Saturday, 27 February 2021 00:00

ዐቢይ ጾም በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ
በዓለም ላይ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ  ምእመኖቻቸው ዐቢይ ጾምን እንዲጾሙ ያዛሉ። በተለይ የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች በጉጉት ከሚጠብቋቸው ጊዜያት አንዱ ይህ ወቅት ነው። የሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ታላቁን ጾም ‹‹Sawma Rabba›› ይሉታል - ጾመ ረቢ - ጾመ ኢየሱስ እንደ ማለት ነው። ጾሙን የሚቀበሉት ከበዓለ ትንሣኤው ከአምሳ ቀናት በፊት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሥርዓት ሳምንታቱ የየራሳቸው ስያሜ እንዳላቸው ኹሉ በሶሪያውያንና በሌሎችም የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች ዘንድ ስያሜያቸው የሚታወቁ ዕለታት አሉ። ከእነዚህም አንዱ ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› (Clean Monday) ነው። ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› የሚሉት ዐቢይ ጾምን የሚጀምሩበት ዕለተ  ሰኞን ነው። እንደሚታወቀው የጾሙ የመጀመሪያ ዕለት ሰኞ ሲሆን፡ ጾም ከብዙ ኃጢአት የምንታቀብበት፣ በንስሐ ሳሙና  የምንታጠብበትና የንጽሕና ምግባራትን የምንፈጽምበት በመሆኑ፡ ይህን ያመለክት ዘንድ የመጀመሪያውን የጾሙን መግቢያ ዕለት ንጹሕ ሰኞ ብለውታል። በሶሪያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የዐቢይ ጾምን ስድስተኛ ዓርብ ‹‹የአልዓዛር ዓርብ›› ይሏታል። ሰባተኛዋን ሰንበት ደግሞ ‹‹ሰንበተ ኦሻና›› (የሆሣዕና ሰንበት) ብለው ይጠሯታል። ምሴተ ሐሙስ፣ የስቅለቱ ዓርብና ቀዳም ስዑርም ከበዓለ ትንሣኤ በፊት የሚታሰቡ ዕለታት ናቸው። (የተጠቀምናቸው ምንጮች ሌሎቹ ዓርቦችና ሰንበታት ስያሜ ይኑራቸው፣ አይኑራቸው አይገልጹም)። አንዳንዶች የምዕራባውያኑ አጠራር ተጽዕኖ አድርጎባቸው ‹‹ንጹሕ ሰኞ››ን፡ ‹‹የአመድ ሰኞ›› (Ash Monday) ብለው ይጠሩታል።

 

ምዕራባውያኑ፡ ዐቢይ ጾምን የሚጀምሩት እንደ ኦርቶዶክሳውያኑ በሰኞ ዕለት ሳይሆን በረቡዕ ነው። ስለዚህ የሚጀምሩበትን ረቡዕ ‹‹የአመድ ረቡዕ›› (Ash Wednesday) ብለው ይጠሩታል። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ልክ እኛ በደመራ በዓል ጊዜ እንደምናደርገው በዕለቱ በግንባራቸው ላይ ከአመድ የመስቀል ምልክትን በማድረግ ስለሚያከብሩት ነው። ይህንንም የንስሐ ምልክት እንደ ሆነ ይገልጻሉ። አመዱም የሚገኘው ቀደም ባለው ዓመት በሚከበረው የሆሣዕና በዓል ላይ ከሚያቃጥሉት የዘንባባ ቅጠል ነው።

በዐቢይ ጾም ውስጥ ከሚታሰቡ በዓላት መካከልም በዓለ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌምን፣ በዓለ ቅዱስ ዮሴፍንና በዓለ ትስብእትን ያከብራሉ።

በግብፅ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ከዐቢይ ጾም በፊት ያሉት ሳምንታት ስያሜ ያላቸው ናቸው። በእያንዳንዱ ሰንበት የትኞቹ ምንባቦች እንደሚነበቡና ምን እንደሚታሰብባቸው እንደሚከተለው ለማየት እንሞክር፡-

ጾሙ ከመጀመሩ በፊት ያለው ሰንበት የ‹‹ቅድመ ጾም›› ሰንበት ሲሆን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፮፥፩-፲፰ ያለው ይነበብበታል። ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ሀብተ ሰማያት›› የሚታሰቡበት ነው። ሦስተኛው እሑድ ‹‹የፈተና ሰንበት›› የሚባል ሲሆን፡  በአራተኛው የጠፋው ልጅ፣ በአምስተኛው ሳምራዊቷ ሴት፣ በስድስተኛው ሳምንት ሽባ የነበረው ሰው (The Paralized man - መጻጉዕ)፣ በሰባተኛው ዕውር ሆኖ የተወለደው ሰው፣ በስምንተኛው ሆሣዕና ይታሰባሉ።

ከምሥራቅ ዐቢያተ ክርስቲያናት መካከል የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ ለሰንበታቱ ስያሜዎች አሏት። የመጀመሪያውን ሰንበት ‹‹የኦርቶዶክሳዊነት ሰንበት›› የምትለው ሲሆን ኦርቶዶክሳውያን በቅዱሳት ሥዕላት ምክንያት የደረሰባቸውን መከራና በኋላም በነዮሐንስ ዘደማስቆ አማካኝነት ድል ማድረጋቸውን የምትዘክርበት ዕለት ነው።

ከሰንበታቱ መካከል ሁለተኛውን ጎርጎርዮስ ፓላማስ የተባለው የግሪክ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ እንዲዘከርበት በስሙ የሰየመች ሲሆን ሦስተኛው ሰንበት ‹‹ቅዱስ መስቀልን የማክበር ሰንበት›› ይባላል። በዐራተኛው ዮሐንስ ዘሰዋስውን ስትዘክር እናታችን ቅድስት ማርያም ግብፃዊትም የምትዘከርበት ሰንበት አለ።

(ምንጭ፡- www.st-takla.org, www.goarch.org, www.oca.org, www.saintbarbarafw.org, www.syrianorthodoxchurch.org)

 

Read 867 times