Saturday, 07 August 2021 00:00

‹‹የቄስ መቃብሩ የሚሳምበት ጊዜ ይመጣል የሚባለው ሰው አልቆ አይደለም›› (ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል ሦስት

Written by  መጽሐፈ ሲራክ
  የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው ተከታታይ እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡                  በደርግ ዘመን ጃንሆይን ገፍተው ጥለው ‹‹እግዜር የለም›› የሚል ሥርዓት እና መሪ መጣ፡፡ ቤተ ክርስቲያን አድሃሪ ናት ተብላ ንብረቶቿ በሙሉ ተወረሱ፡፡ እንደሚታወቀው ፍልስፍናው ግራ እጅ አውጥቶ ‹‹እናሸንፋለን›› ነው እንጂ እግዚአብሔር ይመስገን ማለት አይባልም ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ለጉዳይ ስንሄድ አቤቱታችንን ይሰማሉ፣ ያልናቸውን ለመፈጸም ይሞክራሉ፡፡ እንዲያውም ፍልስፍናው ስለሚያስቸግራቸው በይፋ አይናገሩ እንጂ በእምነት ጉዳይ አንዳንዶቹ ህሊናቸው ቅር እያለው እንደሆነ       ይታወቃል። ልጆቻቸው ክርስትና እንዳይነሱ

ይከለክሉ ነበር፡፡ ግን ሴቶቻቸው ፣ሚስቶቻቸው ልጆቻቸውን ወደሌላ ራቅ ወዳለ ቤተ ክርስቲያን እና ሰዎች ወደማያውቁአቸው ቦታ ሄደው ክርስትና አስነስተው ይመጡ ነበር፡፡ ባሎቻቸው ያኔ ተከታትለው ለምን ክርስትና አስነሳሽ አይሉም ነበር፡፡

 

የሦስቱ ማርክስ ኤንግልስ እና የሌኒን ጉዳይ ሆኖባቸው ተቸግረው ነበረ ያው ጊዜ ለወጠው እሱም ወደቀ፡፡ የእነሱ ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን እናጠፋለን ነበረ ግን ሊያጠፏት አልቻሉም እግዚአብሔር ጠብቆ አሻገረን፡፡

የኢህአዴግ መንግሥት ግን ለቤተ ክርስቲያን ብዙም አልተመቸም፡፡ ይህ  በጣም የሚያሳዝን  ነው፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ሰዎቹ በክርስትናው ውስጥ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ወላጆቻቸው ክርስቲያኖች ናቸው፤ በእምነታቸው የሚታሙ አይደሉም፡፡ እኔ ፳ ቀን ያህል ትግራይ ተቀምጫለሁ፣ ብዙ ቦታም ዞሬያለሁ እናቶቻቸው በእግራቸው ፣ በጉልበታቸው እየሄዱ ሲጸልዩ በዓይኔ አይቻለሁ፡፡ በሌሊት ሁሉ ምህላ ሲያደርሱ አይቻለሁ። ልጆቹ ግን በጭራሽ ተለውጠዋል፡፡ እኔ እራሴ ዝም አላልኩም አቶ ስብሀት ነጋ የሚባለውን የኢህአዴግ ባለሥልጣን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይመጣ ነበርና አንድ ጊዜ ‹‹እናንተ የክርስቲያን ልጆች ናችሁ፤ ኦርቶዶክሳውያን ናችሁ ሙስሊም አይደላችሁም፤ ስልጣን አግኝታችኋል ነገር ግን አንድ ቀን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታችሁ ስትጸልዩ፣ ስትሰግዱ እጅ ስትነሱ ታይታችሁ አታውቁም፡፡ የክርስቲያን ልጆች ሆናችሁ እንዲህ የሆናችሁት ምክንያቱ ምንድነው? ለምሳሌ እስላሞች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ መጀመሪያ መስኪድ ነው የሚገቡት ሰግደው ነው ወደ ሥራ የሚገቡት አልኩት›› በጊዜው መልስ አልሰጡኝም፡፡ ‹‹ባህል እና ቱሪዝም ሚንስትሩ ወንድ ነበሩ ኀላፊው አሁን ሴት ሙስሊም አድርጋችኋል፡፡ ለምሳሌ አክሱም ሄዳ ይሄ ቅርስ ምንድነው ቢሏት? ምን ታውቃለች እርስዋ እስላም ናት ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?›› ብዬ ስጠይቀው አይ ይህችንስ ማስታወሻ ይዝባታለሁ ሲል ትዝ ይለኛል፡፡ 

አጠቃላይ በዘመናቸው ሃይማኖቱን የማዳከም ነገር በግልፅ ይታይባቸው ነበረ፡፡ በእነርሱ ዘመን ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ሃይማኖት ተዳክሞአል፡፡ ክብርዋንም ዝቅ አድርገው አዋርደዋታል ይሄ ለእነርሱም አልጠቀማቸውም፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፦ ከሦስት ዓመት ወዲህስ ቤተ ክርስቲያን ምን ትመስላለች?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ገና ነው እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና ነው፡፡ ዶክተር ዐቢይ አነጋገሩ ጥሩ ነው ሲናገር ልብ ይገነባል ነገር ግን በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ነገር በጣም ተናድጄበት ነበረ፡፡ ለምንድነው ክርስቲያኖች ሲታረዱ ዝም የሚለው?

ለምንድነው ‹‹አዝነናል›› እንኩዋን የማይለው? ሄደን እንጠይቅ ብዬ ጮኼ ነበረ፡፡  እኔ ሌላ ምንም ጥላቻ የለኝም እወደዋለሁ ሰውየውን በተለይ ‹‹ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን›› ያለው ኃይለ ቃል በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከጃንሆይ ወዲህ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ፈጣሪ ይባርክህ›› እያለ ሲናገር የሰማሁት እሱን ነው ከመሪዎቹ፡፡ ከጃንሆይ ወዲህ የኢትዮጵያን ስም ሲጠራ የሰማሁት መሪ የለም ይህ ሰውዬ ሳይሻል አይቀርም ብዬ እምነት ጥዬበት ነበረ፤ አሁን ወደ ውጪ ሄዶ ለሱዳን ‹‹እናዝናለን›› ብሎ ኀዘኑን ሲገልጽ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ሲታረዱ፣ በቆንጨራ ሲጨፈጨፉ አንድ ቀን ስለ ንጹሐኑ ደም ‹‹እናዝናለን›› ብሎ አልተናገረም ፤ የኀዘን ቀን አላወጀም በዚህ ምክንያት ሄደን እንጠይቀው ብዬ ፲፫ ሰዎች ሆነን ልንጠይቀው ቀጠሮ ይዘንም ነበረ ባጋጣሚ ጦርነቱ ተፈጠረ፡፡ አሁንም ብልጽግና የሚባለው እያለ ክርስቲያኖች የሚጨፈጨፉ ፣ ሲሞቱ ዝም የሚል ከሆነ እነርሱም አሉበት፤ክርስቲያኖችንም ለማጥፋት የተነሡ ናቸው ብለን እንጮሃለን ባይ ነኝ እኔ፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፦ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦርነቱ በተጋመሰ ሰዓት ብቅ ብለው ምንም ነገር እንዳልሠራ እጅ እግሬ ታስሮ ነበር ሲሉ ነበር ምናልባት እሱ እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችል ይሆን?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ምክንያት ከሆነ አዝነናል፡፡ እውነት ነው ወይ? ይህ ነገር እውነት ከሆነ ልብ ይነካል፡፡ እንኩዋን እግዚአብሔር አትርፎ ለዚህ አበቃው ነው የምለው፡፡ ወደፊት የከዚህ በፊቱ ቢደገም ‹‹እንዲህ ብለህ አልነበረም ወይ? ዛሬ ማን ያዘህ ዛሬ ነፃ ነህ ክርስቲያኖች ሲጨፈጨፉ ለምን ዝም ትላለህ? በማለት ፊት ለፊት ስለመብታችን እንጠይቃለን ባይ ነኝ እኔ፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፦ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብናነሳ ከሦስት ዓመት ወዲህ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ታርደዋል፤ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ብዙ ሰቆቃ ደርሷል ስለዚህ  ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳት ምን ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦  እሱማ ምኑ ይነገራል እኛ አልሞትንም እንጂ ሞተናል እኮ፡፡ ይኼ ኀዘኑ ልዩ ነው አሁንም አለን ለማለት አያስደፍረንም፡፡ እግዚአብሔር የሚሠራው አይታወቅምና እናያለን፡፡ የሽግግር ወቅት ነው ተብሎ የተደረገም ከሆነ እግዚአብሔር ምሕረቱን ያምጣና ቀን ያውጣልን እስካሁን ቀኑ ጨልሞብናል ነው የምለው፡፡  

ስምዐ ጽድቅ፦ ቤተ ክርስቲያን ዳግም መሰል ጥቃቶች እንዳይከሠቱባት ምን መሥራት አለባት?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦  ማንም ሰው ቢሆን ጥቃት አይወድም፡፡ አሁንም ቢሆን ጠንከር ብሎ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ መከላከል ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሔም የሚመጣበት ነገር ላይ ተግቶ መሥራት አስፈላጊ ነው።  ዝም ብሎ ምን ይደረግ እያሉ መደብደብ ከሆነ ጨርሶ ትጠፋለች፡፡ አሁን በሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን ፣በአቤቱታም ቢሆን በሆነው ነገር ሁሉ ባለሥልጣን ለሆነውና ለሚመለከተው አካል የጉዳዩኝ አሳሳቢነት በግልጽ በማቅረብ መሞገት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ መጮህ ነው፡፡ ይሄው ነው መድኃኒቱ፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፦ በአገልግሎት ዘመንዎ የገጠመዎን ክፉም (መጥፎ አጋጣሚ) የሚሉት ወይም የተደሰቱበት አጋጣሚ ካለ ቢነግሩን?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ መጥፎ ገጠመኝ እና እጅግ ያዘንኩበት ጊዜ ቢኖር አርባ ምንጭ ላይ በቤተ ክርስቲያኔ እና በሃይማኖቴ ላይ የደረሰው አድሎአዊ አሠራር ባየሁ ጊዜ ነው፡፡  አርባ ምንጭ አንድ አራት ዓመት ነበርኩ የከተማዋ ከንቲባ ፕሮቴስታንት ነው፡፡ እንደምናስታውሰው ኢህአዴግ እንደገባ ቦንኬ የሚባል ፈረንጅ የፕሮቴስታንት ሰባኪ ወደ ሀገራችን መጥቶ ነበር፡፡  በጊዜው ይህ ፕሮቴስታንት ከንቲባ ሥልጣኑን ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት ብሔራዊ ሃማኖት ለማድረግ ሞክሮ ነበረ፡፡ የኛን የሃይማኖት ማክበሪያ ቦታ እነሱ ሊገለገሉበት ፈለጉ፡፡ እኔም ‹‹ልክ አይደለም የዛሬ ፴፭ ዓመት ቁጥቋጦ መንጥረን ያቀናነው፣አሐዱ አብ ብለን የቀደስንበት ቦታ የኛ ነው ልትጠቀሙበት አትችሉም›› አልኩኝ ‹‹የኛ ነው እንጂ የናንተ አይደለም›› ብዬ ተከራከርኩ፡፡ እዚህ እናከብራለን ስትሉ ወንድማማቹ ሕዝብ ይጋጫል እና መሆን የለበትም ብዬ ማሳሰቢያ ሰጠሁ ነገር ግን አልሰማኝም፡፡

በመጨረሻም ማመልከቻ ጻፍኩ ‹‹ ይህቺ ነፍጠኛ ቤተ ክርስቲያን ዘላለም አምባገነን እናንተ ብቻ ናችሁ ወይ የኛም ይከበራል›› አለ፡፡ ‹‹ሜዳ ሞልቷል ሕዝብ አታጣሉ ከሌላ ዘንድ ሄደችሁ አክብሩ›› አልኩ  የሰማኝ የለም፡፡ ሃኀምሳ ሽማግሌዎችን ላኩበት የከተማው ከንቲባ ሊሰማን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህን ጊዜ ሕዝቡ ከሊስትሮ ጀምሮ ተነሣ ‹‹እርስዎ የሚችሉትን አድርገዋል አሁን የኛ ፋንታ ነው›› አሉ፡፡ ድንኳን ተተክሎ ካህናት ምሕላ ሲያደርሱ ፖሊስ በጎመድ እንዲመታቸው አስደረገ ይህን ጊዜ ወጣቱ ተነሣ ከአባቶቻችን ፊት እንሞታለን ብሎ ከወታደር ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጠ መናፍቃን በአቦጀዲ ጽፈው የሰቀሉትን ጥቅስ በሙሉ ከከተማው አውርዶ አቃጠለ፡፡ አርባ ምንጭ ላይ ሦስት ቀን ሙሉ መንግሥት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በመጨረሻም የክልሉ ፕሬዚደንት መጥቶ ‹‹ሠራዊትዎን ሰብስቡልኝ›› አለ እኔም ‹‹ምንም ሠራዊት የለኝም›› አልኩት፡፡ ያን ጊዜም ሰዓት እላፊ አውጀው ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ የተገኘ ሰው እንዲመታ ወሰኑ። እኔም ልጆቼን ድንኳን ነቅለው በግዜ ወደ ቤት እንዲገቡ አዘዝኩ፡፡ የኔ መኪና ታስሮ ስለ ነበር እኔንም በሌላ መኪና ወደ ቤት ወሰዱኝ ልክ እቤት ስገባ ደመና በሌለበት በደረቅ ሰማይ በረዶ ዘነበ፤ዶፉን አወረደው ወታደሮቹ ልጆቹን ለመደብደብ ብዙ ሠራዊት ተደብቆ መጣ ሲያይ ምንም ነገር የለም ከተማው ጭር ብሏል፡፡   

የክልሉን ፕሬዚደንት ከንቲባውን ጠርተው ‹‹የታለ መንግሥት የሚገለብጠው ሠራዊት?›› አሉት፡፡ በአመራር ያበላሸኸውን አንድ መነኩሴ በልጦሃል ፤ ኀምሳ ሽማግሌ ላከብህ ከዚህ ወዲያ ምንድነው የምትፈልገው? ለምን እንዲህ አደረግህ›› አለው ወታደሮቹም ለሊት ሰው ሳያያቸው ከከተማው ወጥተው ሄዱ፡፡ እኔም አቤቱታዬን ጽፌ ወደላይ ሄድኩኝ፡፡ ነገሩ ሲመረመር እነሱ ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ፤ምክንያቱም እኔ ሕጉን ይዤ ነበር የተጓዝኩት እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉን ነገር ድል አድርገን ሃይማኖቱን ቦታውንም አስከብሬ  እስከ ዛሬ ድረስ ቦታው እንዳለ ነው፡፡ በጊዜው ያ ትንሽ ያሳዝነኝ ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን ቢያንገላታኝም ድል የኔ ስለነበረ እግዚአብሔርን አመስግኛለሁ፡፡ 

በሕይወቴ የተደሰትኩበት ቀን ኢየሩሳሌም የሔድኩ ቀን ነው፡፡ ከዚያ ደርሼ ከአውሮፕላን ስወርድ መሬቱን ስሜያለሁ፡፡ ክርስቶስ የተወለደበት፣ያስተማረበት ፣ድኅነተ ዓለም የፈጸመበት ሀገር ገባሁ ብዬ፡፡ በልጅነቴ ቅፍርናሆም እያልኩ ወንጌለ ዮሐንስ ሳነብ ደስ ይለኝ ነበረ፡፡ አሁን በእግሬ ረገጥኩት ተመስገን ብዬ የመጨረሻ ደስታ የተደሰትኩት ያኔ ነው፡፡  

ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡኝ ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡

 

Read 292 times