ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን ስታከናውን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላት አይደለም።ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ከምሥረታዋ ጀምሮ ብዙ መሰናክሎችንና ውጣ ውረዶችን አልፋለች።በረጅም ጊዜ ታሪኳ የወጣችውን አቀበት፣ የወረደችውን ቁልቁለት፣ ያቋረጠችውን ሸለቆና ሜዳ የተሻገረችውን ማዕበል አልፋ እንዲሁም የቅዱሳን አባቶቻችን ተጋድሎና መሥዋዕት ታክሎበት እነሆ እዚህ ዘመን ደርሳለች።ቅዱሳን ሰማዕታት አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን እዚህ እንድትደርስ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በዚህ ዘመን ያለን ትውልዶች በመዘከር ከእነርሱ ሰማዕትነት ተምረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀን ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ ድርሻ አለብን።ሐዋርያዊት፣ ዓለም አቀፋዊትና ኵላዊት የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ጠንቅቀን በማወቅ ለሌሎች በማሳወቅ የቤተ ክርስቲያናችንን እውነተኛ ገጽታ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን በዘመናት ሂደት ውስጥ በመንግሥታዊ ሥርዓትም ሆነ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተፈትናለች፤ እየተፈተነችም ትገኛለች። ከ፲፱፻፷ዎቹ ዓ.ም ወዲህ ጀምሮ የነበረውን የቤተ ክርስቲያን ፈተና ብናስብ እንኳ አብዛኛውን ጊዜ መንግሥታዊ መዋቅርን የተላበሰ ነው።አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደርሱት የነበረው ፈተና እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታዊ ሥልጣንን የያዙ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በመተዳደሪያ ደንባቸው ሳይቀር ቤተ ክርስቲያንን ‹‹በጠላትነት›› ከመፈረጅ አልፈው ‹‹የድህነትና የኋላ ቀርነት›› ምሳሌ ሲያደርጓት አስተውለናል።በዚያ መተዳደሪያ ደንባቸው መሠረትም ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድዷትና ሲዘርፏት ኖረዋል።ከዚያ አለፍ ሲልም በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የላቁና የነቁ የአገልግሎት ቦታ ተነፍጓቸው እንዲሁ ሜዳ ላይ ቀርተው ቤተ ክርስቲያን “የካድሬ” መዋያ አድርገዋት ነበር።ሀብት ንብረቷን ከመዝረፍ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ከሁለት በመክፈል በዶግማዋና በቀኖናዋ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደልን ፈጽመዋል፡፡
በተለይ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች እንደመሰከሩት (ለአብነትም ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ) ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከሠላሳ በላይ አብያተ ክርስቲያናት በግፈኞች መቃጠላቸውን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን መገደላቸውን እንዲሁም በሚሊዮኞች የሚቆጠሩት ምእመናን መፈናቀላቸውን አትቷል፡፡
በዚህ ሁሉ በደልና ግፍ ውስጥ የተፈሩና የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መንግሥትን የካሳ፣ የመልሶ ማቋቋምና ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ ዋስትና ጥያቄ በጠየቁበት ወቅት ጉዳዩተገቢውን መፍትሔ ሳያገኝ ቀርቷል።የልብ ልብ የተሰማቸው የጥፋት ኃይሎችም በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ በርካታ ውድመት አስከትለዋል።በዚያ ወቅትም የቤተ ክርስቲያን መቃጠል የምእመናን መገደልና መሰደድ እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው መውደም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ፍጆታ ከመሆን በዘለለ ‹‹መንግሥት›› በጥፋተኞቹ ላይ የወሰደው አስተማሪ ርምጃ ባለመኖሩ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን የህልውና ሥጋት ላይ ጥሏቸዋል።“መንግሥት” ችግሮቹን በአስቸኳይ እንዲያስተካክል በቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው የሥልጣን ርከን ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠይቅም እስካሁን ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ተገቢ መልስ አልተመለሰላትም፤ ክብሯ አልተጠበቀላትም።የወጣ የወረደውና የሚዲያ አጋጣሚ ያገኘው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን እየዘለፈና እያንቋሸሸ ሲቀጥል እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አንጡራ ሀብት የሆኑ ይዞታዎቿን፣ የእምነት ተቋማት፣መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያለሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደቅርጫ ሲከፋፈሏቸውና ቤተ ክርስቲያን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ጭምር ስትከለከል እያስተዋልን እንገኛለን።ሀገርን ከነክብሩና ከነፊደሉ ያስረከበች ታላቋ ቤተ ክርስቲያን ሀገራዊ ውለታዋና ድርሻዋ ተዘንግቶ ሁሉን በእኩል ያስተዳድራሉ ተብሎ ኃላፊነት በተሰጣቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት አማካይነት ፍትሕ ተነፍጋ ማየት እጅግ ያሳዝናል።ድርጊቱም ይህ ትውልድ የቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር ለማስጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ መውሰድ እንዳለበት ያስተምራል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በእምነት የማይመስሉን አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሆን ብለው በቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ላይ እየፈጸሙት ያለው ነውር አዘል ድርጊት ይቅር የማይባል ነው።በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ከቤተ ክርስቲያን ይዞታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ሕግንና መመሪያን መሠረት በማድረግ ችግሮቹ በሰላም እንዲፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያየ ጊዜ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በደብዳቤ ጠይቋል።በዘንድሮው የ፳፻፲፫ ዓ.ም የግንቦት ወር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ መጠናቀቁን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።ውሳኔ ካሳለፈባቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል በክርስቲያኖች ሞት፣ ስደት፣ ንብረት ዝርፊያና፣መንግሥት ክርስቲያኖችን መልሶ በሚያቋቁምበት ሂደት ዙሪያ ሲሆን በተለይም ደግሞ በዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ እየተስተዋለ ያለውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ መንግሥት እንዲገታና የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ሁሉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሠራላቸውና በአስቸኳይ ለቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩ በአስቸኳይ እንዲፈታ ከጠየቀበት አካባቢ መካከል በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ የለሃ ደ/ሣ/ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታ አንዱ ሲሆን ይዞታውም ተከብሮ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ እንዲሆን አሳስቧል።ይህንን ቦታ የወረዳው ባለሥልጣናት በማን አለብኝነት ለሌላ ተግባር ማዋላቸውን ሲኖዶሱ አስቀድሞም ለመንግሥት የበላይ አካላት አስረድቷል።በተመሳሳይ መልኩ በሀድያ ዞን በሆሣዕና ከተማ የአካባቢው ፕሮቴስታንት የመንግሥት ባለሥልጣናት በበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ላይ ያደረሱት በደል እንዲስተካከል ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል።በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአፍሪካ ሕብረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኘውንና ቤተ ክርቲያን ለማስፋፊያነት የጠየቀችው ቦታ ይዞታው እንዲከበርላት ጥያቄ ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ያቀረበች ቢሆንም ከተማ አስተዳደሩ ጥያቄውን ወደጎን በማለት ቦታውን ለሌላ ቤተ እምነትበመስጠት የእምነት ተቋማትን የርቀት መመሪያን ያላከበረ ድርጊት እንደፈጸመ አንሥቷል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኘውን የመስቀል ዐደባባይ ነባር ስያሜ ለመቀየር እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ አንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች አደብ እንዲገዙ ካሳሰበ በኋላ መንግሥትም ይዞታው የቤተ ክርስቲያን መሆኑን ተረድቶ ይዞታውን እንዲያስከብርላትና ቦታው የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ በሚታትሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አስተማሪ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ከዚህ ባለፈም በአጋጣሚም ሆነ ሆን ተብሎ ‹‹የመስቀል ዐደባባይ›› የሚለውን ነባር ስያሜ ‹‹ጎግል ማፕ (Google Map) ላይ ለመቀየር ጥረት ያደረጉና በቀየሩ አካላት ላይ የማጣራት ሥራ ተሠርቶ መንግሥት አስተማሪ ርምጃ እንዲወስድ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል። ከዚህ በተጨማሪም የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የሆነው ጃን ሜዳ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተሠርቶለት ለባለቤቷ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ባሉ አካባቢዎች ከይዞታ ጋር ተያይዞ የሚነሡ ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱ ተጠይቋል።
የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተሠርቶ ለቤተ ክርስቲያን እስኪሰጥ ድረስ ከይዞታዋ ጋር የሚገናኙ ማንኛቸውም ዓይነት ድርጊቶች ከመፈጸማቸው በፊት የቤተ ክርስቲያንን ይሁንታ ማግኘት እንደሚያስፈልግና በዚሁ አግባብ ተፈጻሚ እንዲደረግ ተገቢውን አቅጣጫ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥትን ጠይቋል። በአጠቃላይ ከይዞታ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች በአስቸኳይ ተፈትተው የቤተ ክርስቲያን የቀደመ ክብሯና መብቷ ተጠብቆ እንድትኖር አባቶች፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ በየደረጃው ላሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚል ደብዳቤ ቢጽፉም ከዚህ ቀደም ካለው ልምድ በመነሣት ተፈጻሚነቱ እስካልተገመገመ ድረስ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አይቻልም።
ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም ቢሆን የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን የማሳለፍ ችግር የለባትም፤ የውሳኔ ሐሳቦቹ ተፈጻሚነት ሲፈተሽ ግን ከተፈጸሙት ጉደዮች ያልተፈጸሙት ይበዛሉ። ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት የምታቀርባቸውን ‹‹የይፈጸምልኝ›› ጥያቄዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የአፈጻጸም ሂደቱን መገምገምና የተፈጸሙና ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መለየት ያስፈልጋታል። ከተለዩ በኋላ ደግሞ የተፈጸሙበትንና ያልተፈጸሙበትን ምክንያት መረዳት ጠቃሚ ነው። የአፈጻጸም ሂደቱን መገምገምና አቅጣጫ ማስቀመጥ ከተቻለ የቤተ ክርስቲያን ያስፈጻሚነት አቅም ያድግና በሕግና በሥርዓት የመመራት ልምድ እንዲኖራት ያደርጋታል፡፡
ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ አካሄድ ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት የሌሎችን የጉዳይ አፈጻጸም ሂደት መከተልና መገምገም አለባት። ሌሎች ቤተ እምነቶች ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ቀላል “ዲፕሎማሲ” ጉዳያቸውን ማስፈጸም ከቻሉ የቤተ ክርስቲያን ክፍተት ምን መሆን እንደሚችል መረዳት ጠቃሚ ነው። ለቤተ ክርስቲያናችን መገፋት ዋና መንሥኤ ነው ተብሎ የሚታመነው ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱና በአገልጋዮችና በምእመናን መካከል አንድነትና ትብብር መጥፋቱ ሲሆን ይህም ጠንካራዋንና ተፅዕኖ ፈጣሪዋን ቤተ ክርስቲያን እንዳናይ ብሎም እንድናጣት አድርጎናል። ሰማያዊ ሥርዓቷ በፖለቲካ ሰዎች መጠለፉ ቤተ ክርስቲያን ጊዜዋን ከሐዋርያዊ ተልኮዋ ውጭ በሌላ ነገር እንድታሳልፍ አድርጓታል። በዚህ ዘመን የውጭ አካላት አጀንዳ ተቀባይ ሆና አጀንዳውን በማርገብ ብቻ ተጠምዳ መደበኛ አገልግሎቷን እንዳትፈጽም ብሎም ክብሯንና መብቷን እንዳታስከብር ሆን ተብሎ እየተሠራባት ይገኛል፡፡
ለእነዚህ ወቅታዊና ዘላቂ ችግሮች መፍትሔዎቻቸው ምንድነው ከተባለ ደግሞ ውስጣዊ አሠራርን ማሻሻል፣ አንድነትን መጠበቅ እንዲሁም ከፖለቲካዊ አመለካከት ጥገኝነት ተላቆ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት መሠረት ያደረገ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመፈጸም መትጋት ነው። በምእመናንና በምእመናን መካከል፣ በአገልጋዮችና በአገልጋዮች መካከል እንዲሁም በምእመናንና በአገልጋዮች መካከል ያለውን ልዩነትና መገፋፋት ማጥበብ ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻውም ማስተካከል አስፈላጊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ከቀበሌያዊና ከሀገር አቀፍ አስተሳሰብ ወጥታ አገልግሎቷን ዓለም አቀፍ ለማድረግ መትጋት አዋጭ ነው። እነዚህንና መሰል ስልቶችን ቤተ ክርስቲያን በቅጡ መተግበር ከቻለች አሸናፊነቷ እየጎላ በአንጻሩ ችግርቿ ደግሞ ላይመለሱ እየከሰሙ ይሄዳሉ።
ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር