ሐመርን ያውርዱ
ስምዓ ጽድቅ ያውርዱ
የወሩ የማኅበረ መልእክት
Friday, 12 November 2021 00:00

ለተቸገረ የሚረዳ ብፁዕ ነው

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን የምትደግፈው ኃላፊነቷ በመሆኑ ነው። የሰውን ልጅ ሁሉ የምትረዳውም ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳትለይ ሰው መሆናቸውን በማየት ብቻ ነው። መመሪያዋም “ለድኃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፤ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፣ በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም” የሚለው አምላካዊ ቃል ነው (መዝ.፵፥፩-፪)። ይህ ቃል ለተቸገረ መርዳት በእግዚአብሔር እንድንጠበቅ ከማድረግ በተጨማሪ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ድርጊታችንን ዓይተው፣ ሥራችንን ከግምት ውስጥ አስገብተው እንዲያመሰግኑን ምክንያት ይሆናል። ወደ ሃይማኖት እንዲመጡም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ቤተ ክርስቲያን በመዋቅርም ሆነ ልጆቿ በተናጠል ለተቸገሩት መድረሳቸው ሁሉን ሰብሳቢና ለሁሉ ደራሽ ሲያሰኛት ኖሯል። ሐኪም ሰዎችን የሚያክመው ዘር ሳይለይ፣ ቋንቋ ሳይመርጥ ፣ ወገን ጠላት ብሎ ሳይከፋፍል በጦርነት ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሁሉ መሆኑ ይታወቃል። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ርዳታና ድጋፍ ደግሞ ከሐኪምም በላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ በየዘመናቱ ለተቸገሩት ስትደርስ የኖረችው አምላካዊ ትእዛዝ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሕይወት ለአደጋ መጋለጥ ስለሚያሳስባትም ጭምር ነው። ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በማድረጓም “መልካሙን ሥራችሁን ዓይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” የሚለውን አምላካዊ ቃል በተግባር ትገልጣለች (ማቴ.፭፥፲፮)። ይህም አሕዛብ ሥራዋን አይተው የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ መንገድ ይከፍታል። በዘመናችን በተከሠተው ጦርነት ወገኖቻችን ሀብትና ንብረታቸውን አጥተዋል። ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል አካባቢ ሳይለይ ለስደትና ለረኃብ ተዳርገዋል። በጦርነት የተሰለፉትም ከግራም፣ ከቀኝም እየቆሰሉ ነው። ችግሩ ያሳሰባቸው ወገኖች የተፈናቀሉትን ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን በማድረግ ላይ ናቸው። ምንም እንኳ ርዳታን ምክንያት አድርገው ለችግር በተጋለጡ ወገኖቻችን ቍስል እንጨት የሚሰዱና ሕመማቸውን የሚያባብሱ አካላት ቢኖሩም ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን የምትረዳው ሰው በመሆናቸው ብቻ በመሆኑ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን በማጣት ከችግራቸው እንዲላቀቁ፣ ከሥነ ልቡና ስብራት ተላቀው ነገ አዲስ ሕይወት መኖር እንዲጀምሩ ለማድረግ ጭምር ነው። የተጎዱት ወገኖቻችን ከዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ብዙ መሥራት፣ ልጆቿን አስተባብራ ለተቸገሩት ሁሉ በመድረስ ከመከራ እንዲያወጧቸው ማድረግ ይኖርባታል። ‹‹ለተቸገረ የሚረዳ ብፁዕ ነው›› ሐመር ጥቅምት-፳፻፲፬ ዓ.ም. የማኅበሩ መልእክት ፫ ቤተ ክርስቲያን ዘር፣ ሳትመርጥ፣ ቋንቋ ሳትለይ ሁሉንም የምትረዳውም ተልእኮዋ ሰማያዊ በመሆኑ ነው። በተጎዱት አካባቢዎች የሚገኙ አባቶች ሆስፒታል ሔደው የቈሰሉ ወገኖቻችንን ሲጠይቁ የተመለከትነው፣ ከችግረኞች ጋር አብረው በዓል ሲያከብሩ ያየነው ሰዎች ችግር በገጠማቸው ጊዜ እንድትደርስላቸው ከአምላኳ በመታዘዟ ነው። በግል ከመሮጥ ይልቅ እየተሰባሰቡና እየተደራጁ ለችግረኞች የሚያስፈልጋቸውን በማሰባሰብ ማድረስ ያስፈልጋል። ክርስቲያኖች ይህን የምናደርገው የሰው ልጅ ሁሉ ጉዳት ጉዳታችን መሆኑን ስለምናምንና በሌሎች የደረሰ ክፉ ነገር እንዲደርስብን ስለማንፈልግ ነው። ምእመናን ልጆቿ ለችግር ለተጋለጡት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብና የቍሳቁስ ድጋፍ ለማሟላት የበኩላችንን እናበርክት የምንለው እንደሌሎች በችግረኞች ጉዳት ለመነገድ እና ታዋቂነትን ለማግኘት ሳይሆን ለተቸገረው ሁሉ መድረስ ከአምላካችን የታዘዝነው በመሆኑና እየተሠራ ካለው የበለጠ መሥራት ስለሚጠበቅብን ጭምር ነው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተግባሯ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ማገናኘት ብቻ ሳይሆን በችግራቸው ጊዜ ቀድማ በመድረስ መርዳት መሆኑን መረዳት ይገባል። ቤተ ክርስቲያን ችግረኞችን ከረኃብና ከጊዜያዊ ችግር ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አጽናንታ በገጠማቸው ጊዜአዊ ችግር ሳይሸነፉ ነገ ታላቅ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ ጭምር መንፈሳቸውን ማነቃቃትም እስከ አሁን ከተሠራው የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር መሆኑን ክርስቲያኖች ሁሉ እንረዳ። ስለዚህ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቡና ስብራት የገጠመውንም በመንፈሳዊ ምክር መርዳት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን መረዳት ይገባል። የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት ለአሕዛብ ከሚገለጥበት ይህ ነውና። ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራዊ ተግባራት አንዱ ለችግር የተጋለጡትን ለመርዳት ቀድሞ መገኘት ነው። ማኅበራት፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዘማርያንና ምእመናን ሁሉ እየተባበሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጡትን ሁሉ በመርዳት ለወገን ደራሽነታቸውን፣ ከራሳቸው ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድሙ መሆናቸውን ካስመሰከሩ የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት ለአሕዛብ ሁሉ እንዲገለጥ ያደርጋል። እንዲህ ማድረጋችንም “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፤ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜም ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና” ተብለው ከሚመሰገኑትና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ግቡ ከሚባሉት ወገኖች ጋር አንድ ያደርገናል። በምድርም የአእምሮ ሰላም እንደምናገኝ አስበን ምክንያት ሳናበዛ ሰውን ሁሉ ለመርዳት ጊዜ ሳንወስድ ተግባራዊ ሥራ መሥራት ችግሩ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ተባብረን ወገኖቻችንን ከችግር በመታደግ ለተቸገረ የሚደርስ ብፁዕ ነው የተባለውን አማላካዊ ቃል በተግባር መግለጥ እንደሚገባ ማስገንዘብ እንወዳለን። 
Read 370 times

ማስታወቂያ