ሀገራችን ንግሥናን ከክህነት አጣምረው የያዙም በርካቶች ነበሯት፡፡ ‹‹ቄሱ ንጉሥ›› ተብሎ የኢትዮጵያ መሪ የሚጠራበት የአውሮፓውያን ልማድ በከንቱ የተሰየመ አልነበረም፡፡ አብርሃ ወአጽብሐ፣ ንጉሥ ካሌብ፣ ዐጼ ገብረ መስቀል፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ንጉሥ ሐርቤ፣ ዐፄ ዳዊት፣ ዐፄ ዘርዐያዕቆብ፣ ዐፄ ፋሲለደስ፣ ዐፄ ገላወዴዎስ፣ ወዘተ እያልን ብንጠራ በርካቶች ከላይ ላልነው ሁለትዮሽ ሚናቸው ሁነኛ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡
ንግሥናን ከአገልግሎት አጣምሮ መሄድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ነበረው፡፡ የዳዊትና የሰሎሞን መንግሥትን ማሰብ የጽዮንን ድንኳን የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ከማሰብ ሊነጠል አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በሚያዛቸው በሚመራቸው፣ ነቢያና ካህናት በሚመክሯቸው መንገድ ይራመዱ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ክፉ ቢሠሩ በተግሳፅ፣ ደግ ቢሠሩ በምስጋና ሲጠሩም ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የነገሥታት መንገድም ‹‹ሰሎሞናዊ›› እየተባለ ሲጠራ የነበረው በከንቱ አልነበረም፡፡ ከዚሁ ንጉሣዊ አገልጋይት የመነጨው አመራር ያስከተለው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም በኋላ ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው ቡራኬ በተሾመ ንጉሥ መመራት እንደማይፈልግ በዐመጽ ከገለጸ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እጅዋን እንድትሰበስብ፣ ሃይማኖታዊ አገልግሎቷን ብቻ በመስጠት እንድትወሰን በመርሕ ተቀምጧል፤ በሕግ ተወስኗል፡፡ ይህ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ለምን ሆነብኝ ብላ የምትቆጭብት አልነበረም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትፈለግ የምታገለግል እንጂ ሳትፈለግ ሌላውን የምታገል አይደለችም፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በመስጠት ተወስናለች፡፡
ይሁን እንጂ ሲሸሹት የሚከተለው የኢትዮጵያ ዘመናዊው ፖለቲካ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት አልፈልግም›› በማለት ብቻ መወሰን አልቻለም፡፡ ንጉሥን በመግድል የጀመረው ዐመጽ ጳጳሱን ገድሎ የለየለት ጠላት ወደ መሆን አደገ፡፡ ከዚያም ቤተ ክርስቲያንን በሞግዚትነት የሚመሩ ካድሬዎችን በመሾምና በማንበርከክ በማስጨነቅ ጣልቃ ገብነቱን ማሳየት ጀመረ፡፡ ይህ ውሎ አድሮ ሥርዓት ሲቀየር ይቀየራል በማለት አባቶች በዕንባና በጸሎት መኖር ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ሥርዓት ሲቀየርም የጫናና ጣልቃ ገብነቱ ቀለም እንጂ ይዘቱ ሲቀየር አልታየም፡፡
በተለይም ሥርዓት በሚቀየርባቸው የሽግግር ጊዜያት በቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል መከፋፋልና መጠራጠር የመፍጠር ዘመቻ ተፈራርቆባታል፡፡ በዚህም ምክንያት ጳጳሳት ለስደትና ለእንግልት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ አባቶች በቋንቋና በብሔር እንዲከፋፈሉ ተሠርቷል፡፡ ዛሬም ድረስ ግን ይህ መከራዋ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያን በጎጥና በቀበሌ እንድትበታታን የሚያደርግ የፖለቲካ ልሂቃን ደባ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገር ድረስ ተዘርግቶ ይታያል፡፡ የእገሌ ብሔር ቤተ ክርስቲያን የሚለው እንቅስቃሴም በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም የተጀመረው ጫና ቅጥያ ነው፡፡
አሁን ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ዋነኛ ሰላባ ሆና ያለችው ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ነው፡፡ አንድ የነበረው ሕዝበ ክርስቲያን በየጎራው ተሰልፎ በጥላቻ መተያየቱ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትልቅ ኪሳራ ሆኖ ለትዝብትም ተዳርጎ ይታያል፡፡ ከዚያ አልፎ ካህናት ለማስታረቅ ዋጋ ከመክፍል ይልቅ በየጎራው ቆመው ‹‹በለው በለው›› ሲሉ መታየታቸው በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ለትዝብት ግን ዳርጓቸዋል፡፡
ፖለቲከኞች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መፋተጊያቸው ለማድረግ ሲወስኑ እባካችሁ ተስማሙ ካልሆነም በሜዳችሁ ተጫወቱ ለማለት የሚደፍር እየጠፋ ነው፡፡ ይልቁንም በተቀደደ ቦይ የሚፈሱ ካህናት፣ መነኰሳት፣ መምህራን፣ መዘምራን በየጎራው መታየታቸው የፖለቲከኞች ውጊያ ድልና ሽንፈት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲታይ እየሠሩ መሆኑን ያስረዳል፡፡ አንዱ ካህን የሚሠራውን ስሐተት ሌላው የሚተችበት መንገድም በራሱ ፈተና እያመጣ ነው፡፡ የሚናገሩትንና የሚሠሩትን በማያውቁ አገልጋዮች ቅደስት ቤተ ክርስቲያንን እየተጎዳች ነው፡፡ ከፍተኛ ማሰናካያም ደርድረዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ነጻነትዋን አሳልፋ ያለመስጠት ተጋድሎ ካልጀመረች ትዝብት ላይ የሚጥሉ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ የሚከፋፍሉ፣ የቤተ ክህነቱን ተኣማኒነት የሚያሳጡ ብዙ መዘዞች ይከተላሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ቤተ ክህነቱ ሥራውን መጀመር ያለበት ከራሱ ነው፡፡ ፖለቲካ ከቤተ ክህነት ይውጣ ለማለት መድፈር አለበት፡፡ ፖለቲካ የቄሳር ሥራ ነው እንጂ የእግዚአብሔር ሥራ አይደለም ማለት አለበት፡፡ የክህነት ሥልጣንን ለፖለቲካ ዓላማ ማዋል ፍጹም የሚያስወግዝ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የትናንት ውስብስብ የታሪክ ዘመኗን ለታሪክ ትታ አሁን አዲስ የአገልግሎት የታሪክ ምዕራፍ መጀመር አለባት፡፡ ይህ አዲስ የአገልግሎት የታሪክ ምዕራፍ መከፈት የሚችለው ግን የቄሳርን ለቄሳር በመስጠት ብቻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ነች የምታገለግለውም እግዚአብሔርን ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቷን ሁሉ መተርጎም ያለባት ከዚህ ሚናዋ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በዘር ቤተ ክርስቲያንን መበጣጠስ ይቁም፤ ፖለቲከኞችን በመቃወምና በመደገፍ በሚደረጉ ሰልፎች መታየት ይቁም፤ ከታሪክ ጠባሳዎቻችን እንማር፤ ቤተ ክርስቲያንን ዓለማቀፋዊት ባሕርይ እናላብስ በሚሉ መርሖዎች ቤተ ክህነቱ መስማማት ካልቻለ አስተዛዛቢ ነው፤ ሽንፈትም ነው፡፡
ፖለቲከኞች ካህናት ከፖለቲካ ቆሻሻቸው ይጽዱ፤ ወይም ከአገልግሎቱ ይውጡ፡፡ ፖለቲከኞች ካህናት የቄሳር እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆን እንዴት ይችላሉ? ምን ሊሠሩ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መጡ? ይህ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ ‹‹ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን?›› እንዳለው የሚፈልጓቸው ቀጭን የለበሱ ወገኖች ያሉት የት እንደሆነ በራሱ ቃል ‹‹እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ።›› /ማቴ. ፲፩፥ ፯/ብለን መዋያ አድራሻቸውን ልንጠቁማቸው ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር