ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክት የጠቀሰውን እንደ መነሻ በማድረግ ከላይ የተዘረዘሩትን አስፈላጊነት እንመለከታለን። “ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ። እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል የታደሉ አሉና። ከእነርሱ ጋር አብራችሁ እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነሱ ጋር እንዳላችሁ ሁናችሁ ዐስቡ። (ዕብ. ፲፫፥፩-፫) እንዲል። በዚህ ምንባብ ፍቅር፣ እንግዳን መቀበል፣ የታሰሩትንና የተቸገሩትን ማሰብ እንደሚገባ እንረዳለን። እያንዳንዳቸውን ዘርዘር አድርገን ለመመልከት ያህል፡-
ሀ. በፍቅር መኖር
ይህ ዘመን ክፋት እንደ ጽድቅ የተቆጠረበት ዘመን ነው በሚያስብል መልኩ ፍቅር ጥፍቷል። በቅዱስ ወንጌልም “ከመዓፃ ብዛት የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች” (ማቴ.፳፬፥፲፪) ተብሎ እንደተነገረ ሰዎች ብትፋቀሩ ትኰነናላችሁ የተባሉ ያህል ፍቅርን ወደ ኋላ ጥለውታል። ይሁን እንጂ ሰዎች በዚህ ዓለም እስከ ኖሩ ድረስ እርስ በእርሳቸው ተፈቃቅረው እንዲኖሩ “ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ።” በማለት አስፈላጊነቱን ያስረዳናል።
ደግሞ ማንም የእግዚአብሔር ወዳጅ ነኝ የሚል ሁሉ የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆኑ የሚረጋገጠው ባልንጀራውን መውደድ ሲችል እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “እኛም እርስ በእርሳችን እንዋደድ፤ እግዚአብሔርንም እንውደደው፤ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና። እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል ወንድሙን ግን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፤ የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ ግን የማያያውን እግዚአብሔርን እንደምን ሊወደው ይችላል? እግዚአብሔርን እንወድደው ዘንድ ወንድማችንንም እንወድ ዘንድ ከእርሱ የተቀበልነው ትእዛዝ ይህ ነው። እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን ይወዳል።” (፩ዮሐ.፬፥፲፱-፳፩) በማለት ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ያስረዳናል።
ፍቅር ለሰው ልጅ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነና ከሁሉም እንደሚበልጥ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮህ ነሐስ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው” (፩ቆሮ. ፲፫፥፩) በማለት ካስረዳን በኋላ ሐሳቡን ሲደመድምም “አሁንም እነዚህ ሦስቱ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ፤ ከሁሉም ግን ፍቅር ይበልጣል” (፩ቆሮ. ፲፫፥፲፫) በማለት የሚያስፈልጉንና ገንዘብ ልናደርጋቸው የሚገቡን ቢኖሩም ከሚያስፈልጉን በርካታ ነገሮች ሁሉ ፍቅር የሚበልጥ መሆኑን ያስረዳናል።
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በአግባቡ ተረድቶ ለሕይወት የሚሆን ሥራ ከመሥራት ይልቅ የጥያቄ ብዛትን ብቻ የማዥጎድጎድ ልማድ የነበራቸውና በትምክሕት የተሞሉት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትኛው ሕግ እንደሚበልጥ በጠየቁት ጊዜ ፍቅር ከሁሉም እንደሚበልጥ አስረድቷቸዋል። ይህን በተመለከተ በቅዱስ ወንጌል “ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ምላሽ እንዳሳጣቸው በሰሙ ጊዜ በአንድነት ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከመካከላቸውም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ጠየቀው። መምህር ሆይ ከኦሪት ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች አለው። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው። አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደደው ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። የምትመስላት ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የምትለው ናት። ኦሪትና ነቢያት ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸንተዋል።” (ማቴ.፳፪፥፴፬-፵) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።
ኦሪትም ነቢያትም በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸንተዋል ማለት የኦሪት ትእዛዝም የነቢያት ትንቢትም ፍቅር የባሕርዩ በሆነው ራሱም ፍቅር ነው በተባለው በእግዚአብሔር የተፈጸመና ጸንቶ የሚኖር መሆኑን ራሱ ባለቤቱ አስረድቶናል። የጌታውን የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ የተረዳው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቀር ኑሩ” በማለት ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ሀብት ገንዘብ እንድናደርገው ያስረዳናል።
ለ. እንግዳ መቀበል
ሰው በብዙ ምክንያት በሚፈልገውም ሆነ በማይፈልገው ምክንያት ከቤቱ ይወጣል። የሚቀበለው ይፈልጋል፤ የሚያስተናግደው ይሻል። በዚህ ጊዜ “የእግዚአብሔር እንግዳ” ብሎ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ እንዲያሳድሩት ሰዎችን ይለምናል። በዚህ ጊዜ ራሱን እግዚአብሔርን በአካል እንደተቀበሉት ቆጥረው በደስታ የሚያስተናግዱ አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ቤቱን ለመሥራት የራሳቸው ብቻ አስተዋጽኦ እንጂ ቤቱ የእግዚአብሔር ስጦታ እንዳልሆነ በመቍጠርና የእግዚአብሔርንም ቸርነት ባለመረዳት ማንም እንዳይመጣብኝ የሚሉም አሉ። ሐዋርያው እንግዳ መቀበልን ዕለት ዕለት የሚያዘወትሩን እያመሰገነ የማይቀበሉትን ደግሞ በረከት እንዳይቀርባቸው እያሳሰበ ያስተምረናል።
እንግዳ መቀበል እንደሚገባ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የፋሲካን ሕግ በአስረዳበት ትእዛዝ “የእግዚአብሔርን ፋሲካ ያደርግ ዘንድ ወደ እናንተ የመጣ መጻተኛ ቢኖር ወንዱን ሁሉ ትገርዛለህ፤ ያን ጊዜ ፋሲካ ያደርግ ዘንድ ይገባል፤ እንደ ሀገር ልጅም ይሆንላችኋል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ” (ዘፀ.፲፪፥፵፰) በማለት ስለ ፋሲካ ክብር መገረዝ አለበት ቢባልም ሊቀበሉት እንደሚገባ ግን ያስረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር አምላካችን “በሀገራችሁ ውስጥ እንግዳ ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና፤ ወደ እናንተ የመጣ እንግዳ እንደ ሀገር ልጅ ይሁንላችሁ፤ እርሱን እንደ ራሳችሁ ውደዱት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና” (ዘሌ.፲፱፥፴፫-፴፬) ሲል ለሕዝቡ ያስተላለፈውን አምላካዊ ትእዛዝ እናገኛለን።
ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ከጥንት ጀምሮ እንግዳ መቀበል አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ነው። እንግዳ ይቀበሉ የነበሩ ሰዎች መላእክትን እንዲሁ እግዚአብሔርን በአንድነት በሦስትነቱ ለመቀበልና ከቤታቸው ለማስተናገድ በቅተዋል።
እንግዳ የመቀበል መልካም ልማድ የነበረው ሎጥ መላእክቱን ከቤቱ አስተናግዷል። በቅዱስ መጽሐፍ “ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደላቸው፤ አላቸውም ጌቶች ሆይ ወደ ባሪያችሁ ቤት ገብታችሁ እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገም ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም በዐደባባዩ እናድራለን እንጂ አይሆም አሉት። እርሱም ግድ አላቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፤ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ቂጣንም አስጋገረላቸው፤ እነርሱም በሉ።” (ዘፍ.፲፱፥፩-፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል የታደሉ አሉና።” (ዕብ.፲፫፥፩) በማለት የነገረን እንደ ሎጥ ያሉትን እንግዳ ወዳዶች ሊያመስግን ለእኛም ያላቸውን አርአያነት ሊያሳየን ነው።
ሌላውና የእንግዳ መቀበል ልማድ የነበረው ታላቁ አባት አብርሃም ነው። አብርሃም እንግዳ ካልመጣ ምግብ መመገብ የማይችል ታላቅ አባት ነበር። ይሁን እንጂ ጠላት ዲያብስ ቀንቶበት እግዳ ቢከለክለው አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ከቤቱ ተገኙለት። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ “በቀትርም ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ሥር ተገለጠለት ። ዐይኑንም ባነሣ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፤ ወደ ምድርም ሰገደ፤ እንዲህም አለ አቤቱ በፊትህ ባለሟልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈው፤ ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁንም እንጠባችሁ። ከዛፉም ሥር ዕረፉ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ ካረፋችሁ በኋላ ወደ ዐሰባችሁበት ትሄዳላችሁ። እነርሱም እንዳልህ እንዲሁ አድርግ አሉት።” (ዘፍ.፲፰፥፩-፭) በማለት የአብርሃምን መልካም ሥራ ከመልካም ሥራውም የተነሣ እግዚአብሔርን በአንድነት በሦስትነቱ ማየት እንደቻለ፣ ማየት ብቻም ሳይሆን ከቤቱ ለማስተናገድ እንደታደለ ያስረዳናል።
በሐዲስ ኪዳን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ዛሬ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ እንግዳ ቢቀበሉ በዳግም ምጽአቱ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን” ብሎ እንደሚቀበላቸው አስረድቶናል። (ማቴ.፳፭፥፴፫) ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ካህን ሊሆን የሚወድ ሰው ቢኖር መሆን አለበት ብሎ ከዘረዘራቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ “እንግዳ ተቀባይ መሆን አለበት” የሚል ነው። (፩ጢሞ.፫፥፪) ፤ (ቲቶ ፩፥፰) ለዕብራውያን ምእመናንም እንግዳ መቀበልን አትርሱ ያላቸው ሰዎች በሕይወታቸው ሊፈጽሟቸው ከሚገቡት ተግባራት መካከል ስለሆነና በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ በረከትን የሚያሰጥ ስለሆነ ነው።
ዛሬም በአንድም በሌላም ከቦታቸው ተፈናቅለው፣ በማያውቁት ሀገር እየተንከራተቱ ያሉትን፣ ሀገር እያላቸው ሀገር እንደሌላቸው በግፈኞች እየተሳደዱ በመከራ የሚሠቃዩትን እንግዶች መቀበል እንዳለብን ከዚህ መልእክት ልንማር ይገባናል።
ሐ. እስረኞችን ማሰብ
ሰዎች አጥፍተውም ሆነ ሳያጠፉ ይታሰራሉ። ወደ ዘመነ ሰማዕታት መለስ ብለን የቅዱሳኑን ሕይወት ስንመለከት በዐላውያን ነገሥታት በዐላውያን መኳንንት ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ፣ ለጣዖት እንዲሰግዱ ይገደዱ ነበር። ሃይማኖታችንን አንክድም ለጣዖትም አንሰግድም ሲሉ ይታሰሩ ከዚህም አልፎ ይገደሉ ነበር። ዛሬም በግልጥ የቆመ ጣዖት ባይኖርና ስገዱ ባይባሉም በሃይማኖታቸው ምክንያት በእስር ቤት የገቡት በርካቶች ናቸው። በዚህ ጊዜ ልንጠይቃቸውና ልናረጋጋቸው ይገባል።
መሪዎች በሚያስተዳድሩት ሕዝብ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ፣ የአስተዳደር ብልሹነት ሲሰፍን መምህራኑ፣ በኃላፊነት ላይ ያሉም ሆኑ የሌሉ አካላት “ድሃ ተበደለ ፍርድ ጎደለ” በማለታቸው ይታሰራሉ፤ ብሎም ይገደላሉ። መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ “ዋርሳ አትውረስ” ብሎ ሄሮድስን በመገሠጹ ታሰረ። በቅዱስ ወንጌል “ዮሐንስም የአራተኛው ክፍል ገዢ ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለ ማግባቱና ሄሮድስ ያደርገው ስለነበረው ክፉ ነገር ሁሉ ይገሠጸው ነበር። ደግሞም ከዚህ ሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አስገባው” (ሉቃ.፫፥፲፱) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ንግሥቲቱ አውዶክስያ የድሃዪቱን መሬት በመቀማቷ ገሠጻት እርሷም ለምን ድሃዪቱን አትበድዪ ተባልሁ ብላ ወደ እስር ቤት አስገባችው።
ዛሬም በጥፋታቸውም ይሁን ያለጥፋታቸው በእስር ቤት ያሉ አሉ፤ ባለ ሥልጣናቱ እንደ ጥንቱ ለብልሹ አገዛዛቸው የሚያሰጋ ሲመስላቸው ምክንያት እየፈለጉ ወደ እስር ቤት ማስገባት የተለመደ ነው። በዚህ ሁሉ ሐዋርያው “ከእነርሱ ጋር አብራችሁ እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ” በማለት የእነርሱን መከራቸውን፣ ችግራቸውን፣ ግፋቸውን፣ እያሰብን የሚቻለንን ሁሉ እንድናደርግ፣ ለእነርሱ በቀጥታ የምናደርግላቸው ነገር ባይኖረን እንኳን እነሱን እያሰብን ወደ እግዚአብሔር ጸሎት እንድናቀርብ ያስተምረናል።
መ. መከራ የጸናባቸውን ማሰብ
መከራ በልዩ ልዩ መንገድ ይመጣል። የመከራ መምጫ ምክንያቶችን መዘርዘሩን እንተወውና ዛሬ በርካታ ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው፣ ከሀገራቸው ተሰድደው፣ በባዕድ ሀገር ተጠልለው፣ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎባቸው፣ የሚበሉት የሚጠጡት አጥተው እየተቸገሩ በጽኑ መከራ ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህን አካላት ቢቻል በአካል ሂዶ መጎብኘት፣ ባይቻል ደግሞ ባሉበት ቦታም ቢሆን ከእነርሱ ጋር እንዳሉ ሁኖ ማሰብ ያስፈልጋል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እኔ በሥጋዬ ከእናንተ ጋር ባልኖር በመንፈስ ከእናንተ ጋር አለሁ።” (፩ቆሮ.፭፥፫) በማለት እንደተናገረው ባለንበት ሁነንም ቢሆን እያሰብናቸው እንደሆንን እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በሥጋ ከእነርሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ መከራ የጸናባቸውን ዐስቡ” ሲለን በአካለ ሥጋ መኖርና አለመኖር የራሱ የሆነ ዋጋ ስላለው ነው። ይህ ልዩነት የሚኖረው በቅዱሳኑ ዘንድ አይደለም። በቅዱሳኑ ዘንድ በያሉበት ቦታ ሁነው የፈቀዱትን ማድረግ ይችላሉ። ታሪኩ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የመቶ አለቃው “ቃል ብቻ ተናገር ልጄ ይድናል” (ማቴ.፰፥፰) ባለና በለመነው ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የመቶ አለቃውን ፍጹም እምነት ዐይቶ “እንደ ወደድህ ይሁንልህ” (ማቴ.፰፥፲፫) ሲለው ልጁ ተፈውሷል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል።” (ዮሐ.፲፬፥፲፪) በማለት ጽኑ ቃል ኪዳን እንደገባላቸው በፍጹም እምት ጸንተው በበጎ ምግባር እየተመላለሱ የሚኖሩ ቅዱሳን በአካለ ሥጋ መገኘት ሳይጠቅባቸው ሁሉን ማድረግ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ እንደ መቶ አለቃው ያለ ፍጹም እምነትና እንደ ቅዱሳኑ ያለ ብቃት ለሌለው ሰው በጎ የሚያደርገውና በጎ የሚደረግለት ሰው በአካል መገናኘት ያስፈልጋቸዋል። በጎ አድራጊው በአካል ተገኝቶ የችግረኛውን ሁኔታ ሲመለከት እጅግ ውስጡ ይራራና የሚችለውን ያህል መልካም ነገር ለማድረግ ይፋጠናል። በጎ ነገር የሚደረግለት አካል ደግሞ በጎ አድራጊውን በአካል ሲመለከተው የሚደረግለት ነገር ቢያንስ እንኳን በተደረገለት ጥቂት ነገር አእምሮው ሊጽናና ይችላል። ሐዋርያው “በሥጋ እንደተገኛችሁ ሆናችሁ መከራ የጸናባቸውን ዐስቡ” ያለውም ስለዚህ ነው።
ረኀብ ክፉ ነው፤ ዐቅም ያሰጣል፤ መልክ ይለውጣል፤ ጸባይ ያጠፋል፤ ሲበረታም ይገድላል። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “በሰይፍ የሞቱት በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ዐልፈዋል” (ሰቆ.፬፥፱) በማለት እንደተናገረው የአሟሟታቸው ሁኔታም እጅግ የሚዘገንን ይሆናል። በዚህ ጊዜ መድረስ ያስፈልጋል። መድረስ ብቻ አይደለም በአካል ከእነርሱ ጋር ተገናኝቶ በአንደበትም በተግባርም የሚቻለውን ያህል ማገዝ በእነርሱ ሕይወት ላይ እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።
በአጠቃላይ ሰዎች በኑሯቸው ሁሉ ብቻቸውን ማከናወን የማይችሉትን ከሌሎች ጋር ሲሆኑና አንዱ ከሌላው ጋር በፍቅር እየተሳሰቡ መኖር ሲችሉ፣ የአንዱን ክፍተት ሌላው እየሞላ እርስ በእርስ ሲረዳዱ፣ ለብቻ ሲሆኑ እጅግ የሚያስቸግረውን የሕይወት ውጣ ውረድ ማቃለልና የተመቻቸ ኑሮ መኖር ይችላሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያት በእስር ቤት ያሉትን፣ ፍትሕ የጎደለባቸውን፣ ዳኛ የበደላቸውን፣ ኀዘን የበዛባቸውን ልንጠይቃቸውና ልናረጋጋቸው ያስፈልጋል። እንዲሁም ከቦታቸው ተፈናቅለው፣ ሀብት ንብረታቸው ተወስዶባቸው፣ የሚጎርሱት፣ የሚለብሱት አጥተው መከራ እየተፈራረቀባቸው ያሉ ችግረኞችን እያሰብን አስፈላጊውን ርዳታ ልናደርግላቸው ይገባል። በዚህ መልካም ሥራ ሁላችንም ተሳትፈን ከበጎ ሥራ የሚገኘውን በረከት እንዲያድለን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን።