Saturday, 25 September 2021 00:00

ማዕተብ ሳይኖር ክርስቲያን መሆን አይቻልምን? ክፍል አንድ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ማዕተብ ሳይኖር ክርስቲያን መሆን አይቻልምን?  ክፍል አንድ ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? ስሜ ወለተ ወልድ እባላለሁ። የ፴ ዓመት ወጣት ነኝ፤ ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች እናት ስሆን ባለቤቴ የሌላ እምነት ተከታይ ነው። ከባለቤቴ ጋር የተጋባነው ከቤተ ሰቦቼ ጋር ተጣልቼ የጎዳና ተዳዳሪ በሆንኩበት ወቅት ነው። ስንጋባ የምበላው፣ የምጠጣው፣ የምለብሰው የምኖርበት ሁሉ ስላልነበረኝ ለትዳር ሲጠይቀኝ እሽ አልኩት። የሌላ እምነት ተከታይ መሆኑንም አልደበቀኝም። ግን ሁለታችንም በሃይማኖታችን ልንኖር ተስማምተን ነው የተጋባነው። በኑሯችን ተስማምተን፣ ወዶኝ ወድጄው እኖራለሁ።  ከእርሱ እየተደበቅሁም ልጆቼን ክርስትና አስነሥቻቸዋለሁ። እርሱን ግን ቀስ በቀስ እመልሰዋለሁ ብየ ነበር እርሱም በበኩሉ እኔን ለመመለስ አስቦ መሰል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እኔን ለመስበክና ወደ እርሱ እምነት ለመውሰድ ይሞክራል። ከልጆቼ አንገት ላይ የማስርላቸውን ማዕተብም በየቀኑ ከአንገታቸው እየበጠሰ ይጥለዋል።  ልጆቹን እርሱም ሲመቸው ወደ መስጊድ እየወሰደ የራሱን የእምነት ሥርዐት ያስተምራቸዋል። እኔም የራሴን የኦርቶዶክስ እምነትና ሥርዐት አስተምራቸዋለሁ። እርሱም የእኔ ሃይማኖት ስህተት እንደሆነ ይነግራቸዋል፤ እኔም የእኔ እምነት ትክክል እንደሆነ እነግራቸዋለሁ። በመካከል ልጆች ችግር ላይ ወድቀዋል። እንዳንፋታ ልጆቼን ማን ያሳድግልኛል? እርሱ እንዳያሳድጋቸው ከኦርቶዶክስ እምነት ውጪ ነውና ከሃይማኖት ይለያቸዋል። እኔስ እንዴት ልኖር እችላለሁ። ቤተሰቦቼም እንኳን ከሌላ እምነት ተከታይ ጋር ኖሬ ጥንትም ከቤት አስወጥተውኛልና አሁን አይቀበሉኝም። ደግሞም በመጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን ባልዋንም የምታፈቅር ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ። ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱንም የሚያፈቅር ከእርሷም ጋር ለመኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ” የሚል ትምህርት እንዳለ እሰማለሁ። ለመሆኑ ልጆችም ሆኑ እኔ ማዕተብ ሳናስር ክርስቲያን ሆነን መኖር አንችልምን? መፍትሔውን እንድትሰጡኝ እጠይቃለሁ። እኅታችን ወለተወልድ በመጀመሪያ ለችግሮችሽ ሁሉ መፍትሔ አገኛለሁ ብለሽ አምነሽ ወደ እኛ በመምጣትሽ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። እኛም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን፣ መጻሕፍትን አንብበን፣ ሊቃውንትን ጠይቀን እግዚአብሔር ያቀበለንን እንጽፍልሻለን። ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር በርካታ ውጣ ውረዶች ይኖሩበታል። እኩያት ኃጣውእ፣ የዓለም ፍላጎት፣ ፈተናዎች፣ ወዘተ. ይበረቱበታል። እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ተማፅኖ የታገሠ በበረከት ላይ በረከትን በክብር ላይ ክብርን ያገኛል። መታገሥ ያልቻለ ደግሞ መፍትሔ የማይሆነውን ሁሉ እንደ መፍትሔ እየቆጠረ ወደ ባሰው ችግር እየገባ ሊያገኘው የሚገባውን በረከት ሳያገኝ ይቀራል። እኅታችን በመጀመሪያ ከቤተ ሰቦችሽ የተጣላሽበትንና ከቤት የወጣሽበትን፣ የጎዳና ተዳዳሪ ለመሆንም የተዳረግሽበትን ችግር ባትነግሪንና ባናውቀውም የመጀመሪያው ምክንያት ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን። ይሁን እንጂ ባለፈው ነገር ላይ ብዙ ጊዜ ሳናጠፋ ለሚመጣው ሕይወትሽ ጠቃሚ የሚሆነው ላይ እናተኩራለን። በመሆኑም ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር በሕይወቱ ፈተና ሊደርስበት እንደሚችልም በማመን ለመጣው መውጫ ለሚመጣው ደግሞ ማምለጫ ይሆኑት ዘንድ ሊያውቃቸው የሚገቡ ነጥቦችን እንመልከት። ሀ. ከዐቅማችን በላይ እንደማንፈተን መረዳት፡- በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በሃይማኖት ጸንቶ በበጎ ምግባር እየተመላለሰ ለሚኖር የሰው ልጅ የማይቻል ፈተና አላዘዘም፤ አያዝዝምም። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቀቆብ ‹‹የሚፈተን ሰው ቢኖር እግዚአብሔር ይፈትነኛል አይበል፤ እግዚአብሔር ለክፉ አይፈትንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡›› (ያዕ. ፩፥፲፫-፲፬) በማለት እንደ ነገረን ለምንወድቅበትና ለምንጠፋበት ፈተና አሳልፎ አይሰጠንም፡፡ ይሁን እንጂ ከእምነት መጉደል የተነሣ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ሁሉ ከእኛ አቅም በላይ አድርገን እንቆጥራቸዋልን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይዘን ማለትም በእርሱ አምነን ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምንችል “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” (ማር. ፱፥፳፫) ብሎ ነግሮናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ማንም ሰው ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው የሚችለው ነገር ሊኖር እንደማይችል “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ረኀብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን?” (ሮሜ.፰፥፥፴፪) በማለት በዚህ ምድር ላይ የሚያጋጥሙን መከራዎች ሁሉ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩን እንደማይችሉ አስረድቶናል። ሐዋርያው እነዚህን ሁሉ የዘረዘራቸው እኛ አክብደን እንዳንመለከታቸውና ከመንፈሳዊ ሕይወት እንዳንወጣ ነው። እነዚህ የተዘረዘሩት ሁሉ በቅዱስ ወንጌልም የተዘረዘሩና ስለጽድቅ ብሎ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚያዝን፣ የሚሰደድ በአጠቃላይ መከራ የሚቀበል ሁሉ ብፁዕ እንደሚባል ራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል። ስለዚህ ራሳችንን እያዳከምን የማንችለው መስሎን እንሰናከላለን እንጂ የማንችለውን ፈተናና የማንወጣውን መከራ አያመጣብንምና አስተሳሰባችንን ማስተካከል ያስፈልጋል። ለ. በዐቅማችን ልክ ማሰብና ማቀድ፡- እግዚአብሔር አምላካችን የሚያስብ አእምሮ ሰጥቶ አታስቡ ባይለንም ከአቅማችን በላይ እንድንጨነቅ ግን አይፈቅድልንም። ላደርገው እችላለሁ ብለን ስናቅድም የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስቀድመን፣ ከሥጋዊው ጉዳይ ይልቅ ለመንፈሳዊው ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተን ሊሆን ይገባል። ለእኛ የሚያስፈልገንን ከእኛ በላይ የሚያስብ በጸሎተ ኪዳንም “ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ዘእምፈቃዱ፤ ሳንለምነው የሚያስፈልገንን ከፈቃዱ የሚሰጠን እርሱ ነው” ተብሎ እንደ ተጻፈ እኛ ከመለመናችን አስቀድሞ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል። መዝሙረኛው ዳዊትም “ወኢያሕጥኦሙ እምዘፈቀዱ፣ ከሚፈልጉት ሁሉ አላሳጣቸውም” (መዝ. ፸፯፥፴) ብሎ እንደነገረን ለእኛ የሚሆነንን ሁሉ ይሰጠናል። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ነገር ልናከናውን ስናስብ የምንችለውን ያህል ማሰብና ማቀድ ይኖርብናል።   እኅታችን ወለተወልድ እውነት ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ የማያምን ባል ያላት ሴት እንዲሁም የማታምን ሚስት ያለችው ሰው አብረው ለመኖር ፈቃደኛ ከሆኑና ከወደዱ አይፋቱ ብሎ ተናግሯል። ይህም ግን ቀስ በቀስ ማሳመን ከቻለ ያመነው ቅድስና ላላመነው ይተርፈውና ወደማመን ይመጣል በሚል እሳቤ እንጂ እንዲሁ ይኑሩ ማለት አይደለም። ስለዚህ ሰዎች ቢሆን አስቀድመው መጠናናትና በሃይማኖት መመሳሰል ይኖርባቸዋል። ባይሆን ደግሞ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ከተከሠቱና በሁለቱ መካከል የሃይማኖት መለያየት ካለ ያመነው ያላመነውን አስተምሮና አሳምኖ ወደራሱ ሃይማኖት ማምጣት ይኖርበታል። ይህን ደግሞ በተለይም ልዩነት እንዳለ ከመጋባታቸው በፊት ከታወቀ ማሳመን እችላለሁ ወይ? የሚለውን ከራሱ ዐቅም፣ የትምህርት ብስለት፣ የሃይማኖት ጽናት ወዘተ. ጋር መፈተሽና የሚችለውን ያህል ብቻ ማሰብና ማቀድ ይኖርበታል።  ሐ. አጋጣሚዎችን ሁሉ ለበጎ መጠቀም ፡- ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” (ሮሜ ፰፥፳፰) በማለት እንደተናገረ ችግር ሆነው የተፈጠሩ ክስተቶችን ለበጎ ነገር መጠቀም ያስፈልጋል። በሰው ሰውኛው ሲታዩ ከባድ ችግር የገጠማቸው ይሁን እንጂ ነገሮቹ ለበጎ የሆኑላቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። ታሪኩ በሰፊው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ዮሴፍ ወንድሞቹ በቅንዐት ሰይጣናዊ ተነሣሥተው ሸጠውት ነበር። ይሁን እንጂ እነርሱ በክፋት ቢሸጡትም እግዚአብሔር ግን መሸጡንና መንገላታቱን ለበጎ አደረገለት። ዮሴፍ ከውድሞቹ ጋር ሲገናኝ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፤ አትቆርቆሩም፤ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና” (ዘፍ. ፵፭፥፭) በማለት የተናገረውን ጽፎልን እናነባለን።  እንደሚታወቀው ወንድሞቹ ሸጡት እርሱ “እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛል” በማለት የደረሰበትን ነገር ለበጎ መሆኑን ገለጸ። እኅታችን ከቤተ ሰቦችሽ መጣላትሽ፣ የጎዳና ተዳዳሪ መሆንሽ፣ በብዙ ችግር መሠቃየትሽ፣ በሃይማኖት ከማይመስልሽ ጋር በትዳር ሕይወት አንድ መሆንሽ ሁሉ ታስቦበት ይሁን ባይባልም ከሆነ በኋላ ግን እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን እንዲሠራ መለመንና የብዙዎችን ታሪክ የለወጠ አምላክ የአንቺንም ሕይወት ወደ መልካሙ ሕይወት እንዲለውጠው፣ የዮሴፍን መሸጥ ለመልካም ነገር የተጠቀመ እግዚአብሔር የአንቺንም መቸገር ለመልካም ነገር እንዲጠቀመው ያለማቋረጥ መጸለይ ይኖርብሻል። ከዮሴፍ በተጨማሪ እንደ ሰው ሰውኛው ሲታይ እጅግ ከባድ ችግር የገጠማት እግዚአብሔር ግን ድንቅ ሥራውን የሠራባት የአንዲትን ቅድስት እናት ሕይወት እንጨምር። እርሷም ንግሥት ዕሌኒ ናት። ንግሥት ዕሌኒ ሃይማኖቱ የሚመስላት በበጎ ምግባር የሚመላለስ የምታምነው የሚያምናት ተርቢኖስ የተባለ ባል ነበራት። ነጋዴ ነበርና ለረጅም ጊዜ ንግድ ቆይቶ ሲመለስ ከጓደኞቹ ጋር ከሄዱበት በጥሩ ሁኔታ በመመለሳቸው ደስ ብሏቸው እንዲሁ ሚስቶቻችንም ሌላ ሳይወዱ ሳይለምዱ ብናገኛቸው እንዴት ያማረ ነው እየተበባሉ ሲነጋገሩ ተርቢኖስ ሚስቱን እጅግ ከማመኑ የተነሣ የእኔስ እንኳን ልታደርገው ሐሳቡንም አታውቀውም ብሎ ተናገረ። ከመካከላቸው አንዱ እኔ ሄጄ ወድጃት፣ ለምጃት ብመጣስ ብሎት እርሱም አታደርገውም ተባብለው ተወራረዱ። ሰይጣን የሚያመጣው ፈተና ከባድ ነውና እርሷ ሳትፈጽመው ግን ሁለቱ ባልና ሚስት የሚተዋወቁበትን ቀለበት በሠራተኛዋ አማካኝነት ይዞ ሄዶ ሳይወዳት፣ ሳይለምዳት እንደወደዳት እንደለመዳት አድርጎ ተናገረ። የሚያምናት ባለቤቷ ተርቢኖስም ነገሩን በሰከነ መንፈስ ሳያጣራ የተነገረው ሁሉ እውነት መስሎት “ሥራሽ ያውጣሽ” ብሎ በሳጥን ከቶ ከባሕር ጣላት።        
Read 454 times