸው በ፴ ሜትር ውስጥ በጣም የሾሉ ከፍታቸው ፴ ሳ.ሜ. የሆኑና አንዱ ካንዱ በ፳ ሳ.ሜ. የሚርቁ እንጨቶችን በብዛት ቸከሉ። ኢትዮጵያውያኑ ግር ብለው ሲመጡ እግረኞቹም ፈረሰኞቹም በነዚህ እንጨቶች ላይ እየወደቁ ተሰክተውባቸው እንዲሞቱ ነበር። ይህም አልበቃቸውም፤ ከዚያ ቀጥሎ እሾኻማ ሽቦ እያድበለበሉ አስቀመጡ። ይህም ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አያሾልክም›› የተባለለት ነበር። አሁንም ፍርሃቱ ስላልለቀቃቸው ጠርሙስ ሰብረው ነሰነሱ። ይህም በባዶ እግራቸው የሚመጡ የኢትዮጵያውያንን እግር ሸረካክቶ ለማስቀረት ነበር። ለመሞት አስቀድመው የተዘጋጁት አባቶቻችን ግን ታንክና ተዋጊ ቆራርጦ ባይኖራቸውም፡ ይህን ሁሉ ያልፉ ዘንድ በሃይማኖት ጥብዐት የተቃኘው ወኔያቸው በቂ ነበር። በባዶ እግራቸው በጠርሙስ ላይ ለመራመድ፣ ስስ ልብስ በሸፈነው ገላቸውም የተጠቀለለ ሽቦን ለመሻገር አላመነቱም። ግዙፉን ምሽግ እግዚአብሔርን ይዘው ሰበሩት።

ይህ የኢትዮጵያውያኑ ወኔ ያስገረመው የኢጣሊያው የጦር መሪ የነበረው ጄኔራል ባራቲዬሪ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

‹‹እኛ የሠለጠነው ዓለም ሥልጡን ወታደሮች ምንም አያውቁም ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ። አበሾች ለባሩድና ጥይት ይሳሳሉ። የሚገድሉ ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም። ለዚያውም ቢሆን ፲ እና ፲፭ እርምጃ ያህል ቀርበው ባንድ ጥይት ደራርበው መግደል ይፈልጋሉ። ያለዚያ ተደበላልቀው በጎራዴ መምታት ይመርጣሉ እንጂ ጥይት ማበላሸት አይወዱም። ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለሚያባክነው ለሠለጠነው አገር ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው። ለምሳሌ ደጀን የነበረው የመድፈኛው አዛዥ ካፒቴን ፍራንዚኒ መድፎቹን ይዞ ከጦር ሜዳ እንዲገባ ታዘዘ። ፴ ኪ.ሜ. ያህል ተጉዞ ከጦሩ ሜዳ ገባ። ቦታውን አመቻችቶ አንድ የመድፍ ጥይት ገና እንዳስተኮሰ ተገደለ። ይህም ሊሆን የቻለው ያቺን የመድፍ ጥይት ድምጽ የሰሙ ኢትዮጵያውያን በንዴት ተሞልተው በብዛት ሆነው ስለ ወረሩት ነው። የተመካንባቸው ደጀን የነበሩት መድፎቻችንም ካንድ ጥይት ተኩስ በኋላ ተማረኩ…››።

ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ በሚል መጽሐፋቸው እንደ ገለጹትም ‹‹…ሠራዊቱ ቀለብ ሊያመጣ የሔደው፣ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሊስም የሔደው ኹለት እጁ ነው እንጂ አንድ እጁ ለጦር አልደረሰም። የተኩሱን መድመቅ በሰማ ጊዜ ሠራዊቱ ተሰልፎ ተነሣ። አጤ ምኒልክም ከበቅሎ ወጥተው ወደሱ መንገድ ጀመሩ። ሰልፉ ግን አልተገናኘም። በየፊቱ ክምር እንዳየ ዝንጀሮ ወደ ጦሩ ወደ መድፉ ይሮጥ ነበር።… መድፉ ይመታኛል፣ ነፍጡም ይጥለኛል እሞታለሁ ብሎ ልቡ አልፈራበትም። …የቈሰለውም ሰው ‹አልጋው ይቁም እንጂ ኋላ ስትመለስ ታነሣኛለህ፣ በመሀይም ቃሌ ገዝቼሃለሁ› ይለው ነበር። ጥይትም ያለቀበት እንደ ሆነ የቈሰለውን ሰው ከወገቡ ዝናሩን እየፈታ እያባረረ ወደ ፊት ይተኩስ ነበር። ሰውም ከመንገድ ርዝመት ከተኩሱ ብዛት የተነሣ ደክሞት የተቀመጠ እንደ ሆነ ‹የምኒልክ ወሮታ፣ የጮማው የጠጁ ይህ ነውን?› እየተባባለ እንደ ገና እየተነሣ ይዋጋ ነበር››።

በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነትን ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ከጦርነቱ በፊት ጦርነቱ እንዳይካሔድ ያደረጉት ጥረትና ከጦርነቱ በኋላም ያሳዩት ጠባይ ከፍርሐትም ከተዐብዮም የራቀና ክርስቲያናዊነትን የተሞላ ነበር። የዐፄ ዮሐንስ ልጅ የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአዲ አምባይ የጦር ሰፈር ለጣልያኑ ንጉሥ አስቀድመው ‹‹ለታላቁና ለተከበሩ ንጉሥ ኡምቤርቶ፤ በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን በመካከላችን በመግባቱ ክርስቲያን የሆንን ሕዝቦች እርስ በርሳችን እንድንፋጅ ሆነ፤ ባለፈው ጊዜ የደረሰው ሁሉ የሰይጣን ሥራ ነው። ሰላምን ስለምንፈልግ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ ሰው ይላኩ።›› በማለት መልእክትን መላካቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም ታዲያ ይህ ትሕትና በትዕቢትና በትምክህት ሳይቀየር ንጉሡ ‹‹በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አረግሁአቸው ብዬ ደስ አይለኝም…›› ማለታቸው ይህንን የመንፈሳዊ ልዕልና ያሳያል። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፱)።

‹‹እኔ ሴት ነኝ። ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ…›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፵፰) ብለው የተናገሩት የእቴጌ ጣይቱ ታዋቂ ንግግርም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሲተረጉም ‹‹እግዚአብሔር ከሌለበት ሰላም እግዚአብሔር ያለበት ጦርነት ይሻላል›› ብሎ ከተናገረው ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። (ሮሜ.፲፪፥፲፰)። በእውነትም ሀገርና ሃይማኖትን ከሚያሳጣ ‹ሰላም›ስ ጦርነት ይሻላል።

በርግጥ በአድዋ ድል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ በብዙ መልኩ የሚነገር ነው። በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውንና ሕዝቡን የሚመሩ አባቶችን ሁሉ አዝምታለች፤ ማዝመቷም በጸሎት እንዲያበረቱ ነው። ይህም ለዘማቹ ሁሉ እጅግ የሚያበረታታ ተግባር ነበር። ከዘመቱት መካከል ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ፣ እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የደብረ ሊባኖስ ፀባቴ፣ ከእንጦጦ ማርያም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ኪዳነ ወልድ፣ ንቡረ ዕድ ተክለ ጊዮርጊስ፣ መምሬ ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ተክለ ማርያም፣ አፈ ንቡረ ዕድ ገብረ ማርያም፣ መምህር አርአያ፣ መምህር ገብረ መድኅን፣ ቀኝ ጌታ ቢሆን…ወዘተ ካህናት፣ ሊቃውንት (ከቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ ከሆለታ ኪዳነ ምሕረት….) ይገኙበታል። ሕዝቡ እግዚአብሔር አብሮት እንዳለ እንዲያስብና በዘመቻ መንገዱ ሁሉ የሥነ ልቡናው ብርታት እንዳይሸረሸርም የንዋያተ ቅድሳት አብሮ መዝመት አስፈላጊ ነበር። ከታቦታት-- የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም፣ ከሸዋ የግንባርዎ ማርያም፣ የበር ግቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የአክሱም ማርያምና መድኃኔዓለም…ወዘተ የዘመቱ ሲሆን መስቀሎች፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ ቃጭል፣ ጥላዎች፣ ድባቦች፣ ሥዕላት - በተለይም የግንባርዎ ማርያም ‹አምለሱ› ሥዕለ ማርያም …ወዘተ ዘምተዋል። (በአድዋ ጦርነትና ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ፣ ገጽ ፳፮-፳፰)::

በርግጥ ታቦትና ንዋያተ ቅዱሳትን ይዞ መዝመት ብቻ ለድል አያበቃም፤ እግዚአብሔርን በማያስቆጣ መንገድ መጓዝና ከእውነትና ከፍትሕ ጎን መሰለፍ እንጂ። ቤተ ክርስቲያንም ንዋያተ ቅድሳትንና የሃይማኖት አባቶችን ከማዝመትም በላይ የምእመናንን ሥነ ልቡና የገነባችበት መንገድ ለጦርነቱ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ምናልባትም ያ ባይኖር ድሉም አይኖርም ነበር። ብዙ ጸሐፊዎችም ድሉን ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያያይዙት ለዚሁ ነው።

አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ  የተባሉ ሊቅ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ-ነው መልኳ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው የአድዋውን ድል መሠረት እንደሚከተለው ገልጠዋል።

‹‹… ምኒልክን ለአድዋው ድል ያበቃቸው 

አንዱም ፣ ኦርቶዶክሳዊ እምነታቸውና የልብ ጸሎታቸው ነው።›› (ገጽ፣፷፭)

ዳንኤል ሮኘስ የተባለ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ ‹‹የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቋታላችሁን?›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው መጣጥፍ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል። 

“ወራሪዎች ምድርዋን የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤

ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴ መሣሪያዋ ሆኖ በመገኘቱ በነፃነት ተመልሳ ተገኝታለች››

የአድዋን ድል በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ጋር ያያያዙት ሌሎችም ኢትዮጵያን በአፍሪካ እንደምትገኝ ኢየሩሳሌም አድርገው መቍጠር ጀምረው ነበር። ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹ THE BATTLE OF ADWA:-African victory in the age of Empire›› በተሰኘው ታሪካዊ መጽሐፋችው ‹‹የዓድዋን ድል ተከትሎ በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ዝርዋን አፍሪካውያን የዓድዋን፣ የምኒልክንና የነጻይቱን አገር ኢትዮጵያን ስም በልዩ ሁኔታ ማንሣት ጀመሩ፤ ጥቁር ሕዝቦች እንደ ታላቂቷ ጽዮናዊት ኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ጉዞ ማድረግ ጀመሩ።›› ሲሉ መግለጻቸው ለዚህ ምስክር ነው።

አንድ ጣልያናዊ ተዋጊም ‹‹በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተመላለሰ ወደ ጦርነቱ ግቡ ኢጣሊያኖችን ማርኩ እያለ ትእዛዝ ሲሰጥና ሲዋጋን የዋለ ማነው?›› ብሎ መጠየቁ እየተገለጸ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጋዥነት መገለጹም እዚህ ላይ መነሣት የሚገባው ነው። (በአድዋ ጦርነትና ድል...፣፶፫)። ይህንንም በአንድ ባለ ቅኔ፡-

‹‹ኃይል ውእቱ ዘጊዮርጊስ፣ 

አኮኑ ኵዕናት 

በላዔ ሮማዊት ነፍስ፣ 

ዘጌዴዎን ምኒልክ 

ዘአውረደ በዐውደ ሮምያ 

ጠለ ደም እምርእስ። (በአድዋ ጦርነትና ድል...፣ ፶፪)።

(የሮማዊትን ነፍስ (ሰውነት) የበላ (ድል ያደረገ) የጊዮርጊስ ኃይል እንጂ ጦር አይደለም፣የጌዴዎን ምሳሌ ምኒልክ በሮምያ አደባባይ ከራስ ላይ እስካወረደ ጠብታ ደም።) ተብሎ የተነገረ ነው።

የአድዋ ድል ብሔራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱም መነገር የሚገባው ነው። ‹ኢትዮጵያውያንን እንደ እስራኤል ዘነፍስ መቍጠርና ሀገሪቱንም ጸጋ እግዚአብሔርን የታደለችና ሀገረ እግዚአብሔር እንደ ሆነች አድርጎ ማየት፣ ሀገረ እግዚአብሔር ከሆነች ዘንድም መደፈር የለባትም በሚል እሳቤ ድንበሯን መጠበቅና በዚህም ሂደት መሠዋት የዜግነት ክብር ብቻ ሳይሆን ጽድቅም ነው ብሎ ማመን› ለኢትዮጵያውያን አዲስ እሳቤ ባይሆንም በአድዋ ድል ግን ይበልጥ ጠንክሯል፤ ከዓለም ሕዝብ መካከልም ይህንን ያመኑ እጅግ ብዙ ነበሩ። ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ  የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ በተለይ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ ‹ኢትዮጵያኒዝም› በሚል ስያሜ እንዲጀመር መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው።

ለማጠቃለል ያህል የአድዋ ድል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የመንፈሳዊ ሥነ ልቡና ብርታትና ለሀገርና ለሃይማኖት እስከ ሞት የመጋደል ወኔ የተገኘ መሆኑ ከድሉ እኩል መነገር ያለበት ነው። ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያን ወረራ በሀገረ እግዚአብሔር ላይ እንደ ተደረገ ሰይጣናዊ ጥቃት ነበር የቈጠሩት። ለዚህም ነው ድሉን እንኳን ሰይጣን ድል ከተነሣበት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር በማመሳሰል

‹‹ሞዖ ለሞት 

ሠዐሮ ለጣዖት 

ገብረ ትንሣኤ በሰንበት›› እያሉ ዳግመኛም

‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ 

ተሐፂባ በደመ ሰማዕታት››

ብለው እየዘመሩ ያከበሩት። (በአድዋ ጦረነትና ድል…፣ ፷)።

የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ሰዓታት በቀሩበት ጊዜ እንደ ተዋጊ ሳይጨነቁ፣ ሁሉን ትቶ በተጠንቀቅ ከመቆምና የነደፉትን የውጊያ ስልት ከማሰላሰል ይልቅ ‹እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይበልጣል› በሚል ታላቅ የሥነ ልቡና ዐቅም ዐፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ …ወዘተ በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እያስቀደሱ ነበር። በርግጥ ከዚህም በኋላም ንጉሡ በእርጋታቸው ጸንተው ዕለቱ ጊዮርጊስ በመሆኑ አሁንም ወደማይጕዓጕዓ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ልባዊ ጸሎትን አቅርበው ነበር። በጦርነት መጀመሪያ የመጨረሻው ሰዓት ለዚያውም ዐቅሙ እጅግ የሚገዝፍ ጠላት ከፊት ተደግኖ እንዲህ ዓይነት መረጋጋትን ያሳዩ ሌሎች ተዋጊዎች መኖራቸው እጅጉን አስገራሚ ነው። ይህ በርግጥም መንፈሳዊ ጥብዐት እንጂ ምን ይባላል?

በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፡ ተሰብስበው ሲያስቀድሱ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ቀዳሽ ነበሩ። እርሳቸውም ከቅዳሴ በኋላ ሲያስተምሩ እንዲህ አሉ፡- 

‹‹ልጆቼ ሆይ… ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነው። ኺዱ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ ሙቱ፤ እግዚአብሔር ይፍታህ››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፪፻፫)።

በእውነት የእግዚአብሔር ፍርድ በዕለቱ ተፈጸመ፤ ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።

 

Read 973 times