Saturday, 27 February 2021 00:00

ዐቃብያነ እምነት/ቀዋምያን ለቤተ ክርስቲያን

Written by  ሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ

Overview

ባለፈው ጽሑፋችን ዕቅበተ እምነትን በተመለከተ በጥቅሉ መጻፋችን ይታወሳል። ይህ ጽሑፍም ካለፈው የቀጠለ ሲኾን በተለይ ዐቃብያነ እምነት ወይም ቀዋምያን ለቤተ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ አባቶችን ሕይወትና ጽሑፋቸውን የሚዳስስ ነው።  ኹለተኛው ክፍለ ዘመን በርካታ ፈተናዎችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የጋረጠ ክፍለ ዘመን እንደ ነበር ተመልክተናል። የሮም መንግሥት በግዛቶቹ ሁሉ ክርስትናን ሕጋዊነት የሌለው አዲስ እንቅስቃሴ አድርጎ በመቍጠሩ ክርስቲያኖች እንደ ወንጀለኛና የመንግሥት ተቃዋሚ ተደርገው እንዲታዩ መንገድ ከፍቶ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አዲስ አቀራረብ ያላቸው የዕቅበተ እምነት ጽሑፎች መውጣት ጀመሩ። በዚህ ሂደት የአቴንሱ ዮስጢኖስ የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ፩. ሰማዕቱ ዮስጢኖስ /Justin Martyr (፻-፻፷፭ዓ.እ/AD.) በኹለተኛው ክፍለ ዘመን ከተነሡ ዐቃብያነ እምነት አንዱ የሆነውና በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ጥናት ስሙ በሰፊው የሚነሣው ዮስጢኖስ ነው። (Johannes Quasten, Patrology Vol. I,፻፺፮.) ጥንት የሰማርያ ክፍል በነበረችው፣ ናብሉስ (Neapolis/Nablus) ከኢአማንያን ወላጆች የተወለደ፣ እስከ ሠላሳ ዕድሜው ድረስ የተለያዩ የፍልስፍናና ሌሎችንም የዕውቀት ዘርፎችን ሲያጠና ቆይቶ በ፻፴ ዓ.እ/AD. ክርስትናን የተቀበለ፣ በመጭረሻም ታላቅ የክርስትና ጠበቃ መኾን የቻለ አባት ነው። (Cross, The Oxford Dictionary of the Christian Church, 1974, 770.)  

 

In this time also Justin, a genuine lover of the true philosophy, was still busy studying Greek learning. He too indicate this date, when in his Defense to Antonius he writes: ... (Eusebius, The History of the Church, 4:8.) ታዋቂው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ ዮስጢኖስን በዚህ መልኩ ያነሣዋል። በዚህም የግሪክ ፍልስፍና ትምህርቱንና የፍልስፍና ወዳጅነቱን፣ ብሎም ከዕቅበተ እምነት ጽሑፎቹ መካከል የኾነውን ለአንቶኒዮስ ፒዮስ የጻፈውን አቤቱታ ጨምሮ ይዘክረዋል።  

ዮስጢኖስ ፍልስፍናን በጥልቀት የተማረና ከታዋቂ ፈላስፎች ተርታ መጠራት ችሎ የነበረ፣ ክርስትናን ከተቀበለ በኋላም ለክርስትና  ጠበቃ የሆነ አባት ነው። እውነትን ፈልጎ ከማግኘት ጠንካራ ፍላጎቱ የተነሣ የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን የተማረ ሲኾን፤ ጥልቅ ተመራማሪም ነበር። 

አንድ ቀን ነገሮችን በጥልቀት በሚያሰላስልበት የተመስጦ ጊዜው በባሕር ዳርቻ ሲመላለስ ሕይወቱን የለወጡትን አንድ አረጋዊ አገኘ። አረጋዊው በዕድሜ የገፉ ኾነው ምክንያታዊና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የነበራቸው ዕውቀት አስገርሞት ነበር። ነቢያት፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተናገሯቸው ትንቢቶች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደ ተፈጸሙ፣ የሐዲስ ኪዳንና የክርስትናን ነገር አፍታተው ሲነግሩት ከግሪክ ፍልስፍና የቀደመ ዕውቀት እንዳለ ተረዳ። በክርስትና ውስጥ ያለው እውነት በፍልስፍና ውስጥ ካለው ዕውቀት እጅግ የላቀ እንደኾነም ገለጹለት። ንግግራቸውን ጨርሰው በተለዩት ጊዜ ዮስጢኖስ ራሱ በሰጣቸው ምስክርነቶች ውስጥ የሚከተሉትን ሐሳቦች አስፍሮ ነበር። 

አፍላጦናዊ ለኾነው የፍልስፍና ዘይቤ የተለየ ዝንባሌ ነበረኝ። ሌሎቹንም በሚገባ ተምሬያቸዋለሁ ብዬ አስብ ነበር። ይኹን እንጂ አረጋዊውን ሰው ካገኝኋቸው በኋላ ነገሮች ተቀየሩ። አፍላጦናዊም ኾነ የትኛውም ፍልስፍና የሰው ልጅን የሕይወት ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ እንደማይመልሱ ነገሩኝ። በማነሣቸው ነጥቦች ሁሉ የክርስትናን ምላሽ እያቀረቡ መፈናፈኛ አሳጡኝ። ከዚያች ቀን በኋላ አይቻቸው ባላውቅም እያንዳንዱ ቃላቸው በነፍሴ ውስጥ የጫረው እሳት ሲቀጣጠል ይኖራል። ለነቢያት የተለየ ፍቅር አደረብኝ፣ የክርስቶስን ሐዋርያት ቃል በነገር ሁሉ መከተል ጀመርኩ። ፈላስፋ ስለኾንኩ እያንዳንዱ ሰው በእኔ መንገድ እንዲያልፍ እመኛለሁ። ነገር ግን ከአዳኙ እውነትና ትምህርት እንዲያፈነግጡ ሳይኾን እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ ነው። እኔ የገባኝ ነገር ቢኖር ከፍልስፍና ሁሉ የላቀ እውነት በክርስትና ውስጥ አለ።” (Dialogue ፰.)  

ከዚህ ልዩ አጋጣሚ በተጨማሪ ክርስትናን እጅግ በላቀ አትኩሮት እንዲመለከት ያደረጉትን የቀደሙ ሁኔታዎችንም ያነሣ ነበር። እነዚህም ክርስቲያኖችንና ትምህርታቸውን እንዴት ባለ ንቀት ይመለከት እንደ ነበረና ኋላ ግን፤ “በሰማዕትነት ለመሞት የነበራቸውን ቁርጠኝነት፣ ፍቅራቸውንና መተባበራቸውን ስታዘብ መገረም ጀመርኩ። እንደዚህ ዓይነቱ ብቃት በቀላሉ የሚገኝ እንዳልኾነም መገንዘብ ጀመርኩ” እያለ ተናግሯል። "I myself found satisfaction in Plato's teaching, and used to hear the Christians abused, but when I found them fearless in the face of death and all tat men think terrible, it dawned on me that they could not possibly be living in wickedness and self-indulgence. ..." ( Defence ፩፥፳፱; Eusebius, The History of the Church, ፲፱፻፷፭፣፻፲፩.)

ለአረማውያን የተጻፈ (Against Pagans)

በዚህ አጠራር የሚታወቁት የዮስጢኖስ ጽሕፎች ኹለት ዓይነት መልክ ያላቸው ናቸው፡ አጠቃላይ አሕዛብን የሚነቅፍበትና በቀጥታ ለአንቶኒዮስ (፻፴፯፻፷፩ ዓ.እ/ AD.) የተጻፉ። ቀደም ሲል በአውሳብዮስ የተነሣው የዮስጢኖስ ጽሑፍ በቀጥታ የተጻፉ ለሚባሉት አብነት ይኾናል። ጽሑፉን የጻፈው ወደ ሮም ሄዶ ትምህርት ቤት ከከፈተ በኋላ ነበር። (Hammel, Handbook of Patrology, ፲፱፷፰, ፴፰.) በዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያው ክፍል እንደ ተመለከትነው፤ ገዢው አንቶንዮስ ሕዝቡ እንዲያመልከው አዝዞ ነበር። ብዙዎች በፍርሃት ትእዛዙን ተግባራዊ አድርገውም ነበር። ይህን በተመለከተ የጻፈውን አውሳብዮስ ሲጠቅስ፤ “I think it is not out of place at this point to mention Antonius who d died so recently. Everyone was frightened into worshiping him as a god, though everyone knew who he was and where he came from.” [በዚህ አጋጣሚ፤ በቅርቡ ስለሞተው አንቶንዮስ ብናገር ያለቦታው የገባ አይመስለኝም። ምንም እንኳ ሁሉም ሰው ማን እንደ ነበረና ከየት እንደ መጣ ቢያውቀውም እርሱ ግን እንደ ጣዖት ሊመለክ ፈልጎ ሰውን ሁሉ ሲያስፈራራ፣ ከዚህም የተነሣ ብዙዎች ሲፈሩ ነበር] በሚል አስቀምጦታል። 

ይህ ነገር፤ መነሻውን ፍርሃትና የተለያየ ሰብአዊ ምክንያት አድርጎ እየተለመደ መጥቶ የነበረውን የገዥዎች መመለክ በሰፊው የሚመለከት ነበር። ምክንያቱ ምንም ቢኾን በቀላሉ ሊያልፈው አልፈለገም። ነገሮች ከምን ተነሥተው ወደ የት እንደሚያድጉ መገመት/ማስላት ለአንድ የቤተ ክርስቲያን ሰው ቀዳሚው ተግባሩ መኾን አለበት። ስለዚህም ሁሉም የሚያውቁት ሰው እንደኾነ ተመሳሳይ ፍላጎት ባላቸው ተከታዮቹ ገዥዎች ፊት (ማርቆስ አውሮሊዮስ) ያለ ፍርሃት አስተማረ።

የመጀመሪያውና ክርስትናን በሚጠብቅበት ጽሑፉ፤(First Apology) ቤተ ክርስትያን የምትወነጀልባቸውን የሐሰት ውንጀላዎች እያነሣ ምላሽ ይሰጣል፣ የከሳሾችንም ሐሳብ ከንቱነት ያጋልጣል። ከመግቢያው ጀምሮ ለሮሙ ቄሣር “ከቅድመ ጥላቻ ወጥተህ የክርስቲያኖችን ጉዳይ በምክንያታዊነት ተመልከት” እያለ ይመክራል ይገሥፃል። እየተበደሉ ለሚከሰሱ ክርስቲያኖች ጥብቅና ቆሞ ይከራከራል። (Johannes Quasten, Patrology: Vol. I, ፻፺፱.)

በኹለተኛው የዕቅበተ እምነት ጽሑፉ፤ ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ እና ክርስቲያን ነን፣ በክርስቶስ አምላክነት እናምናለን በማለታቸው በሠይፍ እንዲቀሉ የተደረጉ ሰዎችን እያነሣ መንግሥቱን ይሞግታል። ክርስቲያን መኾን የተለየ ወንጀል አለመኾኑን ይልቁንም ለፍትሐዊነት ለፍቅርና ሰላም መሠረት መኾኑን እያስረዳ ይከራከራል። 

ምሥጢረ ጥምቀትና ቍርባን በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ውስጥ ለማይኖርና  የምሥጢራቱ ተካፋይ ላልኾነ ሰው ምን ያህል የጸነኑ ጉዳዮች እንደኾኑ የታወቀ ነው። ይኹን እንጂ፤ በዘመኑ ከነበሩ ተቃዋሚዎች መካከል ሳይገባቸው የሚተቹ ብዙዎች ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ ተገቢ የኾነውን ምላሽ በመስጠት በዋጋ የማይተመን አገልግሎት አበርክቷል። 

በዚህ አጋጣሚ በእኛም ሀገር በእኛው ዘመን ተመሳሳይ ነገሮች እየገጥሙ እንደኾነ ልብ ይሏል። አንዳንዶች በሕይወቱ ውስጥ ሳይኾኑ አልያም ሳይማሩና ሳይገባቸው ስለ ምሥጢራት በፖለቲካዊ ዐውድ አደባባይ ወጥተው ይናገራሉ። ዓላማቸው ወገንተኝነትን መሠረት ያደረገ ማጥላላትና በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ እንዲበረታ ብሎም ግጭትን የመቀስቀስ ቢኾንም በእነዚህ መረዳቶች ብቻ የማይታለፍ ሁሉን አቀፍ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ምላሹ በእምነት የምሥጢራትን ፋይዳ ለሚረዱት ወገኖች ብቻ ሳይኾን ከሳሾቹ ጭምር የቆሙበትን የሙያ መስክ እንዳላከበሩና እንዳልተረዱ የሚያጋልጥ መኾን ይገባዋል። 

ቤተ ክርስቲያን፤ ከሃይማኖታዊ ትምህርታቸው በተጨማሪ ቁሳውያን የሚመኩባቸውን የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች አጥንተው፣ የተደላደለ ዕውቀትና ጥበብ ይዘው የሚገኙ በርካታ ልጆች አሏት። ልዩነቱ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የማንንም የሐሳብ ድንበር ያለ ሥርዓት ጥሰው አይገቡም። ይህን ሥርዓት የሚያስከብር አገራዊ ሕግ የሚያስፈልግ ቢኾንም፤ በወረቀት የሰፈረው እንኳን ተግባራዊ ሲኾን አይታይም። ማለትም አንዱ ሲነቀፍ፣ ቤተ ክርስቲያንም ያልተገባ ስም ሲሰጣት፣ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ የተደመጡ የቤተ ክርስቲያን ድምፆች ከመጀመሪያው ጠብ አጫሪ በላይ ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላል። በዚህም በወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ውስጥ ያለውን አድሏዊነት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ምቹ ያልኾኑ ሁኔታዎች የዕቅበተ እምነት አገልግሎትን ምክንያት ኾነው የሚያስቀሩ አለመኾናቸው በትኩረት ሊታይ ይገባዋል። ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጡ ጥፋቶች በበረከቱ ቍጥር አገልግሎቱም ሊሰፋ ይገባዋል። ከዮስጢኖስ የምንማራቸው ቁምነገሮች እነዚህ ናቸው። 

* ተዋሥኦ ምስለ ትሪፎን/ከአይሁዳዊው ትሪፎን ጋር የተደረገ ውይይት/Dialogue with the Jew Trypho

ክርስትና ለአይሁድ የሚሰጣቸው ምላሾች የተመዘገቡበት ጥንታዊ ጽሑፍ ይህ የዮስጢኖስ የዕቅበተ እምነት ጽሑፍ ነው። ከዮስጢኖስ ጋር የነበረው ተወያይ የአይሁድ መምህር እንደ ነበር ይነገራል። (Eusebius, The History of the Church, ፬፥፲፰.)

ይቀጥላል!

 

Read 28 times