Thursday, 21 January 2021 00:00

የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችና ሌሎች ይዞታዎቿ ወቅታዊ ፈተናዎች ክፍል ሁለት

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ

Overview

ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ከላይ ካነሣናቸው ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የተከሰተው ክስተትም ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጫናና በደል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ በወረዳው የሚገኘው የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ይዞታው ከ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፡ እስከ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ድረስ ቦታው የሚገኝባት ከተማ በገጠር ከተማነት ቆይታ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ሥር የሆነች ናት፡፡ ታዲያ በዚሁ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የከተማዋ አስተዳደር ወደ ማዘጋጃነት ሲቀየር የሃይማኖት ተቋማት ይዞታ ‹‹ባለበት ይቀጥላል›› ተብሎ ነበር፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላ በ፳፻፲፪ ዓ.ም. ባለ ሥልጣናቱ ሁለተኛ ዙር ጥናት በማለት፡ የቀድሞውን ውሳኔ ችላ ብለው የቤተ ክርስቲያንን የጥምቀት ይዞታ ነጠቁ፡፡

 

ገና ከተማው ሳይቆረቆር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአምሳ ዓመታት ትጠቀምበት የነበረውን ይህን ይዞታ ከተማው ከኋላ መጥቶ በመስፋፋቱ ምክንያት፡ የአስተዳደር አካላቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ፣ ለበዓሉ ቅርስነት ሳይጨነቁ ቦታውን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነጠቁ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከበዓል አከባበሩ ጋር በማይጣረስ መልኩ እንድታለማ እንኳን ዕድል አልተሰጣትም፡፡

ከዚህ የሚከፋው ደግሞ የጉዳዩን ሕገ ወጥነት እና ኢ-ፍትሐዊነት አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡት ምእመናን፣ ለአምሳ ዓመታት ሲገለገሉበት በነበረው የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ላይ የመጠመቂያ ገንዳ በመሥራት እና መስቀል በመትከል በዓለ ጥምቀትን በማክበራቸው፡ በተለይ ጉዳዩን በዋናነት የሚከታተሉትን ክርስቲያኖች፡ የከተማው አስተደደር ክስ መሠረተባቸው፡፡ በሚያሳዝን መልኩም ከ፯-፱ ዓመታት ድረስ የእስር ፍርድ እንዲበየንባቸው ተደረገ፡፡ ያቀረቡት ጥያቄ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መልስ ባላገኘበት ሁኔታ ዘወትር በዓሉን በሚያከብሩበት መልኩ ለማክበር በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ለዓመታት በእስር እንዲቆዩ ፈረዱባቸው፡፡

ስለ ጉዳዩ አስተያየት የሰጡን ቀደም ሲል ያነሣናቸው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ‹‹ይህን ያደረጉት ሙሉ ለሙሉ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የአስተዳደር አካላት ናቸው፡፡ ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባለ ጥላቻ ብቻ የተፈጸመ ነው›› ያሉ ሲሆን፡ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ባደረገችው ጫናም ክልሉ እስረኞቹ ካለ አግባብ መታሰራቸውን በማመን በቅርቡ እንዲፈቱ ማዘዙንም ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ‹‹በዞኑ የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ብዙ መከራ እየደረሰባቸው ነው። መስቀል ያለበት ቲሸርት እንኳን መልበስ አልተቻለም›› ብለው ቤተ ክርስቲያን እና አማኞቿ ላይ እየደረሰ ያለው ፈተና ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን በምሳሌነት አነሣናቸው እንጂ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ለዘመናት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥባቸው የኖሩ እስከ ዛሬም ያሉ ሆነው ሳለ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የዘመቻ ዒላማ እንደ ሆኑና በዚህና በእኛም ቸልተኝነት ምክንያት ለፈተና የተጋለጡ እንደ ሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታዎች የመነጠቃቸውና የመወረራቸው ምክንያት

የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች የመነጠቃቸውና የመወረራቸው ምክንያቶች ብዙና ውስብስብ ቢሆኑም፡ ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው በአጭሩ እንያቸው፡-

፩. ቤተ ክርስቲያኒቱ የጥምቀት እና የመስቀል ማክበሪያ ቦታዎቿን  በሕግ አስከብራ ያለመያዝ ቸልተኝነትና ከክብረ በዓል በኋላ ለይዞታዎቹ ትኩረት አለመስጠት፣

ይህ በግልጽ የሚታይ የእኛው ቸልተኝነት ነው፡፡ ክፍተቱን በደንብ ለመረዳት በሦስት ከፍለነው እንየው፡-

ሀ. ይዞታዎቹን አጥሮ አለማስከበርና መዘንጋት - አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎቹን በዓላቱ ሲደርሱ እንጂ ከዚያ በኋላ የሚያስታውሷቸውም አይመስልም፡፡ ቦታዎቹን አጥሮና ከልሎ ማስከበር ሲገባ በዓሉ ሲደርስ ብቻ ባለ ይዞታ እየመሰልን ብዙዎች ወደ ይዞታችን እስኪገቡ ድረስ መዝጊያ እንደሌለው ቤት ቸል አልናቸው፡፡

ለ. ተጠሪ አካል አለመኖር - አብዛኞቹን ባሕረ ጥምቀቶች በርካታ አድባራትና ገዳማት በጋራ ይጠቀሙባቸዋል፡፡  ነገር ግን ከመካከላቸው ይዞታውን በእኔነት ስሜት ዘወትር የሚከታተል አካል የለም፡፡

ሐ. በጉዳዩ ላይ ማዕከላዊ አመራር አለመኖር - ባሕረ ጥምቀቶችንና የመስቀል አደባባዮችን የቤተ ክርስቲያን ይዞታነት በተመለከተ የሚንቀሳቀስና የሚያስከብር በመዋቅር የታወቀ የሥራ ዝርዝር ያለው ማዕከላዊ አካል አለመኖሩም ለተከሰቱት ጉዳቶች አንድ ምክንያት ነው፡፡

፪. መንግሥት መመሪያ አውጥቶ በመንግሥት ተቋማት ሥር ይዞታዎቹ እንዲተዳደሩ ሲያደርግ ጉዳዩን በቸልታ መመልከት

፫. በማስተር ፕላን አለማካተት - በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ከማስተር ፕላን ትግበራ በፊት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከከተማ መመሥረት እና ከማስተር ፕላን ጥናት  በፊት የነበሩ ይዞታዎች፤ ማስተር ፕላኑ፣ የከተማ መመሥረት እና መስፋፋት ታሳቢ ሳያደርጋቸው ወይም ሆን ተብለው ሳይካተቱ ቀርተዋል (አውጥተዋቸዋል)፡፡

፬ በልማት ሰበብ መንጠቅ - የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታዎችን በከተማ መስፋፋት ምክንያት የሚገኙበት ቦታን ለሌላ ልማት መውሰድ ወይም መንጠቅ ሌላው ፈተና ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት በአብዛኛው ቤተ ክርስቲያንን ሳያማክሩ ቦታውን ስለሚወስዱት ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል፡፡

፭ የአፅራረ - ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ - ኦርቶዶካሳዊት ሃይማኖትን ጠል እና ዕሴቶቿን የማጥፋት ተልእኮ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው በሥልጣንም ሆነ በልማት ስም ቤተ ክርስቲያንን የሚበድሉና ያላትን ሀብት ለመንጠቅ የሚሮጡ ብዙ ናቸው፡፡

፮. የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሚናቸውን አለመወጣት - ጥምቀትና ደመራን የመሳሰሉ በዓላት የሀገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ከመሆናቸውም ባሻገር ለሀገር ከፍተኛ ገቢን የሚያስገቡ የቱሪስት መስህቦች ሆነው ሳለ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ቅርስ ጥበቃ ባለ ሥልጣንን የመሳሰሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝም ብለው ማየታቸው እጅግ የሚያስተቻቸው ነው፡፡ በገቢ ረገድ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ መንግሥት በከፍተኛ መጠን እየተጠቀመ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ለይዞታዎቹ መከበር ቤተ ክርስቲያንን አግዘው ሊንቀሳቀሱ ይገባ ነበር፡፡

፯. የመንግሥት መመሪያዎች ድክመትና የአተረጓጎም ስሕተት

ከመመሪያና ከአተገባበራቸው ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሃይማኖት ተቋማትና ለአምልኮ ማካሄጃ ቦታ አፈቃቀድ በ፳፻፬  ዓ.ም. እና ፳፻፲ ዓ.ም. የወጡ መመሪያዎችን እስኪ በጥቂቱ ለማየት እንሞክር፡- 

የማምለኪያ ቦታ በአዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በሕጋዊ መንገድ ላገኟቸው ይዞታዎች የማረጋገጫ ካርታ ጥያቄዎችን መዋቅሩን ጠብቀው እስከ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡ አሁንም በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በአብያተ ክርስቲያናቱ የሚነሡ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫን የተመለከቱ ብዙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ የይዞታ የማረጋገጫ ካርታና በምዝገባ የአምልኮት ቦታ ተጨማሪ ጥያቄዎች በወቅቱ አለመመለሳቸውና የመመሪያ አተረጓጎምና አፈጻጸም ክፍተቶች መኖራቸው ለቅሬታዎቹ ምንጮች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ፳፻፬ ዓ.ም. ድረስ በሃይማኖት ተቋማት በተለያየ ጊዜ በልዩ ልዩ መንገድ ለተያዙ ይዞታዎች ማረጋገጫ ካርታ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መመሪያም ሆነ የአሠራር ግንኙነቶች አልነበሩትም፡፡ 

በ፳፻፬ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሃይማኖት ተቋማት የተያዙት ይዞታዎችን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ቁጥር ፪/፳፻፬ ዓ.ም. በማጽደቅ

- ከአዋጅ ፵፯/፷፯ ዓ.ም. በፊት የተያዘ (በምን አዋጅ ነጋሪት ጋዜጣ ወይስ አዲስ ልሳን ይገለጽ)

- ከአዋጅ ፵፯/፷፯ ወዲህ ያለ፣ ግንቦት ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. የተያዙ (GIS) ወይም በ፲፱፻፺፯ Linemap የሚታዩ

- ከግንቦት ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. እስከ መስከረም ፱/፲፱፻፺፰ ዓ.ም. በ፲፱፻፺፬ (፲፱፻፺፯) Line map የሚታይ እና ሌሎችም የአሠራርና ማንዋሎችን አዘጋጅቶ ወደ ተግባር በመግባት በተለያዩ ጊዜያት የሃይማኖት ተቋማት ለሚያነሡአቸው የዓመታት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን መመሪያው በራሱ ክፍተት ያለበት ነበር፡፡

የመመሪያው ክፍተት 

በ፳፻፬ ዓ.ም. የወጣው መመሪያ ፬/፪/፳፻፬ ዓ.ም. ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላም የነበሩ የይዞታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ቢደረግም፡ መመሪያው እስከ መስከረም ፱/፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ድረስ ብቻ የተያዙትን ይዞታዎች ሕጋዊ ለማድረግ የፀደቀ በመሆኑ ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ወዲህ የተያዙ የሃይማኖት ተቋማት ሕጋዊ የሆኑበት መመሪያ የለም፡፡ በመሆኑም የበርካታ ሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ ምላሽ አልባ ናቸው፡፡ 

ለ፲፬ ዓመታት ያህል በሕጋዊ መንገድ ያገኘነው (የያዝነው) የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ ሕጋዊ ሰነድ ይሰጠን ጥያቄዎች የአስተዳደር ቢሮውን አጣበውታል፡፡ ነገር ግን መልሱ የሚመለስበት መመሪያም የለም። መልስም የለም፡፡

ያልተፈጸመው ሌላው መመሪያ

የከተማው አስተዳደር በ፳፻፲ ዓ.ም. ለሃይማኖት ተቋማት ለአምልኮት ማካሄጃ ፈቃድ መመሪያ ቁጥር ፩/፳፻፲ ግንቦት ፳፻፲ ዓ.ም.

- የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ በምደባ ስለ መፍቀድ

- ለአምልኮ ማካሄጃ አገልግሎቱ የሚመደብ የቦታ ስፋት

- በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚኖረው ርቀት

- በአካባቢው ከሚገኙ ከራሱ ነባር የአምልኮ ቦታዎች አዲስ የተጠየቀው የአምልኮ ቦታ ቢያንስ በሁለት አቅጣጫ ፫ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ርቀት ሊኖረው እንደሚገባ

በመደንገግ የማምለኪያ ቦታን ለመስጠት የሚያስችል ወጥ መመሪያን አዘጋጅቶ ሥራ ላይ አውሏል፡፡ 

ነገር ግን ከከተማው የመሬት ሊዝ ደንብ ቁጥር ፵፱/፳፻፬ ጋር ተገናዝቦ የሃይማኖት ተቋማት በፍትሐዊነት የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ እንዲያገኙ ፀድቆ ሥራ ላይ ቢውልም በመመሪያው መሠረት በምደባ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቦታ ተሰጥቶ አያውቅም፡፡ መደምደም ይቻል ይሆን) (በቅርቡ ለቤተ ክርስቲያናችን ሦስት ቦታዎችን ብቻ በልዩ ሁኔታ የከተማው አስተዳደር ካቢኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ደረጃውን ጠብቀው ለቀረቡት ‹‹በምደባ ይሰጠን›› ለሚሉ በርካታ ጥያቄዎች እስከ አሁን ምላሽ የለም፡፡) እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ በከተማው አስተዳደር አማካኝነት ለነባር ይዞታዎች ለባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ጥቂት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ቢሰጥም ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ወዲህ ቤተ ክርስቲያን በሕጋዊ መንገድ ለያዘቻቸው ይዞታዎች ማረጋገጫ ካርታ ማግኘት አልተቻለም፡፡ 

በመመሪያ ቁጥር ፩/፳፻፲ ላይ በምደባ የአምልኮት ቦታ ለመስጠት በተቀመጠው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ ከወረዳው እስከ የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ጥያቄ ብታቀርብም አንድም ቦታ  በምደባው መሠረት ተሰጥቶ አያውቅም፡፡

ተደጋጋሚው የምእመናን ሕጋዊ ጥያቄ ተገቢውን መልስ አለማግኘቱ፣ ከከተማው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሃይማኖት ተቋማት ጥያቄ ታሳቢ አለመደረጉና ከማስተር ፕላኑ ጋር በማጣጣም የሃይማኖት ተቋማት መገንቢያ ቦታ አለመዘጋጀቱ የአስተዳደሩ ጉልህ ድክመት ነው፡፡ 

ቀድሞ የአምልኮ ማካሄጃ ቦታዎችን በማዘጋጀት ፍትሐዊነትን በተግባር በማሳየት እና በሕጉ መሠረት የሚያቀርቡለትን ጥያቄዎች በአግባቡ በፍጥነት መልስ በመስጠት የሃይማኖት ተቋማትን ማገዝ ተቀዳሚ ተግባር ቢሆንም መሬት ላይ የሚታየው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየው አላስፈላጊ ፉክክር የተፈጠረውም ሕጋዊው መመሪያና አሠራር ስለ ተገፋ ነው፡፡ የከረሙና የተጠራቀሙ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አለመመለስም የሕዝብን ኃላፊነት አለመወጣት መሆኑንም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡ 

በተለይ የአዲስ አበባ አስተዳደር በ፳፻፬ ዓ.ም. ባወጣው መመሪያ ቁጥር ፩/፳፻፬ መሠረት ለቤተ ክርስቲያን ቦታዎቹን የመጠቀም መብቱን ሰጥቶ ባለ ይዞታነቷን ግን ነጥቆ ቆይቷል፡፡

በመመሪያው መሠረት ቤተ ክርስቲያን  የባለ ይዞታነት መብቷ በመገደቡ ምንም ዓይነት ግንባታ ማከናወን ባለመቻሏ በከተማ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታዎች ለስፖርት ማዘውተሪያነት ካርታ ወጥቶባቸው ከቤተ ክርስቲያን ተነጥቀዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት እና መመሪያው

የሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ ማግኘት መብታቸው ሲሆን መንግሥት ደግሞ ሕግ እና መመሪያን በመከተል ቦታ መስጠት ግዴታው ነው። የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳቸው ለጥያቄ ባይቀርብም በሁሉም ተቋማት እየተስተዋለ ያለውን ከአምልኮ ማካሄጃ ቦታ ግንባታ ጋር ተያይዞ የፉክክር እና የእልህ ጉዞን መንግሥት ሕግ እና መመሪያን በቁርጠኝነት በመተግበር ሊገታው ይገባል።

መመሪያ ቁጥር ፩/፳፻፲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንቦት ፳፻፲ ዓ.ም. ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንኳን የሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ቦታ ግንባታን በተመለከተ መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየን ከመመሪያው በተቃራኒው ነው። መንግሥት መመሪያውን ለመተግበር ለምን ቁርጠኝነቱን አጣ? የሃይማኖት ተቋማቱስ የመንግሥት መመሪያን የመተግበር ውስንነትን ታከው ማኅበራዊ አለመረጋጋትን እያጎሉ የሚሄዱት እስከ መቼ ነው?

በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በዘፈቀደ የአዲስ ግንባታ እና ነባር መኖሪያ የነበረን ቤት ወደ ሃይማኖት ተቋምነት የመቀየር ፍላጎት ሳቢያ በየሰፈሩ እየተፈጠሩ ያሉትን አለመግባባቶች መንግሥት አያውቃቸውምን? ዝምታው ምን እስኪሆን ነው? ተቋማቱስ በፉክክር ወዴት እየሄዱ ነው? ይህ ተግባር በእንጭጩ ካልተቀጨ ወደ ከፉ ግጭት እንዳያመራ ሥጋት አለን።

የመፍትሔ አሳቦች

፩. መመሪያውን በቁርጠኝነት መተግበር - እስከዛሬ የነበረበትን ቸልተኝነት በመገምገም መንግሥት ያወጣውን መመሪያ ካለ መድሎ መተግበር እንዳለበት እናምናለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ አንድ የእምነት ተቋም የሚያደሉና ሌላውን የሚበድሉ ወገንተኛ ሰዎችን ከቦታው ማንሣት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን ቁጥጥሩን በማጥበቅ መመሪያውን በቁርጠኝነት መተግበር ለነገ የማያድር እርምጃ መሆን ይገባዋል፡፡

፪. የቤተ ክርስቲያናችንን ይዞታ በከተማ ፕላን ማዘመን፣ መንግሥት የአንድ ከተማን ማስተር ፕላን ሲሠራ የሃይማኖት ተቋማትን ይዞታዎች ሊዘነጋቸው አይገባም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት የከተማ ማስተር ፕላኖች በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጎድታለች፡፡ ይህ እያደር የሚወልደው ቁጭት ለሀገር ሰላም መደፍረስም ምክንያት ሊሆን ይችላልና መንግሥት ሊያስብበት ይገባል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ማኅበራዊ ትስስርን እና በከተማ ዕድገት ላይ ያላቸውን ድርሻ እንዲያጎለብቱ ማካተት የመንግሥት ኃላፊነት ሊሆን ይገባዋል፡፡

 የማጠቃለያ አሳቦች

፩. ለሀገር ግንባታ፣ አንድነትና ነፃነት ከየትኛውም አካል የበለጠ አስተዋጽዖ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያክል የለም፡፡ በየዘመናቱ በሀገራችን ላይ የተከሰቱ አደጋዎችን ከምእመኖቿ ጋር እየመከተች መልሳ ሀገርን ገንብታለች፡፡ ሀገርን ሊጎዱ በመጡት ተጎድታለች፡፡ እርሷን ሊጠቅሙ የመጡም ሀገሪቱን ጠቅመዋል፡፡

ቢዘረዘር የማያልቅ ብዙ ሀገራዊ አበርክቶ ያላትን ቤተ ክርስቲያን፡ ከምንም አንሥታ ባቆመቻት ሀገር መግፋትና ማግለል ተገቢ አይደለም፡፡ አስተምህሮዋና ምእመኖቿ ላይ ከሚደረገው ጫናና በአንዳንድ አካባቢም ከሚፈጸመው ግልጽ መድሎ ባለፈ፡ እስከ ይዞታዎቿ ድረስ መጥቶ መንጠቅና መግፋት አማኙን ሁሉ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ተግባር ነው፡፡ ከጠላት ጠብቃና ተከላክላ በቆየችው መሬት ከተቻለ ተጨማሪ ሰጥቶ መሸለም እንጂ ያላትን ይዞታ መንጠቅ ያጎረሰ እጅን መንከስ ነው፡፡

፪. መንግሥት የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎች፣ ዞኖችና ክልሎች ካለ አግባብ መልስ ሳይሰጡ የቆዩባቸውን የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች በሕግ አግባብ መልስ የሚሰጡበትን መንገድ መቀየስ አለበት፡፡ ካለ አግባብ የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን ቦታዎችም መመለስ ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ካለ ወንጀላቸው ለተከሰሱ፣ ለተጎዱና ለተሠዉትም ተገቢው ካሳ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡ 

፫. የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካላት እስካሁን ከደረሰው ጥፋትና ኪሳራ ሊማሩ ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን የሚያስከብር፣ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከየትኛውም አካል ጋር ሊወያይና ተከራክሮ ሊያሳምን የሚችል፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በመዋቅር የታወቀ አካል ሊኖር ይገባል፡፡ 

፬. አንድ ባሕረ ጥምቀትን በጋራ የሚጠቀሙ አብያተ ክርስቲያናት፡ ቦታውን በዓመት አንዴ ተጠቅሞ ቸል ከማለት ይልቅ በዘላቂነት የሚጠቀሙበትን መንገድ መቀየስና መተግበር አለባቸው፡፡ ባሕረ ጥምቀቶች ሃይማኖታዊ ጉባኤያት የሚዘጋጁባቸው፣ ወጣቶችና መንፈሳዊ ማኅበራት የሚሰባሰቡባቸው፣ ሥልጠናዎች የሚሰጡባቸውና ሌሎችም መንፈሳዊ አገልግሎቶች ዓመቱን ሙሉ የሚከናወኑባቸው መሆን ይገባቸዋል፡፡ ለዚህ ኃላፊነት ደግሞ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የየአካባቢው ወጣቶችና ምእመናን እንዲሁም መንፈሳዊ ማኅበራት ከየቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ጋር በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

፭. የቤተ ክርስቲያን ምእመናንና አገልጋዮች በተለይ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚሆነው ነገር ንቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመጠበቅ ዘወትር የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ከወረዳ ጀምሮ ለመምራት የሚያስብ አካል ቤተ ክርስቲያንን የማይገፋ መሆኑን ከመምረጣቸው በፊት መመርመር ይገባቸዋል፡፡ 

 

Read 695 times