የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ሚስተር ሰርጂ ላቭሮቭ የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ክርስቲያኖችን ከጥቃት በመከላከል ዙሪያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ማቅረባቸውን የሩሲያን መገናኛ ብዙኃን ዋቢ አድርጎ ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘገበ፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በቅንጅት ጉባኤ ሊያካሄዱ መሆኑን ሚስተር ላቭሮቭ ማስረዳታቸውን ዘገባው አስታውቆ በጉባኤውም የሮማን ካቶሊክ፣ የሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የቤላሩስ፣ የሊባኖስና የአርመን እንዲሁም የሚመለከታቸው የሌሎች ሀገራት ተወካዮች እንደሚገኙ ተገጧል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ ያሉ ክርስቲያኖች በሚደረስባቸው ተደጋገሚ ጥቃት አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ላቭሮቭ ማስታወሳቸውን ያስገነዘበው ዘገባው በኢራቅ፣ በሊቢያ እንዲሁም በሶርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በከፋ ሁኔታ መገኘታቸው ታውቋል፡፡
የሶርያ አረብ ኅብረት ክርስቲያኖችን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ መጠቆማቸውን ያስገነዘበው ዘገባው “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተጎጂ ክርስቲያኖች ድምፅ ከመሆን በተጨማሪ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ በመውሰድ የክርስቲያኖችን ሞትና ስደት ማስቆም ይገባል” ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡