Thursday, 26 August 2021 00:00

ሸኔ ከተባባሪዎቹ ጋር በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ኦርቶዶክሳውያንን የማጽዳት ተግባር እየፈጸመ መሆኑ ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
አሸባሪው ሸኔ ከተባባሪዎቹ ጋር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ኪረሙ ወርዳ ቤተ ክህነት በተለያዩ ቀበሌዎች የሚኖሩ ኦርቶደክሳውያን ክርስቲያኖችን የማጽዳት ተግባር እየፈፀመ መሆኑን የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ገለጡ፡፡    ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ አንድ የአካባቢው የሃይማኖት አባት እንደተናገሩት “ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም በኪረሙ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኙ የሳደሮ ቅዱስ ገብርኤልና ኩቲ ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በቅዳሴ ላይ የነበሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን በሙሉ የሽብር ቡድኑ  ገድሏቸዋል” ብለዋል፡፡  በምእመናንና በአገልጋዮች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ ያስታወቁት እኒህ የሃይማኖት አባት በዚህ ወቅት የተፈጸመው ጥቃት ግን ከዚህ በፊት ከነበረው የባሰ ነው፡፡ ሰሞኑን በጭካኔ የተገደሉት ምእመናን አብዛኛዎቹ በቅዳሴ ላይ እንዳሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከቅዳሴ መልስ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡  አሁን ባለው መረጃ መሠረት ሥልሳ ያህል ምእመናን መገደላቸውን ያረጋገጡት የአካባቢው የሃይማኖት አባት የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልና ከሞት የተረፉትም በየጫካው ሸሽተው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡  የኪረሙ ወረዳ ሦስት ቀበሌ ምእመናን በሙሉ ለሞት፣ ለስደት፣ ለሀብት ንብረት ውድመትና ዘረፋ እንደተዳረጉ የስታወቁት እኒህ የሃይማኖት አባት አካባቢው ወደቀደመ ሰላሙ ቢመለስ እንኳን የሚበሉት ምግብና የሚጠለሉበት ቤት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡    የችግሩን ውስብስብነትና ከአቅም በላይ መሆኑን ለክልሉ መንግሥት ያስረዱ መሆኑን ያስታወቁት እኒህ አባት  በሕይወት የተረፉ ምእመናን ወደ አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች እንዲሄዱ የሽብር ቡድኑ የዘጋውን የቡሬ መንገድ መንግሥት እንዲያስከፍት ጥሪ አቅርበዋል፡፡  ሌላው የሀገረ ስብከቱ አገልጋይ የሆነው ወጣት በበኩሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ታዋቂ ባለሀበት ምእመናንና ሌሎች በሽብር ቡድኑ እንደታገቱ ገልጦ አጠቃላይ ጥቃቱ ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  አገልጋዩ አያይዞም በዚህ ዓመት በነሐሴ ወር ብቻ የዐስራ ስድስት ምእመናን ከብቶች እንደተዘረፉባቸው ጠቁሞ በወረዳው ባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ ባለፀጋ ምእመናን እየታደኑ እንደተገደሉም አስገንዝቧል፡፡ የሽብር ቡድኑ ዋና ዓላማ ክርስቲያኖችን ከአካባቢያቸው በማጽዳት ቤተ ክርስቲያን እንዲዘጋና አገልግሎት  እንዲቆም ማድረግ መሆኑን አክሏል፡፡   በተጨማሪም ሸኔ በምእመናን ላይ ካደረሰው ጭፍጨፋ ባሻገር ከሌላ የተለያዩ ቀበሌዎች ተደራጀተው የመጡ ወጣቶች የኩቲ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ መዝረፋቸውን አገልጋዩ ተናግሯል፡፡  በመጨረሻም ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ እጅ የበርካታ ካህናትና ዲያቆናት ሕይወታ እንደጠፋ ያስረዳው አገልጋዩ ይህ ድርጊትም ሆን ተብሎ ቤተ ክርስቲያንን የመዝጋትና አጠቃላይ የምሥራቅ ወለጋ የገጠሩን ክፍል ከኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የማጽዳት ተግባር መሆኑን በአጽኖት አስረድቷል፡፡ ከሞት የተረፉ ካህናትና ዲያቆናት በሕይዎት የመኖር ዋሰትና ወደሚያገኙበት አካባቢዎች መሰደዳቸውንም አክሏል፡፡       
Read 612 times