Tuesday, 09 February 2021 00:00

“መንፈሳዊ የቱሪስት መዳረሻዎች የትውልዱን ሞራል ከመገንባት ባሻገር መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡ ናቸው” - ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ (የእመጓ መጽሐፍ ድራሲ)

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የቱሪስት መስህቦች ውስጥ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መካናትና የአደባባይ በዓላቷ ናቸው።  በዚህም ሀገርና መንግሥት ተጠቃሚዎች ናቸው።  በተለይ መንግሥት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚያገኘው ገቢ ቀላል አይደለም።  ነገር ግን በአብዛኛው የገቢ ምንጭ የሆኑትን ዘመን የጣላቸውንና ጊዜ  የረሳቸውን ገዳማትና አድባራት በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ፤ ከጊዜ ብዛት የፈረሱና የተጎሳቆሉት ደግሞ እንዲጠገኑ የማድረግ ተግባር ውስጥ ሲገባ አይስተዋልም።  ለከተሞችና ለገጠር ቀበሌዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በሚደረግበት ጊዜ እንኳ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን  ያገለለ እንደሆነ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ በቅርቡ ባሕር ዳር በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ካቀረቡት ሪፖርት ማርጋገጥ ተችሏል።  ለምሳሌ በቅርቡ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወቅት በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈለጉ ግባአቶችንና ሕክምናዎችን የአብነት ተማሪዎች ማግኘት አልቻሉም።  የአብነት ተማሪዎች የሀገሪቱ ዜጋ አንድ አካል ሆነው ሳለ በመንግሥት ከሚቀርቡ ድጋፎችና ማኅበራዊ አግልግሎቶች ውጭ ሲደረጉ ቆይተዋል።    ለገዳማቱና አድባራቱ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ሳያሟሉ ከቱሪዝም ሀብት የሚገኘውን ገቢ ብቻ መሰብሰብ መንግሥትንና ሀገርን ውጤታማ አያደርግም።  መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን እያደረገ ያለው ድጋፍ አናሳ ወይም ጭራሽ የሌለ መሆኑን የተረዳችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ አቅም ካላት በራሷ ከሌላት ደግሞ ልጆቿን አስተባብራ በጊዜ ብዛት የወደቁ ገዳማትን ጠግና የዕለት ቀለብ የሌላቸውን ደግሞ የዕለት ቀለብ ሰፍራ ገዳማዊ ሕይወት እንዲመሩ አድርጋለች።  ከከተማ የራቁ ገዳማትና አድባራት አቅም በፈቀደ ሁሉ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስትሠራ ቆይታለች።

  

ቤተ ክርስቲያን ከምታደርገው ድጋፍ ውጭ አንዳንድ ግለሰቦች አድባራትንና ገዳማትን በራሳቸው ተነሳሽነት በመደገፍ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ይስተዋላል።  አድባራትን የሚሠሩ፣ የዘመመውን የሚያቀኑ፣የዕለት ቀለብ ለሌላቸው ገዳማት የዕለት ቀለብ የሚሰፍሩ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶችን በገንዝብ፣ በጉልበትና በአሳብ የሚያግዙ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች በርካቶች ናቸው።  ከእነዚህ ግለሰቦችና በጎ አድራጊ ምእመናን መካከል ፈለገ ጥበብ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።  ፈለገ ጥበብ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ “እመጓ” የተባለችውን የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን በስጦታ በማበርከት ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለተለያዩ ገዳማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እንዲውል አድርገዋል።  ከዚህ መጽሐፍ ሽያጭ ከተገኘው ከ ፬.፰ ሚሊዮን ብር በላይ ለሰባት ገዳማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ውሏል።  እነዚህ ሰባት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ  በባሕር ዳር ዩኒሰን ሆቴል ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ መልእክት ካስተላለፉት ፈለገ ጥበብ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ ጋር በዕለቱ ዝግጅት ክፍላችን አጭር ቆይታ አድርጓል።  ያደረግነውን ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።  መልካም ንባብ። 

ስምዐ  ጽድቅ፡- ገዳማት በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?

ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ፡- አንዳንዴ በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚስተዋለው ችግር የቱሪዝም ሀብቷን አሟጣ አለመጠቀሟ ነው።  አብዛኛው የቱሪስት መዳረሻዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች ናቸው።  እነዚህ መንፈሳዊ የቱሪስት መዳረሻዎች የትውልዱን ሞራል ከመገንባት ባሻገር መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡም ናቸው።  እነዚህን ቦታዎች በማስጎብኘት የአካባቢው ኅብረተሰብ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ማድረግ ይቻላል።  በተለይ በዚህ መንገድ የገዳማትንና አድባራትን ገቢ በመጨመር ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። 

ሰው አንድን መንፈሳዊ ቅርስ ለመጎብኘት ሲሄድ ከሚያገኘው መንፈሳዊ ርካታ ውጭ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።  ኢትዮጵያ ከሌላው ሴክተር ከምታገኘው ገቢ በበለጠ ከመንፈሳዊ ቅርሶች የሚገኘው ገቢ ይበልጣል።  ስለሆነም ከምንጊዜውም በላይ የበለጠ ገቢን ለመሰብሰብ ገዳማቱንና አድባራቱን መንከባከብ፣ ማደስና ራቸውን በገቢ እንዲችሉ የማድርግ ሥራ ተጠናክሮ መሠራት አለበት።  ይህ ሥራ ደግሞ የመንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያንና የሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ድርሻ ሊሆን ይገባል።  እኔም ባለኝ አቅም የድርሻዬን መወጣት ስለነበረብኝ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅሙ ባይኖረኝም የአእምሮዬ ውጤት የሆነውን መጽሐፌን (እመጓን) ለአድባራትና ገዳማት ማጠናከሪያ እንዲሆን ሰጥቻለሁ።  የመጀመሪያ ሥራዬ የሆነውን ‹‹እመጓ›› መጽሐፍ ለማኅበረ ቅዱሳን በመስጠት ማኅበሩም ከ፬ ሚሊዮን ብር በላይ በመሸጥ ለሰባት አድባራትና ገዳማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ አውሎታል።  ይህ ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ከ፬ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ገዳማቱን በዚህ ደረጃ መደገፍ ከቻለ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣ መንፈሳዊ ቅርሶቻችን ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ ማለት ነው።  

ስምዐ  ጽድቅ፡- ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ለሰባት ገዳማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ መዋሉ ይታወቃልና በቀጣይስ ከርስዎ ምን እንጠብቅ?

ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ፡- መጽሐፉ ዘመን ተሻጋሪ ነው።  ስለሆነም የመጽሐፉ ሽያጭ ይቀጥላል።  ከመጽሐፉ የሚገኘው ገቢም ለሌሎች ገዳማት ፕሮጀክቶች ማጠናከሪያ ይውላል።  ከዚህ ቀደም ከመጽሐፉ ሽያጭ ከተገኘው ገቢ ተጠቃሚ የሆኑ ሰባቱ ገዳማት ሙሉ በሙሉ ችግሮቻቸው ተፈትተዋል ማለት ባይቻልም ግን ተቃሏል ማለት ይቻላል።  ከእነዚህ ውጭ የሆኑ ሌሎች በችግር ውስጥ ያሉ ገዳማትን የተለያየ የገንዘብ ምንጭ እየፈለኩ መርዳት እፈልጋለሁ። ገዳማቱ በችግር ምክንያት ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ሊገቱ አይገባምና።  እንደ እኔ አሳብ በጣም ችግር ላይ የወደቁ ገዳማትን በመለየት ለመደገፍ እቅድ አለኝ።  አንዳንድ ገዳማት ምግብ ሌሎች ደግሞ ትምህርት ቤት ወይም መጠለያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።  ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በተቻለ አቅም ቀስ በቀስ ሟሟላት ያስፈልጋል።  በመሆኑም ዕድሜዬና አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ገዳማቱንና አድባራቱን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።  ከዚህ በኋላ በጽሑፎቼ ገዳማትና አድባራትን ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ።  በየጊዜው የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት አደርጋለሁ።  ‹‹እመጓ›› በሚል ርዕስ የጻፍኩትን መጽሐፍ ለገዳማትና አድባራት መርጃ እንዲውል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተችው ባለቤት ነች።  

በቀጣይም ገዳማትን ለመርዳት ከቤተሰቤና ከባለቤቴ ጋር በመተባበር አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ።  የሥራዬን ውጤት በዛሬው ዕለት በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በማየቴ እጅግ ተደስቻለሁ።  ገዳማቱ በእኔ የእጅ ሥራ መረዳታቸው ከፍተኛ ደስታ ሰጥቶኛል።  የሚገባኝን ያህል አደረኩ ባልልም ሌሎች ሰዎች ገዳማትንና አድባራትን ለመርዳት ምክንያት መሆኔ ያኮራኛል።  ለቤተ ክርስቲያን የግድ ገንዘብ ቆጥሮ መስጠት ላይቻል ይችላል ነገር ግን ባለን መክሊት ሁሉ መረዳት እንችላለን። 

ስምዐ ጽድቅ፡- ገዳማውያኑ እንዳይበተኑ ገዳማቱም ወደ ፍርስራሽነት እንዳይለወጡ ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ፡- የቱሪዝም ሀብት የሀገርን ክፍለ ኢኮኖሚ ከሚያነቃቁ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።  የቱሪዝም ሀብት ሲባል ደግሞ ካለን የተፈጥሮ ሀብት በተጨማሪ ባህላዊ ሃይማኖታዊ፣ አድባራት፣ ገዳማት፣ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን ያጠቃልላል።  እነዚህ  እንዳይጠፉ መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ለቱሪስት አመቺ ማድረግ አስፈላጊ ነው።  የቱሪዝሙ ተጠቃሚ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ባለመሆኗ ከመንግሥት በተጨማሪ ሁሉም ዜጋ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።  ሁሉም የአቅሙን ያህል ካደረገ ሲሰባሰብ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። 

ስምዐ  ጽድቅ፡- ጠንካራ ትውልድን  በጽሑፍ እንዴት መገንባት ይቻላል?

ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ፡- የቀደመውን ትውልድ ከአሁኑ ትውልድ ጋር ማነጻጸር ብዙ ባይጠቅምም የድሮውን ትውልድ ጥንካሬና የሞራል ልዕልና ከሁኑ ትውልድ ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል።  የደከመውን ትውልድ ከነቃው ትውልድ ጋር ማስተባበር ያስፈልጋል።  ደካማውን በመተው ጠንካራውን ደግሞ በማስቀጠል ነው ትውልድ ሊገነባ የሚችለው።  ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ጸጋ ስላላት ጨለማውን ሳይሆን ብርሃኑን ማየት ብንችል ሀገራችን ጥሩ ተስፋ ይኖራታል።  ሀገርንና ትውልድን ለመቅረጽ ከምንጠቀምባቸው ነገሮች አንዱ ጽሑፍ ነው።  ጽሑፉ በተለያየ መንገድ ሊጻፍ ይችላል።  ለማስተማርና ለማዝናናት ሊሆን ይችላል።  ትውልድን ለመቅረጽ ግን አንድነትንና የሞራል ልእልናን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ጽሑፎች መጻፍ አለባቸው።  ይህ ሲሆን ጠንካራ ትወልድን መገንባት ይቻላል።  

ስምዐ  ጽድቅ፡- በመጨርሻ ቀር የሚሉት ነገር ካል?

ፈለገ ጥበብ ደ/ር አለማየሁ ዋሴ፡- ሁላችንም የራሳችን አቅም አለን።  ያለን አቅማችን ተጠቅመንን ጃንጥላ ይዛ የምትለምነውን ቤተ ክርስቲያናችንን ከልመና ልናወጣት ይገባናል።  እኔ ምሳሌ የሆንኩት በርካታ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በሐሳባቸው የሚያግዙ እህትና ወንድሞችን ያመጣል ብዬ ስለማምን ነው።  ሀብታም ብቻ የሚሰጥ እንዳይመስለን፤ ደኀም ይሰጣል።  ነገር ግን ለመስጠት ለመርዳት መወሰንና ፍላጎት ማሳየትን ይጠይቃል።  ስለዚህ እኔ በሰጠሁት መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ለሰባት ገዳማት ፕሮጀክቶች ማጠናቀቂያ ሆኗል፤ የዚህ መጽሐፍ ሽያጭም እስካሁን ድረስ አልቆመም።  በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከመጽሐፉ በተገኘው ገቢ የተረዱ ገዳማት እንዳሉ ሆኖ ምንም የሌላቸውና ችግር ላይ የወደቁ ገዳማት በመኖራቸው ከዚህ በኋላ የሚገኘው ገቢ በሙሉ ለእነዚህ ገደማት ጥቅም ይውላል።

Read 484 times