እውነተኛ የፍቅርና የርኅራኄን ሥራ ያደረገና ያሳየ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የክርስቶስ የርኅራኄ ሥራ የሚመነጨው የባሕርይ ከሆነ ፍጹም ፍቅሩ ነው፡፡ ይህ ፍቅሩ ፍጥረትን ሁሉ ሳይለይ በማያቋርጥ መግቦቱ ያኖረዋል፡፡ ሰዎች ደግሞ ከየትኛውም ፍጡር በተለየ የፍቅሩ ብቻ ሳይሆን የክብሩ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ፈቅዷል፡፡ ስለዚህም ለክፉዎችም ለደጎችም በማያቋርጥ መግቦቱ ይደርስላቸዋል፡፡ ሳይለይ ሳያዳላ መውደድን አሳይቷል፤ አስተምሯል፡፡ የዚህ የፍቅር ትምህርቱ ተቀባይ፣ ወራሽ፣ ሰባኪ፣ አድራጊ ሆና በምድር ላይ የተገለጸችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቶስን መስለው የሚኖሩ ወገኖች ኅብረት ናት፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በርኅራኄ ሥራ ክርስቶስን መስላ መገኘት ግዴታዋ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በችግር በመከራ ውስጥ ላሉ ወገኖች የርኅራኄ ሥራዎችን የመሥራት ታሪክ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ ከተቋቋመ በኋላ እንኳን በተለያዩ የርኅራኄ ሥራዎች ቀዳሚ ሚና ነበራት፡፡ በተለይም በተደጋጋሚ በሀገራችን ይከሰት በነበረው የድርቅ አደጋ የሚጎዱ ወገኖችን በመጎብኘት ግንባር ቀደም ሚና ስትጫወት ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው የ፲፱፻፸ዎቹ ድርቅና ተያያዥ ችግሮች ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ማእከላትን በማቋቋም ለሰዎች በመድረስ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዲኖራት ምስጉን አመራር ሰጥተዋል፡፡ በብዙ ማእከላት ቤተ ክርስቲያን ርዳታ ትሰጥ ነበር፡፡
በተጨማሪም በዚያው ዘመን በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያትም ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይና ዘላቂ ማቋቋሚያ ድጋፎችን እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ወገኖች የሕፃናት ማሳደጊያዎችን በመላው ሀገሪቱ በመክፈት የርኅራኄ ሥራዎችን አስፋፍተው ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ከምእመናን በሚሰበሰብ ገንዘብና ቁሳቁስ፣ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም ለጋሾች የሚመጡ ድጋፎችን በታማኝነት ያሰራጭ ነበር፡፡
በዚህም በወቅቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ጥሩ አመራር ይሰጥ እንደነበር፣ ታማኝ አገልጋዮች፣ ጠንካራ ተቋማት፣ የሰመረ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ግንኙነት እንደነበረም ያሳያል፡፡
ጊዜያት አልፈው በአሁን ዘመን ያለውን ሁኔታ ስንገመግም ደግሞ ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች የተተበተበችበት ጊዜ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሀገራችንን ዘርፈ ብዙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እየተፈታተኗት ነው፡፡ ጦርነት፣ በአየር መዛባት የሚመጡ ጉዳቶች፣ አንበጣ፣ የብሔር ግጭቶች፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የኑሮ ውድነት፣ የውጪ ወረራ ወዘተ እየተፈታተኗት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ በሃይማኖት ምክንያት ራሳቸው የቤተ ክርስቲያንም ቤተሰቦች መከራ ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ለመረዳት ያለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ስደት፣ ሞት እና የንብረት መውደም በቂ ማሳያ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለአደጋዎች ምላሽ የመስጠት የቀደመው ክርስቲያናዊ ዝግጁነት፣ ባህል፣ የተቋም ጥንካሬ፣ የአመራር ቅንነት አላት ወይ የሚል ጥያቄ ማንሣት የግድ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳር ኢትዮጵያ ከገጠማት ፈተና አንጻር የሚጠበቅባትን ያህል ምላሽ እየሰጠች መሆኑን በጥርጥር መልክ የሚታዘቡ በርካቶች ናቸው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ በሀገር ውስጥ ለሚታዩት የተለያዩ ቀውሶች በተለያየ ጊዜ ዘር ሃይማኖት ሳትለይ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የርዳታ እጇን ስትዘረጋ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ካለፉት ዘመናት የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ለማለት ይከብዳል፡፡ እንደ ግዙፍነቷ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ያገናዘበ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ማደራጀቱን የሚያሳይ ርምጃ ብዙም አይታይም፡፡ የርኅራኄ ሥራን የሚያስፋፋ ለወቅቱ ዘርፈ ብዙ ችግር ምላሽ የሚሰጥ በጎ አድራጎት ተቋም መሥርቶ በመላው ሀገሪቱ ማእከላዊነት ባለው መንገድ አድልዎ በሌለበት አግባብ ችግረኞችን የማገልገል ነገር በበቂ አይታይም፡፡ በሀገራችን ያለውንና የሚመጣውን መከራ ገምግሞ፣ ተንትኖ የሚያውቅ፤ በመላው ዓለም ካሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አጥቢያዎች ርዳታ ማሰባሰብ የሚችል፣ የመጣውን ርዳታ በታማኝነት የሚያከፋፍል ተቋም ዛሬ ይዛለች ወይ? የሚለው ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን የርኅራኄ ሥራ መሥራት ያለባት ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው የሀገሪቱ ችግር ላይ ላሉ ዜጎች ሁሉ ነው፡፡ ጠላት ወዳጅ ሳትል ድጋፏን ለሚፈልግ ሁሉ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ላሉ ለራሷ ቤተሰቦችም በበቂ ሁኔታ ርዳታ ለመስጠት ያላት አቅም በቂ መሆኑ ላይ ጥያቄ ይነሣል፡፡ የኮቪድ ፲፱ ወረርሺኝ ባስከተለው ተጽእኖ ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት ለአገልጋይ ካህናት ደሞዝ ለመክፈል እስከመቸገር ደርሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የዘር ጥላቻ፣ የሃይማኖት አክራሪነት ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ ነው፡፡ ክርስቲያኖች እየተገደሉ ነው፡፡ ብዙዎች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በቅድሚያ ፈጣን ምላሽ የሚፈልጉት ከቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ለጉዳተኞቹ ድጋፍ አሰባስባ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ለማይሰጡ ለርኅራኄ ሥራም የተዘጋጀች ሆና በመገኘት በፍጥነት ምላሽ እንድትሰጥ ይጠበቅባታል፡፡
ዛሬ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቀው ከአገልጋዮቿም ባለፈ ችግር ላይ ላሉት ሁሉ ፈጥና የምትደርስ ተቋም ሆና መገኘት እንድትችል ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ፶ ሚሊዮን ሕዝበ ክርስቲያንን ያቀፈች ናት፡፡ ከእነዚህ ምእመናን በትጋት ድጋፍ ማሰባሰብ ቢቻል ለበርካቶች ፈጥና ደራሽ መሆን የሚያስችላት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ባዕለ ጸጋ ምእመናን ያሏት ናት፤ በርካታ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ምእመናን ቤተሰብም አሏት ከእነሱ በርካታ ርዳታ ማሰባሰብ ትችላለች፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ቤተሰቦቿ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ፣ ሐሳብ ማሰባሰብ ትችላለች፡፡ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አቅሙን አሳድጎ ከሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናትና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባላት ጋር አብሮ በመሥራትና ድጋፍ በመጠየቅ ከፍተኛ ርዳታ ማሰባሰብና ማሰራጨት ይችላል፡፡ ቤተ ከርስቲያን በምትሰጠው ርዳታ መጠን፣ ዓይነት፣ አሰጣጥ ሁሉ ከሌሎች ርዳታ ሰጪዎች ሁሉ ከፍ ብላ መገኘት አለባት፡፡ ከግብዝነት የጸዳ፣ አድልዎ የሌለበት፣ ተንኮል ያላዘለ የርዳታ አሰጣጥ ማሳየት ይጠበቅባታል፡፡ በዚህ ደረጃ አቅምን ማሳየት መቻሉን የሚጠራጠሩ ሁሉ ነገሩን በትዝብት ማየታቸው አልቀረም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ግለሰቦችና ቡድኖች በራሳቸው ዓላማና ጥረት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጎላ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ሰይጣን አዘገየን ወይስ ምን?
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይሄንን ለማድረግ የአስተምህሮ ግዴታ እያለበት፣ የታሪክና የልምድ መሠረት እያለው፣ ብዙ እምቅ አቅም ይዞ ሳለ በዚህ በመከራ ጊዜ የሕዝብ ባለውለታ ሆና ቤተ ክርስቲያን ጎልታ መታየት እንድትችል ካላደረገ በእጅጉ ትዝብት ላይ መውደቅ ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አመራር ንቁ እንዲሆን፣ ቤተ ክርስቲያን ያላት ተቋም እንዲጠናከር፣ እንዲሰፋ አድርጎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ካሉ ተቋማት ሁሉ ግዙፍና ሰፊ ሆና እንደመታየቷ ከእርሷ የሚጠበቀው ተግባርም ግዙፍና ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ቢሆን ለሌሎችም መትረፍ ያ ቢያቅት እንኳ ለራሷ ችግረኛ ቤተሰቦች እንኳን በበቂ መድረስ ይገባታል፡፡
ዛሬ ሌላው የሃይማኖት ድርጅት በርዳታ ስም መንጋውን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚያስኮበልልበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይ ካህናቷ ጀምሮ ለተከታይ ምእመንዋ መድረስ ካልቻለች የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ከትዝብት ባለፈም ተሰሚነትን የሚያሳጣ፣ ለሃይማኖታዊ አገልግሎትም እንቅፋት የሚሆን ድክመት ሆኖ ይታይባታል፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ በሀገር ውስጥ ለተከሰቱ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ክስተቶች በቻለችው መጠን ስትረዳ ፣ ተጎጆዎችን ስትታደግ እንደቆየች ቢታወቅም በቂ ነው ግን ማለት አይቻልም፡፡ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ድርጅት ፣የተለያዩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ምእመናንን እና ባለድርሻ አካላትን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በማደራጀት የተለያዩ ርዳታ ስታደርግ ብትቆይም ፶% በላይ ምእመን ላላት ትልቅ ተቋም ግን እጅግ አናሳ ነው፡፡ ስለዚህ ከላይ እስከ ታች ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳር ይንቃ፣ ይብቃ፣ ለሀገር ለወገን ይድረስ፤ የችግረኞችን ዕንባ ያብስ፤ ክርስቶሳዊ መልኩን ከዚህ በበለጠ ሊያሣይ ይገባል እንላለን፡፡