Saturday, 25 September 2021 00:00

የመስቀል በዓል ታሪክ ለልጆች

Written by  ምኒልክ ብርሃኑ
ልጆች! እንደምን ከረማችኹ! …… እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችኹ! …… በዐዲሱ ዓመት ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት እየተዘጋጃችኹ ነው? ጎበዞች! ፳፻፲፬ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲኾንላችሁ እንመኛለን፡፡  ልጆችዬ! በመስከረም ወር ዳመራ በመለኮስ፣ ችቦ በማብራት የምናከብረው ታላቅ በዓል አለ! የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል በዓል ነው፡፡ በዛሬ ቆይታችን ስለመስቀል በዓል ታሪክ፣ ስለደመራና በኢትዮጵያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የት እንደሚገኝ እንማራለን፡፡ አብራችኹን ቆዩ! በድሮ ጊዜ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው ብቻቸውን በጨለማ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በመስቀል ላይም ተሰቀሎ ሁላችንንም አዳነን፡፡ የሰው ልጆችንም ወደ ብርሃን አመጣቸው::  ታዲያ ልጆች! ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ብዙ ሰዎችን ከበሽታ ያድናል፣ ከሕመማቸው ይፈውሳል፣ ከሞት ያስነሣል፡፡ ከዕለታት ባንድ ቀን በክርስቶስ የማያምኑ አይሁዶች መጡና የክርስቶስ መስቀል ለምን ይፈውሳል፤ ሰዎችንስ ለምን ያድናል ብለው በክፋት ተነሣሡ፡፡ ሕዝቡም ከበሽታው እንዳይድን ብለው በምቀኝነት ለመደበቅ ወሰኑ፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በጉድጓድ እንደቀበሩት፤  ልጆች! እነዚያ ክፉ ሰዎች መስቀሉን ለመደበቅ ብለው ትልቅ ጉድጓድ ቆፈሩ፡፡ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥም ቀበሩት፡፡ የቀበሩት ቦታ ማንም ሰው እንዳያውቀው ቆሻሻ ደፉበት። ቆሻሻውም ተጠራቅሞ ተጠራቅሞ ትልቅ ተራራ ኾነ። በዚህም ምክንያት የመስቀሉ ቦታ ሳይታወቅ ብዙ ዓመታት አለፈ፡፡   የተቀበረውን መስቀል ንግሥት ዕሌኒ እንደፈለገችው፤ ልጆች! ከብዙ ጊዜ በኋላ ንግሥት ዕሌኒ የምትባል ታላቅ ንግሥት ነገሠች፡፡ ታዲያ ይቺ ንግሥት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ጉድጓድ ለማውጣት ተነሣች፡፡ ወደተቀበረበት አገር መጣችና የአካባቢውን ሰዎች ጠየቀች፡፡ ነገር ግን የሚነግራት ሰው አጣች፡፡ ከዛም ኪራኮስ የሚባል ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ እርሱም “ለብዙ ዓመታት ቆሻሻ ሲደፋበት ስለቆየ ቦታው እንደሌሎቹ ትልቅ ተራራ ኾኗል፡፡ ስለዚኽ ትክክለኛው ቦታ የቱ እንደኾነ አላውቅም፡፡ ነገር ግን አንድ ዘዴ አለ፡፡ ዘዴውን የምትጠቀሙ ከኾነ እነግርሻለው” አላት፡፡ ልጆች! ኪራኮስ መስቀሉን እንድታገኘው የሚነግራት ዘዴ ምን ይኾን? ዘዴውስ መስቀሉን እንድታገኘው ይረዳታል? አብረን እንከታተል እሺ…. ንግሥት ዕሌኒ ዳመራ እንደደመረች፤ ንግሥት ዕሌኒ ኪራኮስ የሚነግራትን ዘዴ ለማወቅ በጣም ጓጓችና “ምንድን ነው ዘዴው ንገረኝ” አለችው፡፡ እርሱም “እንጨት አሰባስበሽ፣ ደመራ ደምረሽ፣ ዕጣን አድርጊበትና በእሳት አያይዢው፤ ከዛም የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ሲመለስ የትኛው ተራራ እንደኾነ ይጠቁምሻል” ብሎ ዘዴውን ነገራት፡፡ ልጆች ይኽ ዘዴ ይሠራ ይኾን? ደመራ በመደመር ከዛም ጭሱ ወደ ላይ ወጥቶ እንደገና ተመልሶ ቦታውን ይነግራት ይኾን? ጭስ ደግሞ ወደ ላይ እንጂ ወደ ታች አይሔድም፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ምንም የሚሳነው ነገር የለምና ንግሥት ዕሌኒ እንዲሳካላት ሕዝቡን ሰብስባ ጸሎት አደረገች፡፡  ጸሎቱን ከጨረሱ በኋላ እንጨት አሰባስባ ደመራ አስተከለች፡፡ ደመራው ላይ ዕጣን ጨመረችበት በእሳት ለኮሰችው፡፡ የአካባቢውም ሕዝብ ተሰብስበው የሚኾነውን ይከታተሉ ጀመር፡፡ ልጆችዬ! ታዲያ በዚኽ ጊዜ አንድ አስደናቂ ነገር ተከሠተ፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጣና እንደገናም ወደ ታች ተመልሶ ወረደ፡፡ ከዛም አንድ ተራራ ላይ አረፈና ለተራራው ሰገደ፡፡ ሕዝቡ በሚያየው ነገር በጣም ተደነቀ፡፡ ዕሌኒም በጣም ደስ አላት፡፡ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ሁሉም በአንድነት ኾነው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡    መስቀሉ በክብር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳስገቡት፤ ልጆች አያችሁ አይደል የእግዚአብሔርን ሥራ! ለብዙ ዓመታ ተደብቆ የቆየው ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በደመራና በዕጣን ጢስ ተገኘ፡፡ በዚኽ መሠረት ንግሥት ዕሌኒ ብዙ ሰዎችን አሰባስባ ተራራውን ማስቆፈር ጀመረች፡፡ ቁፋሮ የተጀመረበት ዕለት መስከረም ፲፮ ቀን ነበር፡፡ ለሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉ ከጉድጓዱ፡፡ እርሷም ደስ አላት፤ ሕዝቡም ይኽንን ድንቅ ነገር አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ችቦም አብርተው እየዘመሩ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት፡፡ ልጆችዬ! አያችሁ አይደል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ፡፡ እነዛ ክፉ ሰዎች መስቀሉን ቢቀብሩትም ተደብቆ ሊቀር አልቻለም፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በአረጋዊ ኪራኮስ ምክርና ንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ከተቀበረበት በክብር ወጣ፡፡ መስቀሉም እንደበፊቱ ሕዝቡን ከበሽታ ማዳን፣ የሞተን ማስነሣት ጀመረ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላም የክርስቶስ መስቀል ከቁፋሮ የተገኘበትን ቀን መታሰቢያ በማድረግ በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን ደመራ ይደመራ፣ ችቦ ይበራል፣ መዝሙር ይዘመራል፤ በዓሉመ በድምቀት ይከበራ፡፡  የመስቀል በዓል በአገራችን ልጆች! ከላይ እንደተማርነው መስቀል የሚከበርበትን ምክንያት አውቃችኋል አይደል? ታዲያ ይኽ የመስቀል በዓል በተለየ ሁኔታ በአገራችን ኢትዮጵያ በደመቀ መልኩ ይከበራል፡፡ ከዐዲስ ዓመት ቀጥሎ የምናከብረው በመኾኑ የመስቀል በዓል ለእኛ ልዩ ትርጒም አለው፡፡  በቤተ ክርስቲያናችን ደመራ በመደመር፣ ችቦ በማብራት፣ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም፤ እንዲኹም በየሰፈሩና በየአካባቢው ዳመራ እየተተከለ፣ ችቦ እየተለኮሰ ይከበራል፡፡ በይልጥ ደግሞ በመስቀል ዐደባባይ ትልቅ ዳመራ ተተክሎ ሰንበት ተማሪዎች ትርዒት እያቀረቡ፣ መዝሙር እየዘመሩ፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተሰባስበው ሕዝቡ ጧፍ እያበሩ በድምቀት ይከበራል፡፡ ስለዚኽ ልጆች የመስቀልን በዓል ስናከብር የሰላማችንና የድኅነታችን ዓርማ መኾኑን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን፣ የዘላለም ሕይወትን ሊሰጠን መሥዋዕትነት የከፈለበት፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መኾኑን እያሰብን ማከበር ይገባናል።  በሉ ልጆች ለዛሬ በዚኽ ይበቃናል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ በሌላ ታሪክ እስከምንገናኝ ደኅና ሰንብቱ፡፡  
Read 961 times