Thursday, 27 January 2022 00:00

ዘመኑ በጋራ የምንቆምበት ነው

Written by 
የ ምንገኝበት ዘመን መከራ የበዛበት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበርና መደጋገፍ የሚጠይቅ ነው። መከራ ሲገጥመን መተባበር እንደሚኖርብን የማንም ማሳሰቢያና ማባበያ አያስፈልገንም። በአገራችን እየደረሰ ያለው መከራ ሊያስተባብረን ካልቻል ሌላ የሚያፋቅረን ነገር ማግኘት አንችልም። የምንኖርባትን ዓለም ጣዕም የቀየሩት ራሳቸውን ብቻ ለማትረፍ ሲደክሙ የኖሩት ሳይሆኑ በመተባበር ለመከራ የተዳረጉትን ሰዎች ሕይወት ሲታደጉ የኖሩት መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። ከመለያየት ይልቅ መተባበር፣ ከመቀበል ይልቅ ለተቸገሩት መስጠት የቻሉት የሰው ፍቅር የበለጠባቸው፣ ለእነርሱ የሚያስፈልጋቸው ለችግር ለተጋለጡትም የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የተረዱ ናቸው። መስጠት ደስታን ሲሰጥ መቀበል ኃፍረትን ያላብሳል። መተባበርና መደጋገፍ ኃይል ሲፈጥር መለያየት ደግሞ አገርን ስለሚያዳክምና ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው ተብሎ የተነገረውን ስለሚቃረን መተባበር ይገባል። ዘመኑ መደጋገፍና መረዳዳት የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ከራስ ወዳድነት መላቀቅ ታላቅነት ነው። ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱ፣ ሀብት ንብረታቸውን አጥተው በችግር የሚሰቃዩ፣ ወገኖቻቸው አልቀው በኀዘን የተጨበጡ ወገኖቻችን ቍጥር ከሚሊዮን በላይ ሆኗል። የተቸገሩትን መርዳት ሃይማኖታዊ ግዴታችን፣ ሥነ ምግባራዊ መገለጫችን መሆኑን ተረድተን ከሌሎቹ ቀድመን ለተቸገሩ ወገኖቻችን መድረስ የሚገባን ክርስቲያኖች ነን። አገራችን ሰላም ውላ እንድታድር ታላቅ ኃላፊነት እንዳለብን መዘንጋት የለብንም። መልካም በማድረግ የተጎዱትን የምንደግፈው በሌሎች ላይ የደረሰው መከራ እንዲደርስብን ስለማንፈልግ ብቻ ሳይሆን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ በአምላኩ ዘንድ የሚመሰገን በመሆኑ ጭምር ነው። የሃይማኖት ልዩነት ሳንፈጥር ለተቸገሩ ወገኖቻችን ስንደርስላቸው በአንድ በኩል ክርስቲያናዊ አስተምህሯችን ለሌሎች ይገለጣል። ከዚህ በተጨማሪም ክርስቲያኖች የተቸገሩትን በመደገፋችን የሞራል ልዕልናችንን ዓለም ያውቀዋል። ሰዎች ሲቸገሩ ዓይተው የሚያዝኑ ክርስቲያኖች ንዑዳን ክቡራን ተብለው ተመስግነዋል። ወገኖቻችን አገር ለቀው ተሰደው፣ ቀያቸውን ትተው ተፈናቅለው እያየን ለእነርሱ የምናደርገው ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለእነርሱ ማዘናችን ንዑዳን ክቡራን ያሰኘናል ማለት ነው። በእርግጥ ክርስቲያኖች ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሁሉ መልካም የምናደርገው ሰዎች ያመስግኑን፣ ንዑድ ክቡር ይበሉን ብለን አይደለም። ሰዎችን መደገፋችን አምላካችንን ስለሚያስደስተው ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ስንኖር አምላካችንን የሚያስደስት በጎ ምግባር መፈጸም ስላለብን ነው። መከራ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ መተባበርና መደጋገፍ ይኖርብናል። የተፈጠርንለት ዓላማ ሠርተን ያገኘነውን ራሳችን በልተን እንድንደሰት ሳይሆን ሠርተን ካገኘነው ለሌላቸው ወገኖቻችን እንድናካፍል፣ ተባብረን ወገኖቻችንን ከሞት እንድንታደግ ነው። ተጋግዘን ለተቸገሩ ወገኖቻችን በመድረስ ሕይወታቸው እንድትቀጥል፣ ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሓ እንዲያገኙ ስናግዛቸው ደስታችን ፍጹም ይሆናል። በሃይማኖት የሚመስሉን ብቻ ሳይሆኑ የማይመስሉን ወገኖቻችንም በደረሰባቸው ችግር ምክንያት አገር ለቀው ሲሰደዱ፣ በስደት ወደ አሕዛብ አገር ሲሄዱ መታደግ ከክርስቲያኖች ሁሉ የጠበቅ ተግባር ነው። ለወገኖቻችን ራሳችንን ዐሳልፈን ለመስጠት የሚያስችል መንፈሳዊ ጥብዓት ባይኖረን እንኳ ከገንዘባችን ከፍለን ለተቸገሩ ወገኖቻችን መደገፍ ከሚጠበቅብን ክርስቲያናዊ ትሩፋት ትንሹ ነው። እስከ ሞት ድረስ የተቸገሩትን ሐመር ታኅሣሥ-፳፻፲፬ ዓ.ም. የማኅበሩ መልእክት ፫ በመርዳት መታደግ፣ ሰውን ሁሉ መውደድ እንደሚገባን የተነገረን ለራሳችን ከሚያስፈልገን ቀንሰን ሌሎችም እንደሚያስፈልጋቸው አምነን እንድንረዳቸው ነው። እውነተኛ ወገን የሚታወቀው በመከራ ዘመን በመሆኑ አገር ለቀው ለተሰደዱ፣ በችግር አሽክላ ታስረው ለሚሰቃዩ፣ ረሃብና ኀዘን ተጨምሮባቸው ለሚንገላቱ ወገኖቻችን በመድረስ አለኝታነታችንን በተግባር እናሳያቸው። ከመንፈስ ልዕልና የደረሱት ሰዎች ለራሳችን ይቅርብን ብለው ወገናቸውን ሲያስቀድሙ እኛ ደግሞ ቢያንስ ካለን በማካፈል ለወገን አለኝታነታችንን እናረጋግጥ። በዘመናችንም ቅዱሳን ከፈጸሙት ያልተናነሰ ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን የሚገልጠው ጦርነት በተነሣባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ምእመናን የፈጸሙት ተግባር ነው። በጦርነት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱትን፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን ወገኖቻችንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የቋንቋም ሆነ የመልክአ ምድር ልዩነት ሳናደርግ መርዳት ከክርስቲያኖች ሁሉ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው። በአሳብ አንድ ሆነን የወገን ፍቅር በልጦብን ተባብረን የተቸገሩትን ከደገፍን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ”፤ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም” ተብሎ የተነገረውን በተግባር ፈጸምን ማለት ነው። በክርስቲያናዊ ምግባራችን አልጫውን ዓለም ማጣፈጥ፣ ጨለማውን ዓለም ማብራት ሲገባ ገብር ሐካይ መሆን የለብንም።ክርስቲያኖች የተራራ ላይ ብርሃንና የምድር ጨው መሆናችን የሚገለጠው ሠርተን ካገኘነው ለወገኖቻችን ስንተርፍ ነው። ሰዎች ለመከራ በተጋለጡበት ዘመን የተቸገሩትን መረዳት ለተረጅዎች የሚኖረውን ጠቀሜታ ቃላት የመግለጥ አቅም የላቸውም። ተባብረን ወገኖቻችንን ስንረዳቸው ተጎጂዎች የሚያስብልን ወገን አለ ብለው ተስፋቸው ይለመልማል፤ ዙሪያው ገደል የሆነባቸው መውጫ መንገዱ ይታያቸዋል። ተስፋቸው መለምለም ብቻ ሳይሆን ተፈናቃዮች በደረሰባቸው መከራ ምክንያት በረሃብ እንዳያልቁ ያደርጋል። ልጆቻቸው ተርበው ሲያለቅሱባቸው ተስፋ ቆርጠው አምላካቸውን እንዳይክዱና ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ በመተባበር ወገኖቻችንን መርዳት ይኖርብናል። ተፈናቃዮች ዕድሜ ልካቸውን በሰው ድጋፍ ላለመኖርና ሠርተው ተለውጠው ራሳቸውን በመቻል ሌሎችን እንዲረዱም ተግባራዊ ትምህርት ያገኙበታል ብለን እናምናለን።
Read 2715 times