በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓል ጠብቀው ጃንጥላ በመዘርጋት፣ ጨርቅ በማንጠፍ እንዲሁም ቄጠማ በመጎዝጎዝ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚለምኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። በአለባበሳቸው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መስለው ፤ቤተ ክርስቲያን እንደላከቻቸው አድርገው የሐሰት ደብዳቤ በማዘጋጀት እከሌ የተባለው ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ከፍጻሜ እንዲደርስ ለማድረግ፤ በእርጅና ምክንያት እየፈረሰ ያለውን እከሌ የተባለ ገዳም ለማሳደስ . . . ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ከምእመኑ ገንዘብ የሚሰበስቡ በርካቶች ናቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን፣ የእመቤታችንን፣ የቅዱሳንን፣ የሰማእ,ዕታትን እና የመላእክትን ሥዕለ አድኅኖ በመያዝ እና በስማቸው በመለመን ከምእመኑ የሚሰበስቡት ገንዘብ የትየለሌ ነው፡፡
በዚህ ሴቶች፣ ወንዶች በአጠቃላይ ከምእመን እስከ ካህን (እውተነኛ ናቸው ወይ? የሚለው አጠያያቂ ሆኖ) በሚሳተፉበት እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም በሚደረገው የመንገድ ላይ ሕገወጥ ልመና ከሚገኘው ገንዘብ ቤተ ክርስቲያን እየተጠቀመች ነው ወይ? ገንዘቡስ ለታለመለት አላማ ይደርሳል? የሚል ጠያቂ ቢኖር የግለሰቦችን አሊያም የቡድኖችን ኪስ ከማደለብ ውጪ ሌላ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም አንዳች ነገር እንደሌለው በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ረጅም ርቀት ላይ ሣር ጎዝጉዘው እና ድምጽ ማጉያ ይዘው ለማስቀደስ አሊያም ለማንገሥ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄደውን የዋህ ምእመን ከመንገድ አስቀርተው እጅ የሚያዘረጉ ባሕታውያን ሳይሆኑ ባሕታውያን ነን የሚሉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም አትገቡም ፤የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክሉአቸዋላችሁ›› (ማቴ. ፳፫፥፲፬) የተባለባቸው ወደ ቤቱ የሚገሰግሱትን ከመንገድ አስቀርተው ከበረቱ ውጪ በማለማመድ የራሳቸውን ኪስ እያደለቡ ሆዳቸውን የሚሞሉትን ተው የሚላቸው ማን ይሆን? የጅምር ቤተ ክርስቲያን ፎቶግራፍ ይዘው በየንግሡ ‹‹የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ማስጨረሻ›› እያሉ በየዓመቱ ገንዘብ በከረጢት የሚሰበስቡ አዛውንት እናቶችን ለልመናቸው ገንዘብ ከመለገስ ውጪ ‹‹ሕንጻው ምን ላይ ደረሰ? የሚል ጠያቂ የለም፡፡
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያንን ለማደስ አሊያም ለማሳነጽ ገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ በእውነተኛ መንገድ የቤተ ክርስቲያንን ትክክለኛ መረጃ ይዘው በትክክለኛ ሰነድ ገንዘብ የሚሰበስቡ ምእመናን፣ አባቶች፣ እናቶች የሉም ለማለት አይደለም። ነገር ግን በከተማው ውስጥ ሚዛን ደፍቶ የሚታየው ሕገወጥ ለማኞች መሆናቸውን ስንቱ ተገንዝቦት ይሆን?ሁሉም ለለማኙ ክፍል ገንዘብ ከመስጠቱ ባሻገር የሚለምኑላቸው አብያተ ክርስቲያናት መታደሳቸውን፣ መሠራታቸውን አልያም ለውጥ ማሳየታቸውን ጠያቂ የለም፡፡ ቢያንስ የሚለምኑለት ደብር የት እንደ ሆነ ትክክለኛ መረጃቸውን ለማረጋገጥ ሙከራ የሚያደርግም የለም፡፡ በዓላትን ጠብቀው ብቅ የሚሉት የቤተ ክርስቲያን አዛኝ የሚመስሉት ዣንጥላ ዘርጊዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለምነው የምእመናንን ኪስና መቀነት አራግፈው የራሳቸውን ኪስ እና ቤት ሲሞሉ ተው የሚላቸው አካል ሊኖራቸው ይገባል፡፡
የተደራጀ እና ምሉእ መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እዚያው ደጃፍዋ፣ ጉያዋ ሥር ተወሽቀው በስምዋ የሚነግዱትን እንዲሁም ሰድበው ለሰዳቢ አሳልፈው የሚሰጥዋትን የቤተ ክርስቲያን እንቅፋቶች መቆጣጠር ከርስዋ የሚጠበቅ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ለዓለም ድኅነት ቤዛ የሆነበትን ክቡር መስቀል ይዘው በየመንገዱ ምእመናን ካልታሳለማችሁ በማለት መጽሐፍ የሚያሻሽጡ እና ገንዘብ አምጡ የሚሉትን የስም ካህናት ቸል ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የከበረ ስም በእኩይ እና ርካሽ ሥራቸው እያስነቀፉ ዝም ማለት በሥራችሁ ቀጥሉበት፣ በርቱ እንደማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከለላ በማድረግ ምእመኑ በእነሱ የተነሳ ቤተ ክርስቲያንን እንዲንቅ፤ እምነቱን እንዲለቅ እያደረጉ ነውና ቤተ ክርስተያን አጥብቃ ልታስብበት፣ እውነተኛ ልጆችዋን ከሐሰተኞቹ ለይታ ልታውቅና ገደብ ልታበጅላቸው ይገባል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሥርዓተ አምልኮ የምትጠቀምባቸው እና በክብር የምትይዛቸው ቅዱሳት ሥዕላት እንደተራ እና አልባሌ ነገር በየመንገዱ ተዘርግተው ፀሐይ፣ አቧራና ብርድ ሲፈራረቅባቸው ማየት የእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህም ባሻገር የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና መፃረር፣ ክብርዋን ማዋረድ፣ በስምዋ መነገድ ነውና ይህን ለዘመናት የዘለቀ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ እኩይ አድራጎት መቃወም ከቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲሁም ከምእመናን ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልብስ ለብሰው ንዋያተ ቅድሳቷን በመጠቀም ሆዳቸውን ለመሙላት የምእመኑን ኪስ ሲያራቁቱ ዝም ማለት የቤተ ክርስቲያንን ክብር ማዋረድ ብቻ ሳይሆን በምእመናን ፊት ክብርዋን መቀነስ ነውና ቤተ ክህነቱ አጥብቆ ሊያስብበት ፣ ለምን ብሎ ሊጠይቅና በሕግ እስከመጠየቅ ሊደርስ ይገባል። ዛሬ እንኳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድ ተራ ሰው በስሙ ሌላ ሰው አንድ ነገር ሲያደርግ መብቱን ለማስከበር ፊት ለፊት በሚቃወምበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በአለባበስዋ እና በንዋየ ቅድሳትዋ ሲነገድ ስለ መብትዋ እና ስለ ክብርዋ ልትቆም ይገባል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንም በየመንገዱ ጥላ ዘርግተው፣ አንሶላ አንጥፈው እና ሣር ጎዝጉዘው ክብር የሚሰጣቸውን ቅዱሳት ሥዕላት በቧራ ላይ አንጥፈው መለመኛ ሲያደርጉ ለምን ብለው መጠየቅ ይገባቸዋል። ምእመናን በቤተ ክርስቲያን የሚሳለሟቸውን የሚሰግዱላቸውን ቅዱሳት ሥዕላት ከክብር ቦታቸው አውርደው መለመኛ ሲያደርጓቸው ገንዘብ በመስጠት ሊተባበሩአቸው ብሎም ለሚቀጥለው ወንጀል እንዲገፉበት ሊያበረታቱአቸው አይገባም፡፡ ለምን? ብለው መጠየቅ ‹‹መሆን የለበትም›› ብለው መቃወም ከእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ የሚጠበቅ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን እድሳት እና ሥራ ስም የሚሰበሰቡ ገንዘቦች የመጨረሻ መድረሻቸውን ማወቅም አስፈላጊ ነው። ምእመናን ሊረዱ የሚገባቸውን አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት የስሚ ስሚ ከመስማት እና ሜዳ ላይ ገንዘባቸውን ከመስጠት ከቦታው ድረስ በመሄድ ቢለግሡ ከበረከቱም ተሳታፊ ከመሆናቸውም ባሻገር ገንዘባቸውን በማያስፈልግ ሰው ከመሰረቅ ይድናሉና ሊያስቡበት ይገባል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የሆነ መዋቅራዊ ሥርዓት ያላት ምሉእ እንደመሆንዋ መጠን ከመንጋዋ ተለይተው፣ ከበረትዋ ወጥተው እና ቅዱሳት ንዋያትዋን ተጠቅመው በስሟ ስለሚነግዱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ለምእመናን ግንዛቤ መስጠት እንዲሁም ገንዘባቸውን ለማን የት መስጠት እንዳለባቸው ዘወትር ማስተማር ይጠበቅባታል እንላለን፡፡