Friday, 04 December 2020 00:00

ዕቅበተ እምነት (Apology)

Written by  ሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ

Overview

ዕቅበት፤ ዐቀበ ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ። ትርጉሙም መከላከል፣ መጠበቅ (Apology) ማለት ነው። ዕቅበተ እምነት እምነትን መጠበቅ ማለት ሲሆን እምነትም የሚጠበቀው ከኢአማንያንና ከከሓድያን የሐሰት ትምህርት፤ ከመናፍቃን ቅሰጣ፤ ከዓለማዊ ፍልስፍና፤ ከዓለማዊነት (Secularism) ከግለሰባዊ ፍላጎትና ጥርጣሬ ሁሉ ነው። ዕቅበተ እምነት፤ በእምነት ሕይወት ላይ የጸና የግለሰቡን ሰብእና፣ ዕውቀትና ጥበብ መሠረት አድርጎ የሚቀርብ አገልግሎት ነው። እምነት በአማኙ ሁሉን አቀፍ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተግባር የሚገለጽና በግንኙነቶች የሚታወቅ እንደ መሆኑ መጠን ዕቅበተ እምነትም እንደዚሁ በትምህርትና በምግባር አርአያነትን የሚፈልግ ለቤተ ክርስቲያን የመቆም የባለ አደራነት ሥራ ነው።  ዕቅበተ እምነት በሰፊው የሚታወቀው ከሐዋርያት ተከትለው፣ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ወይንም በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩ “ዐቃብያነ ሃይማኖት፣ የእምነት ጠበቆችና ቀዋምያን ለቤተ ክርስቲያን (Apologists)” በሚሉ መጠሪያዎች ከሚታወቁ አባቶች ጋር በተገናኘ ነው። (ቀ/ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገ. ፪፻፷፯) በዋናነት ሁለተኛውን ክፍለ ዘመንና እነዚህን ቀዋምያን እናንሣ እንጂ ጥብቅናው የጀመረው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን፣ ክብር ይግባውና በራሱ በጌታችን ስለ ራሱ በቀረቡ ክርክሮች ነው። የዮሐንስ ወንጌል ም.፩ እስከ ም. ፯ የተዘገቡት ጉዳዮች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። ሐዋርያቱም በዚሁ መንገድ ቀጥለው ለዐቃብያነ እምነት አስረክበዋል። ሃይማኖታችንና ክብራችን ተነካ ከሚሉት ከማኅበረ አይሁድ፣ ራሳቸውን ሲያስመልኩ ከነበሩት የሮም ነገሥታትና የግሪክ ፈላስፎች የተጋረጠውን የወቅቱን ታላቅ ፈተና ተረድተው ለቤተ ክርስቲያን የቆሙት እነዚህ አባቶች ከቀደምቶቻቸው ከሐዋርያት የወረሱት ብዙ ነገር አለ። 

 

በእነዚህ ዘመናት የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖችን፤ በአማናዊው እምነት ላይ ይቀርቡ የነበሩ ክሶችና የሐሰት ውንጀላዎች እንዲፈሩና እንዲጠራጠሩ ያደርጓቸው ነበር። እነዚህን ፈተናዎች እየተጋሩ የነበሩት ዐቃብያነ እምነት፤ በሕይወት፣ በቃል ትምህርትና በመጻሕፍት የክርስትናን ልዕልና ለዓለም አሳይተዋል። 

ዕቅበተ እምነት በዘመነ ሐዋርያት

ጌታችን ከዓለም መርጦና አስተምሮ የሾማቸው ሐዋርያት፤ እነርሱ ያመኑትን በማያምኑ፣ ነገራቸውን በማይቀበሉና አልፎ ተርፎም በሚዘባበቱባቸው ሰዎች ይፈተኑ ነበር። ይህን ፈተና ምክንያት በማድረግ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቃዋሚዎቹን ዝም የሚያሰኝ  ሁሉን አቀፍ ምላሽና ኋላ ለሚመጡት ዐቃብያነ እምነት ታላቅ አርአያ የሆነ ተግባር ይዞ ተገኘ (ሐዋ. ፪፥፲፬፤ ፫፥፲፪ ፤ ፬፥፱)። የክርስትናን ትክክለኛ ምንነት ይዞ ለሁሉም በግልጽ የቀረበው ይህ ምስክርነት እምነትና እውነትን ለመጠበቅ የሚያስፈልግ ቁርጠኝነት በተነሣ ቍጥር በዋናነት ይታወሣል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥም ተመሳሳዩን አገልግሎት በሰፊው ማየት ይቻላል። ቅዱስ እስጢፋኖስ በአይሁድ መካከል ያደረገው ረጅም ንግግርም ሌላው ማሳያ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ በዘመኑ ከነበሩና በራሱና በሚያስተምራቸው ምእመናን ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች እንዴት ሊጠበቅ እንደሚገባ ሁለት መልእክታትን ጽፎለታል። በመጀመሪያው መልእክት፡ “ጢሞቴዎስ ሆይ በውሸት ዕውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ” እያለ ሲመክረው እናስተውላለን። (፩ጢሞ. ፮፥፳)። ይህም ከተረፈ አይሁድ፣ አዋቂዎች ነን ብለው ከሚመኩ ግኖስቲኮችና ከዓለም ፍልስፍና ሃይማኖትን እንዴት ሊጠብቅ እንደሚገባው ሲያስጠነቅቀው ነው። “ከንቱ ነገርን የሚያመጡ ድል የተነሡ ሰዎችን ተለያቸው፣ ጽድቅን በኃጢአት፣ እውነትን በሐሰት፣ አምልኮትን በክሕደት፣ ወንጌልን በኦሪት የሚለውጡትን ተለያቸው” እያለ የነበረውን አደጋ በግልጽ ያሳየዋል። እንዲሁም “መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ” ይለዋል  (፪ጢሞ.፩፥፲፬)።

እምነትን በየጊዜው ከሚመጡ ሰው ዘራሽ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ጠብቆ መጀመሪያ የተገለጸችውን፥ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የጸናችውን ሃይማኖት አጽንቶ መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል። የኦርቶዶክሳውያን ዓይነተኛ መገለጫ የመጀመሪያዋን እውነት በማይለዋወጥና ባልተቆራረጠ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ይዞ መገኘት ብሎም ማስቀጠል ነውና። “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና።” እንዲል ሐዋርያው (ዕብ. ፫፥፲፬)።

ሐዋርያትን ተከትለው የተነሡ ተላውያነ ሐዋርያት (Apostolic Fathers) ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በማስቀጠልና በማጽናት አገልግሎታቸው ውስጥ ለዕቅበተ እምነት የሚውሉ በርካታ ትምህርቶችን በቃልም በጽሑፍም አበርክተዋል። ለምሳሌ ፖሊካርፐስ በሐሰት ትምህርት ብዙዎችን ሲያስቱ የነበሩትን ቫለንቲየስና መርቅያን የተባሉ መናፍቃን እንዴት እንዳሳፈራቸውና ብዙዎችን ከክሕደት እንደ መለሰ ማስታወስ ይቻላል። በተመሳሳይ አበርክቶ ብዙዎችን ማንሣት ቢቻልም የተላውያነ ሐዋርያት ሥራዎች በአብዛኛው ውስጡን የማጽናት ዓላማ የነበራቸው ተደርገው ይወሰዳሉ። በውጭ የነበሩ ተግዳሮቶችን በሚገባ በመለየትና የእነርሱን ማርከሻ ከትምህርተ ሐዋርያት ምንጭ በመቅዳት በጠንካራ ጽሑፎች የተገለጡት ዐቃብያነ እምነት ናቸው። እነዚህ አባቶች ክርስትናን አምነው ከመቀበላቸው አስቀድሞ በነበረ ሕይወታቸው ፍልስፍናን፣ የተለያዩ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችንና ባሕሎችን ጠንቅቀው የተማሩ ነበሩ። ክርስቲያናዊ አገልግሎት ውስጥ በመጡ ጊዜ፤ ያንን ዕውቀት ተገን አድርገው ክርስትናን ለማጥቃት የተነሡትን ሁሉ የሚያሳፍሩ ለመሆን ቻሉ። ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው እምነትን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻልና ከምን መጠበቅ እንደሚገባ ያስተምራል። በየዘመናቱ የተነሡና ቤተ ክርስቲያንን ከወቅታዊ ፈተናዎች ለመታደግ ሲጥሩ የነበሩ አባቶችም አርአያነታቸውን በሚገባ ተከትለው ተጠቅመዋል። ዐቃብያነ እምነትን የተመለከተ የሕይወት፣ የጽሑፎቻቸው ይዘትና ተያያዥ ዳሰሳን የምናስከትል ቢሆንም በእነርሱ አርአያነት እንዴት የዕቅበተ እምነት አገልግሎት ልንሰጥ እንደምንችል ጥቂት ነጥቦችን እናንሣ።

እምነት ከምንና እንዴት ይጠበቃል?

ማመን፤ አለማመን የተባለ ባላንጣ አለው። አለማመንን መርሓቸው ያደረጉ ኢአማንያንም በራሳቸው አጥር ከመወሰን ይልቅ ወደ አማንያን ሕይወት እየገቡ መሠረት በሌለው ምክንያት ሊሞግቱ ይሞክራሉ። ስለዚህ በቅድሚያ እምነት የሚጠበቀው ከኢአማንያን ተንኮልና ሤራ ነው። እምነትንና ቤተ ክርስቲያንን ከምንና እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ ከዐቃብያነ እምነት ብዙ መማር ይቻላል።  በወንጌል እንደ ተነገረውና በሚነሡ ጥያቄዎች አንፃር በዐቃብያነ እምነትም እንደ ተረጋገጠው ክርስትና የመጨረሻው እውነትና ብቸኛው የድኅነት መንገድ ነው። ይህ መሠረታዊ ማሠሪያ በእያንዳንዱ ምእመን ልቡና ውስጥ ገብቶ በእምነቱ ራሱን እስከሚገልጥበት ድረስ መታወቅ አለበት። በመሆኑም ዐቃብያነ እምነት በብዙኃን ከሳሾቻቸው መካከል ጥቂት ሆነው እምነትን መሠረት ባደረገው ከፍተኛ ዕውቀታቸው የሠሯቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ፡- 

አንደኛ፡- የመጀመሪያ ሥራ ይህ ራሳቸውን ክርስቲያኖችን የማጽናት ሥራ ነበር። በዚሁ ጊዜ ክርስትናን አመክንዮአዊ መሠረት የለሽ አድርገው በመቍጠር ጥያቄ ሲያነሡ የነበሩ የግሪክ ፈላስፎች ነበሩ። እነዚህንም በራሳቸው መሣሪያ ማለትም አስቀድመው የተማሩት ቢሆንም ለክርስትና ባስገዙት የፍልስፍና ዕውቀታቸው ፈላስፎችን መሞገት፣ መርታትና ብዙዎችን መመለስ መቻላቸው ታላቅ ድል ሆነ። አገልግሎታቸው በውስጥ ያሉትን ሲያጸና በውጭ የነበሩትን ማምጣት ቻለ። ከዚህ የምንማረው እምነትና እውነት በሕይወታችን ውስጥ በቅለው ፍሬ የሚያፈሩት በብዙ ደጋፊዎች ስለ ተከበብንና ብዙ ስላወቅን ሳይሆን ራሳችን በእምነት በተተከልንበት መጠን መሆኑን ነው። ለሌሎችም ልናስገነዝበው የሚገባውና በኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኑ ሕይወት ውስጥ ሠርጾ በተግባር ሊገለጥ የሚፈለገው የክርስትና የመጨረሻ እውነትነት ነው። 

ሁለተኛ፡- ክርስትናን እንደ አዲስና እንግዳ ትምህርትና እምነት ለሚቈጥሩ ወገኖች ራስን መግለጽ የሚቻልባቸውን መንገዶች አደራጅቶ ማሳየት ነው። ትችቶች የተጨበጠ ማስረጃ ይዘው የቀረቡ ነበሩ ወይስ ካለመረዳትና ከተሳሳተ ግንዛቤ የመነጩ ነበሩ የሚለውን ማሳየት የዚህኛው መንገድ ትኩረት ነው። ስለዚህ የጥያቄዎቹ አመንጪ ለነበሩት አይሁድ የክርስትናን የትንቢተ ነቢያት ፍጻሜነት ለሚከተሉት ክርስቲያኖች በማስረዳትና በምክንያት ለሚሞግቱትም ገዥ የሆነ ምላሽ ማቅረብ ዐቃብያነ እምነት የሚነሡበት የተዋጣ ሥራ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ለሚመጡ ፈተናዎች እንዴት መዘጋጀትና እምነትን መጠበቅ እንደሚቻልም ያስተምራል።  

ከቀደመው ጋር በይዘታቸው ሊለያዩ ቢችሉም ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ላይ በርካታ የሐሰት ውንጀላዎች ይሠነዘራሉ። በተለያየ ምክንያት እውነታውን የሚሸሹና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠሉ ሰዎች ለጊዜው ሊረብሹና ሊያስጨንቁ በሚችሉ ነገሮች ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ ነው። ያልተገባ ስም በመስጠት፣ የሐሰት ትርክቶች በመፍጠር፣ አልፎ ተርፎም በኃይል ተግባር ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን እየተዋጉ ነው። ይህን በመሰለው ጊዜ ላይ የቀደሙትን አባቶች አርአያነት ተከትሎ ለቤተ ክርስቲያን መቆምና እውነትን ይዞ መሞገት ያስፈልጋል። በመሆኑም አገልግሎቱን በተረዱ በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የዕቅበተ እምነት አገልግሎቱ እየተሰጠ ሲሆን በሰፊው ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል። 

ሦስተኛ፡- የበለጠ ዝግጁነትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ አገልግሎት ሲሆን ክርስትናን በአዋጅ ከከለከሉትና የሚያስከትለውንም የሞት ቅጣት ከደነገጉት ነገሥታት ጋራ መጋፈጥ ነበር። እነዚያ የዘመኑ ጉልበተኞች በምክንያት የሚያምኑ አልነበሩም፣ ትምህርትን አይቀበሉ፣ ወደ  እምነትም እንዳይቀርቡ በጣዖቶቻቸው ተሸፍነዋል። የተቃወማቸውን ሁሉ ይገድላሉ፣ በንጹሐን ክርስቲያኖችም መከራ ይዝናናሉ። በዚህ እሳትና ሠይፍ ውስጥ ሳይፈሩና ሳይሳቀቁ በቀጥታ ለነገሥታቱ እየጻፉ የክርስትናን እውነት ይዘው የሞገቱ ዐቃብያነ እምነት ነበሩ።  ዛሬም ቢሆን የዕቅበተ ዕምነት አገልግሎት ይህን መሰሉን ጽናትና ቁርጠኝነት ይፈልጋል።

ዐቃብያነ እምነት፡ ሕይወትና ጽሑፎቻቸው

በዋናነት በሁለተኛው ዘመን የተነሡ ጸሐፍያንን ይመለከታል። ሥራዎቻቸውም በግሪክና ሮም ባሕል ምክንያት፥ በፈላስፎች/ፍልስፍና እንዲሁም በግኖስቲኮች ምክንያት ለተፈጠሩት ተጽእኖዎች መልስ ይሰጣሉ። አንዳንዶቹ በቀጥታ ለነገሥታት የተጻፉና ክርስትና የሚከሰስባቸውን ሐሳቦች ሐሰትነት በማሳየት የሚሞግቱ ናቸው። በክርስቲያኖች ላይ ይቀርቡ ከነበሩ ክሶች መካከል አንዱ “አማልክት የለሾች” የሚል ነበር። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ክርስትና የሚያምነውና የሚያስተምረው አምላክ ከሳሾቹ እንደሚሠሯቸው ጣዖታት የሚታይና የሚዳሰስ ስላልሆነላቸው ነው። ሁለተኛም፤ ክርስቲያኖቹ ምሥጢራትን በሚፈጽሙበት ጊዜ ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም የሚያስተምሩትንና የሚያደርጉትን ሳይረዱት የቀሩት ከሳሾች “የሰው ሥጋ የሚበሉ” ይሏቸው ነበር።

ለመንግሥት አስተዳደር አስጊና ለሥልጣኔ እንቅፋት እየተደረጉ የተወነጀሉበት ሁኔታም ሌላው ፈተና ነበር። እነዚህ ሁሉ ከተሳሳተ ግንዛቤና ከጥላቻ የመነጩ እንደ ሆኑ ቢታወቅም ለጊዜው እውነት መስሏቸው ለሚስቱ ወገኖች መድረስ የሚገባ ነበረ። ስለዚህ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመልኩ እንደ ሆኑ፣ የክርስትናን ጥንታዊ መሠረት፣ የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ መሆኑንና በአንጻሩ የከሳሾች እምነት መሠረት የለሽ መሆኑን የሚገልጽ ምላሽ ይዘው ቀረቡ። ቤተ ክርስቲያን የመንግሥታት ሥጋት ሳትሆን እንዲያውም የማኅበራዊ አንድነት መሠረት እንደ ሆነች፣ ከሀገራት ይልቅ የዓለም ሰላም የሚረጋገጠው በክርስትና እንደ ሆነ በምክንያት ሞገቱ።

በመቀጠል ለከሳሾቹ ቀጥተኛ አጸፋ የሚሆኑ የአምልኮ ጣዖታቸውን ከንቱነት፣ የሥነ ምግባራቸውን ብልሹነትና ከአንድ አምላክ እምነት የወጡበትን ርቀት በይፋ ማጋለጥ ጀመሩ። ይህም በወቅቱ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ የጠቀመ አገልግሎት ነበር። ምክንያቱም ከሳሾች ጊዜና አመቺ ሁኔታ ባገኙ ጊዜ የራሳቸውን ነውር ይረሳሉ። ለራሳቸው የነገ ዕጣ ፈንታ የሰጉበትን ነገር በብዙዎች ተገብተው ይወነጅላሉ። ታዲያ እንደነዚህ ዓይነት የእውነት ጠበቃ የተነሣባቸው ጊዜ የሸፈኑት ግብራቸው ሁሉ ይገለጣል። በዚህ መሠረት ያን ጊዜም የዐቃብያነ እምነት ጽሑፎች የዘመኑን ክፉ ጠባይ የገለጡና የክርስትናን ሉዐላዊነት ለዓለም ያሳዩ ነበሩ። ዛሬም የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የሚሠነዝሯቸውን የሐሰት ውንጀላዎች ከንቱነት የሚያጋልጥ ተመሳሳይ አገልግሎት በበረከተ ቍጥር ለማስነወር የተነሡት ሁሉ ነውራቸው ይገለጣል። አባቶች የክርስቶስን አምላክነት በታሪካዊ ዐውድ ፍንትው አድርገው እንዳሳዩ የእኛ ዘመን የወለዳቸውን መሠረት የለሽ ታሪኮችን በታሪካዊ ዐቃቤ እምነትነት ማጋለጥ ያስፈልጋል።

ታሪክ ከሰዎች የማንነት መገለጫ መንገዶች አንዱ ነው። የታሪክ ተፋልሶ ደግሞ የሰዎችን ማንነት የተመለከተ መሠረትን ለማናጋት ሆን ተብሎ የሚደረግ አጥፊ ተግባር ነው። ስለዚህ ከሃይማኖት መሠረታዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን ለታሪክም ዋጋ ሰጥቶ መቆም ከዐቃብያን የምንማረው ሌላው ቁም ነገር ነው።

የዐቃብያነ እምነት አጠቃላይ ሕይወትና ሥራዎች በዚህ መሰል አጭር አቀራረብ ተሟልቶ ሊገለጽ የሚችል አይደለም። በመሆኑም በቀጣዩ የእያንዳንዳቸውን አባቶች ሕይወትና ሥራዎች ይዘን  እንመለሳለን ፤ እስከዚያው ይቆየን!

 

Read 1486 times