Saturday, 07 August 2021 00:00

‹‹ልጄ በሕይወት እንዲኖር የተሳልኩትን መፈጸም አልቻልኩም!››

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
የተወደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ስሜ ወለተ ሰማዕት ይባላል ባለትዳር እና የሦስት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ስምዐ ጽድቅ ላይ የሚወጡ ጽሑፎችን ተከታትዬ አነባለሁ በዚህም ብዙ መንፈሳዊ ዕውቀት አግኝቼበታለሁ፡፡ በተለይ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ዐምድ ላይ የሚወጡ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው ብዙ ቁም ነገሮችን አስጨብጠውኛል፡፡ እኔም ለዘመናት ውስጤን ሲረብሸው የነበረውን እና መፍትሔ ያላገኘሁለትን ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ ውስጤን ሰላም ለነሳው ጥያቄዬ የሚያሳርፍ መልስ ትሰጡኛላችሁ ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

 

በአንድ ወቅት ሕይወቴን እጅግ የሚፈትን ነገር ገጠመኝ የመጀመሪያ ልጄ ገና በአምስት ዓመቱ በጠና ታመመብኝ፡፡ የበሽታውም ዓይነት የደም ካንሰር ነው፡፡ ሐኪሞች የበሽታውን ዓይነት ከነገሩኝ በኋላ በጊዜው ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ካልታከመ መዳን እንደማይችል ነገሩኝ ሰማይ የተደፋብኝ ነው የመሰለኝ፤ ልጄን እንኳን ውጭ ሀገር ወስጄ ላሳክም በሀገር ውስጥ ደኅና ሐኪም ቤት የምወስድበት ገንዘብ ያልነበረኝ ድኃ ነኝ፡፡  

በጊዜው ከጭንቀቴ የተነሳ በአካባቢዬ ወደነበረው የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ፡፡ አልቅሼ የልቤን ችግር ነገርኩት፤ ልጄን ከሞት እንዲታደግልኝ ተማጸንኩት፤ ይኖር ዘንድ ይህን ክፉ በሽታ ከልጄ ላይ ካጠፋና በሕይወት እንዲኖር ካደረገልኝ እርቃኔን ቤተ ክርስቲያኑን እየዞርኩ በእልልታ እንደማመሰግነው ተሳልኩ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ የወሰድኩትን እምነት እና የቅዳሴ ጠበል በጥብጬ ለልጄ አጠጣሁት፡፡ አምላክ ተማጽኖዬን ሰምቶ ልጄ በተአምር ዳነ፡፡ ሕመሙ ጠፋ ወደ ሆስፒታል ይዤው ስሄድ ምንም በሽታ እንደሌለበት ነገሩኝ፡፡ እኔ ግን ለእኔም ሆነ ለልጄ ስለተደረገለት የተሳልኩትን ስእለት መፈጸም እፍረት ሆኖ ተሰማኝ እንዴት ብዬ እርቃኔን በሰው ፊት እቆማለሁ የሚለው አሸማቀቀኝ፡፡ ውስጤን ግን ለዘመናት እየረበሸኝ ነው፡፡ አምላኬን እንደዋሸሁት፣ ስእለቱን እንዳስቀረሁበት ይሰማኛልና ምን አድርጌ ከዚህ እንደምላቀቅ ቸግሮኛልና መፍትሔ ጠቁሙኝ፡፡  

ውድ እኅታችን ወለተ ሰማዕት ለጥያቄዎ መልስ አገኛለሁ ብለው ለዘመናት ውስጥዎን ሲረብሽዎ የነበረውን ሐሳብ ሳይሸሽጉ በመግለጽ በመጠየቅዎ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ የእርስዎ ጥያቄ ለብዙዎች መልስ ሊሆን ይችላልና እንደሚከተለው እንመልሳለን በጥሞና ይከታተሉን፡፡ 

ስእለት መሳል፡- በቅድሚያ ‹‹ስእለት›› የሰው ልጆች በራሳቸው ፈቃድ ከሚያገኙት ነገር ላይ ለእግዚአብሔር የሚሰጡት አሊያም ስለሚደረግላቸው መልካም ነገር ለእግዚአብሔር፣ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለቅዱሳን፣ ለሰማዕታት፣ ለመላእክት ለመስጠት ቃል የሚገባበት የአምልኮት ሥርዓት ነው፡፡ ስእለት ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር ቸርነት በእመቤታችን ቅደስት ድንግል ማርያም ፣ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን እና በሰማዕታት አማላጅነት በማመን እና በመማጸን ቃል የምንገባበት ነው፡፡ እምነታችንና ታዛዥነታችንን የምንገልጽበትም ነው፡፡

ስእለት መሳል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓትም ነው፡፡ ብዙዎች ልመናቸው እና የልባቸው መሻት ደርሶላቸው እንደየ ስእለታቸው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋል፡፡ ከወንድሙ ከኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሌላ ሀገር በመሸሽ ለብዙ ዘመናት የተቀመጠው ያዕቆብ ‹‹ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበት መንገድ ቢጠብቀኝ፣ ወደ አባቴም በጤና ብመለስ ለሐውልት የተከልሁት ይህ ድንጋይ የእግዚአብሔር ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ከዐሥር እጅ አንዱን እሰጥሀለሁ፡፡›› ዘፍ. ፳፰፥፳፳፪ በማለት ተስሎ ነበር፡፡ ከተሰደደበት ሲመለስም እንደ ስእለቱ እንደፈጸመ እንመለከታለን፡፡ 

የነቢዩ የሳሙኤል እናት ቅድስት ሐናም ልጇን በስእለት ስላገኘች ‹‹እግዚአብሔር የለመንኩትን ልመናዬን ሰጥቶኛል እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን ሙሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል›› በማለት ሕፃኑ ሳሙኤልን ለቤተ መቅደስ ሰጥታለች ፩ኛሳሙ. ፩፥፳፰፡፡ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና እግዚአብሔር ልጅ የሰጣቸው እንደሆነ ለቤተ መቅደስ ያገለግል (ታገለግል) ዘንድ ለቤተ እግዚአብሔር እንደሚሰጡ ብፅአት ገብተው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ስእለታቸውን ሰምቶ እመቤታችን ተወልዳ በሦስት ዓመቷ ለቤተ መቅደስ እንደተሰጠች ተአምረ ማርያም ላይ ተገልጧል፡፡ ከነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች እንደምንረዳው ስእለት መሳል የተሳሉትን በቃላቸው መሠረት መፈጸም በመጽሐፍ ቅዱስ የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ 

አግባብነት ያለው ስእለት መሳል፡- ከላይ እንድተመለከትነው ስእለት መሳል መልካም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ነው። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ፩ኛ ቆሮ. ፲፬፥፵ እንዳለው ሰዎች ስእለትን በምንሳልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር የምናደርገውን የደስታ መግለጫ በአግባቡ እና በሥርዓት ልናደርገው ይገባል፡፡ ልመናችን ከደረሰልን በኋላ እንዳንቸገር አይሆንም፣ አይደረግም፣ አሊያም ባይደርስስ ከሚል ጥርጣሬ በመውጣት ይፈጸማል የሚል እምነት በውስጣችን ሊኖር ይገባል፡፡ የምንሳለውንም ነገር ከመሳላችን በፊት ተጠንቅቀንና አስበን መሳልም ተገቢ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽነው አንዳንድ ሰዎች ላይሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ የማይሆን ስዕለትን ይሳሉና ሲደርስላቸው እንደ ስእለታቸው መፈጸም ይቸገራሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እንዲህ ከተደረገልኝ ወይም ከሆነልኝ ውሻ እየጎተትሁ፣ አይጥን ከነነፍሷ ይዤ እመጣለሁ›› በማለት የማይደርስ መስሏቸው ያልተገባ ስእለትን ይሳላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስእለቶችን ከመሳል አለመሳሉ ይሻላል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ባለማስተዋል የማይገባ ስእለት ተስለው ዋጋ የከፈሉ አሉ። ለምሳሌ ዮፍታሔ “ዮፍታሔም የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ከቤቴ ደጅ ወጥቶ የሚቀበለኝን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አደርገዋለሁ ብሎ ተሳለ።” (መሳ.11፣31) ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኩ ተመዝግቦ እንደምናነበው “ቀድሞ የሚቀበለኝን” በማለት ለእግዚአብሔር ስእለት አቀረበ። እግዚአብሔርም ፈቃዱ ሆኖ የድል ባለቤት አደረገው ሲመለስ ግን ቅድሚያ ወጥታ የተቀበለችው ልጁ ነበረች። ሊቃውንቱ በትርጓሜ ሁል ጊዜ ዮፍታሔ ከዋለበት ሲመጣ ቀድሞ እየወጣ የሚቀበለው ለማዳ በግ ነበረው። በዚያ ልማድ ቀድሞ ወጥቶ የሚቀበለኝ በጉ ነው ብሎ አስቦ እንደነበር አስቀምጠውታል።

ይሁን እንጂ ሁኔታው እርሱ እንዳሰበው አልሆን አለና ቀድማ የተቀበለችው ልጁ ሆነች። ስእለቱን እንዳያስቀር ተቸግሮ እንዳይፈጸም ደግሞ ልጁ ሆናበት ሳይወድ በግድ እያለቀሰ ልጁን መሥዋዕት አደረጋት። ይህ ባለማስተዋል የተሳለው ስእለት ተገቢ ያልሆነ ዋጋ አስከፈለው። እንደዚሁ ሰዎችም የማይሆንና የማይደረግ ስእለት እየተሳሉ ለመፈጸም ሲቸገሩ ባይፈጽሙት ደግሞ የኅሊና ዕረፍት እየነሣቸው ሲጨነቁ ይስተዋላሉ። ስለዚህ የማይባልና፣ የማይፈጸም ነገር መሳል እጅግ ከባድ ስሕተት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ስሕተት ብቻ ሳይሆን ድፍረትና በእግዚአብሔር ላይ መዘባበትም ነው። 

ውድ ጠያቂያችን ወለተ ሰማዕት የእርስዎ የስእለት አቀራረብ ከላይ ለማንሣት እንደሞከርነው አይሆንም ብሎ በመጠራጠር የቀረበ ነው ብለን ባናምንም አግባብ ያለው ስእለት አለመሆኑን መረዳት ይኖርብዎታል፡፡ የተሳሉት ስዕለት ‹‹እርቃኔን ሆኜ ቤተ ክርስቲያኑን እዞራለሁ›› ብለው ቢሳሉም እጅግ የሚያሳፍር በመሆኑ መፈጸም አልቻሉም፡፡ እግዚአብሔርም በእንዲህ ዓይነቱ እና ከአግባብ ውጪ በሆነ ስእለት አይደሰትም፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ የስእለት ስጦታዎች ሁሉ በእምነት ላይ የተመሠረቱ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚደሰትባቸውና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ሊሆን ይገባል፡፡ ሲጀመርም እኛ በዚያ ልክ ተረድተን ባናከብረውም ሰውነታችን የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ በሥጋ መለኮትና በደመ መለኮት የከበረ ንጹሕ ቤተ መቅደስ ነው። ስለዚህ ራቁቴን እሆናለሁ ማለት እኮ የእግዚአብሔርን ማደሪያ አራቁታለሁ ማለትም ነው። በአጭሩ ስለትዎት አግባብነት የሌለው፣ በእግዚአብሔር ላይ መደፋፈር፣ ሊናገሩትም ሆነ ሊተገብሩት የማይገባ መሆኑን መረዳት ይኖርብዎታል።

የተሳሉትን አለማስቀረት፡-  

ስእለትን ለእግዚአብሔር፣ ለድንግል ማርያም፣ ለቅዱሳኑ የምንሳለው እኛ በምናቀርበው የስጦታ ብዛት የሚፈጸሙ ሆነው አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርም ቅዱሳን ስለሚፈጽሙልን ነገር ደስታችንን ለመግለጽ በፈቃዳችን ቃል የምንገባው እንዲሁም ሲፈጸምልን ስጦታችንን በገባነው ቃል (በተሳልነው ስእለት መሠረት) የምናቀርበው ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ስእለት በምንሳለበት ጊዜ በቃላችን መሠረት ስእለት መፈጸም ግዴታ ስለሆነ አለመፈጸም ኃጢአት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ለእግዚአብሔር በተሳልክ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፣ የተሳልከውንም ፈጽም፣ የማትፈጽም ከሆነ አትሳል›› መክ.፭፥፬  በማለት ስእለት በተሳልን ጊዜ መፈጸም ግዴታ መሆኑን ገልጾልናል።

መጽሐፍ ስእለትን ማስገባት መልካም መሆኑን ብቻም ሳይሆን ተስሎ አለመፈጸም ኃጢአት መሆኑንም ‹‹ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና ኃጢአትም ይሆንብሃል መክፈሉን አታዘግይ፡፡ ባትሳል ግን ኃጢአት የለብህም በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደረግ ዘንድ ጠብቅ›› ዘዳ.፲፫፥፩፲፫ በማለት ስእለትን በተሳልን ጊዜ ሳናዘገይ መክፈል እንዳለብን አስረግጦ ይነግረናል። ስለዚህ ስለ ስእለት ያለንን ግንዛቤ ማስተካከል ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ወለተ ሰማዕት ስለተሳሉት የስእለት ዓይነት እና ስእለቱን መፈጸም አለመቻልዎ ደግሞ ውስጥዎን ሲረብሽዎ መቆየቱ በሕይወትዎ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ መገመት አዳጋች አይሆንም፡፡ ለሌላ ጊዜም ቢሆን እንዲህ ዓይቶችን እና ለመፈጸም እጅግ የሚቸገሩባቸውን ነገሮች መሳል ተገቢ አይደለም፡፡ ስእለትን ከመሳልዎ በፊት አስበውበት ሊያደርጉት፣ አቅምዎ በሚፈቅደው መጠን ሊፈጽሙት የሚችሉትንና አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን ሰማዕታትና መላእክት ተደስተው የሚቀበሉትን በተለይም ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ስእለት ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡ ለወደፊቱ በዚህ መልኩ ሕይወትዎትን እንዲመሩ ከጠቆምን ላለፈው ስሕተት ግን ስለ ስእለትዎ ንስሐ መግባት ተገቢ ነው። 

በመሆኑም ወደ ንስሐ አባትዎ ዘንድ በመሄድ እና የሆነውን ሁሉ በማስረዳት በንስሐ አባትዎ የሚሰጥዎትን ትእዛዝ መፈጸም ይኖርብዎታል፡፡ የቀኖናውን መጠን በዚህ ጽሑፍ መወሰን እንደ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን አይቻልም፤ ነገር ግን በመጀመሪያ የማይሆን ስእለት በመሳልዎ ከዚያም የተሳሉት ሲደርስ የተሳሉትን ባለመፈጸምዎ በድለዋልና ቀኖና እንደሚያስገባ መናገር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ወደ ንስሓ አባት መሄድ ዋናው መፍትሔ ስለሆነ የምንመክርዎት ምክር አሁንም ወደ ንስሓ አባትዎት ይሂዱና መፍትሔውን ይቀበሉ ብለን ነው። አምላከ ቅዱሳን ከተጨነቁበት ነገር ያወጣዎ ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁን።

Read 413 times