Saturday, 25 September 2021 00:00

የታፈነው የምሥራቅ ወለጋ ኦርቶዶክሳውያን የሰቆቃ ድምፅ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየደረሳባት ያለው መከራና መገፋት ከዚህ ቀደም ከነበረው በደል ቢከፋ እንጂ የሚቀል አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው በፀረ ክርስቲያን ኃይሎች እኩይ ድርጊት እንደቀልድ ስትቃጠልና ስትዘረፍ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ምእመናንም ኦርቶዶክሳዊ መሆናቸው ብቻ እንደ በደል ተቈጥሮ በየጊዜው ደማቸው በከንቱ ሲፈስ፣ሀብት ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲቃጠል፣ ከሞት የተረፉት ደግሞ ለስደትና  ለከፋ ሥነ ልቡናዊ ጫና ሲዳረጉ ማየትን እየለመድነው ከመምጣታችን የተነሳ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ድርጊቱን በሁሉም አግባብ እንዳናወግዘውና እንዳንታገለው አድርጎናል፡፡  በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል ኦርቶዶክሳውያንን መግደልና ቤተ ክርስቲያንን ማውደም መብት መስሎ እስኪታይ ድረስ ለወንጀል ድርጊቱ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፡፡ አጥፊዎች በሕግ አግባብ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ባለመኖሩ የወንጀል ድርጊቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ማዘኗና የምእመናን ዕንባ መፍሰሱ አላቆመም፡፡ በተለይ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየደረሠ ያለው ሰቆቃ ትውልድ የማይረሳው ቤተ ክርስቲያን በጥቁር ታሪክነት የምትጽፈው ነው፡፡ በነዚህ ጥቂት ዓመታት ብቻ በሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣በሶማሌ፣ በባሌና በአርሲ፣በጅማ በደቡብ ክልል፣ በሰሜን ሸዋና በከሚሴ እንዲሁም በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ምድር ላይ  በርካታ ግፎች ተፈጽመዋል፤ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል፤ ምእመናን በጭካኔ ታርደዋል፤ አካባቢያቸውን ጥለውም እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡  ሰሞኑን ማለትም ከነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ጀምሮ በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ኪረሙ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ባሉ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች አፅራረ ቤተ ክርስቲያንና አፅራረ ምእመናን በአብያተ ክርስቲያናትና በምእመናን ላይ አሰቃቂ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ በጥቃቱም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በዝርፊያና በቃጠሎ ወድመዋል፤ በርካታ ምእመናንም ለሞት፣ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ምንጮች አይተናል፤ ሰምተናልም፡፡ ዝግጅት ክፍላችንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን የአካባቢውን የሃይማኖት አባት አነጋግሮ መረጃ አጠናቅሯል፡፡  በዚህ መሠረት በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥር በአገልግሎት ላይ ያሉ አባት ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ እንዳስታወቁት በሀገረ ስብከቱ በየጊዜው የተለያዩ አዳዲስ ችግሮች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን አንሥተው፤ በተደጋጋሚ በአካባቢው በሚከሠቱ የፀጥታ ችግሮች የተነሣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን ለከፋ ጉዳት ሲጋለጡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን በጭካኔ መገደላቸውን እንዲሁም የበርካቶች ሀብት ንብረት መዘረፉንና ምእመናን ከየአካባቢያቸው ተፈናቅለው በሕይወት የመኖር ዋስትና ወደሚያገኙበት ቦታ መሰደዳቸውን ያረጋገጡት እኒህ አባት በሀገረ ስብከቱ የገጠሩ ክፍል አገልጋይ የነበሩ ካህናትና ምእመናን ከፊሎቹ ተገድለው ሌሎቹ ደግሞ ለስደት በመዳረጋቸው በዚህ ወቅት የቤተ ክርስቲያን ጣራና ግድግዳው ብቻ መቅረቱን አክለዋል፡፡ “በሀገረ ስብከቱ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት ሰንደን ከያዝናቸው መረጃዎች ውጭ ያልተነገረላቸውና በፀጥታ ሥጋት ምክንያት መረጃ ያላገኘንባቸው በደል የደረሰባቸው በርካታ አካባቢዎች አሉ፡፡ እስካሁን ድረስ መረጃ ያልተገኘባቸው አካባቢዎች ቢጨመሩ በምሥራቅ ወለጋ ያለቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ሁኔታ የህልውና አደጋ ላይ እንደወደቀች አመላካች ይሆናል” ሲሉ የሃይማኖት አባቱ ተናግረዋል፡፡ እኒህ አባት አያይዘውም “የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች በአካባቢያቸው ያሉትን ችግሮች በየጊዜው ለሀገረ ስብከቱ በሚያሳውቁበት ወቅት እኛም ጉዳዩ ውሎ ሳያድር ለሚመለከተው የመንግሥት አካልና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ስናሳውቅ ቆይተናል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በመንግሥትም ሆነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ያን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል የሚል ግምገማ የለኝም” ያሉት እኒህ አባት ከዚህ ቀደም በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት በተለያዩ የወረዳ ቤተ ክህነቶች ሥር ያሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል ወይም ተዘርፈዋል” ሲሉ አክለዋል፡፡ በመቀጠልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በዚህ ዓመት ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ጀምሮ በኪረሙ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ መውደማቸውን አስታውቀው “በርካታ ምእመናንና አገልጋዮች ተገድለዋል፤ እንዲሁም ተፈናቅለዋል” ብለዋል፡፡ እንደ አካባቢው የሃይማኖት አባት ገለጻ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ለማጥቃት የጥፋት ኃይሎቹ ክርስትና ሃይማኖትንና ተከታዮቹን ምእመናንን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ‹‹በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሣሪያ ደብቃችኋል›› በሚል ሽፋን ከፍተኛ ጥቃት ፈጽሞባቸዋል፡፡  እኒህ አባት አክለውም “ቤተ ክርስቲያን የወንጀለኛ መደበቂያም ሆነ የመሣሪያ ማከማቻ ያለመሆኗ እየታወቀ ሆን ተብሎ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን ለማጥፋት” የጥፋት ኃይሎቹ የተጠቀሙበት ምክንያት ነው፡፡ በቅርቡ በጥፋት ኃይሎቹ የተገደሉት አገልጋዮችና ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ ላይ እንዳሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከቅዳሴ አገልግሎት ተመልሰው ወደየቤታቸው በሚሄዱበት ጊዜ እንደሆነ የገለጹት እኒህ የሃይማኖት አባት የተገደሉ አገልጋዮችና ምእመናን ቁጥር እስካሁን ድረስ በውል ማወቅ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡  አያይዘውም “በሀገረ ስብከቱ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት  የቤተ ክርስቲያንን ውድቀት የሚፈልጉ አካላት ለጥፋት ኃይሎቹ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ጥቃት ለመፈጸም እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የወንጀለኛ መደበቂያና የመሣሪያ ማከማቻ እንደሆነች አስመስለው የሚናገሩ ፀረ ቤተ ክርስቲያን ኃይሎች መኖራቸው ለቤተ ክርስቲያን መጎዳት ዓይነትና ምክንያት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡  በመቀጠልም የጥፋት ኃይሎቹ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን እየመረጡ ይገድላሉ፤ ያፈናቅላሉ፤ ካሉ በኋላ እኝህ አባት “በኪረሙ ወረዳ የቤተ ክህነት ሥር በአብዛኛው ሁሉም  እየተመረጡ የሚገደሉት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ጉዳዩ  ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ለማጥቃት ያለመ እንደሆነ የሚያስረዱ ከበቂ በላይ ምልክቶች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አጥፊዎቹ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና አገልጋዮችን ከመግደልና ከማመፈናቀል በተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠልና ጣራና ግድግዳቸውን ነቅሎ የመውሰድ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ሌላው የኪረሙ ወረዳ ቤተ ክህነት አገልጋይ የሆኑት አባት ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ እንዳስታወቁት “ወቅታዊውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያን ችግር ውስጥ እንድትወድቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥለዋታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችና የቤተ እምነቶችን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአካባቢው ስለተፈጠረው  ውድመት የተጠራና የተጠናቀረ መረጃ ባይኖርም ቊጥራቸው ከዚህ በላይ ሚሆን በርካታ ምእመናን መገደላቸውና መፈናቀላቸውን ከዚህም የተነሣ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ባዶ መሆናቸውን ያስረዱት እኝህ አባት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምእመን ከአካባቢው እየተፈናቀለ እና ጉዳዩም ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ በመሆኑ መንግሥት አስቸኳይና ተከታይ የሆነ የሰላምና የደኅንነት ሥራዎችን ሊሠራ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ “በአካባቢው ያሉ ለችግር የተጋለጡ አብያተ ክርስቲያናትንና ምእመናንን ለመጎብኘት የክልሉ መንግሥት የደኅንነት ድጋፍ እንዲያደርግልን ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘንም” ሲሉም እኝህ አባት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በክልሉ በመንግሥት በኩል አልፎ አልፎ ከሚገባው ቃል ውጭ ተጨባጭ መፍትሔ ማምጣት እንዳልተቻለም አክለዋል፡፡ አካባቢው የጦርነት ቀጠና በመሆኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ወደ ወረዳው አጣሪ ልዑክ መላክ አልቻለም” ያሉት እኝህ አባት ይሁን እንጂ ወረዳ ቤተ ክህነቱ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ለክልሉ መንግሥት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቃቸውን አንሥተዋል፡፡ ከጥቃት በሕይወት የተረፉ ምእመናን በተለያየ አካባቢ ተጠልለው እንደሚገኙ የገለጡት እኝህ አባት የክልሉ መንግሥት ምእመናኑ ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ የተጠናከረ ጥበቃ እያደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ አባቶች አብዛኛውን ጊዜ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የመጡ በመሆኑ የፀጥታ ችግሩ ከተፈጠረ ጊዜ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን እየዘጉ ወደመጡበት እየተሰደዱ ነው” ሲሉ የሃማኖት አባቱ አስረድተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በታጣቂ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው እንዳለፈ አክለው ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረው አገልግሎት ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከነበረው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተወዳዳሪ የነበረ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንኳን የድሮው ትውፊት ሳይቋረጥ ‹‹ቁራሽ›› ለምነው ይማሩበት የነበረ አካባቢ እንደነበረ ያስታወሱት እኝህ አባት አገልግሎቱ እጅግ ሰፊ የመሆኑን ያህል የአገልጋይ እጥረት የሌለበት አካባቢ እንደነበረም አንሥተዋል፡፡ አያይዘውም “አሁን ካህናት ሞተውና ፈልሰው፣ የነበረውም አገልግሎት ተዳክሞና አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተው ይገኛሉ” ብለዋል፡፡ በከፍተኛ ወጭ የተገነቡት ተዘግተው የሚገኙት እነዚህ በርካታ ግዙፍ አብያተ ክርስቲያናት ቆርቆሯቸው እየተነቀለ እየተወሰደ መሆኑን ያስረዱት የሃይማኖት አባቱ በርካታ ተማሪዎች ይዘው በማስተማር ላይ የነበሩ ሊቃውንት ጉባኤያቸውን በትነው ተሰደዋል ካሉ በኋላ “የቤተ ክርስቲያናችን የአገልግሎትና የዕውቀት ምንጭ በመበተኑ በአካባቢው ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት አቁማለች” ሲሉም ሲሉም ሐዘናቸውን ገልፀዋል፡፡  እንደ እኒህ አባት አገላለጽ ከሆነ ችግሮቹ በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ በአካባቢው ያሉ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ጥቃቱ ኦርቶዶክሳውያን ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የጥፋት ኃይሉ የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ ይቀጥልበታል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀድም በአካባቢው አልፎ አልፎ የፀጥታ ችግሮች ቢኖሩም ከ ፳፻፲፫ ዓ/ም ጀምሮ ግን ችግሩ ተባብሶ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ጥሏል ያሉት እኝህ አባት “ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በብዙ መከራ ውስጥ ነውና መከራና ፈተና ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን አዲስ አይደለምና በሰሞኑ በነበረው ጭፍጨፋ ቤተ ክርስቲያናችንን ለወንበዴ ጥለን አንሄድም ያሉ አባቶችና ምእመናን ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም “እነዚህ የሕይወት ዋጋ የከፈሉ ምእመናንና አባቶች የእምነት ትርጉም የገባቸውና የሐዋርያትን መንገድ የተከተሉ ሰማዕታት ናቸው፡፡ በአገልግሎት ላይ እያሉ መሞትና እምነቴን አልክድም ቤተ ክርስቲያኔንም አላስደፍርም ብሎ መሠዋት ሰማያዊ ክብር እንደሚያስገኝ ጠንቅቀው ያወቁ ናቸው” ብለዋል፡፡ አክለውም በሕይወት የተረፉት ምእመናንና አገልጋዮችም የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ እግዚአብሔር መሆኑን አምነው ወደ እርሱ ማዘንና ዕንባቸውን በፊቱ ማፍሰስ ይኖርበናቸዋል” ሲሉ የመከሩት እኝህ አባት መንግሥትም ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡  በተጨማሪም “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው የግል ጉዳያቸውን የሚያራምዱ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው ቤተ ክርስቲያናችንን ባያጠቋት፣ ባያሳድዷትና አደጋ ላይ ባይጥሏት መልካም ነው፡፡ ምእመናንም የቤተ ክርስቲያንን ውድቀት የሚመኙ በርካታ አካላት መኖራቸውን በመረዳት ለእነዚህ ፀረ- ኦርቶዶክስ ኃይላት ቦታ መስጠት ተገቢ አይደለም” ሲሉ መክረዋል፡፡ በመጨረሻም መንግሥትም በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር ሁኔታ እጅግ ውስብስብ መሆኑን  ተረድቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባና ቤተ ክህነትም ከመንግሥት ጋር ተነጋግሮ የአካባቢው ፀጥታ እንዲከበር ጥረት ቢያደርግ መልካም እንደሆነ የሃይማኖት አባቱ አንሥተዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ ለኮማንደር ታሪኩ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለማንሣታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ መረጃውን የሰጡንን  የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ሥማቸውን ያለጠቀስነው ለደኅንነታቸው ሲባል እንደሆነ ለመግለጥ እንወዳለን፡፡      
Read 279 times