Saturday, 26 June 2021 00:00

‹‹የቄስ መቃብሩ የሚሳምበት ጊዜ ይመጣል የሚባለው ሰው አልቆ አይደለም›› (ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል አንድ

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

ብዙዎች የበረሃው ምንጭ ይሏቸዋል። ቤተ ክርስቲያንን ማሳነጽ፣ የፈረሱትን ማሳደስ ምእመናንም አስተባብሮ ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት ጸጋቸው ነው። በዚህ ዕድሜያቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በየገጠሩ፣በየበረሃው ተዘዋውረው ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን አደራ ለመወጣት ዛሬም ይተጋሉ። በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁልጊዜ ከፊት ናቸው፤መጠየቅ ያለባቸውን ይጠይቃሉ፣መገሠፅ ያለባቸውን ይገሥፃሉ። ሲያስተምሩም እንደዚያው የዛሬው እንግዳችን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሙሉ ታሪካቸውን ከራሳቸው አንደበት እንስማ መልካም ንባብ        ስምዐ ጽድቅ፦ ብፁዕ አባታችን ሙሉ ስምዎን ከነ መዓርግዎ ቢነግሩን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ አባ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነኝ።  ስምዐ ጽድቅ፦ እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወትዎ ይንገሩን የት ተወለዱ? የት አደጉ? እናትና አባትዎ ስማቸው ማን ይባላል? ሞያቸውስ? ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ የተወለድኩት በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ልዩ ስሙ የትኖራ ሚካኤል የሚባል ቀበሌ ሰኔ ፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ነው። አባቴ  ስማቸው መምሬ ኃይለ ማርያም ድብቁ ይባላሉ እናቴ ደግሞ ወ/ሮ ስናፍቅ ወልደ ማርያም ይባላሉ የቄስ ልጅ ናቸው። አባቴ ጥሩ  የተማሩ ካህን ነበሩ፤ በሙያቸውም ሙሉ ሰው ነበሩ። ቅኔውን፣ ድጓውም፣አቋቋምን ፣ ቅዳሴውንም ሁሉ አጠናቀው የያዙ ነበሩ። በዚያ ላይ የሀገር አባት ነበሩ። ወንድሞች እና እኅቶች አሉኝ ከኔ በላይ ብዙ ልጆች ነበሩ ሞት ወስዶአቸዋል። ከኔ በታችም አሉ። 

 

ስምዐ ጽድቅ፦ የአብነት ትምህርትዎን የት የት ተከታተሉ? ምን ምን ተምረዋል?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ትምህርት የጀመርኩት በተወለድኩበት አካባቢ ነው። ገና በሕፃንነቴ   ከንባብ ጀምሮ ውዳሴ ማርያምን፣ መልክአ ማርያምን፣ መልክአ ኢየሱስን እያጠናሁ አድጌያለሁ ፤ዳዊቱን ጥሩ አድርጌ ደግሜያለሁ። እስከ ዲቁና ድረስ መጀመሪያ ከአባቴ ከዚያም አባ አፈ ወርቅ ከሚባሉ መምህር ዘንድ እንዲሁም አባ ወርቁ ከሚባሉ መነኵሴ ዘንድ በተከታታይ ተምሬአለሁ።

ስምዐ ጽድቅ፦ ቀጣዩን የአብነት ትምህርት የት የት ተከታተከሉ የትምህርት ቤት ገጠመኝዎን ጭምር ቢነግሩን?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ገጠመኜ የሚጀምረው ከልጅነቴ ነው። መዓረገ ዲቁናን ተቀብዬ በምቀድስበት ወቅት ነቀርሳ የሚባል ክፉ በሽታ አንገቴ ላይ ይዞኝ ለሰባት ዓመታት በመከራ ውስጥ ወድቄ ነበረ። በሽታው እየፀናብኝ መጣ መላ ሰውነቴ ፈነዳ፤ በተለይ በሽታው የጀመረበት አንገቴ ላይ ስለነበር ኃይለኛ መድኃኒት ሲቀበርበት ፈነዳ። የሚገርመው ውኃ ስጠጣ በፈነዳው በኩል ወደ ውጪ ይፈስ ነበር። ከዚህ የነቀርሳ በሽታ የዳንኩት በተአምር ነበር። በጊዜው በሽታው እየፀናብኝ ሲሄድ አለቅሳለሁ፤ እናቴም እኔን እያየች ታለቅስ ነበር። እውነት ነው ወደ ጉሮሮ መውረድ የነበረበት ውኃ አንገት ላይ ባለ ቀዳዳ ወደ ውጪ ከፈሰሰ በኋላ መዳን ተአምር ነው።   

በዚህ አደገኛ በሽታ ሰባት ዓመት ከተሠቃየሁ በኋላ ለጸበል ወደ ሚጣቅ አማኑኤል ሄድኩ። በጊዜው የተከተለኝ ሰው አልነበረም ብቻዬን ነበርኩ። እዚያ የምበላው ነገር ችግር ሆኖብኝ ነበር ለበሽታው ተብሎ አተር ስንዴ የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች አይበሉም። ባቄላ ብቻ ነበር የሚበላው ልመና እንዳልወጣ አቅም አልነበረኝም ውሻ እንኳ ተከላክሎ በየሰው ቤት ሄጄ ለምኖ መብላት አልችልም ነበር ፤ኅዳር የመኸር ወቅት ስለነበር ነዶ ከሚታጨድበት የገበሬ ማሳ ላይ  ቃርሚያ እየለመንኩ ጸበል መከታተል ጀመርኩ። ቀን ቀን ስለምን ውዬ ፲፩ ሰዓት እመለሳለሁ ‹‹ጨው በል›› የሚባል ቀዝቃዛ  ወንዝ አለ እዚያ ታጥቤ ዋናው ጸበል ስገባ በሽታዬ ቀለል ይለኛል። ጸበሉ እንደ ትኩስ ወተት ሞቅ ይላል ስጠጣው አንገቴ ላይ ባለው ቀዳዳ እንዳይፈስ በእጄ ጥብቅ አድርጌ ይዤው ነው። 

እንዲህ እያደረግሁ በመንፈቁ በአንገቴ ዙሪያ ያበጠው ሁሉ እንደ በረዶ ሟሟ የቈሰለው ዳነ ፤ሁሉም ሥቃይ አበቃ፤ እኔም ከእሥራት ተፈታሁ። በተአምራቱ ከተፈወስኩ በኋላ እዚያ መቀመጥ አልፈለግሁም፤ሕይወቴ ከተመለሰ እጄን ለልመና በመዘርጋት በምጽዋት መኖር አልተመኘሁም ትምህርቴን ለመቀጠል አሰብኩ፤በዚያ በኩልም አንኮበር ቅርብ ነበረና ቅኔ ለመማር ወደ አንኮበር አቀናሁ። አንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ስደርስ የቅኔ መምህሩ መምህር ወልደ ጊዮርጊስ ወጥተው ሽቁጥቁጥ ብለው ተቀበሉኝ። ጥሩና ታላቅ ባህታዊ አባት ነበሩ። ጻሎታቸው ምሁርነታቸውም ልዩ ነበር። ገና እንዳዩኘ በጣም አዘኑ የእግሬ ቅጥነቱ በጣም የሚያስፈራ ስብር ብሎ የሚወድቅም ይመስል ነበር። የምለብሳትም አንዲት በርኖስ ብቻ ነበር ያለችኝ በኃዘኔታ እያዩኝ ‹‹እንዴት ትሆነዋለህ? ልመናውንስ ትችለዋለህ ወይ?›› አሉኝ። እኔም ‹‹እግዚአብሔር ያውቃል›› አልኳቸው።

እንዳልኩትም እግዚአብሔር አወቀልኝ ‹‹ በሉ ጎጆ ሥጡት አሉ›› ተማሪ ትቶት የሄደው ጎጆ ቤት ነበረና እሱን ሠጡኝ እዚያ ገብቼ ትምህርቱን ጀመርኩ። ቅኔውን በደንብ የሚያውቅ አንድ ዓይነ ሥውር ነበረ እሱን እየመራሁ ያስጠናኝ ጀመር ሁሉም ነገር ወዲያው ገባኝ። እዚያው መምህር ለመሆንም ቻልኩ። 

ስምዐ ጽድቅ፦ እዚያ ምን ያህል ጊዜ አስተማሩ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ቅኔውን በደንብ ከለየሁ በኋላ ብዙ መቆየት አልፈለኩም ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄጄ መጽሐፍ መማር ፈልጌ ነበር፤ መምህሬ እዚያው እንድቆይ ይፈልጉ ነበርና ጠፍቼ እንዳልሄድ መጽሐፌን ደበቁብኝ። መጀመሪያ ሳይቸግራቸው ስለ ደብረ ሊባኖስ ነግረው ልቤን ያነሣሡት እርሳቸው ናቸው። አንድ ቀን ደብረ ሊባኖስ ደርሰው ሲመለሱ ‹‹ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ አዲስ ትምህርት ቤት ከፍተው የመጻሕፍት ትርጓሜያትን ለመማር ተማሪዎች እየተመዘገቡ ነው ጥሩ ትምህርት ቤት ተከፍቶአል›› ብለውኝ ነበር። እኔም  ወደዚያ ለመሄድ ስነሣ እርሳቸው እኔን ይወዱኝ ስለነበር እንድሄድ አልፈለጉም ነበር ሆኖም ግን እርሳቸው እንዳይከፋቸው በዚያ ትንሽ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ፈቃዳቸውን ጠይቄ ሲፈቅዱልኝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄድኩ። 

እዚያም እንደሄድኩ ወዲያው ተቀበሉኝ እግዚአብሔር ፈቅዶ አቡነ ባስልዮስ ለጸበል እንደመጡ ‹‹እንዲህ ያለ ተማሪ መጥቶአል›› ሲሏቸው አስጠሩኝና ስለመጣሁበት ቦታና ስለ ትምህርቴ ጠየቁኝ። ሁሉንም በዝርዝር ነገርኳቸወ። ወዲያው ዜማ ለመማር አባ ንጉሤ ከሚባሉ መምህር ዘንድ ገባሁ።  

እዚያ ስገባ ረጅም ሰዓት እጾም ሳላስቀድስ አልበላም ነበር በከንቱ ውዳሴ ተጠልፌ ነበር እነርሱም ‹‹ሳያስቀድስ አይበላም›› እያሉ ጦሜን ቁፋሮ ይዘውኝ ሲሄዱ በባዶ አንጀቴ መቆፈር አልቻልኩም እያዞረኝ አፈሩ ላይ እውድቅ ጀመር ። ውዬ ቂጣ ነው ጋግሬ የምበላው እንጀራ አልበላም ያ አቅም አሳጥቶኝ ለካ የሳምባ ምች መትቶኝ ስለነበር እያሳለ አስቸገረኝ። ሳንባዬን በበሽታው ተጠቅቶ ስለነበር መተንፈስ አቃተኝ። ዜማ እጮሃለሁ ብል አልቻልኩም። ቀለም ትምህርቱን ጨረስኩና ወደ ሌላው እሻገራለሁ ስል ትንፋሼ ስላጠረኝ ምንም ማድረግ አልቻልኩም። በበሽታዬ ምክንያት ዜማውን ትቼ ወደ ቅኔ ቤት መግባት አለብኝ ብዬ ወሰንኩና እንደገና ተመልሼ ወደ አንኮበር ሄድኩኝ። ከዚያም የሚያስለኝ የሳንባ ምች በሽታዬ ሲሻለኝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመልሼ መጽሐፍ ቤት ገባሁ።  

ስምዐ ጽድቅ፦ ወደ መምህርነት እንዴት መጡ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ፦ ብዙ ባልቆይበትም መመህርነትን የጀመርኩት በአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነው። ደብረ ሊባኖስ መጽሐፍ ቤት ገብቼ ከተማርኩ በኋላም በተማሪዎች ተመርጬ አስተማሪ ሆንኩኝ። እዚያ በአስተማሪነት እየሠራሁ ሳለ አቡነ ማቴዎስ እንሳሮ አካባቢ ሰቃ መድኃኔ ዓለም (በዛሬው አጠራር ሰሜን ሸዋ) የሚባል ደብር ያሠሩት ትምህርት ቤት ነበረ ለዚያ ትምህርት ቤት መምህር ይፈልጉ ነበርና መምህራችን እኔን ሰጡአቸው እንደታዘዝኩት በ፲፱፻፷ ዓ.ም እዚያ ሄጄ ማስተማር ጀመርኩ። ቦታው ሞቃታማ ስለነበር ወባ ያዘኝ የቀኝ ዓይኔም ክፉኛ ታመመ ብታከመውም ሊድን አልቻለም እስካሁንም ድረስ ያመኛል በደንብ አያይልኝም። 

ስምዐ ጽድቅ፦ ወደ ምንኵስናው ሕይወት  እንዴት ገቡ? መቼ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ከ፲፱፻፶ እስከ ፲፱፻፷ ዓ.ም ተማሪ ቤት ነበርኩ መጽሐፍ ቤት በ፲፱፻፷ ዓ.ም ሰቃ ሄድኩና ማስተማር ስጀምር ምንኵስናውንም የተቀበልኩት ከዚያ በኋላ ነው። ነገር ግን ከተፈጥሮዬ ገና ሕጻን ሁኜ የእግዚአብሔር መንፈስ እርሱ በመራኝ የምንኵስና ሕይወት ይታይብኝ ነበረ። መቁጠሪያውን ምን እንደሆነ እንዴት እንደሚቆጠር ሳላውቅ በእጄ ላይ አንጠለጥላለሁ፤አባቴ ለፍልሰታ ሰዓታት ሲሄድ ሌሊት ተከትዬ እሄዳለሁ። ብዙ ጊዜ ትኩረት የምሰጠው ወደ ብሕትውናው ነው። ምን ጥቅም እንዳለው አላውቅም ማዕድም ሙሉ ቀን ጾሜ ከወላጆቼ ጋር ነው የምቀርበው ታዲያ በዚህ ‹‹እርሱ ሳያስቀድስ አይበላም›› እያሉ በውዳሴ ከንቱ ነደፉኝ፤ ልጅ ደግሞ ሙገሳ ይወዳል። አንጀቴን አሥሬ ልክ ባሕታውያን የሚሠሩትን ለመሥራት እሞክራለሁ። ከወንድሞቼ ጋር አልተኛም ለብቻዬ ነው ቆጥ ሥር የምተኛው፤ መቁጠሪያዬን ይዤ  ሰዓታት እያዳመጥኩ ነው ያደኩት። ይህ አስተዳደጌ ነው ወደ ምንኵስናው ሕይወት ያስገባኝ። 

ስምዐ ጽድቅ ፦ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ትምህርትዎን ቀጠሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ አልቀጠልኩም ያኔ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ ደብረ ሊባኖስ መምጣቴን ማን እንደነገራቸው አላወኩም ግን ወደ አዲስ አበባ እንድመጣ በስልክ አስጠሩኝ። እንግዲህ ይህ የሆነው ደርግ ሊገድላቸው ትንሽ ሲቀራቸው ማለት ነው። ስደርስ ‹‹መተሐራ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እንድትሄድ›› ብለው ደብዳቤ ሰጡኝ። እኔ እንኳን በስብከት ካልሆነ አስተዳደር አልችልም ብያቸው ነበር። እርሳቸው ግን ‹‹አስተዳደርና ስብከት አንድ ነው፤ ያው ነው ግዴለም›› አሉኝና እሺ ብዬ ሄድኩ። መተሐራ ኃይለኛ ሙቀት ነበር ፀሐዩ በጣም ያቃጥላል እዚያም በአገልግሎት የቆየሁት ሦስት ዓመት ከሁለት ወር ነው።  

ስምዐ ጽድቅ፦ መዓርገ ጵጵስናን መቼ ተቀበሉ?  በጵጵስና መዓርግዎስ የት የት አገለገሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ መተሐራ እያለሁ ለጵጵስና ታጭቼ ውድድር ውስጥ እንደገባሁ ነገር ግን በድምጽ ብልጫ እንደወደኩ ተነገረኝ ። እኔም ‹‹ እኔ መቼ አቅሜ ይፈቅዳል ለምን ውድድር ውስጥ ገባሁ?›› ብዬ ነበር። ቅዱስነታቸው በድምጽ መውደቁ ለሞራሉ ጥሩ አይሆንም አሉና ወደ አዲስ አበባ መምጣት አለበት አሉ። ከኔ ጋር አባ መዘምር በኋላ አቡነ ቶማስ እሳቸውን መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል እኔን መርካቶ ተክለ ሃይማኖት መደቡን።

ከመተሐራ እንደመጣሁ ብርድ መታኝ እና ወደ ሦስት ወር ታመምኩኝ በዚያ ብዙ ተፈትኛለሁ። በመሀል ግን የመተሐራ ሰዎች እንድመለስላቸው ፓትርያርኩን ጠይቀው ነበርና እሳቸውም አስጠርተውኝ ‹‹ክርስቶስ ለማነው የሞተው?›› አሉኝ ‹‹ለሰው›› አልኩአቸው        ‹‹አንተም ለሰው ሙት እዚያ ይፈልጉሀል›› አሉኝ። ‹‹ከበረሃ ና አሉኝ መጣሁ፤ አሁን ደግሞ ወደ በረሃ ሂድ ብለው ካሉኝ እሺ እሄዳለሁ›› አልኳቸው። የተክለ ሃይማኖት ካህናት ደግሞ ‹‹እኛስ ልጆችዎ አይደለንም? ገና ሥራ መጀመራቸው መሄድ የለባቸውም በዚያ ጥሩ አስተማሪያችን ናቸው ብለው›› አቤት አሉ።

Read 818 times