Saturday, 25 September 2021 00:00

“ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን የዕውቀት ምንጮች ናቸው” ዲ/ን አንድነት ተፈራ ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ በጥሞና ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው፡፡   ስምዐ ጽድቅ፡- ከአገልግሎቱ ጋር ተያይዞ ክፍላችሁና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቅንጅት ምን ይመስላል? የገጠማችሁ ተግዳሮትስ ምንድን ነው? ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ላይ በሚሠራው ሥራ ላይ ከገዳማቱና ከየአብነት ትምህርት ቤቶቹ እንዲሁም ከአህጉረ ስብከት ጋር በጋራ ጥናት በማጥናት ነው፡፡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችም ጭምር በውይይትና በንግግር የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ሥራዎች ከመሠራታቸው በፊት የሚሠሩትን ሥራዎች በጥናት መለየት የመጀመሪያው ተግባር ሆኖ ለሥራው ተግባራዊነትም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅትና ትብብር ይደረጋል፡፡ ሁልጊዜም ግልጽ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ሥራዎችን እንጀምራለን፡፡  በርካታ ሥራዎች በጥንካሬ እንደሚሠሩት ሁሉ በሥራዎች መካከል ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡ ማኅበሩ በሚሠራቸው ሥራዎች ወቅት ከሚገጥሙት ችግሮች መካከል የአህጉረ ስብከት ኃላፊነት መጓደልና ሥራዎችን በኃላፊነት ወስዶ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ችግር በስፋት ይስተዋላል፡፡ ሌሎች ደግሞ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በመረከብ ተማሪዎችን መልምለው ከማስገባት አንጻር የአብነት ትምህርት ቤቱ በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ኃላፊነታቸውን አይወጡም፡፡ ነገር ግን ከፕሮጀክቶቹ  በፊት በሚፈጽሟቸው ተግባራት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረምን ሲሆን የመግባቢያ ሰነዱም ማድረግ ያለባቸውን ነገር ሁሉ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ቢሆንም ግን  አብዛኛው አህጉረ ስብከት ከመግባቢያ ሰነዱ ውጭ በሆነ መንገድ ፕሮጀክቶቹን ይረከባሉ፡፡ ማኅበሩ በዋናነት የሚያደርገው ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ ማስረከብ ሲሆን አህጉረ ስብከቱ ደግሞ ተማሪዎችንና መምህራንን የመመልመል፣ በጀት የመመደብና አጠቃላይ የማስተዳደር ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ይህንን እያደረጉ አይደለም፡፡ ምእመናንም የተሠሩ ፕሮጀክቶች ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያደርጉት እገዛ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ስናስብ የሚያጋጥመን  የገንዘብ ችግር ነው፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ፕሮጀክቶችን ለመጀመርና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ ተቸግረናል፡፡ የቁሳቁስ የዋጋ ግሽበት ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ የግንባታ ቁሳቁስ የዋጋ ግሽበት ሀገራዊ በመሆኑ ነገሩን ትንሽ አክብዶታል፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- በአገልግሎት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ምንድን ነው? ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- ችግሮች ሲኖሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እናደርጋለን፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት መመሥረታቸው ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ፋይዳ ለሚመለከታቸው አካላት ማስረዳት ሌላኛው የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከአካባቢው ምእመናን ጋር ሁለንተናዊ ውይይቶች በተጋጋሚ ይካሄዳሉ፡፡ አቅምና ፍላጎት ያላቸውን አህጉረ ስብከት በመለየት ቅድሚያ እንዲሰጡ በማድረግ ተግዳሮቶቻችንን እንቀንሳለን፡፡ ለፕሮጀክቶቹ ቀድመው በጀቶች እንዲያዙ፣ የተማሪዎችና የመምህራን መረጣ እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል፡፡ ፕሮጀክቶችም ቶሎ ቶሎ ክትትል ይደረግባቸዋል፤ በክትትሉ መሐል የተገኙ ክፍተቶችንም ለማረም ጥረት ይደረጋል፡፡ እንደ አጠቃላይ ፕሮጀክቶች በታቀደው መልኩ እንዲከናወኑ ጥረት በማድረግ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ይሞከራል፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- በዚህ ወቅት ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት እየተሠጣቸው ያለው ትኩረት ምን ይመስላል?  ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- ምንአልባት የአብነት ትምህርት ቤቶችና የገዳማት ደረጃ በዚህ ዘመን ተሻሽሎ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ኅብረተሰቡ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ለገዳማት እየሰጠው ያለው ትኩረትና ተቆርቋሪነት ከድሮው ጋር ሲነጻጸር በጣም አናሳ ነው፡፡ ከዚህ ቀደሞ የአብነት ተማሪዎች ‹‹በእንተ ስማለማርያም›› ብለው በሚማሩበት ወቅት ኅብረተሰቡ ያግዛቸው ይደግፋቸው ነበረ፡፡ በዚህ ዘመን ግን የዚያን ዓይነት ድጋፍና ክብካቤ የለም፡፡ በዚያን ወቅት ገዳማት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ነበሯቸው፤ በየአካባቢው ያለው የኅብረተሰብ ክፍልም ኃላፊነት ወስዶና የእኔ  ብሎ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግበት ሁኔታ ነበር፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ፈተናዎች እንኳን ቢኖሩም ተደጋግፎ የማለፍ ልምድ ነበር፡፡ ኅብረተሰቡም ለአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ለተማሪዎችና ለገዳማትና መምህራን የነበረው ክብር በዚህ ዘመን ካለው በእጅጉ ይለያል፡፡ ከአብነት ትምህርት ቤቶች የሚገኘው ሀገር በቀል ዕውቀቶች የሚታመንባቸው ሲሆን ትውልዱን በግብረ ግብ ስብእና ከመቅረፅ አንፃር የተለየ ድርሻ አላቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ በወቅቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት አዎንታዊ ፋይዳ ጎልቶ የታየበትና ለኅብረተሰብ አካላትና ከባለድርሻ አካላት ተቀባይነትና ድጋፍ ያገኙ ነበር፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን ልጆቹን ወደ አስኳላ (ዘመናዊ ትምህርት ቤት) ከመውሰዱ በፊት የአብነት ትምህርት ተምረው እንዲያልፉ ያደርግ ነበር፡፡  በዚህ ዘመን ደግሞ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ያለን አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ በመንግሥትም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትኩረት ከዕለት ዕለት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ ከሀገር በቀል ዕውቀት ይልቅ ለውጭ ዕውቀትና ለባዕድ አስተምህሮ እየተገዛ መምጣቱ ከአብነት ትምህርት ቤቶች የሚገኘው ሀገር በቀል እውቀት በከፍተኛ ደረጃ እየተዘነጋ ይገኛል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳማትን ‹‹ኋላ ቀር›› አድርጎ መመልከት መጀመሩ ትኩረት እየተነፈጋቸው በመምጣቱ ተረሱ፤ ተጣሉም፡፡ ይህም ከፍተኛ የአገልጋይ እጥረትን አምጥቷል፡፡ ለአንዳንድ የአብነት ትምህርት ቤቶች መጥፋትም ምክንያት ሆኗል፡፡  ለምሳሌ አቡሻኸር፣ አጫብር፣ የቆሜ ዜማ እንዲሁም የተጉለቴ አቋቋም ለመዳከምና ለመጥፋት ከተቃረቡት ትምህርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የገዳማዊ ሥርዓቱም ሆነ የአብነት ትምህርት ቤቶች ይዘት የተለወጠ ባይሆንም ነገር ግን ብዙ ትኩረት ማነስና ፈተናዎች የበዛባቸው ሆነዋል፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚኖራቸው ፋይዳ ምንድን ነው? እነዚህን ተቋማት ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል? ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳትን ማጠናከር ጥቅሙ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም  ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሀገር መሪዎች በአብነት ትምህርት ቤቶች ያለፉ ነበሩ፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተዳከሙ ማለት የቤተ ክርስቲያን ዓለማና ሐዋርያዊ አገልግሎተቷ ተቋረጠ ማለት ነው፡፡ መናፍቃንን ተከራክረው የሚረቱ፣ ያላመኑትን የሚያሳምኑ እንዲሁም ያልጸኑትን የሚያጸኑ በአብነት ትምህርት ቤት ተምረው የሚወጡ አገልጋዮች ናቸውና፡፡ ስለዚህ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማስቀጠል የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማስቀጠል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ሕልውናና መሠረቶች ያሉት አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ላይ ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምራን፣ካህናትና ሊቃውንት የሚወጡት ከአብነት ትምህርት ቤቶችና ከገዳማት ስለሆነ ነው፡፡  ከአብነት ትምህርት ቤቶችና ከገዳማት የሚገኘው ዕውቀት ሌላ ቦታ የማይገኝ ሀገር በቀል በመሆኑ ለሀገርና ለትውልድ እድገት ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በአብነት ትምህርት ቤቶች ያለው ሀገር በቀል ዕውቀት በሌሎች ዓለም ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የለም፡፡ እነዚህ ዕውቀቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀቶች ብቻ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ማለት ደግሞ የሀገር ዕውቀት ነው፡፡ አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት የሕዝብን ሥነልቡና በመጠበቅና ግብረገብ የሆነና ሀገር ጠባቂ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለውና ለሀገሩና ለሕዝብ ፍቅር ያለው ትውልድ የሚፈጥሩት እነዚህ ተቋማት ተቋማት ላይ በትኩረት መሥራት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልድና ሀገር ላይ መሥራት ማለት ነው፡፡ በትክክል የተሠራበት ትውልድ ሀገር ይገነባል፡፡ ያልተሠራበት ደግሞ ሀገር ያፈርሳልና የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ያላቸውን ድርሻ ተረድቶ ማጠናከርና መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት የተጠናከሩ እንዲሆኑ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡  ከአብነት ትምህርት ቤቶች ተምረው ለሚወጡ ተማሪዎች ተገቢው ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለትምህርት ቤቶቹም ተገቢ የሆነ በጀት ሊበጀትላቸው ይገባል፡፡ መምህራንም ተገቢ ክብር ተሰጥቷቸው ለድካማቸው የሚገባ ክፍያ ሊያገኙ ይገባል፤ የተሻሻለ ሕይወትም ይገባቸዋል፡፡ ምእመናን ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት የበለጠ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕንፃ ከመሥራት የሰውን ልጅ መሥራት ላይ ትኩረት ቢያደርጉ ይመከራል፡፡ ምእመናን ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ለገዳማት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡  ከአብነት ትምህርት ቤቶችና ከገዳማት የሚገኘው ሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገር ጠቃሚ መሆኑን መንግሥት ተረድቶ አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችና የገዳማት ውጤቶች ለሀገሪቱ የቱሪዝም ምንጮች ናቸው፡፡ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ደግሞ ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንና ከእርሷ የሚመነጨው ሀገር በቀል ዕውቀቶች የሀገር ውበትና ጌጦች መሆናቸውን መንግሥት በቅጡ ሊረዳ ይገባል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ከዛሬው በተሻለ ትኩረት ቢሰጣቸው መልካም ነው እላለሁ፡፡  ስምዐ ጽድቅ፡- ቀረ የሚሉት ሐሳብ ካለ? ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን የዕውቀት ምንጮች ናቸው፤ ስለዚህ ምንጮች ከደረቁ የዕውቀት የዕውቀት ምንጮቻችን ሊደርቁ ስለሚችል በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በንቃት ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት የሚናፍቁ ነፍሳትን እንድንደርስላቸው ከተፈለገ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ገዳማትን ማጠናከርና ያሉባቸውን ቀዳዳዎች መድፈን ያስፈልጋል፡፡   ስምዐ ጽድቅ፡- ለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡  ዲ/ን አንድነት ተፈራ፡- የክፍሉን አጠቃላይ አገልግሎት እንዳካፍላችሁ ስለጋበዛችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ፡፡  
Read 715 times