Saturday, 07 August 2021 00:00

“ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን የዕውቀት ምንጮች ናቸው ክፍል አንድ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያልተበረዘና ያልተከለሰ እንዲሁም ወጥ የሆነ የአምልኮና የአስተዳደር ሥርዓት ያላት ናት፡፡ ይህም በዓለማችን ካሉት አጠቃላይ አብያተ ክርስቲያናት የተለየች ያደርጋታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷንና ትውፊቷን ለማስቀጠል የተለያዩ ተቋማትን መሥርታ እንቅስቃሴ ከጀመረች ዘመናትን አስቆጥራለች፡፡ ካሏት የአስተዳደር ክፍሎች በተጨማሪ በፈቃደኝነት በቤተ ክርስቲያን ሕግና ደንብ የተመሠረቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ለምእመናን ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት  በተለያየ መልኩ ሲደግፉ ይታያሉ፡፡በርካታ ማኅበራት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ጭምር ተመሥርተው የቤተ ክርስተያንን አገልግሎት ለመደገፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ቀላል የማይባሉ ጊዜያትን አሳልፈዋል፡፡ በሀገራችን ከመንፈሳዊ ማኅበራት እንቅስቃሴ አንፃር ስንመለከት ከዛሬ ሠላሳ ዓመታት ወዲህ በይፋ የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ በሁለንተናዊ ዘርፍ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ሲደግፍ ቆይቷል፡፡  በተለይ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ዘርፎች መካከል ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡ ማኅበሩ በአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ላይ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌሉባቸው የሀገራችን አካባቢዎች የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲኖራቸው በማድረግ  አብነት ትምህርት ቤቶች ያሏቸውን ደግሞ እንዲሁም በሰው ኃይልና በቁሳቁስ የማጠናከር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡  ገዳማዊ ሥርዓቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ እና ገዳማት ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ለማስቻል  ጊዜያዊና ዘላቂ ድጋፎችን አድርጓል፡ እያደረገም ይገኛል፡፡ ገዳማውያን በዕለት ጉርስ በዓመት ልብስ እጦት  እንዳይበተኑ ከበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሀብት ሰብስቦ እገዛ ያደርጋል፡፡ በአብነት ትምህርት ቤቶች ረገድም ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌል እንዳታጣ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ ዝግጅት ክፍላችንም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ ከሆኑን ዲ/ን አንድነት ተፈራ ጋር በክፍሉ አጠቃላይ  አገልግሎ ዙሪያ አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ ከኃላፊው ጋር ያደረግነውን ቆይታም በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- የክፍሉ ዋና ዋና ተግባራት ምን ምን ናቸው? ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ በዋናነት በትኩረት እየሠራ የሚገኘው አብነት ትምህርት ቤቶችና በገዳማት ላይ ነው፡፡ ክፍሉ ለገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ከጊዜያዊ ድጋፍ ጀምሮ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ቋሚ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች በሰው ሠራሽ፣ በተፈጥሮና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ተጎጂ ሲሆኑ ክፍሉ የሚያስፈልገውን ጊዜያዊና ቋሚ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለገዳማቱ የቀለብ፣ የአልባሳት፣ የንዋ ቅድሳት እንዲሁም የተለያዩ የመባ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ እንደሚታወቀው የአብነት ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ‹‹በእንተ ስማ ለማርያም›› ብለው በሚያኙት ቁራሽ ይማሩ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ለምኖ የመማር ባህሉ እየተቀየረ በመምጣቱ የአብነት ተማሪዎች ለከፋ የቀለብ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ ስለሆነም ክፍሉ ለአብነት ተማሪዎች የቻለውን ያህል የቀለብ አቅርቦት ያደርጋል፡፡ ድጋፍ በመደረጉም በተወሰነ ደረጃ የሚዘጉ የአብነት ትምህርት ቤቶችን መታደግ ተችሏል፡፡ ጉባኤያትን ከመታጠፍ፣ ተማሪዎችን ከመበተንና ከመፍለስ የመታደግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባለመቅረፉ አንዳንድ የአብነት ትምህርት ቤቶች እስከ አሁን ድረስ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡  በርካታ የአብነት ትምህርት ቤቶች አሁንም ድረስ አገልግሎት አቁመዋል፤ ተማሪዎቻቸውም የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተሰደዋል፡፡ ግማሾቹ ሎተሪ አዟሪ ሆነዋል፤ ሌሎችም ደግሞ  በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ሆነዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ እርሻ ሥራ ተመልሰዋል፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ተተኪ ወይም ተረካቢ የቤተ ክርስቲያን አገልጋን ማግኘት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እነዚህንና መሰስል ችግሮችን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይቻልም የአብነት ትምህርት ቤቶች መደበኛ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉና የአብነት ተማሪዎችም በትምህርታቸው እንዲገፉ ክፍሉ የአልባሳት፣ የምግብ፣ የመጻሕፍት እንዲሁም የማደሪያ  ድጋፎችን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በክፍሉ ውስን አቅም የተነሣ አገልግሎቱን በሚፈለገው መልኩ ለማስቀጠል ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡  የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ቁጥር ብዙ ነው፤ ፍላጎቱም በዚያው ልክ ሰፊ ነው። ገዳማት ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲችሉ ቋሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ዕለታዊና ወርሓዊ ገቢ እንዲያስገኙ የማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡  አሁንም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ገዳማት በተለያዩ ልማቶች ገቢን በማመንጨት ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተለይ ከልማት ጋር ተያይዞ  ንብ ማነብን ጨምሮ የእርሻና የከብት ርባታ ሥራዎችን በመሥራት ገዳማውያኑ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጭምር እየተሠራ ነው፡፡ ክፍሉ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ለገዳማት ከሚያደርገው ልዩ ልዩ ቋሚና ጊዜያዊ ድጋፎች በተጨማሪ ልዩ ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ጭምር ይሰጣል፡፡ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎቹ የአብነት ተማሪዎቹም ሆኑ ገዳማውያኑ ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑና ከኅብረተሰቡ ጋር ተግባብተው እንዲያገለግሉና እንዲገለገሉ ያግዛቸዋል፡፡ በተለይ ገዳማት የእርስ በእርስ የልምድ  ልውውጥ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል፡፡  በቋንቋቸው ተምረው የሚያስተምሩ የአብነት ተማሪዎችን ከማፍራት አኳያ እንዲሁ ክፍሉ ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌሉባቸው አካባቢዎች ያሉ አድባራት የዕለት ተዕለት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ከሌላ አካባቢ አገልጋይ እያመጡ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገልጋይ እጥረት በመኖሩም መናፍቃን ምእመናንን በቀላሉ እንዲወስዱ ያደርጋል፡፡ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ይህንን ችግር በመረዳት የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌሉባቸውን አንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም፣ ያሉትን ደግሞ የማጠናከር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በባሌ፣ በነጌሌ፣ በወላይታ፣በከንባታ፣ በሀላባና ጠንባሮ፣ በዳውሮ፣ በጋሞጎፋ፣ በኢሉባቦር በጅንካ፣ በአፋር፣ በሶማሌ አህጉረ ስብከት በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ሰፊ ሥራ የተሠራባቸውና እየተሠራባቸው ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በቀጣይም በተለያዩ አህጉረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋትና የማጠናከር ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ የዚህ ተግባር ዓላማ አብያተ ክርስቲያናት በራሳቸው ቋንቋ የሚያስተምሩ፣ የሚቀድሱና የሚዘምሩ አገልጋዮችን ማፍራት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስቀጠል፣ ምእመናንን ለማጽናት፣ ያላመኑትን ለማሳመን በየአካባቢው አገልጋዮችን ማፍራት ለነገ የማይባል ነው፡፡ ይህ ተግባር የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ፣ አገልግሎቱም የተቃና እንዲሆን ያደርጋል፡፡  ክፍሉ በዋናነት እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት ባሻገር የአብነት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ዘመናዊ (የአስኳላ) ትምህርት እንዲማሩ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነፃ የትምህርት ዕድል ተመቻችቷል፡፡ በተመቻቸላቸው ነፃ የትምህርት ዕድልም ብዙዎቹ ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በሁለት ጎን የተሣሉ አገልጋዮች ለመሆንም በቅተዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ተምረው በአብነት ትምህርት ቤቶች ያላለፉ ወጣቶችም ጭምር የአብነት ትምህርት እንዲማሩ፣ የተማሩት ደግሞ ዘመናዊ ትምህርትን እንዲማሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ የክፍሉ ሥራዎች በጣም ሰፊ ቢሆኑም የተጠቀሱት ግን ጥቂቶቹ ናቸው። በአጠቃላይ ክፍሉ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ፕሮጀክቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- አዳዲስ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ከማቋቋም ውጭ ለቀደምት የአብነት ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት አልተሰጣቸውም ይባላልና በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?  ዲ/ን አንድነት፡-  ማኅበረ ቅዱሳን የአቅም ውስንነት ስላለበት ሁሉም ቦታ ላይ መድረስ አይችልም። ይህም በመሆኑ በየአካባቢው ያለው አገልጋይም ሆነ የኅብረተሰብ ክፍል የአብነት ትምህርት ቤቶችን ከመጠበቅና ከማልማት አኳያ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤተ ክርስቲያን የአሠራር ክፍተት ለአንዳንድ የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል። ይህም ሆኖ ግን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የአብነት ትምህርት ቤቶች አልተዘነጉም፡፡  ማኅበሩ በተለይ በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ በሁለት ወሳኝ መንገዶች እየሠራ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው የአብነት ትምህርት ቤቶች ባልተስፋፉበት አካባቢ ማስፋፋት ሲሆን የአብነት ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የማጠናከርና ደረጃቸውን ማሻሻል ሁለተኛው የማኅበሩ ሥራ ነው፡፡  በዚህ ሂደትም በርካታ ክርስቲያኖችና የአብነት ትምህርት ቤቶች ያሉበትን የሰሜኑን የሀገራችን ክፍል በተለየ ሁኔታ መጀመሪያ የቅኔ የምስክር ት/ቤቶችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ይገኛል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እስካሁን ድረስ በአብነት ትምህርት ቤቶችና በገዳማት ዙሪያ ሠርቶ ያስረከባቸው ፕሮጀክቶች አንድ መቶ አርባ ስድስት  ደርሰዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹም የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳማትን በእጅጉ ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ርክክብ ያልተደረገባቸው በሥራ ላይ ያሉ ከዐሥር በላይ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ማኅበሩ እየሠራ ያለው ሁሉንም አካባቢዎች ማዕከል በማድረግ ነው፡፡ ለአንዱ አካባቢ የተለየ ትኩረት ለሌላው ደግሞ ዝቅተኛ ትኩረት አይኖረውም፡፡ ሥራዎች የሚሠሩት እንደአስፈላጊነቱና እንደ ክፍተቱ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ የቅኔ ምስክር ትምህርት ቤቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ እየሰጠን እየሠራን ነው፡፡ ምእመናንና ባለድርሻ አካላት የሚተባበሩ ከሆነ ደግሞ ሁሉም ዘንድ ለመድረስ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በየአካባቢው ያለው ምእመን በአካባቢው ያለውን የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ለመፍታት ቢነሣ ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ በጥናትና መሰል ሙያዊ ድጋፎች እገዛ ያደርጋል፡፡   
Read 427 times