ይህ ሁሉ የሚያስረዳን የክህነት አገልግሎት ለእውነተኛው ድኅነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና ቤተ ክርስቲያን አምልታና አስፍታ የምታስተምረው፣ ምእመናንንም ከእግዚአብሔር ጋር የምታገናኝበት መንገድ መሆኑን ነው። በተለይም በዘመናችን ያለው ትልቁ ተግዳሮት ለክህነት ያለው አመለካከት ከውስጥም ሆነ ከውጭ እጅግ የተዛባ መሆኑ ነው፡፡ ከውስጥ ያለው ተግዳሮት ክህነትን እንደሚገባ ባለመያዝ ከውጭ ያለው ደግሞ ከነአካቴውም አያስፈልግም በማለት የሚሰነዘረው ጦር እጅክ የከፋ መሆኑ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በአካል ያገኛቸውንና የፈወሳቸውን በሽተኞች ሳይቀር ወደካህን መላኩ የክህነትን አስፈላጊነት በአጽንኦት የሚያስረዳን ነው።
ቤተ ክርስቲያን ከነቢያትና ከሐዋርያት የተለየ አስተምሮም፣ አካሄድም የሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸምም የላትም። ምክንያቱም በክርስቶስ ማዕዘንነት በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ተመሥርታለችና። መጽሐፍ ቅዱስ “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልና፤ የሕንጻው የማዕዘን ራስ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም ሕንጻ ሁሉ የሚያያዝበት የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ግንብ የሚያድግበት ነው። (ኤፌ.፪፥፳-፳፩) በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ ጥንት ከአበው ጀምሮ ከዚያም በነቢያትም ሆነ በሐዋርያት የነበረው የክህነት አገልግሎት ዛሬም ሕያው ሆኖ አለ። እውነተኛውና ትክክለኛው ሥርዓተ አምልኮት ይፈጸም ዘንድም እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ስጦታ አድሎናል። በዚህ ጽሑፍ በተከታታይ እትሞቻችን ከምንነቱ በመነሣት በዘመናት የነበረውን ህልውና በተለይም በዘመናችን ያለበትን ተግዳሮትና በተወሰነ መልኩ የመፍትሄ አቅጣጫም ለመጠቆም እንሞክራለን።
፩. የክህነት ምንነት
ክህነት፡- ተክህነ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም አገለገለ፣ ተሾመ፣ ዲቁና፣ ቅስና ተቀበለ፣ መንፈሳዊ ሥልጣን ተቀበለ ማለት ነው።
“ተክህነ፤ ተካነ፤ ክህነት ተሾመ፣ ተቀበለ፣ ካህን ሆነ፣ ካህን ተባለ ለማገልገል።ክሂን ከሹመት በኋላ ማገልገልን፣ ተክህኖ ከማገልገል በፊት መሾምን፣ የሹመትን ጊዜ የተቀቡበትን ዕለትና ሰዓት ያሳያል። ክህነት፤ መካን፣ ማስካን፣ ካህንነት፣ ተክኖ ማገልገል፣ አገልግሎት፣ መንፈሳዊ ሹመት” (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ ፭፻፳፪)
ከላይ የተወሰደው ሐሳብ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው የሰጡት ትርጕም ነው፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ክህነት አገልግሎት ሲሆን ይህን አገልግሎት የሚሰጠው አካል ደግሞ ካህን ይባላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ካህን፤ ክህነት፡- በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ካህን ይባላል። አገልግሎቱ መሥዋዕትን በመሠዋትና ጸሎትን በመጸለይ ይፈጸማል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፩፻፺፪) በማለት አገልግሎቱ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ጉዳይ በሚያመላክት አገላለጽ ያስረዳል፡፡
ከሁሉቱም አገላለጽ እንደምንረዳው ክህነት አገልግሎቱ ሲሆን ካህን ደግሞ አገልጋዩን የሚወክል ነው። አገልግሎቱም ሆነ አገልጋዩ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ግንኙነት ሲሆን ይህን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን አገልግሎት የሚፈጽመው አካል ካህን ሲባል አገልግሎቱ ደግሞ ክህነት ይባላል ማለት ነው። ይህ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሚከናወን አገልግሎት በልዩ ልዩ አገላለጽ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ክህነት፡-
ሀ. መለኮታዊ ጥሪ (ሰማያዊ ምርጫ) ነው።
ክህነት መንፈሳዊ አገልግሎት ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን ደግሞ አምላካዊ ምርጫ ሊኖር ያስፈልጋል። እኛ ስለፈለግን ብቻ ካህን መሆን አንችልም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት “እኔ መርጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም” (ዮሐ.፲፭፥፲፮) በማለት ያስተማራቸው ይህን ያስረዳናል። ስለዚህ ይህ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚከናወን መንፈሳዊ አገልግሎት መለኮታዊ ምርጫ ነው።
እዚህ ላይ ምርጫ አለ ሲባል ለአገልግሎት እንጂ ለመንግሥተ ሰማያት ወይም ለገሃነመ እሳት እንዳልሆነ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህንም በነቢዩ በኤርምያስ ሕይወት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም ቃል ወደእኔ እንዲህ ሲል መጣ፡- ‹በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፡፡››› (ኤር.፩፥፭) በማለት እግዚአብሔር ኤርምያስን ለነቢይነት እንደመረጠውና እንደለየው እንረዳለን፡፡ መመረጡ ለአገልግሎት ማለትም በአሕዛብ ዘንድ ነቢይ ሆኖ እስራኤልን እንዲመራ እግዚአብሔርን እንዲያገለግል ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉም ክህነትም አምላካዊ ምርጫ ነው።
ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክህነትን መለኮታዊ ጥሪ መሆን በተመለከተ “እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም” (ዕብ.፭፥፬) በማለት ከብሉይ ኪዳን ምሳሌውን ጠቅሶ ይህ አምላካዊ ጥሪ ደግሞ ዘለዓለማዊ እንደሆነ ማንም እግዚአብሔር ለዚህ አገልግሎት ሳይጠራው በራሱ ካህን መሆን እችላለሁ ማለት እንደማይችል ያስረዳናል። በቅዱስ ወንጌልም “ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያወጡአቸው ዘንድ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ በርኵሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ማቴ.፲፥፩) ተብሎ ተጽፏል።
ለ. ክህነት ለሰማያዊ አገልግሎት መለየት ነው
መለየት ነው ሲባል በአካል ተለይቶ ከሕዝቡ ይወጣል ማለት አይደለም። አገልግሎቱ መንፈሳዊና ሰማያዊውን መንግሥት የሚያስገኝ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ለመንፈሳዊና ሰማያዊ አገልግሎት ከሌላው ማኅበረ ሰብ በተለየ አምላካዊ ሥልጣን ተሰጥቶት ለተቀደሰ አገልግሎት ተወስኖ መኖርን የሚያመለክት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ “ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ፡- በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ አላቸው” (ሐዋ.፲፫፥፪-፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ የሚያስረዳን በራሱ በመንፈስ ቅዱስ ለተጠሩለት ሠራ ለሰማያዊው አገልግሎት ማለት በምድር እያሉ ግን ሰማያዊውን ርስት ለሚወርሱበትና ሌላውንም ለሚያወርሱበት አገልግሎት መለየታችውን የሚያመለክት ነው።
ሐ. ክህነት ታማኝ መጋቢነት ነው
ካህኑ የመንጋዎች መጋቢ ነው። የሚመግበው ደግሞ ሰማያዊውን ምግብ ነው። በቅዱስ ወንጌል “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው” (ሉቃ.፲፪፥፵፪) ተብሎ እንደተጻፈ ክህነት የሚባለውም ይህን የተቀደሰ አገልግሎት አምኖና የሚያስከፍለውንም ዋጋ ተረድቶ መግባት ነው። ክብር ያለበት መከራም በዚያው ልክ አለበትና። መንጋውን ለመመገብ ሲባል መጋቢው ራሱ ሊራብ ይችላል። መንጋውን ሰማያዊ ምግብ ሊመግብ ሲተጋ እርሱ ደግሞ በምድራዊው ምግብ መራቡ አይቀርምና ይህን ሁሉ ጫና መቀበል ታማኝ አገልግሎት ያስብላል። ይህን አደራ ለተወጣው ደግሞ ታማኝ ከመባል በላይ ብፁዕ ያስብላል።
፪. ክህነት በዘመናት
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት ዘካርያስ ካህን፣ ነቢይ ወሰማዕት ዘርእየ ተቅዋመ ማኅቶት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እስከ ዘለዓለም ድረስ ምድርን ያለ ካህናትና ዲያቆናት አልተዋትም፤ ካህን፣ ነቢይና ሰማዕት የተባለ ዘካርያስ የብርሃን መቅረዝን አየ” (ዚቅ ዘህዳር ጽዮን) በማለት እንደገለጸው የክህነት አከልግሎት ከሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ የነበረበት ሁኔታና ራሱ ክህነቱ የሚገኝበት መንገድ ግን እንደየዘመናቱ የተለያየ ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
ሀ. በብሉይ ኪዳን
የመጀመሪያው ካህን አዳም ነው። ከሰማንያ አሐዱ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ “ወእምዝ አልበሶ እግዚአብሔር ለአቡነ አዳም ልብሰ መንግሥት ወአክሊለ ስብሐት ወዕበየ ግርማ ወክብር ዲበ ርእሱ ወአስተቀጸሎ አክሊለ መንግሥት ወበህየ ረሰዮ ንጉሠ ወካህነ ወነቢየ ወአንበሮ እግዚአብሔር ዲበ መንበረ ክብር፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር አባታችን አዳምን የምስጋና አክሊን፣ ልብሰ መንግሥትን፣ የግርማ ከፍተኛነትን፣አለበሰው በራሱ ላይም የመንግሥትን አክሊል አቀዳጀው። በዚህ ጊዜ ንጉሥነትን፣ ክህነትን፣ ነቢይነትን ሰጠው በክብር መንበር ላይም አስቀመጠው። (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ፩፥፵) የሚል ክፍለ ምንባብ እናገኛለን። በዚሁ መጽሐፍ “ወእምዝ ሰምዑ መላእክት ቃለ እግዚአብሔር ልዑል እንዝ ይብል ኦ አዳም ናሁ ረሰይኩከ ንጉሠ ወካህነ ነቢየ ወመስፍነ ወመኰንነ ኵሉ ፍጥረት፤ በዚህም ጊዜ መላእክት የእግዚአብሔር ቃል አዳም ሆይ እነሆ ካህን፣ ንጉሥ፣ ነቢይ መስፍን ለፍጥረት ሁሉ ገዥ አደረግሁህ ሲል ሰሙ።” (ቀሌምንጦስ ፩፥፵፫) ተብሎም ተጽፎ እናገኛለን።
ይህ ከላይ የተጠቀሰው ክፍለ ምንባብ የሚያስረዳን እግዚአብሔር አምላካችን ለአባታችን ለአዳም ከአደለው በርካታ ጸጋዎች መካከል አንዱ ክህነት መሆኑን እና የመጀመሪያው ካህንም አባታችን አዳም እንደሆነ ነው። የአዳምን ካህንነትና የክህነት አገልግሎት ይፈጽም እንደነበረም በመጽሐፍ ቅዱስ “በዚችም ቀን አዳም ከኤዶም ገነት ሲወጣ ለበጎ መዓዛ ነጭ ዕጣን፣ ቀንዓትና ልባንጃ ስንቡልም ኀፍረቱን በሸፈነበት ቀን በጥዋት ፀሐይ ሲወጣ ዐጠነ” (ኩፋ.፭፥፩) ተብሎ ተመዝግቦ እናገኛለን። ይህን የክህነት አገልግሎት ማለትም መሥዋዕት የመሠዋት አገልግሎትን በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ያከናውኑ የነበሩት አበው ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ የልዑል እግዚአብሔር ካህን ተብሎ ተመዝግቦ የምናገኘው ካህኑን መልከ ጼዴቅን ነው።
መልከጼዴቅ
ከአዳም ቀጥሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ካህን የተባለ መልከ ጼዴቅ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት፡፡ “የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅ አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ፡፡ አብራምንም ባረከው፤ አብራም ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔር ቡሩክ ነው አለው፡፡ አብራምም ከሁሉ ዐሥራትን ሰጠው” (ዘፍ.፲፬፥፲፰-፳)
ነቢዩ ዳዊት “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ ብሎ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም” (መዝ.፻፱፥፬) በማለት ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ትንቢት አስረድቷል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ለዕብራውያን በላከላቸው መልእክቱ “የሳሌም ንጉሥ የልዑል እግዚአብሔርም ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ደል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፡፡ አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፤መጀመሪያ የስሙ ትርጓሜ የጽድቅ ንጉሥ ነበር፤ በኋላም የሳሌም ንጉሥ ተባለ፤ የሰላም ንጉሥ ማለት ነው፡፡…ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል” (ዕብ.፯፥፩-፫)
የመልከ ጼዴቅ ክህነት ከላይ በተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የልዑል እግዚአብሔር ካህን እንደሆነ፣ በራሱ በእግዚአብሔር የተሾመ መሆኑን የሊቀ ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ምሳሌ ተብሎ ተገልጾ እናገኘዋለን። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቁ በቅዱስ ያሬድ “አክሊለ ሰማዕት ሰያሜ ካህናት፤ የሰማዕታት አክሊል የካህናት ሿሚ” ተብሎ የሚነገርለት ማንም የሚሾመው የሌለው ሹመቱ የባሕርዩ የሆነ የካህናት አለቃ ነው። ካህኑ መልከ ጼዴቅም በሰው እጅ ስላልተሾመ የክስርቶስ ምሳሌ ሁኖ ይጠቀሳል።
በሕገ ኦሪትም እግዚአብሔር ሕግን ሠርቶ ለሙሴ ከሰጠው በኋላ አሮንን መርጦ በክህነት አገልግሎት እንዲኖር እንዲሁ ከሌዊ ዘር የተወለደ ሁሉ በዚህ ክህነት ገልግሎት እንዲኖርና እግዚአብሔርን እንዲገለግሉ በሙሴ አማካኝነት ሥርዓት ሠርቶ ሕዝቡ በዚህ አገልግሎት ሲጠቀሙ ኖረዋል።
ለ. በሐዲስ ኪዳን
ክህነት፡-በዕለተ ዕርገቱ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች አንዱ የሐዲስ ኪዳኑ የክህነት አገልግሎት ነው፡፡ “ወእምዝ አውጽኦሙ አፍኣ እስከ ቢታንያ ወአንሥአ እደዊሁ ወአንበረ ላሌሆሙ ወባረኮሙ፡፡ ወእንዘ ይባርኮሙ ተረኀቆሙ ወዐርገ ሰማየ፤እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው፡፡እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡›› (ሉቃ.፳፬፥፶-፶፩) በማለት ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈልን ዛሬ ያለውን የክህነት ደረጃ ከአጻዌ ኆኅት ጀምሮ እስከፓትርያርክ ድረስ በአንብሮተ እድ (እጅን በመጫን) ሾሟቸው ዐረገ፡፡
ይህ የሐዲስ ኪዳን ክህነት እንደ ኦሪቱ በዘር፣ በቤተ ሰብ የሚወረስ ሳይሆን ርትዕት በሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ያለና የሚገባውን ትምህርት የተማረ እንዲሁ እግዚአብሔር ለዚህ አገልግሎት የመረጠው ሁሉ የሚሾመው ሹመት ነው፡፡ የኦሪቱ ክህነት አማናዊ ሥርየትን አያስገኝም የሐዲስ ኪዳኑ ክህነት ግን “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻ እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው በሰማይም የተፈታ ይሆናል” በማለት እውነተኛውን ክህነት ማሰር መፍታት የሚያስችለውን ክህነት ሰጣቸው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር መምህረ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሀብተ ክህነትን ከሰጣቸው በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ባልጸና ሰውነታቸው ቢፈተኑ እንደማይጸኑ ያውቃልና አንድ ትዝዛዝ አዘዛቸው ትእዛዘዙም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “እነሆም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፡፡›› (ሉቃ.፳፬፥፵፱)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለዐርባ ቀን ያህል ኪዳንንና ትምህር ኅቡዓትን ሲያስትምራቸው ከቆየ በኋላ በዓርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ወደ ሰማይ ሲያርግ ከላይ እንደጠቀስነው ለሰው ልጅ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ጸጋ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱን ደግሞ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሏቸው ዐረገ፡፡ ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ሀገር የሰላም ከተማ ማለት ነው፡፡ ዛሬም እነተኞች ካህናት ሰላም ከሰፈነባት ሰላም ከማይለይባት የሰላም ከተማ ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን፣ ጉባኤ ቤት፣ ገዳም ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ከፈተና የሚያጸኑንንና አስቀድሞ የተሰጡትን ጸጋዎች ከእኛ እንዳይነጠቁን ለማድረግ የሰላም ከተማ ከተባሉት ቤተ ክርስቲያን ቤተ ጉባኤ እና ከገዳም መለየት የለብንም፡፡ይህ ሲባልም ሁሉ ገዳም ይግባ ማለት እንዳልሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡በገዳም ያለ ከገዳሙ፣ጉባኤ ቤት ያለ ከጉባኤ ቤቱ እንዲሁም በአርባ በሰማንያ ቀን ከሥላሴ ተወልዶ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የተቀበለ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን መለየት የለበትም ሲለን ነው
ሐ. በሊቃውንት
ክህነት በሐዲስ ኪዳን አማናዊ ሥርየተ ኃጢያትን የሚያሰጥና ሰማያዊ የሆነ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የሐዲስ ኪዳን ክህነት ከሐዋርያት ጀምሮ በሊቃውንትም ዘንድ ሳይቋረጥ እስከ አሁን ደርሷል፡፡ እንዳልተቋረጠ የሚያረጋግጥልን ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አእይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት፤ እናንተ ካህናት ሆይ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናችሁና ኃጢአተኛውን እንደወንድማችሁ ገሥጹት፡፡” በማለት በቅዳሴው ገልጾት እናገኛለን፡፡ ይህም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ፤ እናንተ ያለም ብርሃን ናችሁ በማለት የሰጣቸውን ክህነት እንዳይዘነጉ በማስታዎስ ያላቸውን ልዕልና ያስረዳል፡፡
ክህነቱ ቢቋረጠጥ የሌለን አገልግሎት አድርጉ እያለ ኃላፊነታቸውን ባላስረዳ ነበር፡፡ እንዲሁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ.፳፰፥፳) በማለት ያስረዳቸው በእነርሱ እግር ተተክተው የሚያገለግሉትን ሁሉ እንጂ ሐዋርያት በአጸደ ሥጋ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይኖራሉ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም “ኦ አንትሙ አበዊነ ንቡራነ እድ ሥዩማን እለ መትልወ ሐዋርያት እስመ ነሣእናክሙ አስተብቋዕያነ ለነ ለኀበ እግዚአብሔር፤ የሐዋርያት ተከታዮች የሆናችሁ በአንብሮተ እድ (እጅ በመጫን) የተሾማችሁ አባቶች ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእኛ የምታማልዱ እናንተን ተቀብለናችኋል እኮን” በማለት ያስረዳው ክህነቱ ያላቋረጠ መሆኑን ሲያስረዳን ነው፡፡
እንግዲህ ይህ አገልግሎት በምድር ያለ ግን ሰማያዊ ክብርን የሚያሰጥ፣ በምድር ለሰማያዊ ክብርና ጸጋ የሚወጡበት የሚወርዱበት ነው፡፡ አገልግሎቱም አገልጋዮችም ከእግዚአብሔር የተሰጡ እንደሆኑም ሊቁ ያስረዳል፡፡ በዚህ እትም ምንነቱንና በዘመናት የነበረ ወደፊትም የሚኖር መሆኑን ከተመለከትን ቀሪ ጉዳዮችን ደግሞ በሚቀጥለው እንመለከታለን፡፡ ይቀጥላል…