Friday, 16 October 2020 00:00

ክብረ ክህነት (ከባለፈው የቀጠለ)  ክፍል ሦስት ፬. ክብሩ 

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ውድ አንባብያን ባለፉት ተከታታይ እትሞቻችን የክህነትን ምንነት፣ ክህነት በዘመናት ምን ይመስል እንደነበር፣ ክህነት እንዴት ይሾማል የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል በዚህ ዕትም ደግሞ ክህነት ክብሩ ምን ይመስላል የሚለውን እንመለከታለን መልካም ንባብ። በመጽሐፍ ቅዱስ የክህነት አገልግሎትን የሚያከናውን አካል እጅግ ተመስግኗል። ክህነት አንዱ አገልግሎት ምእመናንን መመገብ ነውና መጋቢውን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው።” (ሉቃ.፲፪፥፵፪) በማለት ይገልጸዋል። ብፁዕ ከመባል በላይ ደግሞ ክብር የለም። ይህ ሰው የተመሰገነው በእግዚአብሔር ቃል ነው።  ሰው መልካም ሥራ ሠርቶም ይሁን ሳይሠራ በሰው ዘንድ ሊመሰገን ይችላል። አመስጋኙ ከራሱ የግል ጥቅም አንጻር ተነሥቶ ሊያመሰግነው ይችላል። ወይም ደግሞ የሚመሰገነው አካል ካለበት መዓርግ የተነሣም እንዲሁ በአድር ባይነት ሰዎቹ ሊያመሰግኑት ይችላሉ። ያለምንም ማዳላት በትክክል አይቶ የሚፈርድ፣ አይቶ የሚያመሰግን በትክክል በሠራነው ሥራ የሚያመሰግነን ማለትም በአድር ባይነት ወይም እጠቀም ሳይል የሚያመሰግን እግዚአብሔር ነው። የክህነት አገልግሎትን የሚያከናውነውን ማለትም መንጋዎችን የሚመግባቸውን አገልጋይ ያመሰገነው እጠቀም ሳይል ሁሉ ያለው እግዚአብሔር አምላካችን ነውና በእግዚአብሔር ዘንድ ከመመስገን በላይ ክብር የለም የተባለው ለዚህ ነው።  የካህናትን ክብር በተመለከተ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተሰኘ ድርሰቱ “ህየንተ ሱራፌል ብነ ላእካነ ምሥጢር ካህናት እለ ያቄርቡ መሥዋዕተ ንጹሐ ወቍርባነ ነባቤ ወዕጣነ ውኩፈ ዘመዓዛሁ ሠናይ። ህየንተ ሊቃናት ብነ ዲያቆናት ንጹሓን እለ አቅለሉ ክነፊሆሙ ለተልእኮ ምሥጢር በዲበ ዛቲ ጠረጴዛ፤ በሱራፌል ፈንታ መዓዛው ያማረና ተቀባይ የሆነ ዕጣንን፣ ተናጋሪ ቍርባንንና ፣ ንጹሕ መሥዋዕትን የሚያቀርቡ የምሥጢር መልእክተኞች ካህናት አሉን። በሊቃናት ፈንታ ቅድስት በምትሆን በቤተ ክርስቲያን ለመላላክ እግራቸውን ያቀለሉ ንጹሓን ዲያቆናት አሉን።” (ሰዓታት፣ኵሎሙ) በማለት ክህነት ግሩምና ድንቅ ክብር እንደሆነ ያስረዳናል። መላእክት በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ እጅግ የተከበሩ እግዚአብሔርን ማገልገል ተግባራቸው የሆነላቸው የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረታት ናቸው። እግዚአብሔር አምላካችን መላእክትን ስሙን ቀድሰው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ድንቅ በሆነ ጥበብ እንደፈጠራቸው የሰውን ልጅም እንዲሁ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በጸጋ ላይ ጸጋን አጎናጽፎታል። ለመላእክት ያላደላቸውን የክህነት አገልግሎትም አድሎታል። ስለዚህ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመላእክት ፈንታ ካህናት፣ በሊቃናት ፈንታ ዲያቆናት አሉን እያለ በክህነት አገልግሎት የሚያገለግሉ አካላት ምን ያህል ክብር እንዳላቸው ያስረዳናል። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ክህነት ባስተማረው ትምህርትና ገብረ እግዚአብሔር ኪደ በተረጎመው መጽሐፍ “የብሉይ ኪዳን ካህናት ሰውነትን ከለምጽ የማንጻት ሥልጣን ነበራቸው፤ እንዲያውም የማንጻት ሥልጣን ሳይሆን የነጹ መሆን አለመሆናቸውን መመርመርና የነጻውን ነጽቷል ብሎ ማወጅ ነበር። እንዲህም ሆኖ ግን ካህናት ምን ያህል ይከበሩ እንደነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ይቻላል። የዘመነ ሐዲስ ካህናት ግን ሥልጣን የተቀበሉት በሥጋ ለምጽ ላይ ሳይሆን በነፍስ ለምጽ ላይ ነው፤ ከተመለከቱ በኋላ ንጹሕ መሆን አለመሆኑን ሳይሆን በእርግጥና በፍጹም ለማንጻት ነው” (በእንተ ክህነት፣ ገጽ፶፭) በማለት ይገልጻል። ሊቁ ከዚህ አያይዞም “የብሉይ ኪዳኑ ክህነት እንዲህ ይከበር ነበር። ነገር ግን ለሥልጣኑ ከመቅናት የተነሣ ዳታንና አቤሮን በማይገባ መንገድ በመሻታቸው መቅሠፍት ደርሶባቸዋል። የብሉይ ኪዳኑ ክህነት መቅሠፍት ካመጣ የሐዲስ ኪዳኑን ክህነት መናቅማ ምን ያህል የባሰ መቅሠፍት ሊያመጣ ይችላል “ በማለት በአጽንዖት ያስረዳል። (ዝኒ ከማሁ) የሐዲስ ኪዳን ክህነት ከሥጋም ከነፍስም ደዌ ይፈውሳል። የብሉይ ኪዳን ክህነት ከሥጋ ደዌ መፈወስን ለማወጅ ብቻ ክብር ከነበረው የሐዲስ ኪዳን ክህነት ደግሞ ከሥጋም ከነፍስም ደዌ የሚፈውስ ነውና እጅግ ሊከበር ይገባዋል። የተከበረም ነው።  ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ “ክብር የሚገባውንም አክብሩ” (ሮሜ ፲፫፥፯) በማለት እንደገለጸው ክህነት ክብር የሚገባው ስለሆነ እግዚአብሔርም አክብሮታል፤ ሐዋርያትም አክብረውታል፤ ሊቃውንትም አምልተውና አስፍተው ክብር እንደሚገባው ጽፈዋል፤ አስተምረዋልም። ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የካህናትን ክብርና መዓርግ በተመለከተ “ዝኬ ውእቱ ኪዳነ ቃልከ ዘታወሥኦሙ ለካህናት እንዘ ትብል ጼዉ ለምድር። ዘትቤሎሙ ለካህናት ብርሃኑ ለዓለም። ዘትቤሎሙ ለካህናት አዕይንተ ቤተ ከርስቲያን። ዘትቤሎሙ ለካህናት ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን። ዘትቤሎሙ ለካህናት አምሳለ መላእክት። ነዓኬ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርክ ሕዝበከ ወርስተከ ለዓለመ ዓለም፤ ለካህናት የነገርሃቸው ቃል ኪዳንህ ይህ ነው። የምድር ጨው ናችሁ ብለህ። ካህናትን የዓለሙ ብርሃን ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የቤተ ክርስቲያን መብራት ናችሁ ያልሃቸው። ካህናትን የመላእክት ምሳሌ ናችሁ ያልሃቸው። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሕዝብህንና ርስትህን ለዘለዓለሙ ትባርክ ዘንድ ና” (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ) በማለት ያስረዳል። ሊቁ የካህናትን ክብር በተመለከተ የተናገረውንና የክብራቸው መገለጫ የሆኑ ነጥቦችን ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው። ቃል ኪዳን፡- ቃል ኪዳን በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የስምምነት ውል ነው። ይህን በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ኪዳን በቁሙ ውል ቁም ነገር፣ የፍቅርና የአንድነት መሐላ፣ ሰላማዊ ሕግ፣ ሁለቱን ወገን አንድ የሚያደርግ፣ ስለረብና ስለ ጥቅም በተስፋ የቆመ የተጣፈ ሥርዓት፣ ቢያፈርሱት ጉዳትና ጠብ የሚያመጣ ጥቅም የሚያሳጣ” (፭፻፳፱) በማለት ያስረዳሉ። ይህ በሁለቱ መካከል የሚደረገው ቃል ኪዳን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በካህናት መካከል በተለየ መልኩ ተደርጓል። ይህ ልዩ ቃል ኪዳን ደግሞ ዘለዓለማዊ የሆነና ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት የክህነት አገልግሎት ነው። ይህን ቃል ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሐዋርያት  “እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ። ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” (ማቴ. ፳፰፥፲፱-፳) በማለት አስረድቶናል። ይህ ቃል ኪዳን ጽኑዕ ነው። እግዚአብሔር ለካህናት የሰጣቸው ጽኑዕ ቃል ኪዳን የካህናትን ክብር የሚያመለክት ነው። ሰው ከባለሥልጣን ጋር፣ ከባለሀብት ጋር፣ ታላላቅ እና ዝነኛ ከሚባሉ ሰዎች ጋር ሲሆን ለራሱም ክብር ይሰማዋል፤ በሰው ዘንድም ይከበራል። ካህናትን እግዚአብሔር የገባላቸው ቃል ኪዳን “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” የሚል ነው። ሰው ከሰዎች ጋር ሆኖ ከተከበረ እግዚአብሔር በዘመኑ ሁሉ አብሮት ያለማ እንዴት አብዝቶ ይከበር? ስለዚህ የክህነት አገልግሎት እጅግ ክቡር ነው። በክህነት አገልግሎት የሚኖሩት አካላትም እንዲሁ እጅግ የከበሩ ናቸው። ቃል ኪዳን የሚጠብቁትን ይጠብቃል የማይጠብቁትን ደግሞ ያጠፋል፡፡ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ፈለግሁ፡፡ ባንድ ወቅት ዳክየ እና እባብ ባልነጀርነት አበጅተው ሲኖሩ ወደአንድ ቦታ መሄድ ፈለጉና ጉዞአቸውን ሲጀምሩ ከመንገድ ላይ ታላቅ ወንዝ አገኙ፡፡ ይህን ወንዝ ዳክየ መሻገር ትችላለች እባብ ግን መሻገር አይችልም፡፡ ስለዚህ ጓደኝነታቸውን ተጠቅመው በመካከላቸው አንድ ቃል ኪዳን አስቀመጡ፡፡ ይህም ዳክየ አዝላ ልታሻግር እባብም ላይተናኮላት (ላይነክሳት) ነበር ፡፡ በዚህ ቃል ኪዳን ተስማምተው ጉዟቸውን እንደጀመሩ ከመሀል ወንዝ ላይ እባብ ዳክየን ነከሳት፡፡ በዚህ ጊዜ ምን ብለህ ነበር ስትለው የቀረብኩትን ሁሉ መንከስ ልማድ ሆኖብኝ አላስችልህ ብሎኝ ነው አለ፡፡ ግን በሚገርም ሁኔታ የተነከሰችው ዳክየ መዋኘት አልችል ብላ ስትጠልቅ እባብም አብሮ ጠልቆ ሞተ፡፡ ስለዚህ ቃል ኪዳኑን ባለመጠበቁ የራሱ መሞትና መጥፋት ሳያንሰው ያዘለችውንም አጥፍቷል፡፡ ስለዚህ ቃል ኪዳን ቢጠብቁት ይጠብቃልና ይህ የቃል ኪዳን ምልክት የሆነውና የምግብ ሁሉ ማጣፈጫ የሆነው ጨው በውስጣችሁ ይኑር ተብለናል፡፡ ይህም ቃል ኪዳናችሁን እስከመጨረሻው ጠብቁ ሲለን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ከካህናት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ቢጠብቁት የሚጠብቅ፣ ክብር የሚያድል፣ ባይጠብቁት ደግሞ ፍርድ የሚያመጣ ነው። የምድር ጨው፡- የጨውን ምንነት በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው ‹‹አሽቦ፣ አሞሌ፣ በቈላ፣ በበረሓ ከውኃማ መሬት የሚገኝ፤ በውኃ የሚቀልጥ፣ የሚሟሟ፤ መጣጣ ሖምጣጣ መባልዕትን የሚያጣፍጥ፣ ከሁሉ ገብ፣ በብዙ ወገን የሚፈለግ›› (ገጽ ፯፻፶፪) በማለት ያብራሩታል፡፡ እንደ ኪዳነ ወልድ አገላለጽ የሚጣፍጥ ብቻ ሳይሆን የሚያጣፍጥ፣ በብዙ ወገን የሚፈለግ ማለት በብዙ ወገን የሚሠራ የምግብ ዓይነትን የሚያሳምር፣ ምግብ ለሚያሻቸው ፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፡፡ ጨው በሰዎች ሕይወት ላይ ታላቅ ቦታ ያለው ነው፡፡ ማንኛውም ነገር ለሥጋዊ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ በሆነ ቊጥር ለመንፈሳዊ ሕወት አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮችም፣ ማነጻጸሪያ እየሆነ ይጠቀሳል፡፡ ጨውም በሰዎች ሥጋዊ ሕይወት ላይ ካለው ታላቅ ቦታ አንጻር ለመንፈሳዊው ሕወትም ምሳሌ እየሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ጨው ለምግበ ሥጋ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን ያደለን ታላቅ ሥጦታም ነው፡፡ መራራውን ከምሬቱ፣ የጎመዘዘውን ከጎምዛዛነቱ፣ አልጫውንም ከአልጫነቱ አውጥቶ ጣዕምና ለዛ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ ጨው ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውል ነበር፡፡ የተወሰኑትን እናንሣና ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ ጋርም ምን ያህል ግንኙነት እንዳለው እንመለከታለን። ሀ.ለመድኃኒትነት፡- ጨው በቁስል ውስጥ ተፈጥረው ቁስልን የሚያባብሱና ቁስሉ እያምረቀዘ እንዳይደርቅ የሚያደርጉ ነፍሳትን ያጠፋል፤ የቆሰለውንም ያደርቃል፡፡ የጨውን መድኃኒትነት የተረዱ ሰዎች በሥራ ላይ እያሉ ስለት ሲቆርጣቸው በፍጥነት በቁስሉ ላይ ጨው ያስሩበታል፡፡ ቁስሉም በፍጥነት ይደርቃል፡፡ ‹‹በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልታተበም፤ ንጹሕ ትሆኝ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም፡፡›› (ሕዝ.፲፮፥፬) በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም በተናገረበት አንቀጹ ምሳሌአዊና ሰውኛ በሆነ ዘይቤአዊ አነጋገር የጨውን መድኃኒትነት ያስረዳል፡፡  ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል የጨውን መድኃኒትነት አስረድቷል። ይህ የጨው መድኃኒትነት በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ያለ እውነታ ነው። እናንተ የዓለም ጨው ናችሁ የተባሉት ካህናት መድኃኒቱን በእጃቸው የያዙ ሲሆኑ የክህነት አገልግሎቱም እንዲሁ ዘለዓለማዊ የሆነ መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ነው። ማንኛውም ሰው ይከበራል ከተባለ አንድ እጅግ አስፈላጊ ነገር በእጁ አለ ማለት ነው። ካህናቱም መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ የሚገኝበት፣ ከእግዚአብሔር የምንገናኝበት ክህነት በእጃቸው ያለ ናቸውና እጅግ ክቡራን ናቸው። ለ. ለመብአነት:- በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የቊርባን መስዋዕት እርሾ የሌለበት እንዲሆን ሲነገራቸው ነገር ግን በጨው የጣፈጠ እንዲሆን ታዝዘዋል፡፡ ይህንም አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቊርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት፤ እርሾ ያለበት ነገር፣ማርም ለእግዚአብሔር ቊርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡም፡፡ የምታቀርቡት ቊርባን ሁሉ በጨው ይጣፍጣል፤ የአምላክህም ቃል ኪዳን ጨው ከቊርባንህ አይጒደል፤ በቊርባናችሁ ሁሉ ላይ ጨው ትጨምራላችሁ፡፡›› (ዘሌ.፪፥፲፩-፲፫) በማለት የጨውን ተፈላጊነትና በብዙ ወገን የሚኖረውን አገልግሎት አስረድቶናል፡፡ ይህንም በማድረጋቸው ቃል ኪዳናቸውን የመጠበቃቸው ምልክት እንደሆነም አስረድቷቸዋል፡፡ የክህነት አገልግሎቱም ሆነ ካህናቱ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የጸና ቃል ኪዳን ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ኢኃደጋ ለምድር እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ምድርን ያለ ካህናትና ያለዲያቆናት አልተዋትም” በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ክህነትን ለካህናቱ ሲሰጥ ካህናቱን ለምእመናን በስጦታነት አድሎናል። በአንጻሩ ደግሞ ካህናቱም ለእግዚአብሔር የተሰጡ ልዩ መባእ ናቸው። ይህ የእግዚአብሔርና የሰው በክህነት አገልግሎትና በካህናት በኩል የሚኖረው ግንኙነት የክህነቱን ክብር እጅግ ከፍ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሁሉ የሚቻለው አምላክ ከሰው ጋር ለመገናኘት የመረጠው መልካም መንገድ የክህነት አገልግሎት መሆኑ ነው። ካህናቱም ከሰው ተለይተው ለዚህ አገልግሎት የተመረጡ ሥራቸው እግዚአብሔርን ማገልገል ሆኖላቸው እንዲኖሩ ለጊዜው በወላጆቻቸው አቅራቢነት በዋናነት ግን በእግዚአብሔር ልዩ ምርጫ ለዚህ አገልግሎት የተለዩ አካላት ናቸው። ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ ከመሰጠት በላይ ክብር ስለሌለ እነሱም የተከበሩ ናቸው እነርሱ የተመረጡለት አግልግሎትም እንዲሁ ክቡር ነው። ሐ.ለምግብ  ማጣፈጫነት፡- ጨው የሌለው ምግብ ሊጣፍጥ አይችልም፡፡ ስለዚህም ምግብ ሲሠራ ያለ ጨው አይሠራም፡፡ በመጽሐፈ ኢዮብም ‹‹በቊጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ የክትክታ ሥር ደግሞ ምግባቸው ነው፡፡›› (ኢዮ.፴፥፬) በማለት ሁሉም እጅግ የሚፈልገውና ለሕይወቱም አስፈላጊ እንደሆነ ተጽፎልናል፡፡ በተፈጥሮ ጨውነት ያላቸውን ዕፅዋት እንስሳትም ሰዎችም ሳይቀሩ አብዝተው ይፈልጓቸዋል፡፡ ከብት የሚጠብቁ እረኞች በሜዳ ሲውሉ ከቋጠሩት ምግብ ይልቅ ጨው ጨው የሚሉትን ዕፅዋትና አትክልት ይፈልጓቸዋል፡፡ ስለዚህም ምግቡ ያለጨው አይሠራም ቢሠራም አይጣፍጥም ‹‹ምግብ ያለጨው ይበላልን የጎመን ዘር ጭማቂስ ይጣፍጣልን›› (ኢዮ.፮፥፮) በማለት ጻድቁ ኢዮብ የጨውን አስፈላጊነት ያስረዳናል፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ያለ ጨው የተዘጋጀ ምግብ ጭራሽ እንዳማይበላ ነው የነገረን፡፡ ምክንያቱም ስለማይጣፍጥ ነው፡፡ መራራውን የሚያጣፍጥ፣ የጎመዘዘውን የሚያለስልስ መሆኑንም ሰዎች ስለተረዱ ምግባቸውን ያለ ጨው አይሠሩትም፡፡ ሥጋዊው ምግብ ያለ ጨው  እንደማይጣፍጥ ሁሉ መንፈሳዊው ሕይወታችን ያለክህነት አገልግሎትና ያለ ካህናት አይጣፍጥም። ይህንም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስረዳ  “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን እንግዲህ በምን ይጣፍጣል? እንግዲህ የሚጠቅመው የለም፤ ሰዎች ወደውጭ አውጥተው የጥሉታል፤ በእግራቸውም ይረግጡታል እንጂ።” (ማቴ. ፭፥፲፫) በማለት አስተማረ። በአበው ብሂልም ‹‹ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ጨው ቢያልጥ በምን ያጣፍጡ›› ተብሎ ይነገርለታል፡፡  ካህናት የሰው ሕይወት የሚጣፍጥበት ጨው ናቸው። የሰውን ልጅ መክረው አስተምረው ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለስ የሚያደርጉ፤ አልጫ የሆነውን ዓለም አጣፍጠው ለመንግሥተ ሰማያት እንዲገባ የሚያደርጉ ናቸው። ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት የወረደው ከድንግል ማርያም የተወለደው ያን ሁሉ መከራ የተቀበለው የሰውን ልጅ ለማዳን ነው። ካህናትም የተመረጡት የሰው ልጅ ድኅነትን ያገኝ ዘንድ ነው። ለዚህ አገልግሎት ከመመረጥ በላይ ክብር የለምና አገልጋዮችም እጅግ የተከበሩ ናቸው። አገልግሎቱም እንዲሁ የከበረ ነው።  መ. በጠላት ጦር የተያዘ መሬት ላይ ይጣላል፡- ጨው በብዙ ወገን ተፈላጊ ነው ብለናል እና ሰዎች በማጣፈጫነት እንደሚጠቀሙበት ሁሉ ለማድረቂያነትና ምድርን ወና ለማድረግም ይጠቀሙበታል፡፡ ጨው የተጨመረበት መሬት ወና ይሆናል እንጂ እህል አያበቅልም። ጠላትን ድል ለማድረግ ኃይሉን አሳጥቶ፣ ሀብት ንብረቱን ወርሶ፣ አስጨንቆ ነውና መሬቱ ላይ ጨው በማድረግ መሬቱ እንዳያበቅል በማድረግ ይጠቀሙበታል። ሰለዚህ ሰዎች ጠላትን ድል ለማድረግ ከሚጠቀሙበት የጦር መሳሪያም አንዱ በመሆን ያገለግላል፡፡  ጨው የጠላት ድል መንሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ሁሉ ካህናቱና የክህነት አገልግሎቱም ጠላት ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት ታላቅ መሣሪያ ነው። ኃጢአት ቢሠሩ ንስሓ ገብተው ዲያብሎስን ያሳፍሩበታል። በተረፈ ቄርሎስ እና በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ እንደተገለጸው  እኩይ ፍልስጣ ዕለት ዕለት እየተከታተለ የሚጽፈውን ኃጢአታችንን ካህናቱ ፊት ቀርበን ስንናዘዝ እንደ ቅርፊት እየተላጠ ይወድቅልናልና ምእመናን ድል ይነሱበታል። ክብሩም ለምእመናንም ሆነ ለካህናት የጠላት ድል መንሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ መሆኑ ነው። (ተረፈ ቄርሎስ ፲፱፥፩-፬)  የዓለሙ ብርሃን፡- የብርሃንን ምንነት በተመለከተ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው “መምህር፣ አብነት፣ መፈክር፣ መተርጕም፣ ገልጦ የሚያስረዳ” በማለት ይገልጹትና አያይዘውም አብርሀ የሚለውን “አበራ፣ አስበራ፣ አሳየ፣ ገለጠ፣ አስረዳ” (ገጽ ፪፻፹፯) በማለት ያብራሩታል።  ስለዚህ ካህን የዓለም ብርሃን ነው ሲባል በጨለማ፣ በድንቁርና፣ ባለማወቅ ወዘተ የሚኖርን ሕዝብ ወደ ብርሃን የሚወስድ፣ ካለማወቅ ወደማወቅ የሚያሸጋግር ማለት ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ሲያስረዳን ለሐዋርያት የነገራቸው “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። ከእንቅብ በታች ሊያኖሯት መብራትን አያኖሩም፤ በመቅረዝዋ ላይ አኑረዋት በቤት ላሉት ሁሉ ታበራለች እንጂ። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ.፭፥፲፬-፲፮) በማለት ነው። በድንቁርና ዓለም ለሚኖረው ዕውቀትን፣ ባለማወቅ ጨለማ ለተዋጠው ብርሃን ትሆኑታላችሁ ሲል ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መሻገሪያ የሚሆኑበትን ሥልጣነ ክህነት ሰጣቸው። ትልቁ ክብር የሚባለውም ይህ ነው። መብራት እንደሚታወቀው ራሱ እየቀለጠ፣ በእሳት እየነደደ ለሰው ግን ብርሃኑን ይለግሳል። ካህናት ሥራቸው ለራሳቸው ምድራዊና ጊዜያዊ ጥቅም ሳይኖራቸው ራሳቸውን በተጋድሎና በመከራ እያኖሩ ሰውን ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ማስገባት ነው። ሰውን ከማዳን ፣ ሰውን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከማሸጋገር፣ ለሰው ምክንያተ ድኅነት ከመሆን በላይ ክብር ስለሌለ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያከበራቸው በእንደዚህ ያለው ሀብትና ጸጋ ነው። የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፡- ካህናት የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፣ እንዲሁም አዕይንተ እግዚአብሔር  ተብለዋል። “የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው ዐይንህ ብሩ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ነው፤ ዐይንህ ታማሚ ቢሆን ግን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ነው።“ (ሉቃ.፲፩፥፴፬) በማለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው ካህናት የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች ናቸው ሲባል ምን ያህል ታላቅ ክብር እንዳላቸው እንድንረዳ ነው። የሰውነት ክፍሎቻችን እርስ በእርሳቸው ተረዳድተው ይኖራሉ አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም። አንዱ ሌላውን አልፈልግም ሊል አይችልም። የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን ብዙ የአካል ብልቶች አሏት። ለሰውነት ክፍሎቻችን ብርሃኑ ዐይን እንደሆነ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎችም ካህናት ዐይኖች ናቸው። ለዚህ ነው የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች በማለት ሊቁ የገለጻቸው።  የቤተ ክርስቲያን መብራት፡- በጸሎተ ቅዳሴያችን “ተውህቦ መራኁት ለአቡነ ጴጥሮስ ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልእክት ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን፤ ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው፤ ለዮሐንስ ደግሞ ድንግልና ተሰጠው፤ ለጳውሎስም መልእክት ተሰጠው የቤተ ክርስቲያን መብራት ነውና” ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። በጸናውና በጎላው ሲነገር ይኖራል። ቅዱስ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ፣ ለቅዱስ የሐንስ ድንግልናን፣ ለቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ መልእክት ተሰጣቸው እያለች ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዳቸው ጎልቶ የሚታየውን አገልግሎት በማንሣት ስታመሰግናቸው ትኖራለች። የሐዋርያት ተከታይ የሆኑት ካህናትም በዚህ ድንቅና ግሩም አገልግሎታቸው የቤተ ክርስቲያን መብራት ተብለዋል።  የመላእክት አምሳል፡- ካህናት ለመላእክትም ያልተሰጣቸውን ልዩ የአገልግሎት ጸጋ እንደተሰጣቸው ከላይ ተመልክተናል። እንዲሁ በዚህም ክፍል ላይ ሊቁ የመላእክት አምሳል በሏቸዋልና የሰውን ልጅ ወደ እግዚአብሔር በማድረስና ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ አገልግሎት የሚኖሩ ስለሆኑ እንደ መላእክት ናቸው ተብለዋል። ክብር ማለት ደግሞ ይህ ነው ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ግን የመላእክት አምሳል መባል ታላቅ ክብር ነውና።  ከላይ የተዘረዘሩት የካህናትንና የክህነት አገልግሎትን እጅግ ክቡርነት የሚያስረዱን ናቸው። ጉዳዩን በጥልቀት እንድንረዳው ይረዳን ዘንድ ተጨማሪ ማስረጃ ከሊቃውንትም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት። ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው “የካህኑን ምክሩን፣ ትእዛዙን፣ ተግሣጹን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና፤ የነፍስን ደዌ የሚያርቅ ይቅርና የሥጋ በሽታ የሚያድን ባለመድኃኒትስ ወደ ሥጋዊ በሽተኛ በመጣ ጊዜ ለመድኃኒቱ ከማይስማሙ ምግቦችን ከመመገብ ይከለከል ዘንድ ያዝዘዋል፤ መራራ መራራ ቅጠልን ፣ምረቱ ጭንቅ ሽታው ክፉ የሚሆን ከብዙ ወገን የተቀመመ መድኃኒትን ያጠጣዋል፡፡ በድውዩ አካል የተለያየ ሕዋሳትን አንድ ያደርግለት ዘንድ፡፡ (ሃ.አበ.፴፯፥፫)  ምእመናኑ ለካህናት የሚኖራቸው ክብር እጅግ ከፍተኛ መሆን እንዳለባቸው የሚያስረዳን  ነው። ይህ ባይሆን ግን ቅጣት እንደሚያስከትል በመጽሐፍ ቅዱስ በተመዘገቡ ታሪኮች መረዳት እንችላለን። ለማሳያ ያህል የተወሰኑትን እንመልከት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ስለዚህ እላችኋለሁ ለሰው ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ ግን አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገር ግን በዚህ ዓለምም ቢሆን በሚመጣውም ዓለም ቢሆን አይሰረይለትም” (ማቴ.፲፪፥፴፩-፴፪) በማለት አስተምሯል። ይህ ቃል በድጋሚ “በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለምም ቢሆን በሚመጣው ዓለምም አይሰረይለትም” (ሉቃ.፲፪፥፲) ተብሎ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ክፍለ ምንባቦች በብዙ መንገድ የሚተረጎሙ ናቸው። የመጀመሪያው ትርጓሜ የሰውን ልጅ የሰደበ ማለት ወልድን ዕሩቅ ብእሲ ያለ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን ዕሩቅ ብእሲ ያለ ግን አይሰረይለትም ማለት ነው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የኃጢአቱን ክብደት ለማነጻጸር እንጂ ይቅር የማይባል ኃጢያት አለ ማለት አይደለም። ኃጢአቱንም ያበላለጠበት ምክንያት ወልድን ምንም እንኳ እንዲህ ማለት ይገባል ማለት ባይሆንም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለታየ ምክንያት አላቸው መንፈስ ቅዱስን ግን ዕሩቅ ብእሲ ለማለት ምንም ምክንያት የለምና። ሰውን እንኳ በምክንያት መስደብ አግባብ ባይሆንም ያለምክንያት መስደብ እጅግ ኃጢያት ነው። ስለዚህ ኃጢያቱን ከኃጢያት እያከበደ የሚያስተምረን እኛ እንድንረዳው ነው።  እንደዚሁ ሁሉ በቀጥታ ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ ጋር የሚገናኘውን ትርጓሜ ለማንሣት ያህል ምእመንን የሰደበ ይሰረይለታል፤ ካህንን የሰደበ ግን አይሰረይለትም ማለት ነው። እንዲህ ያለበት ምክንያት በፍጹም ስርየተ ኃጢያት የለም ማለት አይደለም የኃጢያቱን ክብደት ለመግለጽ እንጂ። ይህም የክህነትን እጅግ የከበረ ሥልጣንነት ያስረዳል። በሚታየው ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ሥልጣን ሰጥቷቸዋልና ካህናት ሊከበሩ ይገባል ሲለን ነው።  በትንቢተ ኢሳይያስ በትርጓሜው ተጽፎ እንደምናገኘው በንጉሡ በዖዝያን ዘመን ካህኑ አዛርያስ ከንጉሡ ቀኝ እየተቀመጠ ፍርዱን ይገሥበታል (ይሽርበታል)። በዚህ ጊዜ ለምን ትገሥብኛለህ? ብሎ ሲጠይቀው “እምቤተ መንግሥት የዐቢ ክህነት፤ ከቤተ መንግሥት ክህነት ይበልጣል” ይልብሀልና ይገባኛል በማለት ይመልስለታል። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በአባቴ ከቤተ መንግሥት ብወለድ በእናቴ ከቤተ ክህነት እወለድ የለምን? በማለት ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊያጥን ገባ። ልምፅ ወጣበት፤ ከቤተ መቅስ አስወጥተው በአይሁድ ባህል ለምፃም ለንግሥና አይሆንም ነበርና ከከተማ አውጥተው በግዞት ድውያን ከሚኖሩበት ቦታ አስቀመጡት። በዚህ ጊዜ በዘመኑ የነበረው ነቢይ ኢሳይያስ ሳይገሥጽ በመቅረቱ በእርሱም ላይ ለምፅ ወጣበት፤ ሀብተ ትንቢቱም ተነሣው። (ኢሳ. ፮፥፩ አንድምታ ትርጓሜ) በአጠቃላይ የምድር ጨው፣ የዓለሙ ብርሃን፣ የቤተ ክርስቲያን ዐይኖች፣ የመላእክት አምሳል ወዘተ መባል ምንም እንኳ ክብሩ ሲበዛ ኃላፊነቱም እንዲሁ የሚበዛ ቢሆንም እጅግ የተለየ ክብር ማግኘት ነው። በዚህ ዓለም ስንኖር ጨው፣ ብርሃን፣ ዓይን ምን ዓይነት አገልግሎትና ጠቀሜታ እንዳላቸው መረዳት ቀላል አይደለም። ለሰውነታችንም እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። ካህናትም እንዲሁ ከእግዚአብሔር አምላካችን ከምናገኘው ልጅነት ጀምሮ ተስፋ የምናደርጋትን መንግሥተ ሰማያትን እስከ መውረስ ድረስ በሚኖረን ህልውና እጅግ ወሳኝና አስፈላጊዎቻችን ናቸው። ይህ ማለት መንግሥተ ሰማያትን ከወረስን በኋላ አገልግሎታቸውና ክብራቸው ያበቃለታል ማለት አይደለም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደገለጸውና ከላይም እንደጠቀስነው አገልግሎታቸው ሰማያዊ ነውና የሚያልፍ አገልግሎት የላቸውም። ስለዚህ ምንም እንኳን የካህናትንም ሆነ የክህነቱን  ክብር በዚህ አጭር ጽሑፍ አጠናቅቆ መግለጽ ይቻላል ባይባልም በጥቂቱም ቢሆን እንድንረዳው በዚህ መንገድ ተመልክተነዋል። በሚቀጥለው ኃላፊነቱን በተመለከተ እንመለከታለን እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ሰጥቶ ቀጣዩን ለማየት ያብቃን አሜን።   
Read 1167 times