‹‹ወራሪ እየተባልን ከመገደልና ከመሰደድ ወጥተን የሀገር ባለቤትነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል››
ክፍል ሁለት
ስምዐ ጽድቅ፡- የዘር ማጥፋት መከላከያ ተቋምና ሌሎች ማኅበራት በሀገር ውዳድና በቤተክርስቲን አባቶች መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም ማኅበረ ቅዱሳን ከእነዚህ ማኅበራት ሕብረት ጋር ያደረገው ቅንጅታዊ አሰራር አለው ማለት ይቻላል?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- አንዳንዱ ማኅበራት በቅርቡ ቢመሰረቱም ወቅታዊና አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የማኅበራቱ ምስረታ ዘገየ ቢባል ነው እንጂ አስፈላጊነታቸው ግን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በጠቅላላ ጉባኤ እየወሰነ የሚሠራቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የማኅበሩ አባላት በቀናኤነት ባሉበት አካባቢና በተሰማሩበት ሙያ ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፡፡ በቅርቡ ከተመሰረቱት ማኅበራት ጋር በተለይም “ከዘር ማጥፋ ተቋም” ጋር ይፋዊ የሆነ የሥራ ግንኙነት እስካሁን ድረስ የለንም፡፡ ነገር ግን በሽማግሌዎች ማኅበራትም ሆነ በዘር ማጥፋት መከላከያ ተቋሙ ውስጥ የእኛው ደጋፊና አባላት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ አካላት ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ይጠቅማል ያሉትን ሥራ ከሠሩ በአንድም በሌላ ማኅበሩ ሠርቷል ማለት ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን በይፋ ከእነዚህ ማኅበራት ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፤ እንመካከራለን፤ እንደጋገፋለንም፡፡ እነዚህ ማኅበራት በቅርቡ የተቋቋሙ በመሆናቸው ጠንካራ የሆነ መዋቅራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጊዜ ወስደን ጠንክረን እንሠራለን፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ቤተ ክርስቲያን በሚደርሱ ጥፋቶች ምክንያት በተደጋጋሚ መግለጫ ከማውጣቷ ባለፈ በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ምን ብትሠራ መልካም ነው ይላሉ?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ቤተ ክርስቲያን እካሁን ድረስ ከላይ እስከ ቤተሰብ ድረስ ያለውን መዋቅሯን የምትገለገልበት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጣቸውን ምእመናን መጠበቅ ሳትችል መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ መስጠት ምእመናንንና ቤተክርስቲያንን ለተደራራቢ ጥፋት ማጋለጥ ነው፡፡ በምእመናንና በካህናት ላይ ንቅናቄ መፍጠር እና በፍጥነት ማደራጀት ያስፈልጋታል፡፡ ካህናትና ምእመናን ዘመኑ መቀየሩን እንዲያስተውሉ ማድረግ፤ ኦርቶዶክሳውያንን ሀገር አልባ የማድረግ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መኖሩን ለምእመናንና ለአገልጋዮች ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችንን ከመነጠቃችን በፊት ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ያለውን እውነታ መልሳ መላልሳ ማስገንዘብ አለባት፡፡ ፖለቲካውንም በባዕዳን እጅ ከመነጠቃችን በፊት መልሶ የራስ ማድረግ መታሰብ ያለበት ትልቅ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ለምእመናንዋ፣ ለአገልጋቿ በተግባር የተደገፈ ሁለንተናዊ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት አለባት፡፡ ወራሪ እየተባልን ከመገደልና ከመሰደድ ወጥተን የሀገር ባለቤት መሆናችንን በፍጥነት ልናረጋግጥ ይገባናል፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ቤተ ክርስቲያን አጋርነቱ ምን እየሠራ ይገኛል? በቀጣይስ ምን ለመሥራት አቅዷል?
አቶ ፋንታሁን ዋቄ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለአገልግሎት የጠራው መኅበር በመሆኑ ያቅሙን ያህል እየለፋ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በዋናነት እየሠራ ያለው ሰውን ነው፡፡ የሰው ልጅ በሃይማኖት፣ በምግባር እንዲጸናና ዙሪያውን በአግባቡ እንዲረዳ የማድረግ ሥራዎችን ለረጅም ጊዜ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ መልካም እንዲሆኑ፣ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸውና፣ ሀገራቸውን እዲወዱ እንዲጠብቁ የማድረግ አገልግሎቶችን እፈጸመ ይገኛል፡፡ በአገልግሎት መሀል ፈተናዎች ሁሌም ይኖራሉና ፈተናዎችን ከመቀነስና ከመከላከል ረገድ ከሞላ ጎደል ማኅበሩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ስለሆነም ምእመናንና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተው በሃይማኖታቸውና በምግባራቸው ጸንተው ለዘላለም እንዲቆዩ ያስፈልጋል፡፡
ምእመናን በዚህ ወቅት በተለያዩ ችግሮች በተሰደዱና በተፈናቀሉ ጊዜ በሥነ ልቦናና በረሀብ ተጎጂዎች እንዳይሆኑ ባለጸጎችን በማስተባበር አስፈላጊው ሁሉ ሰብአዊ ድጋፍ በማኅበሩ በኩል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ምእመናን ተሥፋ ቆርጠው እንዳይሰደዱና ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ በማኅበሩ በኩል ያላሰለሰ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ምእመናንን እያሳደዱ ወደ አንድ ቦታ በመሰብሰብ በቀጣይ “ጂሃዳዊ ጦርነት” ማወጅ አላማቸው እንደሆነ በመረዳት፤ ማኅበረ ቅዱሳንም ምእመናን ባደጉበትና በኖሩበት አካባቢ ተረጋግተው እንዲቆዩ የማድረግ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ለወደፊቱም ከዚህ የተሻሉ ሥራዎችን ይሠራል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለወደፊቱ ከቤተ ክርስቲያን ልዩ የሆነ ሥራ ባይሠራም ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን የልጅነት ሥራ ተቀብሎ ለመሥራት ግን ቁርጠኛ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከጥቃት የምትጠብቅበትን መዋቅር ሠርታ መንቀሳቀስ ከቻለች ማኅበሩ ቀዳሚ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳንን የሁሉ ነገር መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ምእመናንን ማሳሳት በመሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ማድረግ የሚችለው የድርሻውንና የአቅሙን ብቻ ነው፡፡ ምእመናን፣ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት አገልጋዮች ደግሞ የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው፡፡ ሀገር ላይ ችግር የለም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ዋጋ ያስከፍላልና በማንኛውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በምትዘረጋው መዋቅር ውስጥ ማኅበሩ ተሳትፎውን በማሳደግ የራሱን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል፡፡
በክልል በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ጨርሶ ማጥፋት ባይቻልም መከላከል ግን ይቻላል፡፡ በኦሮምያ ክልል የክርስቲያን ዘር የተባለን ሁሉ ጨርሶ ለማጥፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዳሉ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙት ተግባራት አመላካቾች ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን ተግባር ከማውገዝ በዘለለ ስልታዊና ሕጋዊ አካሄዶችን ተከትለን በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም በየጊዜው መግለጫ እያወጣ የተፈጠረውን ችግር ማቃለል ሳይሆን ሰዎች ያለ አግባብ እንዳይገደሉ፤ እንደይፈናቀሉ እና ሀብት ንብረታቸው እንዳይቃጠል እንዳይዘረፉ መሥራት አለበት፡፡ ችግሮች ከደረሱ በኋላም የተጎዱ ወገኖችን ማፅናናት፣ ማቋቋም፣ ካሳ መክፈል፣ የሕይዎት ዋስትና መስጠት እንዲሁም ችግር በፈጠሩ የመንግሥት አካላትም ሆነ ግለሰቦች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት እስኪደርስላችው ድረስ ምእመናን ቀድመው ያላቸውን አቅም አሟጠው የራሳቸውን ደኅንነት ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ ምእመናን “መንግሥት ይደርስልናል” ብለው መዘናጋት የለባቸውም፡፡ ‹‹መንግሥት” የተባለው ቆሞ የሚያሳርድ ከሆነ ለወደፊቱ ሰላምን ያመጣል ብሎ መተማመን ከንቱ ድካም ነው፡፡
በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት መዋቅራዊና ሥርዓታዊ በመሆኑ መደረግ ያለበት ነገር ሁሉ መደረግ አለበት፡፡ ኦርቶዶክሳውያንን ለማጥፋት የደህንነትና የጸጥታ መዋቅር እያለ ደህንነት ሊሰማን ስለማይችል በደህንነቱም በፀጥታ መዋቅሩም ዘልቀን እስካልገባን ድረሰ ሞታችን ሞት ሆኖ ስለሚቀጥል በተጠቀሱት ሁለት ዘርፎች ላይ የተሻለ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ ሥራ ያነሰ በሙሉ ኦርቶዶክስንና ኦርቶዶክሳውያንን ያጠፋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ኦርቶዶክሳውያንን ሀገር አልባ የማድረግ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መኖሩን አገልጋዮችና ምእመናን መገንዘብ አለባቸው፡፡