Wednesday, 07 April 2021 00:00

ቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥት

Written by  ዳዊት ደስታ
እንደ መግቢያ የሰው ልጅ አብሮ ለመኖር እንዲችል አካሄዱን የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት ወደ ተፈለገውም ዕድገትና ብልጽግና እንዲደርስ የሚያስችሉት ሁለት የሥልጣን ተቋማት (ቤተ-መንግሥት እና ቤተ-ክህነት) አሉ። እነዚህ ተቋማት አንዱ ለመንፈሳዊ፣ ዘላለማዊና ሰማያዊ ጉዞውና ፍላጎቱ ሌላው ለሥጋዊ ጊዜያዊና ምድራዊ ጥቅሙና ዕድገቱ ላይ ተመሥርተዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በጥብቅ ግንኙነት ለረጅም ዓመታት አብረው ዘልቀዋል፤ ትስስሩም በሁለቱም መፈላለግ ላይ የተመሠረተ ነበር። መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርሕ ተግባራዊ አፈጻጸሙ አጠያያቂ ነው፤ ሁለቱም በተመሳሳይ ሕዝብ ላይ ስለሚያተኩሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ‹‹መነካካታቸው›› አይቀሬ ነውና። በሀገራዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር መተባበር በየትኛውም አኳኋን ‹‹ፖለቲከኛ›› ሊያሰኝ አይገባም፤ ለሃይማኖቱም ምድራዊ ህልውና የሀገር ሰላምና ልማት ያስፈልጋልና። የሁለቱም ህልውና የተመሠረተው በሕዝቡ ላይ መሆኑ ያገናኛቸዋል ብቻ ሳይሆን ወደ የራሳቸው ፍልስፍና በመሳብ ሂደት ውስጥ ያነታርካቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ‹‹በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት›› ናት፤ ምድራዊው መንግሥትም በሕዝብ ተመሥርቶ፣ ለሕዝብ የሚሠራ፣ ሕዝባዊ ነው። እናም ሁለቱም ያለ ሕዝብ (ሰዎች) ሀልዎታቸው ሊነገር አይችልም።

 

ግንኙነቱ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት ትስስር በዓለምም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የነበረ፣ ዛሬም ድረስ የሚስተዋል ነው። የኢትዮጵያ ነገሥታትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፤ የረጅም ጊዜ ቁርኝት ነበራቸውና። በብሉይ ኪዳን በንግሥት ሳባ የተጀመረው ግንኙነት (፩ነገ.፲፥፩)፤ በኋላ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በ፴፬ ዓ.ም. በዘመኑ የአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር በነበረው (ጃንደረባው ባኮስ) አማካይነት ክርስትናን ስትቀበል (የሐዋ.፰፥፳፮-፵፪) የበለጠ ተጠናከረ። ይህ ክስተት ከተለመደው የግሪኮ-ሮማን ዘመን የክርስትና ታሪክ (ክርስትና በተራ ሕዝቦች ተጀምራ ወደ ነገሥታቱ ከምትጎተትበት ሁኔታ) ጋር ተቃራኒ ነበር፤ በተገላቢጦሹ በኢትዮጵያ ክርስትናን ለሕዝቡ የሰበከው የቤተ መንግሥቱ ጃንደረባ ነውና።

ቤተ ክህነት ነገሥታቱን ቀብታ በማንገሥ ሕዝቡም ለእነርሱ እንዲገዛ ባላት ተሰሚነት በማሳመን፣ ለሕዝብ ጠንካራ ማኅበራዊና ሥነ ልቡናዊ ግንባታ ግንባር ቀደም ሚናን ተጫውታለች። ነገሥታቱም አንድም ሃይማኖተኞች ስለ ነበሩ፣ በሌላም መልኩ ደግሞ ለፖለቲካዊ አስተዳደራቸው እጅግ ስለምታስፈልጋቸው ማለትም የመንግሥታቸው ህልውና የሚለካው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት መጠን ስለ ነበር፡ ቤተ ክርስቲያንን የሙጥኝ ብለዋት አልፈዋል፤ በአንድ መልኩ ሲደግፏትና በሌላ ጊዜም ሲገፏት፡ ማለትም ሲጠቀሙባት ኖረዋል።

ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሁሉ ጉዞዋ ለሀገር ያበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች አሉ። እነሱም በሀገር ግንባታ፣ ከመንግሥት ጋርግንኙነት በመፍጠር፣ በመልካም ዜጋ ግንባታ፣ በፖለቲካ፣ በሀገር ጥበቃ እና አርበኝነት የነበራት አበርክቶ ቀላል አይደለም። ድርሻዋም ምን እንደ ነበር የሚከተሉትን ጥቂት ማብራርያዎችን እንመልከት።

በሀገር ግንባታ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝቦች ዘንድ ተፈርታ እና ተከብራ እንድትኖር ካደረጓት ነገሮች አብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሠራቻቸው ሥራዎች ናቸው። አንድን ሀገር ሀገር የሚያሰኘው ሕዝቡ እና የአኗኗር ዘይቤው፡ ያለው መልክዐ ምድሩና ሕዝባዊ ሥርዓተ ማኅበር ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ መሠረት እና ጉልላት፣ድር እና ማግ ናት። ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የኩራት ምንጭ መሆንዋን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦም ቤኪ የተናገሩትን ጠቅሶ በፍቅር ለይኩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ድርሻ እንዲህ አስፍሮታል። ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፣ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መሥራቾች የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያን ልሂቃን ናቸው። የተነሡትም ከአብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ። 

እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚስዮኖች ራሳቸውን አላቀው በቤተ ክርስቲያናን ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እንደመነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ፷፰ ላይ ይገኛል፤ ይህም፡- ‹‹መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።›› የሚለው ነው። አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቅድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ሥነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር። ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አፍሪካውያን በሙሉ ለነፃነት፣ ለባህላቸው፣ ለልዑላዊነታቸው፣ ለማንነታቸውና ለሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር። ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሀቅ ላይ ተመሥርተው ነበር። እነዚህ የጠቀስናቸው አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፣ በአህጉራችን ላይ የመጀመሪያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ANC) የተወለደውም ከእነዚሁ ከሀገራችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው...የፓርቲያችን የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቄስ ጆን ዱቤም የዚሁ የደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበሩ…።›› በማለት ገልጿል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች እንዳትንበረከክ የሰበኩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እነ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትን እና እነ አቡነ ሚካኤልን ማን ይረሳቸዋል። የሀገር ፍቅርን ከነኩራቱ፣ ጀግንነትን ከነጥብዓቱ፣ ፊደልን ከነቁጥሩ፣ ዘመንን ከነቀመሩ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከተችው ቤተ ክርስቲያናችን ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገራችን በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የነበራትን ሚና ለመረዳት የመንግሥት አወቃቀር በኢትዮጵያ ምን እንደ ነበር በሚገባ ማጤን ይገባል።

ለምሳሌ ከንግሥት ማክዳ ከቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ከመጽሐፍ ቅዱሱ ከንጉሥ ሰሎሞን የዘር ሐረግ የተገኙ ነገሥታት ሥዩመ እግዚአብሔር (በእግዚአብሔር የተቀቡ እየተባሉ) የቤተ ክርስቲያናችን ብፁዓንና ቅዱሳን ፓትርያርኮች እየቀቡ ያነግሡአቸው እንደ ነበር የኢትዮጵያን ታሪክ የተማረ ሁሉ የሚያውቀው እውነት ነው። እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት ድረስ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት ንግሥናቸውንም ሆነ አስተዳደራቸውን የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ከዚህም የተነሣ ንጉሡ እና ፓትርያርኩ የጠበቀ ቁርኝት እንደነበራቸው በሁሉ የታወቀ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ መሠረታዊ መገለጫዋ ናት ብሎ የጻፈው (ያዕቆብ ቡልቲ ፳፻፲፪፡፲) ነው። አክሎም  በገጽ ፲ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ጠቃሚ ድርሻ በኢትዮጵያ እድገት ላይ ተጫውታለች›› በማለት ይገልጻል። ሲያብራራም ‹‹በትምህርት መስክ የትምህርት ሚኒስቴር በመሆን እንደዚሁም በልማት መስክ ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን በማቋቋም በዚህ ኮሚሽን የገጠር የንጹሕ ውኃ ሥራ፣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል ላይ እንዲሁም ንጽሕና እና ጤና አጠባበቅ ላይ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦን አስፍሯል።››

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ መንግሥት ግንባታ ለኢትዮጵያ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ምን እንደ ነበር ማሳየት ተገቢ ነው። ለሀገር ግንባታ ካበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች መካከልም የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው። የተስተካከለ ሥነ ምግባራዊ ሰብእና ያለው፣ አርበኛ ጀግናና ሀገር ወዳድ ትውልድ መፍጠር፣ ማኅበራዊ ጥንካሬ በመፍጠር፣ በአፈርና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ሀገር በቀልና ዓለማቀፋዊ ትምህርቶችን በማስፋፋት፣ የባህልና የቱሪዝም፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ቅርጻ ቅርጽ፣ የኪነ ሕንፃ፣ የሥነ ዜማ ጥበባዊ ሀብቶችን በማስፋፋት በማስጠበቅ ብሎም ለዓለም በማስተዋወቅ፣ በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርንና ሀገራዊ አንድነትን በመፍጠር፣ በድህነት ቅነሳ፣ አካል ጉዳተኞችን በማብቃት፣ የሀገርን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በማፋጠን፣ ሰላምም በማስፈን፣ ለምሁራን በጥናትና ምርምር ማዕከልነት እንዲሁም ዘመናዊ ሕክምና ባልነበረበት ወቅት የሕክምና ማዕከል ሆና ስታገለግል መኖሯ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ከመንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የሀገሪቱ መሪ እና አስተዳዳሪዎችን በማስተማር በማብቃት በመሾም ሲያጠፉ በመገሠጽ የመሪነት ሚናዋን እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ድረስ ስትጫወት የነበረች ሲሆን እስከዚሁ ዘመንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት የነበረ ሲሆን እስከዚሁ ዘመን ድረስ ምንም ዓይነት ልዩነት በቤተ መንግሥቱ እና በቤተክህነቱ መሀል አልነበረም ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ከላይ እንደገለጽነው መንግሥት እና ሃይማኖት ተለያይተዋል። ‹‹የመንግሥት እና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደ ቀኝ እና ግራ እጅ ነበር›› ብሎ የጻፈው ዓለማየሁ ብርሃኑ የተባለው አጥኚ የሀገሪቱ ንጉሥ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል መሆን እንደ ነበረበትም እንዲሁ አእምሮ የተባለ ምንጭን (፲፱፻፸) ጠቅሶ ገልጧል። የሀገሪቱን ሕግ የሚያወጡት እንደዚሁም ሀገሪቱን ሲመሩ እና ሲያስተዳድሩ የነበሩትም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባላት በመሆናቸው የሃይማኖቱ ጠበቆች ነበሩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሁነኛ የመንግሥት የልማት አጋር ስትሆን በሁሉም የሀገራችን ስፍራዎች ሁሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በጥብቅ በሥነ ምግባር እና በምጣኔ ሀብት አብራ የምትሠራ መሆንዋን ይገልጻል። አክሎም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀገሪቱ ሁነኛ የልማት አጋር በመሆን የምትጫወተው ሚና ቀላል እንደማይባል ነው። (ዓለማየሁ ብርሃኑ፣ ፳፻፲፱)

ዓለማየሁ ብርሃኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስፈላጊነት በከተማ ልማት (Relevance of Ethiopian OrthodoxTewahido Church Institutional Setup for Rural Development:) በሚል ርእስ ባዘጋጀው የ፪ኛ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፉ ላይ ገጽ ፲ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ እንደ መሆንዋ በሀገሪቱ ላይ በርካታ አሻራዎችን አኑራለች። በሀገር አንድነት እና በሰላም ግንባታ፣ በሀገር ነፃነት እና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአርበኝነት ሚናን ስትጫወት ነበር›› ሲል ገልጧል። አክሎም ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የራስዋ የሆነ ፊደል ያላት በዛም የምትጽፍ እና የምታነብ እንድትሆን፣ የራስዋ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ያላት የራስዋ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያላት አሁንም የምትጠቀምበት ፊደል፣ ቁጥር እና የዘመን መቁጠሪያ የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንደ ሆነ፤ በ፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ባፈራችው በቅዱስ ያሬድ የተገኘው የዜማ ስልት ከመንፈሳዊው አገልግሎት ባሻገር ለዓለማዊው ዜማም መሠረት ሆኖ ሀገር እንደምትገለገልበት ይገልጻል።

በመልካም ዜጋ ግንባታ

የመልካም ዜጋ ግንባታ የሀገራችን መንግሥት መርሕ ነው። በሥነ ትምህርት (በትምህርት ፖሊሲው) ላይ በዓላማ ከተቀመጡ ቁልፍ ቃላት አንዱ መልካም ዜጋ መፍጠር ነው። እርግጥ የዘርፉ ምሁራን እንደሚስማሙበት የሥነ ምግባር እና ሥነ ዜጋ ትምህርት መልካም ዜጋ ፈጥሯል ወይ የሚለው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። 

በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት በቅርቡ እንደገና ተሻሽሏል። መልካም ዜጋ ሀገሩን የሚወድ ሙስና (ጥፋትን) የሚንቅ በበጎ ሥነ ምግባር የታነፀ፣ ክፉውን የሚጠላ ነው። እርግጥ እንደዚህ ያለ ዜጋ ለመፍጠር የሥነ ዜጋ ትምህርት እና የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር መምህራን አልቻሉም። መልካም ዜጋ የሚፈጠረው ስለ መልካም ዜግነት በመጽሐፍ በማስተማር ብቻ ሳይሆን መልካም ዜጋ ሆኖ በማሳየትም ጭምር ነው። የመልካም ዜጋ ግንባታ የሚጀመረው እንደ ሕንፃ ከታች ነው። ብዙ ጊዜ በሀገራችን ስለ መልካም ዜጋ ግንባታ የሚሰበከው ግን ልጆች ካደጉ በኋላ ነው።

 

ሕጻናት ከሕፃንነታቸው ጀምረው መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ በፈሪሀ እግዚአብሔር ሰውን በማክበር በትሕትና እንዲያድጉ የቤተ ክርስቲያንን ሚና ማንም ሊተካው አይችልም። ሀገር የምትፈልገው መልካም ዜጋ ከሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ከሃይማኖት ተቋማትም ጭምር ነው። መንግሥት ይህን ዐውቆ ለመልካም ዜጋ ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ ትልቅ ቦታ በመስጠት በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከጎናቸው ሊቆም እና አብሯቸው ሊሠራ ይገባዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በሥነ ምግባር የታነፀ መልካም ዜጋ ማፍራት ትችልበታለች። ታዲያ ለዚህ ተግባሯ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ሊያደርግላት ይገባል። ይህ ሲሆን ሙስናን የሚጠየፍ በመልካም አስተዳደር የተመሰከረለት ተስፋ የሚጣልበት ከክፉ ሥራ ሁሉ የራቀ የሀገሩን ጥቅም ለሌላው አሳልፎ የማይሰጥ ሀገሩን የሚወድ ለሀገሩ የሚሞት ዜጋን ማፍራት ይቻላል።

በፖለቲካ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከትላንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ማንም ሊተካው የማይችለውን ሚና እየተጫወተች ያለች ሀገር ናት። ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ሀገራችን እንደ ሀገር ሉዓላዊነትዋ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገችው ዛሬ ድረስ በየትኛውም ዓለም እንድንኮራ መመኪያ እና መኩሪያ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ናት። ምዕራባዊ ባህል እና ፍልስፍና ያልተቀላቀለባት ቅድስት፣ አሐቲ፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት ናት። ለሀገራችን በፖለቲካው መስክ ደግሞ እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት ድረስ ነገሥታቱን ቀብታ በማንገሥ በንግሥናቸው ዘመንም ስታማክር በማጠናከር፣ መልካም ሲሠሩ በማመስገን ክፉም ሲሠሩም ያለ ፍርሀት በመገሠጽ ተቋማዊ ኃላፊነቷን በትጋትና በቁርጠኝነት ስትወጣ ኖራለች። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገር ወዳድ ልጆችን ወልዳ ያሳደገች፣ ጀግንነትንና የሀገር ፍቅርን ያስተማረች ለሀገር መሞት ክብር መሆኑን የእምነት አባቶቿን እነ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤልን ፊት አውራሪ በማድረግ ፋሺስት ኢጣሊያን የተፋለመች፣ ታቦት አውጥታ ዐውደ ውጊያ ድረስ የዘመተች የሀገር ባለ ውለታ ቤተ ክርስቲያን ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የሀገራችን ልዕልና ቋንቋችን እና ማንነታችን ተጠብቆ በራሳችን ቋንቋ የምንናገረው በራሳችን ፊደልም የምንጽፈው ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው መስክ በነበራት ንቁ ተሳትፎ ማንነታችንና ክብራችን ተጠብቆልን ስለ ኖረ ነው። 

ዛሬ ላይ ግን ጥንት የነበራት ፖለቲካዊ ሚና በዓለማዊነት አገዛዝ ስም ተዳፍኖ ሀገርን የሚያበጣብጥ፣ የሕዝብን ሰላም የሚያናጋ የዘረኝነት መንፈስ በሰሜን እና በደቡብ በምስራቅ እና በምዕራብ ተንሰራፍቶባታል። ይህም ቤተ ክርስቲያን በሀገር ፖለቲካ ላይ የነበራት ሚና መቀማት ውጤት እና የውጭ ኃይሎች ሥውር የማፈራረስ ተልእኮ እንዲሁም የሴራ ፖለቲካቸው (የሴራቸው) ውጤት ነው። አሁንም ቢሆን ሀገራችን ዕሴቷንና ባህሏን ጠብቃ እንደ ሀገር መቆም የምትችለው የእምነት ተቋማት ጠንካራ ዘመኑን የዋጀ አመራር ሲኖራቸው ነው። 

ኢትዮጵያዊነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ከሰሀራ በታች ባሉ በቅኝ ግዛት ጊዜ የተጀመረ ፖለቲካዊ ሃይማታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን የተጀመረውም ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው በደቡብ አፍሪካ ነው።

እንቅስቃሴው በ፲፰፻፹ እ.አ.አ. በአፍሪካ ያሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ በአንድ ለመሰብሰብ የተመሠረተ ነው እንደ ትመቡ ተሪቢያል ቤተ ክርስቲያን እና የአፍሪካ ቤተክርስቲያን (Tembu tribal church and the Church of Africa. ቃሉን መጀመሪያ የተጠቀመው Mangena Mokone የተባለ ሰው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ባገኘ ጊዜ እንደ ሆነ እና ዘረኝነትን ለመዋጋት እና ቅኝ ገዥዎችን ለመቃወም የተጀመረ እንቅስቃሴ እንደነበረ የሚገልጸው ብሪታኒካ ኮነሰስ ኢንሳይክሎፒዲያ ገጽ ፮፻፴፱ ላይ ነው። በዚሁ መጽሐፍ ላይ በናይጄሪያ፣በካሜሮን፣በጋና እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ይህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይገልጻል። 

ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለመሳለም የሚሄዱ የኢትዮጵያ መነኮሳት እና ምእመናን እስከ ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ መልካም የሆነ የውጭ ግንኙነት ይፈጥሩ እንደነበር እና በሀገራችን ስላለው ጥሩጥሩ ነገር እንደ አምባሳደር በመሆን በደረሱበት ሁሉ ለሚያገኙት በመንገር ሀገራቸውን ማስተዋወቃቸውን የሚነግሩን በአ.አ.ዩ.የታሪክ  እና የቅርስ ጥናት የት/ት ክፍል መምህር የሆኑት ዲ/ን ጌታቸው መረሳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና በመካከለኛው ዘመን የውጭ ግንኙነት በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው ገጽ ፫ላይ ነው።

በሀገር ጥበቃ እና አርበኝነት

የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቀው በሀገር የቁርጥ ቀን ልጆች የሥጋ የደም እና የአጥንት ዋጋ የነፍስ ዋጋ በመክፈል ነው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንግንባር ቀደም በመሆን ሀገርን ከጠላት በመከላከል እና ወራሪ ኃይልን በጸሎትም እንደዚሁም ልጆችዋን ወደ ዐውደ ጦር ግንባር በመላክ ለሀገር ያላትን ታማኝነት ከየትኛውም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቤተ እምነቶች በላይ ለዘመናት ስታሳይ ኖራለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰውን ግደሉ ብላ አታስተምርም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ሲመጡ በመጀመሪያ በጸሎት፣ በትሕትና እና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነገሮች እንዲያልቁ ትጥራለች እንደዛ ሆኖ ማለቅ ካልቻለ ግን ወደ ዐውደ ጦር የሚያስወጣ ግዳጅ ሲመጣ ታቦት አውጥታ እግዚኦታ አድርሳ ልጆችዋን ለጦርነት ትልካለች። አሸንፈውም ሲመጡ ጀግንነታቸውን በመጽሐፍ በሐውልት ትዘክራለች፣ የሞቱትን ፍትሐት ፈታ ወደ ላይኛው መንግሥት በክብር ትሸኛቸዋለች። 

 

Read 1732 times