የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ካለ አብነት ትምህርት ቤት ማሰብ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ሳይበረዝ እና ሳይደለዝ ከዘመናችን እንዲደርስ ብዙዎች የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ታላቅ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ወንበር ዘርግተው፣ ጉባኤ አስፍተው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድን በማፍራት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የማይደርቅ ምንጭ ሆነው ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል፡፡
የአብነት መምህራን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነገ ህልውና ዕድሜያቸውን ሙሉ አገልግለዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በቅድስት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተተክለው ብዙ ፍሬን አፍርተዋል፤ የማይደርቁ ምንጭ ሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምንጩ ጠጥታ እንድትረካ የበኩላቸውን ሲተጉ ኖረዋል፡፡ ዓለም እና የዓለም ነገር ሳይማርካቸው ዐረፍተ ዘመን እስኪገታቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ትጉሃን አባቶች መካከል ደግሞ አንዱ የኔታ ገብረ ሕይወት ገብረ ኢየሱስ ናቸው፡፡ እኛም የአባታችንን የሕይወት ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትምህርታቸውንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን ባጠቃላይ እስካረፉበት ኅዳር ፳፮ ቀን ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ያለውን ዜና ሕይወታቸውን በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦
በደብረ ሊባኖስ ገዳም የመጻሕፍተ ትርጓሜ መምህር የነበሩት ታላቁ ሊቅ የኔታ ገብረ ሕይወት ገብረ ኢየሱስ ከአባታቸው ከመምሬ ተድላ ወልዱ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ካሰች ለማ በወሎ ክፍለ ሀገር ኮረም ወረዳ ልዩ ስሙ ሰፍያ በሚባል ቀበሌ በቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ.ም ተወለዱ፡፡
የኔታ ገብረ ሕይወት ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከወላጅ አባታቸው ከመምሬ ተድላ ወልዱ ንባብና የቃል ትምህርት ተምረዋል፡፡ ለመንፈሳዊ ትምህርት ካላቸው ጉጉት የተነሣ በታላቅ ወንድማቸው አማካይነት ወላጆቻቸውን ተደብቀው በዚያው ወሎ ክፍለ ሀገር ሙጃ ወረዳ ላስታ መዋዒት ቅድስት ማርያም ወደሚባል አካባቢ በመሄድ መሪጌታ ፈቃዱ መረጮ ከሚባሉ መምህር መዝሙረ ዳዊት ጨምሮ ሌሎች የንባብ ትምህርቶችን ተምረዋል፡፡ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ መምህራቸው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው በዚያው በሙጃ ወረዳ ጦቃ ቅዱስ ዮሐንስ አጥቢያ የመምህራቸው የቅርብ ወዳጅ የነበሩት ባህታዊ ገብረ መስቀል ዘንድ ተቀምጠው የጀመሩትን የዳዊት ንባብና የቃል ትምህርት አጠናቀዋል፡፡ በወቅቱም የትግራይ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የዲቁና መዓርገ ክህነት ተቀብለው በትውልድ ቦታቸው ለጥቂት ጊዜ በዲቁና ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ወደ ትምህርታቸው በመመለስም እዚያው ሙጃ ወረዳ ወፍጫት መድኃኔ ዓለም በሚባል ቦታ ከነበሩት ከመሪጌታ መኮንን ሊበን ለሦስት ዓመታት ቅኔ ከነ አገባቡ ተምረዋል፡፡ ቀጥሎም በዚያው በወሎ ክፍለ ሀገር በዳኅና ወረዳ በአመለ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በድጓ መምህርነት ሲያገለግሉ ከነበሩት ከየኔታ መኮንን ዳቤ ድጓንና ምዕራፍን በሚገባ ተምረዋል፡፡ ከዚያም በዚያው በላስታ ላሊበላ ወረዳ ወደሚገኘው ወደ ሣር ዝና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በወቅቱ የድጓ መምህር ከነበሩት ከመምህር ኃይለ ማርያም ዘንድ ተቀምጠው የምዕራፍንና የድጓ ትምህርታቸውን እንደገና አጠናክረው በመማር አጠናቀዋል፡፡
የድጓ ትምህርታቸውን ለማስመስከር ወደ ቤተ ልሔም ለመሄድ በዕቅድ ላይ እንዳሉ በጤና መታወክ ምክንያት ሐሳባቸው ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ወደ መቄት ወረዳ ወንተላ ቅድስት ማርያም በመሄድ መምህር አየለ ከሚባሉ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ አቋቋም ተምረዋል፡፡
የኔታ ገብረ ሕይወት የአቋቋም ትምህርታቸውን በመማር ላይ እንዳሉ ቀድሞ ያማቸው የነበረው ሕመም ስለተመለሰባቸው ወደ ታሪካዊው ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ጠበል በመጠመቅ ሙሉ ጤንነታቸውን ስላገኙ በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም በተግባር ቤት ለአንድ ዓመት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር ጉንድ ተክለሃይማኖት በመሄድ መምህር ድኅማ ከሚባሉት ሊቅ የዳዊት፣ የነቢያት፣ የሰሎሞን፣ የውዳሴ ማርያም፣ የቅዳሴ ማርያም፣ የኪዳንና የትምህርተ ኅቡዓት ትርጓሜንና የባሕረ ሐሳብ ትምህርትን ተምረዋል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከመምህር አፈወርቅ በቅጽል ስማቸው አባ አቡሻኽር ከሚባሉት ሊቅ አቡሻኽርን በሚገባ ተምረዋል፡፡
በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ተመልሰው በመምህር ገብረ ኢየሱስ ስም ከተመሠረተው አዳሪ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመግባት ከመምህር ብርሃኑ ወልደ ሥላሴ የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን በሚገባ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
በመመህርነት ከመመረቃቸውም በፊት በመማር ላይ በነበሩበት ጊዜ ቀን የተማሩትን ማታ ማታ በማስተማር የዚያን ጊዜ ተማሪዎች የነበሩትን በኋላም ፦
1ኛ. የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን የዳዊት፣ የነቢያት፣ የሰሎሞን ትርጓሜና የባሕረ ሐሳብ ትምህርትን፣
2ኛ. ያረፉትን ብፁዕ አቡነ ቶማስን የውዳሴ ማርያም፣ የቅዳሴ ማርያም፣ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜና የባሕረ ሐሳብ ትምህርትን፣
3ኛ. ያረፉትን ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስን የዳዊትን ትርጓሜ፣ሌሎችንም ደቀ መዛሙርት የዳዊት፣ የነቢያትና የሰሎሞን ትርጓሜ፣ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያምን ትርጓሜ እንዲሁም የባሕረ ሐሳብን ትምህርት ያስተማሩ፣ ታላላቅን ያፈሩ ታላቅ መምህር ነበሩ፡፡
የኔታ ገብረ ሕይወት በመምህርነት ከተመረቁ በኋላ ከ፲፱፻፷፩ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ድረስ ለ፲፰ ዓመታት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ምክትል መምህር በመሆን፣ ከ፲፱፻፸፱ ዓ.ም በሞተ ሥጋ እስከተለዩበት እስከ ኅዳር ፳፮ ቀን ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ድረስ በዋና መምህርነት ባጠቃላይም በገዳሙ ለ፴፬ ዓመታት ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አስፍተው በማስተማር አያሌ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል፡፡
የኔታ ገብረ ሕይወት በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም ከደብረ ሊባኖስ ወደ ዋልድባ ገዳም ለምናኔ ሲሄዱ በወቅቱ ጦርነት ስለነበር ዋልድባ መድረስ ስላልቻሉ የሄዱበት ሳይታወቅ በአራት ወራቸው በጉንድ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ያሉ መሆናቸው ስለታወቀ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ማኅበር ሰዎችን ልከው ወደ ገዳሙ እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል፡፡ የማስተማር ሥራቸውን እንደቀድሞው በመቀጠልም እስከ ከ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ለ፲፰ ዓመታት በማስተማር ፲ መምህራንን አውጥተው አስመርቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በገዳሙ ተግባር ቤት በተለያየ የሥራ ቦታ እየዋሉ ማታ ማታ የውዳሴ ማርያም፣ የቅዳሴ ማርያምና የባሕረ ሐሳብ ትምህርት ያስተማሯቸው ደቀ ማዛሙርት ብዙዎች ናቸው፡፡
የኔታ ገብረ ሕይወት በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም በድንግልና ኑረው በ፲፪ አበው ምንኵስና የተቀበሉ ሲሆን በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም ደግሞ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የቅስና መዓርግን ተቀብለዋል፡፡ የኔታ ገብረ ሕይወት ገብረ ኢየሱስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት እንዳያስተምሩ፣ አጎንብሰው መጽሐፍ እንዳይመለከቱ ከዶክተሮች መመሪያና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ‹‹ከወንበሬ (ከጉባኤዬ) ሕይወቴ ታልፋለች እንጂ ትምህርቱን አላቋርጥም፤ ማዕደ እግዚአብሔር አይታጠፍም›› በማለት እስከ ዕለተ ሞታቸው ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡
ወንጌልን በቃል ሳይሆን በሥራ የተረጎሙ ትዕግሥትን እንደሸማ የተጎናጸፉ፣ ትልቅ ትንሽ ሳይሉ ሁሉን አክባሪ የነበሩት የኔታ ገብረ ሕይወት በተለይም በጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ መጻሕፍትን ሲመለከቱና ሲያመሠጥሩ እንዲሁም እስከ ኅዳር ፳፫ ቀን ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ድረስ ሲያስተምሩ ቆይተው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በተወለዱ በ፸፪ ዓመታቸው ኅዳር ፳፮ ቀን ፲፱፻፺፭ ከዚህ ዓለም በሞተ በሥጋ አርፈዋል፡፡
በረከታቸው ይደርብን
ምንጭ ፦ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ጥር ወር ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ፶ኛ ቁጥር ፳