Wednesday, 07 April 2021 00:00

አሐቲ ቤተ ክርስቲያን

Written by  ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ እንደሰበከው
ውድ አንባብያን በዚህ ዓምድ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ነገ ምን መሆን እንዳለባት የሚያሳይ፣  ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባል ቤተ ክርስቲያን ልትደርስበት የሚገባትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ልማታዊ አቅጣጫዎችን ማሳየት፣ ትውልዱም የድርሻውን እንዲወጣ ማመላከት ነው። በመሆኑም አስቀድመን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን በተከታታይ አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ።  እንደ እግዚአብሔር ቸርነት በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው "አሐቲ ቤተ ክርስቲያን፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፤" የሚል ይሆናል።

 

በዘወትር ጸሎታችን አንድ አማኝ በየዕለቱ ምስክርነት የሚሰጥባቸው እምነቶች አሉት። ማንኛውም ክርስቲያን በቀኖናችንና በታዘዘው መሠረት ጸሎት የሚጸልይ ከሆነ ጸሎተ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጸሎት) የምንለውን ጸሎት ሳይጸልይ ሊውል አይችልም። ሌሎች ጸሎቶች እንኳን ከደረሱ በኋላ መጨረሻ የሚጸለየው ጸሎተ ሃይማኖት ነው። ይህ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ትእዛዝ ነው። ይህ የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው ስንል ጸሎተ ሃይማኖት እንዳለ ተአምኖ ሃይማኖት ስለ ኾነ ነው። የምናምነውን እምነት የምንመሰክርበት ክፍል ነውና፤ "ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ፤" የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ሁሉ በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ከዚያ በኋላ ደግሞ "ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ. . ." እያልን እንቀጥላለን። "ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ . . ." እንላለን። "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት፤" በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን። 

እነዚህም አሥራ ሁለት አንቀጾች ናቸው፤ እናምናለን፥ እናምናለን፥ እናምናለን እያልን አሥራ ሁለቱን እንገልጻለን። በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ደግሞ በሰፊው በተለይ በሐዋርያት አመክንዮ ብዙዎቹን የምናምናቸውን ነገሮች እየዘረዘርን እናምናለን፥ እያልን የምናምነውን እየገለጽን በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን፤ አንድ እንሆናለን፤ እንተሳሰራለን። በዚህ መንገድ ከምንገልጻቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ "ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት፤" ሐዋርያት በሰበሰቧት፣ ከሁሉም በላይ በሆነች (በምትበልጠው)፣ በአንዲት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። እንላለን። በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የማመን ጉዳይ በአንድ አብ እንደምናምነው፣ በአንድ ወልድም እንደምናምነው፣ በአንድ መንፈስ ቅዱስ፣ በሦስት አካላት፣ በሦስት ስም፣ በሦስት ግብር፣ በአንድ ባሕርይ፣ በአንድ አገዛዝ፣ በአንድ መለኮት፣ በአንድ አምላክ፣ እንደምናምነው ነው። እግዚአብሔር ወልድ በደሙ በመሠረታት ከሁሉም በላይ በምትሆን በአንዲት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን። ይህን ምስክርነት እየሰጠን ሁል ጊዜ እንጸልየዋለን። ቢያንስ በጋራ ጸሎት ጊዜ፣ በቅዳሴውም ጊዜ፣ በሌላኛውም ጊዜ፣ እንጸልየዋለን። 

በአብ ማመን በወልድ ማመን፣ በመንፈስ ቅዱስ  ማመን ምን ማለት እንደሆነ እናውቅ ይሆናል። ወይም በተሻለ መጠን ተምረን ይሆናል። ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ ስንወጣ በጣም የምንቸገርበት መሠረታዊ ችግር ይህ እምነት ምን እንደሆነ አለማወቅ ነው። ይህን ካለማወቅ የተነሣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የፖለቲካ ልዩነትም ኾነ ሌላም ጸብ ሲኖራቸው፣ የተለያየ ልዩነት ሲያጋጥማቸው፣ በቤተ ክርስቲያንም ይለያያሉ። እንደሚታወቀው  በውጭ ሀገር ሁለት ቄስ የግድ አያስፈልግም፤ አንድ ቄስና አንድ ዲያቆን ካሉ የፈለጉ ምእመናን ተሰባስበው አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይከፍታሉ። እነዚህን ችግሮች ስናያቸው አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ላይ ነች። ይህ ፈተና ከምን የመነጨ ነው? የሚለውን ስናነሣው በእኔ ግምትና መረዳት መሠረታዊ ችግሩ ቤተ ክርስቲያን የምንላትን አካል በደንብ አለማወቅ ይመስላል። ርእሳችን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ይቺ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት፤ ኩላዊት ናት፤ የሁሉም ናት፤ ከሁሉም በላይ ናት፤ ሐዋርያዊት ናት፤ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው የምናምነው። "እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት፤" ብለን የገለጽነው እሱን ነው። ከዚህ በመነሣት ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን።

፩. የቤተ ክርስቲያን ምንነት 

በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው? እንደምታውቁት ኦርቶዶክስ ያልሆኑ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች አሉ። እነርሱ ቤተ ክርስቲያን ሲሉና እኛ ቤተ ክርስቲያን ስንል ልዩነት አለው? ወይስ የለውም? መሠረታዊ ልዩነት ነው ያለው። በተለይ በምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖችና በምሥራቁ ዓለም ክርስቲኖች መካከል ካሉት መሠረታዊ ልዩነቶች አንዱና ዋናው ይህ ነው። ቤተ ክርስቲያን የምንላትን አካል በማወቅ ረገድ ለምሳሌ የፕሮቴስታንቱ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚለው አንድ ጉባኤ ላይ አንድ አዳራሽ ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ የተሰባሰቡትን የሰዎች አንድነት ኅብረት ድምር ነው። በኦርቶዶክስ ግን ቤተ ክርስቲያን የምትባለው እንደዚህ አይደለም፤ ያለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንልምና። ክርስቶስ ራስ የሆነላት፣ ተጋድሏቸውን ፈጽመው አሁን በአጸደ ነፍሳት ያሉ ቅዱሳንና በምድር ያለን የኛ የምእመናን አንድነት ነው ቤተ ክርስቲያን የሚባለው። እዚህ ያለነው ስብስብ ብቻ ማለት አይደለም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየትም ቦታ ያሉ፣ ርትዕት በሆነች ሃይማኖት አምነው የሚጓዙ፣ ተጋድሏቸውን ያልፈጸሙ ምእመናንና ተጋድሏቸውን ፈጽመው፣ በአጸደ ነፍስ በገነት ያሉ ቅዱሳን አንድነት ናት። ሁለቱ አይለያዩም፤ በአጸደ ነፍስ ያሉትም ከኛ ጋር አንድነት አላቸው። እኛም ከእነሱ ጋር አንድነት አለን። ይህን ሐሳብ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በተለይ በደንብ መረዳት አለባችው። 

ከፕሮቴስታንቱ ዓለም ጋር አንዱ ልዩነታችን ቅዱሳን ያማልዳሉ፥ አያማልዱም የሚለው ነጥብ ነው። እውነት ለመናገር ለእነርሱ በአጸደ ነፍስ ያሉት፣ በሌላ ዓለም ያሉ፣ ሌሎች አካላት ተደርገው ነው የሚታሰቡት። ለኛ ግን ሌሎች አይደሉም፤ እነርሱም የክርስቶስ አካላት ናቸው። እኛም የክርስቶስ አካላት ነን። ክርስቶስ ደግሞ ስንት አካላት ነው ያለው? አንድ አካል ነው፤ እርሱ አንድ እውነተኛ የወይን ግንድ ነው። እኛ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ነን፤ እናም ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ሁለት አይደለችም። በገነት ያለችው ሌላ፣ በሰማይ ያለችው ሌላ፣ በምድር ያለችው ሌላ አይባልም። ቤተ ክርስቲያን የምትባለው የእነዚህና የሁላችን አንድነት ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌ.፪፥፳-፳፪ ላይ "በሐዋርያት እና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።" ይላል። በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ያለው ከነማን ጋር ነው? ብለን ስንጠይቅ፥ መልሱ ‘ተጋድሏቸውን ከፈጸሙ ቅዱሳን ጋር’ የሚል ነው። የማዕዘኑም ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የተመሠረትነው በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ሁሉ አንድነት ናት። እኛ አሁን በመንፈስ እንሠራለን፤ ተጋድሏችንን ፈጽመንም ወደ እነርሱ ሄደንም (በአጸደ ነፍስ) መቀላቀል እንሻለን፤ እንፈልጋለን። የጉዞው ዓላማም ይህ ነው፤ ስንጾም፣ ስንዘምር፣ ስናመሰግን፣ ስንጸልይ በመንፈስ ነው አብረን የምንሠራው። 

ይህን አንድነት የሚያስረዱ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ፩ እስከ ፰ እሱ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ተካዩም አባቴ ነው፥ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ።" እኛ በዚህ የወይን ግንድ ላይ ያለን ቅርንጫፎች ነን። በሰማይ ያሉ ቅርንጫፎች አሉ፤ በምድር ያሉ ቅርንጫፎች አለን። የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ይህን በደንብ አድርጎ አብራርቶ ተናግሯል።  ከተናገረው ለማሳያ ብናነሣ "እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ፤" እያለ የዘመረው አለ። ምሳሌው የቤተ ክርስቲያን ነው፤ ግንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። "እንተ በምድር ሥረዊሃ፤" ሥሮቿ በምድር ያሉ፤ "ወበሰማይ አዕጹቂሃ፤"  ቅርንጫፎቿ ደግሞ በሰማይ ያሉ፤ አንድ የወይን ሐረግ ቤተ ክርስቲያን ናት እንላለን። ለእመቤታችንም መስለው የዜማ መምህራን ይዘምሩታል። እመቤታችንም  የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፤ ግንዱ አንድ ነው፤ ያ የወይን ግንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በሰማይ ያለ ቅርንጫፍ አለ፤ በምድር ያለን ሥር ተብለን የተገለጽን ቅርንጫፎች ወይም ሥሮች አለን። መሠረታዊው ሐሳብ ይህ ነው፤ ይህን የሚያረጋግጥ በእኛ አገልግሎት ውስጥ ብዙ ምንባባትና ምስክሮች አሉ፤ ብዙ ተአምራትም አሉ፤ እሱን እንገልጻለን። 

፪. የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት 

የቤተ ክርስቲያን ትርጉሙ የእኛ እና የሰማይ ቅዱሳን አንድነት ከሆነ የቤተ ክርስቲያን ፬ ባሕርያት አሉ። ፩ኛ. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ፪ኛ. ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት፤ ፫ኛ. ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ናት፤ ፬ኛ. ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ነች። በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚያምን ሰው እነዚህን አራቱን ባሕርያት አስተካክሎ ማወቅና ማመን አለበት። በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚፈጠሩ ውዝግቦች መልስ የሚያገኙት አራቱን ባሕርያት ስንረዳ ነው። በቀጣይ እነዚህን ነጥብ በነጥብ እናያለን። 

፩ኛ. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፡- በመጀመሪያ በኤፌሶን ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፬ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የሚለውን ነጥብ ነው የምናየው። ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ የሚለውን ኤፌሶን ፬፥፬ ላይ አንዲት ጥምቀት፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት ይላል። በአንድ እምነት ያለ ጉባኤ ስንት ቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይችላል? ቅዱስ መጽሐፍ  ቤተ ክርስቲያን አንዲት እንደሆነች ያስረዳል።  

በዚህ ረገድ ከሌሎቹ ጋር አሁንም መሠረታዊ ልዩነት አለን። በሌሎችና በእኛ መካከል ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የሚባለው ምን ስትሆን ነው? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ ልዩነት አለ። ለምሳሌ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የምትለው በሮማው ጳጳስ ሥር ስትኖር ብቻ ነው። ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያን አንድነት አስተዳደራዊ (ADMINISTARTIONAL) ይሆናል። በዚያ ሥር የሌለ አይቆጠርም ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያንም ራስ፥ የሁሉ የበላይ ፖፑ ይሆናል ማለት ነው። በኦርቶዶክስ አስተምህሮ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደዚህ አይደለም። ራሳቸውን የቻሉ የግብጽ፣ የአርመን፣ የሶሪያ፣ የሕንድ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ልክ እንደዚህ በእውነተኛይቱ አንዲት ሃይማኖት ያሉ አስተዳደራቸው ግን የተለየ ነው። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ሲኖዶስ አላቸው፤ የራሳቸው ጳጳሳትና ፓትርያርክ አላቸው፤ የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው። አስተዳደሩ ፭ ወይም ፮፤  ፳ም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚገልጸው አንድ አስተዳደር ወይም ዓለም ሁሉ በአንድ ፖፕ ወይም በአንድ ፓትርያርክ መተዳደር አይደለም። ከተቻለ የአስተዳደር አንድነት መልካም ነው፤ ለምሳሌ ዓለም ሁሉ ኦርቶዶክስ ሆኖ በአንድ ፓትርያርክ ቢመራ ችግር ነው ማለት አይደለም። ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርጋት ግን አስተዳደር ሊኾን አይችልም። 

ቤተ ክርስቲያንን የመሠረታትና አንድ የሚያደርጋት ክርስቶስ ብቻ ነው። እንዴት አድርጎ አንድ ያደርገናል? ለምሳሌ ከላይ የጠቀስናቸው አኀት አብያተ ክርስቲያናት እንዴት ነው አንድ የሚኾኑት? ሁላችንም አንዲት እምነት አምነን፣ አንዲት ጥምቀት ተጠምቀን፣ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል፣ ክርስቶስ በእኛ ሲያድር እኛ ሁላችን የክርስቶስ አካል እንሆናለን። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ራስ የኾነ የክርስቶስ አካላት ይኾናሉ። ሁሉም የወይን ግንዱ የክርስቶስ ቅርንጫፎች ናቸው። ስለዚህ አንድ የሚያደርገን ትልቁ ምስጢር ሥጋ ወደሙ ነው። በአንዲት ሃይማኖት፣ በአንዲት ጥምቀት፣ በአንድ ሥርዓት ተፈጽሞ፣ አንድ ሥጋ ወደሙ ስንቀበል  አንዲት አካልነታችን ይረጋገጣል። ክርስቲያኖች የትም ምድር ቢኖሩ አንድ የሚያደርጋቸው ወይም ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርጋት የወይኑ ግንድ የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። ክርስቲያኖች ቅርንጫፍ የምንሆነው እኛ የእሱን ሥጋና ደም ስንበላና ስንጠጣ እርሱ በእኛ ሲያድር እኛም በእርሱ ስንሆን በአንዱ ክርስቶስ ሁላችንም አንድ ግንድ ላይ የተተከልን ቅርንጫፎች ስንኾን አንድ እንኾናለን። 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ቁጥር ፲፭-፲፯ ላይ እንዲህ ይላል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ። የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ ድምጼንም ይሰማሉ። አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ፤ ይላል። እረኛው አንድ፤ መንጋውም አንድ፤ ሁለት መንጋ የለም። ሌሎች በረቶች ውስጥ በጎች አሉ፤ ሌሎች ቤተ እምነቶች ውስጥ አሉ። የዋሃን ሰዎች በቅን ሕሊና፥ በንጹሕ ልቡና ሁሉም ትክክለኛ መንገድ መስሎዋቸው እግዚአብሔርን ከልብ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። "እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፤" እንደተባለው፤ እነዚያን ልቦች እግዚአብሔር ያገኛቸዋል። ባገኛቸውም ጊዜ ‘እዛው በረት ውስጥ መሆን ትችላላችሁ አይደለም የሚላቸው፤’ ወደ አንዲቷ በረት ያመጣቸዋል እንጂ። ወደ አንድ እምነት፣ ወደ አንድ ጥምቀት፣ ወደ አንድ ሥጋ ወደሙ ያመጣቸውና አንድ ያደርጋቸዋል። ሁለት በረት የለም፤ ሁለት መንጋ የለም፤ ሁለትም እረኛ የለም፤ እረኛው አንድ፥ መንጋውም አንድ እንጂ። ይህ አንድነት ከላይ እንደተባለው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው። 

የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ሲፈጸሙ፥ በተለይ በቅዳሴ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አንዲትነት ይበልጥ ግልጽ ይኾናል። ይህ ምን ማለት ነው? በጸሎተ ቅዳሴ የምንሳተፈው በአጸደ ሥጋ ያሉ ካህናት፣ ልዑካኑና አስቀዳሾቹ ብቻ አይደሉም። ቅዱሳን በሙሉ ይሳተፋሉ፤ ለማሳያ ያህልም አሐዱ ከመባሉ በፊት ካህኑ "አቤቱ ይህቺ መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ዕለት ምነኛ የምታስፈራ ናት? በማለት ይጸልያል። አስቀድሞ ሥራውን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ መኾኑን መስክሮ ያስረክባል። ሥጋ ወደሙ ሲፈትት፣ ማንኛውንም ነገር ሲያደርግ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ አይደለም የሚያደርገው፤ አንተ አድርገው ነው የሚለው። "ኦ እግዚኦ በከመ አሜሃ ባርክ ወፈትት ወሃብ፤" አቤቱ ጌታዬ ሆይ ያን ጊዜ በጸሎተ ሐሙስ ኅብስቱን፥ ወይኑን ለውጠህ ሥጋህን ደምህን እንዳደረክ ዛሬም ይህን ኅብስትና ወይን አንተ ሥጋህን ደምህን አድርገህ፥ አክብረህ ስጥ ነው፤ የሚለው። ካህናቱ ተሰይመው ሲያገለግሉ የሚለውጠው፥ የሚያከብረው ራሱ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ስላለ የእርሱ የሆኑ ቅዱሳን በሙሉ ደግሞ አሉ። 

በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በእስክንድርያ አባ ብንያም የሚባል ጻድቅ ፓትርያርክ ነበር። የአባ መቃርስ ገዳም አርጅቶ ስለ ነበር እደሳው ተፈጽሞ ቅዳሴ ቤቱን ሲፈጽም፥ መንበሩን ሲባርክ አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይህን መንበር አንተ ባርክ፤ እያለ የሚጸልየውን ጸሎት ጸለየ። በዚህ ጊዜ የበቃ ስለ ነበረ "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ሲያማትብ አየሁ፤" ይላል። በዓይነ ሥጋችን እንኳን ባናየው ሁሉን የሚፈጽመው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ ፓትርያርክ የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን እጅ ሲያየው ደንግጦ ወደቀ። ሲወድቅ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አነሣውና አይዞህ አትፍራ ብሎ አበረታው። ወደ ማዕዘኑ ዘወር ሲል ደግሞ አንድ ጺሙ ዥርግግ ያለ ያማረ ትልቅ አረጋዊ አየ። ልክ ይህን ሲያይ በተመስጦ ውስጥ ሳለ እንዲህ ብሎ አሰበ። በማስተዳድራት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍት ሀገረ ስብከት ቢኖረኝ ይህን ሰው ጳጳስ አድርጌ እሾመው ነበር። ግን ክፍት ሀገረ ስብከት የለኝ ምን አድርጌ ልሹመው? ይህን በሕሊናው ሲያስብ ይላል ታሪኩ ያ ከወደቀበት ያነሣው ቅዱስ ገብርኤል ይህንማ አንተ ልትሾመው አትችልም። እርሱ የፓትርያርኮች ሁሉ አባት አባ መቃርስ ነው፤ ዛሬ ቤተ መቅደሱን ስለምታከብር ስለምትባርክ፥ ጌታም እንዳየኸው በመንበሩ ላይ ስለሚባርክ አብሮ ተገኝቶ ነው፤ አለው። 

ክቡራን አንባብያን አስተዋላችሁን? ስለዚህ ስናስቀድስ የሚያስቀድሱት ቅዱሳን ሁሉ ጭምር ናቸው። የበቁት ያዩዋቸዋል፤ በቅዳሴ ጸሎታችን ላይ "ዝ ውእቱ ጊዜ ባርኮት ወዝ ውእቱ ጊዜ ዕጣን፤" ይህ የማመስገን ጊዜ ነው፤ የዕጣን ጊዜ ነው፤ ብለን እናመሰግናለን። በተጨማሪም "ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፥ ወብስራት ለገብርኤል፤. . . ተውህቦ ልቡና ለዳዊት፥ ተውህቦ ጥበብ ለሰሎሞን፤ እያልን እያንዳንዳቸውን ቅዱሳን እያነሣን ሰጪዉን አክባሪዉን በከበሩት በቅዱሳኑ በኩል እናመሰግነዋለን። በቅዳሴው ጊዜ ዕጣኑን የምናሳርገው እኛ ብቻ አይደለንም፤ እነዚያ ቅዱሳንም ናቸው እንጂ። ይህንን ስለምናውቅ ከእመቤታችን ጀምሮ ቅዱሳንን ሁሉ እናመሰግናለን። መልክአ ቁርባንም ላይ እናነሣቸዋለን፤ "ሰላም ለኪ" ከሚለው ጀምሮ "ሰላም ለክሙ ጻድቃን ወሰማዕት እለ አዕረፍክሙ በሃይማኖት፤"፣ "ሰላም ለክሙ ጻድቃን ዛቲ ዕለት ኵልክሙ፤" እያልን በዚህች  ዕለት ያረፋችሁ ቅዱሳን ሁሉ ለእናንት ሰላምታ ይድረሳችሁ፤ እናንተ ለእኛ ጸልዩልን፤ እያልን እንጠራቸዋለን። እነሱም እያንዳንዳቸው ለኛ ይጸልያሉ፤ ያማልዱናል። 

ቅዳሴውን በሙሉ ማስታወስ ይከብዳል እንጂ ከዳር እስከ ዳር ብናየው ቅዱሳን እንዳሉበት እንረዳለን። ለእያንዳንዱ ቅዱስ በዚያ ሰላምታ እንሰጣለን፤ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷ ምን ያህል እንደሆነ እንይ። ለቅዱሳኑ ብቻ አይደለም ሰላምታ የምንሰጠው፤ ዲያቆኑ "ተአምኁ በበይናቲክሙ፤" ሲለን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ሰላም እንባባላለን። ለክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን፤ አምልኮ እናቀርባለን፤ እንሰግዳለን። እሱም ይባርካል፤ ይለውጣል፤ ያነጻል፤ ይቀድሳል፤ ይቅር ይለናል፤ ይዋሐደናል። እኛን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ያለው ለዛ ነው። ስንጾም፣ ስናስቀድስ ከእነዚሁ ቅዱሳን ጋር በመንፈስ አብረን እንሠራለን፤ መሠራት ማለት ይህ ነው። አሁንም ከእነርሱ ጋር እንድንሠራ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን። በእውነት ከዲያብሎስና ከሰራዊቱ ማኅበር ጽዋ ከመቆጠር በቸርነቱ ያድነን። 

ስለዚህ በእኛ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት ስንል አስተዳደራዊ ሳይኾን ምስጢራዊ /sacramental/ ማለትም ሥርዓተ አምልኮታዊ ነው። አንድነቷም የሚታየው ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በመፈጸም፣ አብሮ በማስቀደስ፣ ኪዳኑን በማድረስ፣ በመቁረብና በመሳሰሉት ነው። አንድ ሰው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር ስለ እነማን ሁሉ እየተናገረ ነው ማለት ነው? ስለ ቤተ ክርስቲያን ስንናገር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ነው የምንናገረው። ስለ ቤተ ክርስቲያን ስንናገር ስለ ክርስቶስ ነው የምንናገርው። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር የተማሩ ሰዎች የሚፈጥሩዋት የሰዎች ስብስብ /comminuity/ አይደለችም። በኾነ ነገር ዙሪያ የተደራጁ የሆኑ ሰዎች ስብስብ ወይም አንድነት ማለት አይደለም። በመረጡት ሰው እየተዳኙ ወይም እየተመሩ የሚሄዱበት አንድ ስብስብ ማለት አይደለችም። 

የቤተ ክርስቲያን ምስጢር ሊገባን ያስፈልጋል፤ ቤተ ክርስቲያን ብለን የምንጠራት በምድር ላይ በዕውቀት፥ ቤተ ክህነት በሚባል መዋቅር የምትመራ አስተዳደራዊ ተቋም ማለታችን ብቻም አይደለችም። ቤተ ክህነት በምድር ያለነው ክርስቲያኖች ይህን ምስጢር እያወቅንና እየተመገብን እንድንኖር የሚረዳ ተቋም ነው። ቤተ ክህነት ቤተ ክርስቲያን ሳይኾን ምእመናንን የሚያስተበብር፣ የሚመራ ምድራዊ ተቋም ነው። አገልጋይ ካህናትንና ምእመናንን የሚያመጋግብ፣ ንዋያተ ቅዱሳትንና ሌላውንም የቤተ ክርስቲያን ሀብት የሚያስተዳደር አካል ነው። ስለ ቁሳዊውና ስለ ሰዎቹ የተደራጀ መዋቅር ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አጠቃሎ የሚይዝ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክህነት  መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሊሆን ያስፈልገዋል። ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ነው፤  ቤተ ክርስቲያን ግን ምስጢራዊ ናት፤ ሃይማኖታዊ ናት፤ ለዚህ ነው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን የምንለው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስንል የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት  ማለታችን እንዳልሆነ ማወቅ ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስንል በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ያለውን አስተዳደር ያካትታል። 

ከመጠሪያነት ባለፈ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ከዚያ ያለፈችና ሰፊ ሃይማኖታዊ ምስጢራትን የተሸከመች መሆኑን ማወቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፯፥፳-፳፫ እንዲህ የሚል ቃል አለ። "ሁሉ አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም።" ከፊቱ ስላሉት ነው ጌታ እንደዚህ ያለው "ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ በእኔ ስለሚያምኑት ስለ ሁሉም ነው እንጂ፤" አለ። "አንተ እንደላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፤" ይልና "እኛም አንድ እንደሆን፥ አንድ ይሆኑ ዘንድ እኔም በእነርሱ፥ አንተም በእኔ ስትሆን በአብ ፍጹም አንድ እንዲሆኑ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤" በማስተዋል ላነበበው "እኛም አንድ እንደሆን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤" ይልና "እኔም በእነርሱ፤" ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ማለት እርሱ በእኛ ውስጥ ሲኖር ነው። ይህ አስተዳደሩን የሚመለከት አይደለም፤ ሃይማኖታዊና ምስጢራዊ ነው የምንለው ለዚህ ነው። አንድነት ማለት ክርስቶስ በእኛ አድሮ ክርስቶስ ካደረባቸው ቅዱሳን ጋር አንድ ስንሆን ነው። ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የሚለው አስተዳደራዊ ሳይኾን ሃይማኖታዊ የሚሆነው በዚህ ነው ማለት ነው። 

ስለዚህ ክርስቶስ እየተናገረ ያለው በጊዜው አብረውት ስለነበሩት ብቻ ሳይኾን ለምሳሌ እኛ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጾ በሚያስተምርበት ወቅት አልነበርንም፤ ብዙ ሰዎች አልነበሩም ግን በሥጋዌው፥ ሰው በመሆኑ ስለ እኛ ያ ቀረበው ጸሎት ነው። እግዚአብሔር ሁላችንም ላይ አድሮብን አንድ እንድንሆን ይርዳን። ቅዱስ ጳውሎስ "እኛ ሁሉን እንማርካለን፤ የክርስቶስ ልብ አለንና፤ እንዳለው ክርስቶስ በሁላችንም ላይ ቢያድርና ሁላችንም ክርስቶሳዊ ሀሳብ ቢኖረን መለያየትና መከፋፈል ባልተፈጠረም ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ ዮሐንስም ክርስቶስ አድሮባቸው ሳለ ሊጣሉ አይችሉም። ምክንያቱም በእነርሱ የሚሠራው ክርስቶስ አንዱ ክርስቶስ ስለ ኾነ እንዴት ሊለያዩ ይችላሉ? ፈጽሞ አይችሉም። ተመልከቱ እኛ ክርስቶስ በሁላችን ቢያድር ልንለያይ እንችላለን እንዴ? አንችልም። የምንለያየው እኛ ከክርስቶስ ስለ ተለየን ነው። ይህን በሚገባ ማወቅ አለብን። ክርስቶስ በእኛ ከሌለ ተመልከቱ እንግዲህ ሥጋዊ ደማዊ አስተሳሰባችንን ይዘን፥ በዚህ ዓለም የተማርናቸውን ትምህርቶች መሠረት አድርገን፥ የዚህን ዓለም መርሆች እያጣቀስን እንዲህ መሆን አለበት እንዲህ መሆን የለበትም ብንል ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ ልናመጣ አንችልም። እኛ ራሱ ከክርስቶስ አንድ ሳንሆን ምንም ዓይነት አንድነት ልንፈጥር አንችልም።

 

Read 1645 times