Search results for: ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ - ሐመረ ጽድቅ
ውድ አንባብያን ባለፈው እትማችን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን ተከታታይ ጽሑፍ እንደምናቀርብ ቃል ገብተን የመጀመሪያውን ክፍል አቅርበንላችኋል። በመጀመሪያው ክፍልም የቤተ ክርስቲያንን ምንነት፣ የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት አራት እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። የሚለውን ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ወር እትማችን ድግሞ ከባለፈው የቀጠለውንና ሁለተኛውን የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ “ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት” የሚለውን አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አንድ ሰው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲያስብ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ማሰብ የለበትም። በፖለቲከኞች ውስጥ አንድ የሚያደርግ ምንም የእግዚአብሔር መንፈስና ረቂቅ ኃይል የለም። ምድራዊና ጊዜያዊ ዓላማ፣ አሠራርና አስተሳሰብ ነው የሚያሰባስባቸው። በክርስትና ግን እንደዚህ አይደለም፤ በክርስትና ትልቁ ነገር ከእግዚአብሔር ጋራ እንድ መሆን ነው። አሁን ተመልከቱ ክርስቶስ ሳያድርብን ስለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ነው እኛ መቆርቆር የምንችለው? አናስብ ማለት አይደለም ግን ሐሳባችንን እንኳን በየትኛው መንገድ ልናቀርብ እንደሚገባን እንድናውቅ ነው። አንድ ሰው ንስሐ ሳይገባ፣ ሳይቈርብ፣ እውነተኛ ሳይሆን፣ ክርስቶስ በእርሱ ሳያድር እንዴት ሆኖ ስለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መናገር ይችላል? በጣም ከባድ ነው። በመናገራችን አንድነቱ የሚመጣ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፤ በመናገራችን ሳይኾን የክርስቶስ በመሆናችን ነው አንድነቱ የሚመጣው። በሁላችንም ክርስቶስ ከአደረ፥ የክርስቶስ ማደሪያ ከኾንን አንድ መሆናችን አይቀርም። አሁን ከክርስቶስ የተለየን ሽፍቶች ተጣልተን ምን አንድነት ልናመጣ እንችላለን? ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት በዚህ አንድነት ማመን አለብን። ክርስቶስ እንዳለው እርሱ በእኛ ማደር ይፈልጋል፤ ለሚያንኳኳው ጌታ የልባችንን በር ከፍተን ልናስገባው ያስፈልጋል።
ውድ አንባብያን በዚህ ዓምድ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ነገ ምን መሆን እንዳለባት የሚያሳይ፣ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባል ቤተ ክርስቲያን ልትደርስበት የሚገባትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ልማታዊ አቅጣጫዎችን ማሳየት፣ ትውልዱም የድርሻውን እንዲወጣ ማመላከት ነው። በመሆኑም አስቀድመን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን በተከታታይ አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ።
እንደ እግዚአብሔር ቸርነት በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው "አሐቲ ቤተ ክርስቲያን፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፤" የሚል ይሆናል።
ክፍል አንድ
መግቢያ
“ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስ ወይም ቤተ ክርስቲያን ልትባል የምትችለው ቢያንስ አራት ነገሮን ከራሱ ከክርስቶስ ከተማርነውና ከሐዋርያት ባገኘነው ላይ ብቻ ጠብቃ ስትገኝ ነው። እነዚህም ሐዋርያዊ ትውፊት፣ ሐዋርያዊ ትምህርት፣ ሐዋርያዊ ክህነትና ሐዋርያዊ ሥርዓተ አምልኮን ጠብቃ ስትገኝ ነው። ትምህርቱና ትውፊቱ ለሥርዓተ አምልኮ መሠረቶች ናቸው። ክህነቱ ደግሞ የአምልኮቱ መፈጸሚያ ነው። ያለ እውነተኛ ሃይማኖትና ሥርዓተ አምልኮት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ወይም መንፈሳዊ ውሕደት እንደማይቻል ሁሉ ያለ ሐዋርያዊ ክህነት ደግሞ ትክክለኛ አምልኮትን መፈጸም አይቻልም። ይህ ማለት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖራቸው የሚችለው መንፈሳዊ ግንኙነትም እንበለው ውሕደት ያለ እውነተኛ ክህነት ሊፈጸም አይችልም ማለት ነው።”
(የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያሪክ፣ ቀዳሜ ቃል)
ከላይ የተወሰደው ጽንሰ ሐሳብ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ በተሰኘው መጽሐፍ በቀዳሜ ቃል ላይ ያስቀመጠው መልእክት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በቦታና በጊዜ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሁኔታዎች አይወሰንም፡፡ ፍጥረታቱን በቀጥታ ለመገናኘትም እርሱን የሚያግደው ነገር የለም፡፡ እርሱ እንደወደደና እንደፈቀደ ፈጥሮ በመግቦቱና በአምላካዊ ጥበቃው እየተገናኘም ይኖራል፡፡ እርሱ ፈቅዶና ወዶም የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበትን መንገድ እጅግ አብዝቶታል፡፡ ከዚህ ከብዙው መገናኛ መንገዱ መካከል ክህነት አንዱ ነው፡፡ ይህ የክህነት አገልግሎት ከህገ ልቡና ጀምሮ እስከ አሁን አለ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ከላይ በዲያቆን ብርሃኑ የተጠቀሰው ጽንሰ ሐሳብ የሚያስረዳን እግዚአብሔር በዚህ የክህነት አገልግሎት አማካኝነት ከሰው ልጆች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ሲያደርግ እንደኖረ ወደፊትም እንደሚኖር ነው፡፡ ዲያቆን ብርሃኑ በመቀጠልም “አንዳንድ ሰዎችን የልቡናቸውን ቅንነት አይቶ እግዚአብሔር ቢቀበልላቸው እንኳን ለድኅነት ይበቁ ዘንድ መንገዳቸውን ወደ ትክክለኛው እምነትና ሥርዓተ አምልኮት ይመራቸዋል። ለምሳሌ ያህል ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቆርነሌዎስን ጸሎቱን፣ ምጽዋቱንና የልቡን ቅንነት አይቶ ተቀብሎ ጠርቶታል። ቅዱስ ጳውሎስን ደግሞ ቀናዒነቱንና ለአመነበት ነገር ራሱን አሳልፎ መስጠቱን አይቶ ጠርቶታል። ሁለቱንም በተአምራት ከመለሳቸው በኋላ መጀመሪያ ያደረገው ግን ከካህናት ጋር ማገናኘትና ከቤተ ክርስቲያን ሊያገኙት የሚገባቸውን እንዲያገኙ ማስቻል ነው። መልሶ ከራሱ ያዋሐዳቸው በዚህ ሐዋርያዊ መንገድ ነው።” (ዝኒ ከማሁ) በማለት ያስረዳል፡፡