Tuesday, 24 November 2020 00:00

ከሶማሌ እስከ ጉራፈርዳ …

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ቤተ ክርስቲያን በፀረ ክርስቲያን ኀይሎች ትላንት ተፈትናለች፤ዛሬም እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ ታግለው ከማይጥሏት ገጥመው ከማያሸንፏት ጋር ግብግብ የገጠሙት እነዚህ ኀይሎች  የመውጊያውን ብረት ቢቃወሙ ለነሱ ይብስባቸው ሆናል እንጅ ቤተ ክርስቲያን የኋላ ኋላ ማሸነፏ እንደማይቀር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማሳደድ አካላዊ ዕረፍት ይነሷቸው እንደሆን እንጅ ዘለዓለማዊ የሆነውን መንፈሳዊ ዕረፍትን ግን አይነሷቸውም፡፡ ክርስቲያኖችን እንደ ክፉ አውሬ እያደኑ መግደል ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ውሎ ያደረ አረመኔያዊ ተግባር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየነው ያለው ደግሞ ተደጋጋሚና ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡  በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲቆም ቤተክርስቲያኗ ለመንግሥት በተደጋገሚ ጥያቄ ብታቀርብም በጉልህ የታየ መፍትሔ ባለመገኘቱ ፀረ ክርስቲያን ኀይሎች የልበ ልብ እየተሰማቸው በተደጋጋሚ እጅግ አስከፊ ጥቃት እየፈጸሙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ መረጃዎች ማወቅ እንደተቻለው በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ጥቃት በአብዛኛው በሶማሌ፣በኦሮምያ፣ በደቡብ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልሎች ነው፡፡ 

 

ሰሞኑን  በደቡብ ክልል በቤንች ሽኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ፣ በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ እንዲሁም ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለንና ወምበራ ወረዳዎች ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ክርስቲያኖች መገደላቸውን፣መቁሰላቸውን ፣መሰደዳቸውን እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው መቃጠሉንና መዘረፉን አስመልክቶ  ጥቅምት ፳፬ ቀን  ፳፻፲፫ ዓ/ም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ  አውጥቷል፡፡  ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው  በቅርቡ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸውና ማልደው በመነሳት አምሽተው በመግባት ምድርን ቆፍረውና አርሰው፣ ዘርተውና አጭደው፣ በድካም ኑሮአቸውን የሚገፉ ንጹሓን ምእመናን ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ሕፃናት ጭምር ሳይቀሩ የጅምላ ጭፍጨፋ በማካሄድ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉ እንዳሳዘነው አስታውቋል፡፡ በተለይ የጉራፈርዳንና የምዕራብ ወለጋን ጥቃት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ የሰማው መሆኑን ጠቅሶ ቅዱስ ሲኖዶስና ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ያሳዘነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ ድርጊቱን አውግዟል፡፡

“አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት በግፍ ለተገደሉትና ሕይወታቸውን ላጡ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ልባዊ ሐዘናችንን እየገለጽን ዳግም እንዲህ ዓይነት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም መንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ” ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንንም  በቀጣይ ለጋራ ሰላምና አንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 

በደቡብ ክልል ቤንች ሽኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የሸካ ቤንች ሽኮ እና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ጽዮን አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም የሚከተለውን መረጃ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ ነግረውናል፡፡

በእርሳቸው መርጃ መሠረት በአካባቢው የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን ጨምሮ ከአምስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በጸጥታ ችግር ምክንያት ከጉራፈርዳ ወረዳ ተፈናቅለዋል፡፡ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ከተፈናቀሉት ምእመናን ይልቅ አሁን በአካባቢው መጠነኛ መረጋጋት በታየበት ወቅት የተፈናቀሉት ምእመናን ቁጥር እንደሚበልጥ አስረድተዋል፡፡ ከወረዳው አጠቃላይ ተፈናቃዮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሲሆኑ ሀገረ ስብከቱም ምእመናኑ በጸጥታ ስጋት መፈናቀላቸው አሳስቦት ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ በየደረጃው ካሉ የመንግሥት አካላት ድጋፍና እገዛ እንዲደረግና ወደ ቀደመ  ቀያቸው በቶሎ እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡ 

ምንም እንኳን በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የደረሰ ጥቃት ባይኖርም ለደኅንነታቸው ሲባል ግን ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ያህል መደበኛ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተዘግተዋል፡፡ በአካባቢው ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የሞቱ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ከአሥራ አምስት በላይ ናቸው ተብሎ ቀደም ሲል የተነገረ ሲሆን በዚህ ሰዓት በትክክል በተደረገ ጥናት መሠረት ግን ዐሥር ያህል ብቻ እንደሞቱ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ቁጥራቸው በውል የታወቀ ከዐሥራ ስምንት በላይ ምእመናን ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአካባቢው ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በማገልገል ላይ የነበሩ ካህናት እንዲሁ በጸጥታ ሥጋት አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል፡፡ 

በቀጣይም በአካባቢው በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናን እንዲሁም በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ታጣቂ ቡድኑ ተጨማሪ ጥቃት ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት ከማሳወቅ በተጨማሪ ምእመናን ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ መልእክት ተላልፏል፡፡ 

የወረዳና የዞን የመንግሥት አመራሮች ችግሩ ከደረሰ በኋላ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ሥራቸውም ሀገረ ስብከቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ወረዳው ከዞን አመራሮች እንዲሁም ከክልል የመንግሥት ኀላፊዎች ጋር ተቀናጅቶ ሲሠራም ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን የክልሉ መንግሥት አንዳንድ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ‹‹ኃላፊነታችሁን ቀድማችሁ ባለመወጣታችሁ ነው የጸጥታ ችግር የተፈጠረው›› በማለት በተጠርጣሪነት የመያዝ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አካባቢው በክልልና ፌዴራል መንግሥት ኮማንድ ፖስት ሥር ያለ ሲሆን የዞንና የክልሉ መንግሥት በጋራ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የክልሉ መንግሥት ለተፈናቃዮች አስፈላጊ ነው ያለውን ሁሉ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ መልካም ጅምርና ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው፡፡ 

ለጥበቃ የማያመቹ አንዳንድ አካባቢዎች ካልሆኑ በስተቀር የፌዴራል መንግሥት በቂ ጥበቃ ለየአብያተ ክርስቲያናቱ መድቦ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በሚያስመሰግን ሁኔታ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱም ለተፈናቀሉ ምእመናን የማጽናኛ ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ የዕለት ደራሽ ምግቦችንና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ተሰብስቦ በቀጥታ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ 

የተፈናቀሉ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በአንድ ድንኳን ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን ብቻ ለይተው ሳይሆን ሁሉንም የማጽናናት ሥራ ሠርተዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ለምእመናንና ለሌሎች ኢትዮጵያውያን እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሃይማኖትን የለየ ባለመሆኑ ይህንን ማድረጉ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች አማንያን ዘንድ በጥሩ እይታ እንድትታይና የበለጠ እንድትከበር አድርጓታል፡፡ 

በሚከናወነው የሰብአዊ ድጋፍ እርዳታ ሁሉ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከጎናቸው እንደነበሩ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምክንያት በቦታው ባይገኙም ስልክ እየደወሉ መመሪያና አቅጣጫ ከመስጠት በተጨማሪ አባታዊ የማጽናኛ ቃል አድርሰዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልእክት “ግፍንና በደልን ማለፍ የምንችለው እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ወደቀደመ ቀያቸው ለመመለስ ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ እግዚአብሔርን በጸሎት እየለመነ ነው፡፡ በአካባቢው ብሎም በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ክፉ ጊዜ እንዳይመጣ፤ ወላጆችን ነጥቆ ልጆችን ያለአሳዳጊ የሚያስቀር ልጆችን ነጥቆ  ወላጆችን ያለቀባሪ ጧሪ የሚያስቀር ዘመን ተመልሶ እንዳይመጣ ለፈጣሪም ለመንግሥትም አቤት እንበል” ብለዋል፡፡ 

“የተፈናቀሉ ምእመናንም እኛን የሃይማኖት አባቶችን እንዲሁም ከፌዴራል እስከ ዞንና ወረዳ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሉትን በመስማት ወደቀያቸው መመለስ አለባቸው እንላለን፡፡ ምእመናን ወደቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ደስ በሚል ሁኔታ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እንዳይራቡና እንዳያዝኑ እያደረገ ይገኛል፡፡ ምእመናንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎናቸው መሆኑን አውቀው በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና የተለመደ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ አባታዊ መልእክት እናስተላልፋለን፡፡” 

ችግር አሁንም በቀጣይ ሊኖር ስለሚችል ምእመናን ሃይማኖታቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ምእመናንም ጉዳት ለደረሰባቸው አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ጊዜውን ተጋግዞ ማለፍ ቢቻል መልካም ነው፡፡ መንግሥትም መሰል የጸጥታ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ቀድሞ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የዜጎችን ደኅንነትና የሕይወት ዋስትና የማረጋገጥ ኀላፊነት ያለበት መንግሥት መሆኑን አውቆ መሠራት ያለባቸውን ሁሉ ቀድሞ በመሥራት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ሊያረጋግጥላቸው ይገባል፡፡ 

ዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለቤንች ሽኮ ዞን የጸጥታ ዘርፍ ኀላፊ ኮማንደር ምናሉና ለዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ስልክ የደወልንላቸው ቢሆንም ሁለቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስልክ ባለማንሳታቸው የእነርሱን ምላሽ ማካተት አልቻልንም፡፡  

 

Read 218 times