Tuesday, 29 September 2020 00:00

የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ‹‹የኔ›› ለሚሉት የሃይማኖት ተቋም ተልዕኮ አስፈጻሚ መሆናቸው ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የሀድያ ዞን የመንግሥት አመራሮች ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ወደጎን ትተው ‹‹የኔ›› ለሚሉት የሃይማኖት ተቋም ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆነቻውን የሀድያ፣ ስልጤ፣ ከንባታና ደቡብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ገለጡ፡፡  ብፁዕነታቸው ይህንን የገለጡት የዞኑ የመንግሥት አመራሮች በሆሳዕና ከተማ አስተዳድር የሚገኘውን “ጎፈር ሜዳ” የተባለውን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ ቦታ መንጠቃቸውን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡  በሀድያ ዞን ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ለከፍተኛ ጫና እየተዳረጉ እንደሆነ ብፁዕነታቸው በመግላጫው ያስረዱ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ለሀገር እያበረከተች ካለችው ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ አንጻር ልትጠበቅ፣ ልትደገፍና ልዩ ትኩረት ሊሰጣት ሲገባ ሚዛናዊ ባልሆኑ አንዳንድ የመንግሥት ሹማምንቶች የሚደርስባትን መገለልና የመብት ጥሰት በዚህ ዘመን መመልከት እጅግ ያሳዝናል ብለዋል፡፡  እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ ዞኑን የሚመሩት አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ከፍተኛ ጥላቻና እልህ በተቀላቀለበት ሁኔታ የሚታይና የማይታይ ጥቃት እየፈጸሙባት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ይህንን አስተዳደራዊ በደልም ከክልሉ መንግሥት እስከ ፌዴራል ያሉ የመንግሥት አካላት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡  ‹‹የአደባባይ በዓላትን ማክበሪያ ቦታ መጠየቅ መብት ሆኖ ሳለ በምላሹ ‹‹ወራሪ›› ብሎ መሳደብ ግን ትንኮሳ ነው›› ያሉት ብፁዕነታቸው ‹‹ወራሪ›› ብለው በሚተነኩሱ የመንግሥት አካላት ላይ የርምት ርምጃ እስካልተወሰደባቸውና መንግሥታዊ አሠራሩ እስካልተስተካከለ ድረስ ተማምኖና ተግባብቶ ለመቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡  አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንና የምእመናንን መብት በኃይል ሚገረስሱ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግጭት ለመፍጠርና ሀገርና ሕዝብን ሰላም ለማሳጣት የሚያልሙ እነደሆኑ ተናግረዋል፡፡  በሀድያ ዞን የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ለከፍተኛ ሥነ ልቡናዊና አካላዊ ጥቃት እየተጋለጡ እንደሆነ ያስረዱት ብፁዕነታቸው በተለይም በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች በጾም ወቅት የፍስክ ምግብ በፍስክ ወቅት ደግሞ የጾም ምግብ እንደሚያቀርቡላቸው ተናግረዋል፡፡  በዩኒቨርስቲው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ማዕተባቸውን የመበጠስና ነጠላቸውን የመንጠቅ ድርጊት ይፈጽሙባቸዋል፡፡ በቅርቡ በኮንታ አካባቢ በክርስቲያኖች ቤት ድረስ እየሄዱ በስለት ይወጓቸው እንደነበር ብፁዕነታቸው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ድርጊት መነሻ ደግሞ የስሁት ትርክት አቀንቃኞችና የራሳቸውን ሃይማኖት በሌላ ላይ ለመጫን ያለሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው ሲሉ ብፁዕነታቸው አያይዘው ተናግረዋል፡፡   
Read 296 times