Saturday, 02 January 2021 00:00

የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችና ሌሎች ይዞታዎቿ ወቅታዊ ፈተናዎች

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ

Overview

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ካበረከተቻቸው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽዖዎቿ መካከል ሀገር በወራሪ ኃይል እንዳትደፈርና መሬቷ እንዳይወሰድ በቁርጠኝነት መታገሏ እንደ አንዱ ይጠቀሳል። ‹‹ሀገር ከሌለ በማን ላይ ኖረን እግዚአብሔርን እናመልካለን?›› በሚል የኔነት ስሜትና ‹‹ለሀገሬና ለቤተ ክርስቲያኔ ብሞት በሰማይ ዋጋ አለኝ›› በሚል በጎ አስተሳሰብ የየዘመናቱን ትውልድ ቀርጻ ለአርበኝነት አብቅታለች። ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በሰማያዊ ተስፋ አንጻ ትውልድን ባታፈራ ኖሮ ሰይፍ ይዞ ለሃይማኖቱና ለሀገሩ የሚዋደቅ በእንቢ ባይነት መድፍን የመማረክ ወኔ ያለውን ጀግና፡ ሀገራችን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ ላታፈራ ትችል ነበር። በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርቲያናችን የተቃኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ያለ መለያየት ሁሉም በአንድነት የፈጣሪ ክቡር ፍጡርና የአምላክ ባሪያ ነው›› ብሎ ያምናል። ይህ ትልቅ ሥነ ልቡናዊ ዐቅም ነው፤ ከነጮችና ከወራሪዎች በታች ያልጣለው የሞራል ልዕልናው ነው። በእጅ ከሚዳሰሱ፣ በዐይን ከሚታዩና በጆሮ ከሚሰሙ የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ እኩል ሊነሣ የሚገባው ትልቅ አበርክቶ ነው። ከዚህም ባለፈ የሀገር ግዛት እንዳይወረር፣ መሬቷ እንዳይደፈርና ቅርሶቿ እንዳይመዘበሩ ቤተ ክርስቲያን ካህናቷን ታቦት አስይዛ፣ ምእመናኗንም ከያሉበት ጠርታ አብራ ዘምታለች። በውጤቱም ኢትዮጵያን ከብዙ አፅራረ ሀገር አድናለች። ርስቷንም ጠብቃለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በልጆቿ ደም ከጠላት ሁሉ ጠብቃ ባቆየቻት ሀገር ውስጥ፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምእመን ላይ እስከ መሠዋት ድረስ የሚያደርስ መከራ፤ በሀብት ንብረቷ ላይም የመውደምና የመነጠቅ አደጋ በተቀናጀ መልኩ ሲደርስባት ቆይቷል። በመሬት ይዞታዎቿ ላይ እየታየ ያለው ባለ ይዞታነቷን ያለማረጋገጥና የመንፈግ ተግባርም ከዚሁ ጋር በአንድነት ሊታይ የሚችል፤ መመስገንና መሸለም የሚገባትን በአንጻሩ የማንገላታት ተግባር ነው። በሀገሪቱ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሕጋዊ መንገድ ይዘው ለረጅም ጊዜ የተገለገሉባቸውን መሬቶች ዛሬም የባለ ይዞታነት መብት እየተጠየቀባቸው ነው። የባሕረ ጥምቀትና የመስቀል አደባባዮች፡ በዓላቱ ለብዙ ዐሥርት ዓመታት ሲከበሩባቸው ቢቆይም፡ አብዛኞቹ የይዞታ ማረጋገጫ ለቤተ ክርስቲያን ያልተሰጠባቸው ናቸው። በምእመናን በሕጋዊ መንገድ ለዓመታት የተጠየቁ የ‹‹ቤተ ክርስቲያን ቦታ ይሰጠን›› ጥያቄዎች የመንግሥት የቢሮ ኃላፊ በመጣ ቁጥር እንደ አዲስ ሲታዩና አንዳንዴም ቦታዎቹ ለሌሎች የእምነት ተቋማት ሲሰጡ ዛሬም ይስተዋላል። ለምሳሌ፡-  ለ፪ ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነው ቦታ - እንደ ማሳያ በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ፳፬ ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ለ፪ ወጣቶች መሠዋት ምክንያት የሆነውን ክስተት በምሳሌነት ማንሣት እንችላለን። በአካባቢው ቅርብ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ የአካባቢው ምእመናን በተለይም ሕፃናትና አረጋውያን ጠዋት ኪዳን ለማድረስና ማታም በሠርክ ጸሎትና ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ እጅግ ከአካባቢ ርቀው በመሄድ እንደሚቸገሩ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ፲፬ ዓመታት በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል። የሚመለከተው የመንግሥት አካል በቦታው ቤተ ክርስቲያን እንዳይሠራ ለመከልከል ምንም ሕጋዊ ምክንያት አልነበረውም። ይባስ ብሎ የቤተ ክርስቲያንን የዓመታት ጥያቄ ችላ በማለት ለሌላ የእምነት ተቋም ከኋላ ለመጣ ጥያቄ ቦታውን ሊሰጥ መሆኑን የአካባቢው ምእመናን ደረሱበት።  ይህንን የሚያስረዱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ስም በተሰየመው በጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን መብትና ጥቅም አስከባሪ ማኅበር (ጴጥሮሳውያን ኅብረት)፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የመረጃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ተክሉ ‹‹በአንዳንድ አካላት ቤተ ክርስቲያን መሬቱን እንደ ወረረች ተደርጎ መነገሩ አግባብ አይደለም። እዚያ አካባቢ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበራትም። የአጥቢያ ምእመን ማልዶ ቤተ ክርስቲያን መሔድ ከፈለገ ወይ ወደ ቅዱስ ዑራኤል፣ ወይም ወደ ቦሌ ኆኅተ ብርሃን ማርያም፣ አሊያም ወደ ቦሌ መድኃኔ ዓለም፣ ወይም ደግሞ መገናኛ አካባቢ ወዳለው ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ረጅም መንገድን እንዲሄድ ይገደዳል።  በእነዚህ ቦታዎች መካከል ደግሞ ከፍተኛ ርቀት አለ። ዐቅመ ደካሞች ሁሉ ወደነዚህ ቦታዎች ለመሔድ እጅግ ይቸገራሉ። በዚህም ምክንያት ከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. አንሥቶ የአምልኮ ቦታ ጥያቄው ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ቀርቧል። በኋላም በ፳፻፰ ዓ.ም. ምእመናኑ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ አቅርበው፡ ፓትርያርኩም መስከረም ፳፻፱ ዓ.ም. ላይ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ጥያቄውን በደብዳቤ አቅርበዋል። ለጥያቄው አስረጅ የሆኑ ከ፶ (አምሳ) ገጽ በላይ ሰነዶች ከጥያቄው ጋር አብረው ለከተማ አስተዳደሩ ደርሶት ነበር። ነገር ግን መልስ አልተሰጠበትም። ምእመናኑ ግን ጥያቄያቸውን ፈጽሞ አላቋረጡም ነበር። ከመነሻው ጀምሮ የሚንቀሳቀሱት በተደራጀ መልኩ ነበር። ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የቆዩት ከሰባት ሺህ ሰዎች በላይ የፈረሙበት ሰነድን ከብዙ ማስረጃዎች ጋር ይዘው ነበር›› በማለት አስረድተዋል። በቦታው ላይ ስለተከሰተው የደም መፍሰስ አቶ ግርማ ተክሉ አያይዘው ሲያስረዱም ‹‹ይህ የተከሰተው ፍትሕ በአግባቡ ባለመሰጠቱ ምክንያት ነው። በቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያንን ለመሥራት ለብዙ ዓመታት የቆየ ጥያቄ እያለ ከክስተቱ ከአንድ ወር በፊት ለጠየቀ ለሌላ የእምነት ተቋም ቦታውን ሊሰጡት ነበር። ለዚህም ማስረጃው አለን። ደብዳቤው በእጃችን ላይ አለ። የአካባቢው ምእመን በዚህ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት በመገፋፋት ትዕግሥቱ አልቆ ነው ቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያንን የሠራው። ከዚህ በኋላም እንኳን የከፋ ጥፋት ሳይከሰት ችግሩን መፍታት እየተቻለ፡ የሁለት ወንድሞቻችን ደም እንዲፈስ ሆነ›› ብለዋል። አቶ ግርማ ተክሉ ከዚህ ሁሉ በኋላ፡ ዘግይቶም ቢሆን የከተማው አስተዳደር ቦታውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠቱ አመስግነዋል። ይህ በተለምዶ ፳፬ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ የተፈጠረው ሁኔታንና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ጥያቄዎችን በተመለከተ፡ የመንግሥት የአፈጻጸም መመሪያና ሕግጋቱ ምን እንደሚሉ መገንዘብም ተገቢ ነው። አንድ የእምነት ተቋም የአምልኮ ቦታን ለማግኘት ምን ምን ማሟላት እንደሚገባው መገንዘብም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ግንዛቤ መያዝ ‹‹ይህ ጥያቄ ልክ ነው፤ ይህኛው ልክ አይደለም›› ለማለት ያመቻልና፡ እስኪ ጠቅለል አድርገን እንመልከተው። የአምልኮ ማካሄጃ ቦታን ለመመደብ የሚሟሉ መስፈርቶች በ፳፻፲ ዓ.ም. በወጣው መመሪያ መሠረት፡ አንድ የእምነት ተቋም በከተማ ውስጥ የአምልኮ ቦታን ለማግኘት በቅድሚያ ሊያሟላቸው የሚገቡ ወይም ጥያቄውን ትክክለኛ የሚያደርጉት መሥፈርቶች አሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡- ፩ኛ. ለአምልኮ ማካሄጃ ሊመደብ የሚችለው ቦታ ቅይጥ የመኖሪያ መሬት አጠቃቀም ውስጥ ሆኖ የመዳረሻ መንገዱ ስፋት ቢያንስ ፲፭ ሜትር መሆን ይኖርበታል። ፪ኛ. በአካባቢው ከሚገኘው ከራሱ ነባር የአምልኮ ቦታ አዲስ የተጠየቀው የአምልኮ ቦታ ቢያንስ በሁሉም አቅጣጫ ፫ ኪሎ ሜትር ሬድየስ የሚርቅ መሆን አለበት። ፫ኛ. በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ፭ መቶ ሜትር ሬድየስ ይሆናል። ፬ኛ. ለአምልኮ ማካሄጃ አገልግሎት ቦታ የሚጠይቅ የሃይማኖት ተቋም በሚጠይቅበት አካባቢ ማለትም በሁሉም አቅጣጫ በ፩.፭ (በአንድ ነጥብ አምስት) ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ባለ በወረዳው ውስጥ የተመዘገቡ ቢያንስ ሰባት ሺህ ነዋሪ ምእመናን መኖር አለባቸው። በተጨማሪም በአካባቢው ተመሳሳይ የሃይማኖት ተቋም ካለ በሁሉም አቅጣጫ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ባለው ክልል ውስጥ ያሉት ምእመናን በአዲሱ የሃይማኖት ተቋም ሊመዘገቡ አይችሉም። ፭ኛ. ከአምልኮ ማካሄጃ አገልግሎት ጋር አብረው የማይሄዱ ማለትም ከአህጉር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ ከጦር ካምፖች፤ ከዋና ዋና የንግድ ቦታዎች፤ ከቆሻሻ መጣያ ቦታዎች፤ ከደኅንነት ተቋማት እና ከሌሎች የአምልኮ ሁኔታን ሊያውኩ ከሚችሉ የመሬት አጠቃቀም ቦታዎች ያለው ርቀት ቢያንስ ከ፭ መቶ ሜትር በላይ ርቀት ያለው መሆን አለበት። ነገር ግን በሥራ ላይ የዋሉ ሌሎች ሕጎች ካሉ በሕጎቹ ላይ የሰፈረው ርቀት ገዢ ይሆናል። እነዚህን መስፈርቶች መሠረት አድርገን ቀደም ሲል ያነሣነውን ደም ያፋሰሰውን የቤተ ክርስቲያን ቦታ ይሰጠን ጥያቄን ስናየው፡ በሁሉም መንገድ ሕጋዊና ተገቢ ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን ዓይነት ብዙ ሌሎች መልስ ያልተሰጠባቸው ጥያቄዎችም አሉ። እንደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነትና እንደ ጴጥሮሳውያን ኅብረት ገለጻ፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የይዞታ ማረጋጋጫ እንዲሰጣቸው የተጠየቀባቸው የአድባራት እና ገዳማት እንዲሁም የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎች ብዛት ፻፹ (አንድ መቶ ሰማንያ)  ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ለ፵ (አርባ) የአድባራት እና የገዳማት፣ እንዲሁም ለ፴፰ የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷል። ቀሪዎቹ ግን እስከ አሁን ገና በጥያቄ ላይ ናቸው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ ይዞታዎች ደግሞ ለሌላ አካል ካርታ ተሰጥቶባቸው ይገኛሉ። በተለይ የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች የዚህ ዓይነቱ ንጥቂያ ሰለባዎች ሆነዋል። እስኪ የሚከተሉትን ለዚህ በምሳሌነት እናንሣ፡- ጃንሜዳ፣ ሆሣዕናና መሎ ኮዛ ወረዳ እንደ ማሳያ ጃንሜዳ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ጃን ሜዳ›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙት ‹‹ትልቅና ሰፊ ሜዳ፤ የንጉሥ ሜዳ፤ ንጉሡ የጦር ሠራዊት ሰልፍ የሚያይበት ከባለሟሎቹ ጋር ጉግስ የሚጫወትበት ሜዳ›› ይሉታል። በዋናነት በጥምቀት በዓል ማክበሪያነት የሚታወቀው ይህ ቦታ የተቀየሰው በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው። ‹‹የጃንሜዳ ባሕላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች›› በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያዘጋጁት አቶ ዓባይነህ ታደሰ ጃንሜዳ የመንግሥት ጉዳዮች ማስፈጸሚያ የሹመትና ሽረት አዋጅ መንገሪያ እንደ ነበረ የልጅ ኢያሱ ንግሥና በኋላም ሽረት ሁሉ የተነገረበትና የተደገሰበት እንደ ነበረ ያወሳሉ። በጃንሜዳ ላይ ብዙ የዘመቻ የሰልፍ ትርኢቶች ተደርገውበታል። በ፲፱፻፵ዎቹ የክብር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር ወደ ኮርያ ሲዘምት፣ በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ለዕድገት በኅብረት የዕውቀትና ሥራ ዘመቻ፣ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲዘምቱ ሰልፋቸውን የጀመሩት ከጃንሜዳ ነበር። በዘመነ ደርግ ለተደረጉ ልዩ ልዩ ዘመቻዎች የክተት መነሻም የነበሩበት አጋጣሚም እንደ መኖሩ ሁሉ በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ዘመን በማዕከላዊ መንግሥት ሥር የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች ወደየ ክልሉ እንዲዛወሩ ሲደረግ መነሻቸውን ያደረጉት ጃንሜዳ ነበር። በቅርብ ጊዜ ታሪኩም የገና ጨዋታን ጨምሮ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ተመራጭ መሆኑ ይታወቃል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (፲፱፻፳፫-፲፱፻፷፯) በጃንሜዳ ስለ ነበረው የጥምቀት በዓል አከባበር አቶ ዓባይነህ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው ከጻፉት ውስጥ በጥቂቱ እዚህ ላይ አስፍረነዋል። ‹‹በከፍተኛ ደረጃ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ የሚያከብረው የክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓል ዓመታዊው የጥምቀት በዓል እንደ ሆነ ይታወቃል። በዓሉ በድምቀት የሚከበርበት ቦታ ከ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ጀምሮ በጃንሜዳ እንዲሆን በመወሰኑ በዚሁ ሥፍራ ያለማቋረጥ ሲካሄድ ቆይቷል። ‹‹የጥምቀት በዓል የሚከበርባቸው ሌሎች ጥምቀተ ባሕሮች በአዲስ አበባ ከተማ ቢኖሩም የጃንሜዳው ጥምቀተ ባሕር በየዓመቱ ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱና ሚኒስትሮች ከሕዝብ ጋር ተገኝተው የሚያከብሩበት፣ የኦርቶዶክስ ፓትርያርኩም ሥነ ሥርዓቱን የሚመሩበት በመሆኑም የተለየ ዝና ሊያገኝ ችሏል። ‹‹በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ዓመታዊው የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ ሲከበር በተለየ ችግር ምክንያት ካልሆነ ንጉሡ በሥፍራው መገኘታቸው የተለመደ ሥርዓት ነበር። ይህም ሁኔታ በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል የቆየውን መተሳሰር ያመለክታል። በ፲፱፻፳፬ ዓ.ም. በጤና መጓደል ምክንያት፣ ከ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ወደ አውሮፓ በስደት ምክንያት በመሄዳቸው በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ጉብኝት በመሄዳቸው ምክንያት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ንጉሡ በዓሉን ሳያከብሩ መቅረታቸው ተመዝግቧል። ‹‹በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ የተለያዩ የሀገር መሪዎች ከንጉሡ ጋር መገኘታቸው የዚህን ሥፍራ ታሪካዊ ገጽታ የሚያጎላ ሆኖ እናገኘዋለን። በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. በዓሉ ሲከበር ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የነበሩት የዴንማርክ ንጉሥና ንግሥት በጃንሜዳ ተገኝተው ነበር። በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ፖምፒዱ በጃንሜዳ ተገኝተው የጥምቀት በዓልን አከባበር ተመልክተውታል።  ‹‹የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ከሌሎቹ በተለየ ትኩረትን የሳበው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። አንደኛው፦ የታቦታት ብዛት በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ አሥራ ሁለት ታቦታት ባንድ ላይ ውለው ስለሚያድሩ ከተለያዩ የከተማው ክፍሎች አጅቧቸው የሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ስለሚበዛ በዓሉን ሊያደምቀው ችሏል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፡- ንጉሡና ንጉሣውያን ቤተሰቦች ሚኒስትሮች፣ፓትርያርኩ በጃንሜዳ በዓሉን ማክበራቸው ስፍራው ከሌሎች ባሕረ ጥምቀቶች የበለጠ ደረጃ እንዲያገኝ አስችሎታል። ጃንሜዳ የተመረጠበት ምክንያት የማዕከላዊው መንግሥትና ቤተ ክህነት ኃላፊዎች የጥምቀት በዓል ማክበሪያና በንጉሡ /በጃንሆይ/ ማዕርግ ስለ ተሰየመ መሆኑ ታውቋል። ንጉሡ ከሥልጣን ከወረዱም በኋላ ዋናው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሆኖ ለመቀጠል ችሏል።›› (ዓባይነህ ታደሰ፣ የጃንሜዳ ባሕላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች፣ retrived from: http://m.facebook.com/architectyohannis/posts/2938117996198309?local2=ms_MY) ጃንሜዳ ከሰማንያ ዓመታት በላይ (ከ፲፱፻፴፫ ጀምሮ) በጥምቀት በዓል ማክበሪያነት ያገለገለ ቦታ ነው። በርካታ  የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የባሕል እና ሃይማኖታዊ እሴቶች የተሰናሰኑበት ራሱ ታሪክ የሆነ ሥፍራ ነው። ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት  የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና የባሕል ማዕከል  ጥምቀትን የዓለም ቅርስ አድርጎ ሲመዘግብ  በርካታ ማስረጃዎች እና የሃይማኖታዊ ኩነቶች ናሙና ከተወሰደባቸው ታሪካዊ ቦታዎችም አንዱ ነው። ይህ ታላቅ ቦታ በቀደሙት ዘመናት፡ አሁን ካለው ይዞታ በላይ የነበረው ቢሆንም በተለያየ ዘመን ልዩ ልዩ አካላት ተናጥቀውት  አሁን ላይ የሚገኘው ፴፫ ጋሻ ገደማ ነው። የቦታው ታሪካዊ ባለ ይዞታም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው። ነገር ግን ይህች ታሪካዊት የቦታው ባለ ይዞታ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባላወቀችበት ሁኔታ ከዘጠና ከመቶ በላይ ይዞታው የአዲስ አበባ ስፓርት ኮሚሽን ካርታ አውጥቶበት ‹‹ባለ ይዞታ ነኝ›› እያለበት ይገኛል። ይህ ባለ ይዞታነቱን የሰጠውንም ሆነ የተቀበለውን አካል ከታሪክም ሆነ ከሞራል አንጻር የሚያስነቅፍ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያንን የማግለል ተግባር ነው። የቦታውን ቅርስነትም የሚጎዳ አስተዋይነት የጎደለው ውሳኔ ነው። በመሆኑም ይህን አግባብ ያልሆነ ውሳኔን ቤተ ክርስቲያናችን ለከተማው አስተዳደር ስሞታ አቅርባ በመከታተል ላይ  ትገኛለች። ታሪካዊው ጃንሜዳ የዓለም ቅርስ፣ የሀገር ሀብት እና የገቢ ምንጭ ሆኖ፤ በዋናነት ሃይማኖታዊ አከባበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት እንዲቀጥል  የከተማው አስተዳደር ሊያስብበት ይገባል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአትክልት ተራ ሆኖ እጅግ መቆሸሹ ለጥምቀት በዓል አከባበር እንደማያመች በመረዳት ለማጽዳት በከተማው አስተዳደር እየተደረገ ያለው ርብርብ፡ የቦታውን ባለ ይዞታነት ለቤተ ክርስቲያን መልሶ ፍትሕን በማረጋገጥ ሊደገም ይገባል። የከተማ አስተዳደሩ ይህንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ ፈጥኖ የሚመልስ ከሆነ በእውነቱ የታሪክና የቅርስ አለኝታነቱን ማስመስከር የሚችል ይሆናል። ሆሣዕና በሆሣዕና ከተማ የጥምቀተ ባሕር ቦታው  ለረጅም  ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተይዞ አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየ ጥንታዊ ይዞታ ነው። ይህ ጥንታዊ ይዞታ እስከ ፳፻፲፩ ዓ.ም. ድረስ ስድሳ ሺህ ካሬ ሙሉ ነበር። በዞኑ አሁን ባለው ኢ-ፍትሕዊነት ጥንታዊው የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታ ተነጥቋል። አሁን በከተማው ውስጥ የገበያ ቦታ የሆነው የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የነበረና የተነጠቀ ነው። ከብዙ ጥረት በኋላ ሃያ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን ብቻ ለመስጠት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም እርሱንም መልሰው ከልክለዋል። በዚህ ላይም አስተያየት የሰጡን አቶ ግርማ ‹‹የዞኑ አመራሮች ሲፈልጉ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለይቶ የሚያጠቃ መመሪያ ያጸድቃሉ። እንዲሁም ፍትሕ በመንፈግ የግል ሃይማኖታቸው ተከታይ ለሆኑት ፓስተሮች ከሠላሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ካሬ ያድላሉ። የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ይዞታ ግን ይነጥቃሉ›› ሲሉ የምእመናኑን ምሬት አስተጋብተዋል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስም በተመሳሳይ ባለ ሥልጣናቱ ለቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥላቻ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኗ ያነሣችውን ተገቢ ጥያቄ በሕግ አግባብ ከመመለስ ይልቅ ነገሩን የፖለቲካ ቅርጽ በመስጠት ከማወሳሰባቸው ባሻገር ‹‹ወራሪ›› እያሉ መሳደብ የሚቀናቸው መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መግለጻቸው ይታወሳል። ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ከላይ ካነሣናቸው ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ የተከሰተው ክስተትም ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጫናና በደል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። በወረዳው የሚገኘው የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ይዞታው ከ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፡ እስከ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ድረስ ቦታው የሚገኝባት ከተማ በገጠር ከተማነት ቆይታ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ሥር የሆነች ናት። ታዲያ በዚሁ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የከተማዋ አስተዳደር ወደ ማዘጋጃነት ሲቀየር የሃይማኖት ተቋማት ይዞታ ‹‹ባለበት ይቀጥላል›› ተብሎ ነበር። ከዓመታት ቆይታ በኋላ በ፳፻፲፪ ዓ.ም. ባለ ሥልጣናቱ ሁለተኛ ዙር ጥናት በማለት፡ የቀድሞውን ውሳኔ ችላ ብለው የቤተ ክርስቲያንን የጥምቀት ይዞታ ነጠቁ። ገና ከተማው ሳይቆረቆር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአምሳ ዓመታት ትጠቀምበት የነበረውን ይህን ይዞታ ከተማው ከኋላ መጥቶ በመስፋፋቱ ምክንያት፡ የአስተዳደር አካላቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ፣ ለበዓሉ ቅርስነት ሳይጨነቁ ቦታውን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነጠቁ። ይህን ሲያደርጉ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከበዓል አከባበሩ ጋር በማይጣረስ መልኩ እንድታለማ እንኳን ዕድል አልተሰጣትም። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ የጉዳዩን ሕገ ወጥነት እና ኢ-ፍትሐዊነት አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡት ምእመናን፣ ለአምሳ ዓመታት ሲገለገሉበት በነበረው የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ላይ የመጠመቂያ ገንዳ በመሥራት እና መስቀል በመትከል በዓለ ጥምቀትን በማክበራቸው፡ በተለይ ጉዳዩን በዋናነት የሚከታተሉትን ክርስቲያኖች፡ የከተማው አስተደደር ክስ መሠረተባቸው። በሚያሳዝን መልኩም ከ፯-፱ ዓመታት ድረስ የእስር ፍርድ እንዲበየንባቸው ተደረገ። ያቀረቡት ጥያቄ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መልስ ባላገኘበት ሁኔታ ዘወትር በዓሉን በሚያከብሩበት መልኩ ለማክበር በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ለዓመታት በእስር እንዲቆዩ ፈረዱባቸው። ስለ ጉዳዩ አስተያየት የሰጡን ቀደም ሲል ያነሣናቸው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ተክሉ ‹‹ይህን ያደረጉት ሙሉ ለሙሉ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የአስተዳደር አካላት ናቸው። ድርጊቱ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባለ ጥላቻ ብቻ የተፈጸመ ነው›› ያሉ ሲሆን፡ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ባደረገችው ጫናም ክልሉ እስረኞቹ ካለ አግባብ መታሰራቸውን በማመን በቅርቡ እንዲፈቱ ማዘዙንም ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ‹‹በዞኑ የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ብዙ መከራ እየደረሰባቸው ነው። መስቀል ያለበት ቲሸርት እንኳን መልበስ አልተቻለም›› ብለው ቤተ ክርስቲያን እና አማኞቿ ላይ እየደረሰ ያለው ፈተና ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህን በምሳሌነት አነሣናቸው እንጂ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ለዘመናት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥባቸው የኖሩ እስከ ዛሬም ያሉ ሆነው ሳለ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የዘመቻ ዒላማ እንደ ሆኑና በዚህና በእኛም ቸልተኝነት ምክንያት ለፈተና የተጋለጡ እንደ ሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።  ይቀጥላል  
Read 807 times