Saturday, 23 January 2021 00:00

‹‹ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የሀገር መሠረቶች በመሆናቸው ተጠብቀው ለትውልድ ሊተላለፉ ይገባል››                             ብፁዕ አቡነ አብርሃም  (የባሕ ርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ገዳማትና የአብነት  ትምህርት ቤቶች የሀገር መሠረቶች በመሆናቸው ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የባሕ ርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ገለጹ፡፡ ብፁዕነታቸው ይህንን የተናገሩት ‹‹የእመጓ ፍሬዎች›› በሚል ስያሜ በማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ከእመጓ መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ የተከናወኑ ሰባት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ ጥር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በባሕ ርዳር ዩኔሰን ሆቴል በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው፡፡ የገዳማትን ችግር ለመፍታት ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ባለድርሻ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሡት ብፁዕነታቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያናቸው በእርጅናና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የፈረሱ ገዳማት እንዲታደሱና የዕለት ጉርስ የሌላቸው ቀለብ አግኝተው የተጠናከረ ገዳማዊ ሕይወት እንዲመሩ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት ላይ እየሠራ ያለው መልካም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው “ከዚህ በፊት ብዙ ሠርቷል፤ ብዙም እየሠራ ነው፤ወደፊትም ብዙ እንደሚሠራ እናምናለን›› ብለዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን “ፈለገ ጥበብ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን በስጦታ በመለገስ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ችግር ያለባቸው ገዳማት እንዲረዱበት ማድረጋቸው የሚያስመሰግንና ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው” ያሉ ሲሆን መጽሐፉ እጅግ ተነባቢ በመሆኑ ከንባብ ባህል ርቆ የቆየውን ትውልድ ወደ ንባብ ባህል እንዲመለስ ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ተፈራ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት የአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎቸቸው እንዲሁም ገዳማዊያን ገዳማት ማንኛውም ዜጋ ከመንግሥት የሚያገኘውን ማኅበራዊ አገልግሎት እያገኙ ባለመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አስተባብራ የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማትንና መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ታደርጋለች ብለዋል፡፡  የእመጓ መጽሐፍ ደራሲ ፈለገ ጥበብ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ በዕለቱ ባስታለፉት መልእክት አብዛኛው የቱሪስት መዳረሻዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች እንደሆኑ አስረድተው እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች የትውልዱን ሞራል ከመገንባት ባሻገር መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡ ቦታዎች ናቸው ካሉ በኋላ የገዳማቱን ገቢ በመጨመር ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡  የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው በበኩላቸው በሀገራችን በአብዛኛው ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉት ጥንታውያን ገዳማት መሆናቸውን ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት  የጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምርና ገዳማቱ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  
Read 515 times