Friday, 04 December 2020 00:00

ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ሕመምተኞች ያላት አስተዋጽኦ

Written by  በዶ/ር እንግዳ ግርማ

Overview

፩. መግቢያ የአእምሮ ጤንነት ችግር የአስተሳሰብ፣ የስሜት፣ የጠባይ እንዲሁም ሌሎች የአእምሮ ተግባራት መዛባት የሚያመጡት የጤና እክል ነው። ይህም በአንጻሩ ቀላልና ጊዜያዊ ከምንላቸው የውጥረት ስሜቶች እስከ ከባድ የአእምሮ መቃወስ የሚያካትት ነው። ምንም እንኳን ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች የውጥረት፣ የጭንቀት፣ የእንቅልፍ ማጣት ወይም የጠባይ መቀየሮችም በጊዜያዊነት ወይም ከፍ ባለ መጠን በተደጋጋሚ ይከሠታሉ።  የአእምሮ ችግር መንሥኤዎች ብዙና የተለያዩ ናቸው። ሥነ ሕይወታዊ (Biological)፣ ስነ ልቡናዊ (Psychological)፣ ማኅበራዊ (Social) መንስኤዎች ብሎ መክፈል የተለመደና እስካሁን ተቀባይነት ያለው የአስተሳሰብ ማቀፍ ነው። ማኅበራዊ (social) መንሥኤ በሚለው ውስጥ ባህላዊ (cultural) እና መንፈሳዊ (Spiritual/Religious) ሁኔታዎችም ይካተታሉ።  የአእምሮ ሕመም ሲባል ራሱን የጣለ፣ የተዳደፈ፣ ቆሻሻ የሚለቅም፣ አደገኛ ሰው ማሰብ የተለመደ ነው። በርግጥ እጅግ በጣም ጥቂቱ የአእምሮ ሕሙማን ብቻ እንዲያ ያለውን የአእምሮ መቃወስ ምልክቶች ያሳያሉ። የሚበዙት ሕመሞች ምክንያት አልባ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ እንቅልፍ ማጣት ወይም ከአእምሮ ዕድገት ጋር የተገናኙ ችግሮች ናቸው። በዐይን አይቶ ለመለየትም አይቻልም። ሁሉም ሊባሉ በሚችል ደረጃ ዘመናዊ የንግግር ወይም የመድኀኒት ሕክምና ያላቸው ቢሆንም አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ወደ ጤና ተደራሽ አይደለም። በሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ካላቸው ሰዎች መካከል ከመቶ ውስጥ ሰማንያ ዘጠኝ  የሚሆኑት ህክምና አያገኙም። (ምንጭ) በቂ ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው የአእምሮ ሕሙማን በጣም ብዙ የሕይወታቸውን ዘመናት በመታሰር፣ ተስፋ በመቁረጥና በመደብደብ እንዲሁም በብቸኝነት ያለሥራ ያሳልፏቸዋል። የቤተሰብ ኑሮና ብዙ የሀገር ንዋይ እንዲሁ እንደባከነ ያልፋል። 

 

፪. ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ጤና 

ሀ. የአእምሮ ጤንነትን በመጠበቅ 

ስላለን የተደከመበት የማይመስለን የአእምሮ ደኅንነታችንን አስቀድመን እንደተመለከትነው ከሥነ ሕይወታዊ መሠረቶች ባሻገር ያሉ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ውቅሮች በብዙ ድካም የተዋቀሩ ናቸው። ለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ ተወጥታለች። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ ምእመን በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ፣ በምግባር ላይ ትሩፋት አምላኩን ለመምሰል በጎ ዘር የተዘራበት እንደሆነ በማስተማር ወደ በጎነት፣ መልካምነት፣ ቅንነት፣ ቅድስና፣ ንጽሕና ወዘተ. እንዲያድጉ ከልጅነት ጀምሮ ዕለት ዕለት ታስተምራች። ይህም ልጆቿ በጎ ኅሊና እና አዎንታዊ አስተሳሰብ (Positive thinking) እንዲኖራቸው ትምክህታቸው በሆነ ከሃሌ ኵሉ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚያምኑ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እንዲህ ያለው አዎንታዊ አስተሳሰብና ማድረግ እችላለሁ የሚለው እምነት ምእመናንን ከጭንቀት፣ ከውጥረትና ተስፋ ከመቁረጥ በብዙ መልኩ ይጠብቃል። ከዚህም ባሻገር ኦርቶዶክሳውያን በየማኅበረሰባቸው በእድር እንዲሳተፉ፣ ራሳቸውን ሳይኮፍሱም ሳያሳንሱም ከሌሎች ጋር በሰላም እንዲኖሩ ሆነዋል።

በጎ አስተሳሰብና አምላኩን መጠጊያ ያደረገ “ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” የሚለው እምነት ምእመናን ድሃ ቢሆኑ ሀብታም፣ ሊቅ ቢሆኑ ደቂቅ፣ ከሰሜን ቢሆኑ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ ቢሆኑ ከምዕራብ ያለምንም ፍርሃትና የበታችነት ስሜት በእኩል መንፈስ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረን ሁሉ በማክበር በኅብረት እንዲያመሰግኑ፣ በአንድ አንድ ሰንበቴ ማኅበር አንድ ጽዋ  እንዲጠቱ አድርጓል። እንዲህ ያለው ኅብረት በደስታና በኀዘን፣ በድሎትና በእጦት በማንኛውም የኑሮ ውጣ ውረድ ሥነ-ልቡናዊና ማኅበራዊ ድጋፍ የሚገኝበት ሁነኛ መንገድ በመሆን ያገለግላል።

መኖር ሰለቸኝ፣ ራሴን አጥፍቼ አርፋለሁ፣ ለምን እኖራለሁ እና የመሳሰሉት የሚያስቆዝሙ ሐሳቦች በተለያዩ የአእምሮ ሕመሞች ምክንያት ወይም የሕይወትን ትርጉም በማጣት ይመጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰውን ልጅ የምድር ኑሮ ትርጉም ማስተማሯ ምእመናን የሕይወት ትርጉም እንዳይጠፋቸውና በቀቢጸ ተስፋ እንዳይኖሩ ትልቅ መሠረት ሆኗል። 

ከዚህም በላይ የኦርቶዶክሳውያን ልጆች የሰብእና አወቃቀር ዋነኛ ማንጸሪያ ፈጣሪያቸውና አምላካቸው ስለሆነ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻቸው “ይህን እግዚአብሔር ይወደዋል” በማለት ራሳቸውን እንዲጠይቁ እና ከክፋትና ጥፋት እንዲጠበቁ ሆነዋል። ሌሎች ላይ ቅያሜ ከመፍጠር፣ ጫና ከማድረግ፣ ከመጉዳት ተጠብቀዋል። 

ሌላው ትልቁ የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ምሥጢረ ንስሓ ነው። ምእመናን ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው ባሻገር ስለጭንቀታቸው፣ የዕለት ተዕለት ተግዳሮቶቻቸው፣ ማኅበራዊ ውጣ ውረዶቻቸው፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውን ከመምህረ ንስሓቸው ጋር ይወያያሉ። እነዚህን ሁሉ የሚያዳምጥ ጆሮ ማግኘቱ በራሱ ትልቅ ዕረፍት የሚሰጥ ነው። ለየተግዳሮቶቻቸው ጊዜ ሰጥቶ መመካከርና የመፍትሔ ሐሳብ ማምጣት መቻል ደግሞ ትልቅ መንፈሳዊ ሕክምና ነው። ጭንቀት፣ ውጥረትና ሌሎች የአእምሮ ጫናዎችና ሕመሞች በዚህ መልክ ሲታከሙ ኖረዋል። 

ሰዎች ኀዘን በደረሰባቸው ጊዜ የሚጽናኑባት እጅግ ጠቃሚ ሥርዓት ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት። ኀዘን ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑ በየደረጃውና በየጊዜው በካህናትና በምእመናን የማጽናናት ሥራ ትሠራለች። በዚህም ሰዎች ከኀዘን ጋር የተገናኘ የአእምሮ ጭንቀትም ሆነ ሌላ ሕመም እንዳይከሠትባቸው ስትረዳ ቆይታች። ድንገተኛ አደጋ/ጥቃት የደረሰባቸውን በቃለ እግዚአብሔር ማጽናናት፣ የተቻለ ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ እና ምእመናን ላዘኑና ለተጎዱ እንዲደርሱ ማበረታታት የቤተ ክርስቲያን የዘመናት ተግባር እንደሆነ ይታወቃል። ሰዎች ከአሰቃቂ ክሥተት በኋላ ከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት እንዳይከሠትባቸው እንዲህ ያለው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በሰሞኑም ደጋግመን እያየን ያለነው ይህንኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ገጽታ ነው። 

ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ደኅንነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ በአደጋ፣ በሕመምና በጭንቀት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመልካሙም ጊዜ ጭምር ነው። እንዲህ ላለው የቤተ ክርስቲያን አበርክቶ ሰ/ት/ቤቶች ጥሩ ምስክሮች ይሆናሉ። የኦርቶዶክሳውያን ልጆች በሥነ ምግባር እንዲታነጹ፣ ሀገራቸውን እንዲወዱ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለወላጆቻቸውን የሚታዘዙ እንዲሆኑ በሰ/ት/ቤት ተኮትኩተው ያድጋሉ። ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ፣ ከሱስ ተጠብቀው፣ እርስ በእርስ እየተዋደዱ እንዲኖሩ በማድረግ ሰ/ት/ቤቶች የፈጠሩት ትልቅ የአዳጊዎችና ወጣቶች ኅብረት ብዙ ትውልድ የሚታደግ የአደባባይ ሀቅ ነው። 

በመምህረ ንስሓ በኩል ከወላጆች፣ በሰንበት ት/ቤት በኩል ከአዳጊዎችና ወጣቶች፣ በስብከተ ወንጌል በኩል ከመላ ቤተሰቡ በመድረስ ሰላማዊ የክርስቲያን ቤተሰብ እንዲኖራቸው፣ ወላጆች ለልጆች ፍቅርና ክብካቤ እንዲሰጡ፣ ልጆች በሥነ ምግባር ታንጸው፣ ወላጆቻቸውን አክብረው እንዲያድጉ በማድረግ ወላጆቻችን ከጭንቀትና ከውጥረት፣ ልጆቻችን ከአስተዳደግ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ብዙ የአእምሮ ጤና እክሎች መታደግ፣ ወይም መቀነስ ሌላው የቤተ ክርስቲያን የሚታይ አስተዋጽኦ ነው። 

በሥነ ልቡና ዓለም ብዙ ካጨቃጨቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሃይማኖተኝነት (መንፈሳዊነት) ነው። በዘመናዊ የሥነ ልቡና እና የአእምሮ ህክምና ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠኑ ካሉ ርእሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ መንፈሳዊነት/ ሃይማኖተኝነትና አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነት ያላቸው ውስብስብ ግንኙነት ነው። አሁን ባለው መረጃ መሠረት መንፈሳዊነት ለአማኞች ከፍተኛ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል። ለአካላዊ ሕመም የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በርትተው እንዲኖሩ ማስተማር ዛሬ ሳይንስ ስላለ ሳይሆን በዘመኗ ሁሉ የአገልግሎቷ ማጠንጠኛ አድርጋ ስትፈጽመው የኖረችው ዋነኛ አገልግሎቷ ነው። መንፈሳዊነት ከሰማያዊ ጥቅሙ ሌላ እንደ ዳረጎት አእምሯቸውና አካላቸው የተረጋጋ ለሕመም ተጋላጭነታቸው የቀነሰ እንዲሆን ያደርጋል። 

ለ. በማከም/በፈውስ 

ቤተ ክርስቲያን የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ምእመናን ዕረፍት የሚያገኙባት ባለ መድኃኒት እንደሆነች እሙን ነው። ከቀላል እስከ ከባድ የአእምሮ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች እንደምሳሌ ብናይ በሥርዓተ ጸሎቱ፣ በስብከቱ፣ በመዝሙሩ የመንፈስ ዕረፍት፣ የአእምሮ መረጋጋት ያገኛሉ። ይህንንም እንደ የቡድን ህክምና ልናየው እንችላለን። ከዚህም በላይ በንስሓ አባቶቸ በኩል የየግል ጭንቀቶቻቸውን ምእመናኑ እንዲወያዩ እና እንዲፈቱ ታደርጋለች። የቤተ ክርስቲያን ምክር ተስፋ በመቁረጥ፣ በከፍተኛ ኀዘን፣ በቤተሰብ አለመረጋጋት ውስጥ ለሚገኙም የጭንቀታቸው ማቃለያ የችግራቸው መፍቻ መንገድም ሆኖ ያገለግላል። 

በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሕሙማን የሚበዙት ወደ ጸበል ቦታዎች ይሄዳሉ። ቁጥራቸው በዘመናዊ የህክምና ተቋማት ከሚገኙት በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ። ሁሉም ወደ ሀኪም ቤት ቢመጡ ያለው የአእምሮ ህክምና መሠረተ ልማት ከሚቋቋመው እጅግ የበዛ ይሆናል። ስለዚህ የአእምሮ ሕሙማን ጸበልተኞችን አቅፋ በመያዝ ምግበ ነፍስ እየመገበች ታኖራቸዋለች። የሱስ ሕመም ያለባቸው ወጣቶችን በቅጽሯ ቆይተው፣ መንፈሳቸውን አድሰውና አገግመው እንዲወጡ ትሠራለች። ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰብ የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ታዘጋጃቸዋለች። እንዲህ ያለ ጉልህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ከሕሙማኑ ባሻገር ወላጆችና ቤተ ሰቦችም ከፍተኛ ዕረፍትና የመንፈስ እድሳት እንዲያገኙ ያደርጋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው በሳይንስ ከምንረዳው በላይ ከሆነው የፈውስ አገልግሎቷ ባሻገር በቤተ ክርስቲያን እየተከናወነ ያለውን የሚመለከት ነው። 

፫. ቤተ ክርስቲያን ለአእምሮ ጤና 

ስንዱ እመቤት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን በኢትዮጵያ ለአእምሮ ጤና ያበረከተችው ተቆጥሮ የማያልቅ ነው። መዋቅሯም ይህን ለማድረግ የተመቸ ነው። ከዚህ የበለጠ ለማድረግ የተለየ አወቃቀር አይፈልግም። ምእመናን ላይ መሥራትና ለሁሉም ዘርፍ ዘመኑን መዋጀት ይገባል።

ሀ. ምእመናንን ማስተማር 

ማንኛም ዓይነጽ ሕመም ልንታመም እንደምንችለው ሁሉ የአእምሮ ሕመም ሊያመን ይችላል። የአእምሮ ጤና መቃወስ በተለየ መልኩ የደካማነት ወይም የኃጢአት ምልክት አይደለም። ስለዚህ ምእመናን ማንኛውም አካላዊ ሕመምን እንደሚያዩት እንዲረዱት ማድረግ የሕሙማን መገለልና ሥቃይ ይቀንሳል። 

ወደ ህክምና ቦታ ወይም ቤተ ክርስቲያን የመምጣት እድላቸውን ይጨምራል። ይህን ውጤት ለማምጣት ስለሕመምና ደዌ በተነሣበት አጋጣሚ ሁሉ ስለ አእምሮ ሕመም ማስተማር አስፈላጊ ነው። በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ሥፍራዎች የተጠቀሱትን የአእምሮ ሕሙማን የምሕረት ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ሳይጸየፋቸው ፈውስን እንዳደረገላቸው እያነሡ ማስተማር ምእመናን ማግለልን እንዲጸየፉ ይረዳል። 

ከዚህ በተጨማሪ ሁሉን ማዳን የሚችለው ክርስቶስ በልዩ ልዩ መንገዶች እንደሚፈውስ፣ ዘመናዊው ሕክምናም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ፣ ምእመናን እየተጠመቁ መድኃኒት መውሰድ እንደሚችሉ፤ መድኃኒት እየወሰዱ ባሉበት ጊዜም አስቀድመው መጠመቅና ከተጠመቁ በኋላ መድኃኒቱን መውሰድ እንደማይከለከሉ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወይ በመድኃኒት አልያም በጸበል ከሚል ፉክክርና ድርቅና ወጥተው፤ እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ እንደሚፈውስ ተረድተው እንዲጠቀሙ ማበረታታት ይገባል። 

ለ. ምሥጢረ ንስሓ 

ንስሓ ለድኅነተ የተሰጠን የቸርነት በር ነው። እጅግ ብዙ ምእመናን በዚህ የምሥጢር በር እየገቡ ከአምላካቸው ጋር የተለየውን ኅብረት ይመልሳሉ። ለምእመናን የአእምሮ ደኅንነት ስላለው ፋይዳ ከላይ በአጭሩ ለመጥቀስ ሞክረናል። 

ይህን ለምእመናን መንፈሳዊም ሆነ ምድራዊ ሕይወት ወሳኝ የሆነ ምሥጢር አሠራሩን ማዘመን ብዙ ክርስቲያኖችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። የምእመናንን የንስሓ ሕይወት የሚከታተል ክፍል ማቋቋም፣ ምእመናን በንስሓ ሕይወት እንዲጠቀሙ ማበረታታት ቀዳሚ ተግባራት ሊሆኑ ይችላሉ። ካህናት አባቶች ከተነሳሕያን ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት፣ በሚያናግሩበት ጊዜ ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች፣ ስለሚወያዩባቸው ዋነኛ ፍሬ ሐሳቦች የሚያትት የሥልጠና መመሪያ ማዘጋጀት እና ማሠልጠን። ከመንፈሳዊው ጥበብ በተጨማሪ በዘመናዊው የንግግር ህክምና (Psychotherapy) በጥናት የተረጋገጡ መንገዶችን መጠቀም የሚችሉ ብዙ ካህናትን ማፍራት ያስፈልጋል። ብዙ በቀቢጸ ተስፋ ያሉ ወንድሞችና እኅቶችን የበለጠ ለመርዳት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። 

ሐ. የሱስ ማገገሚያ ሥርዓት መዘርጋት 

ወጣቶች በየጸበል ቦታ  የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ምግብ  እየተመገቡ “አምጣ አምጣ” የሚላቸውን የሱስ ስሜት ተቋቁመው ይቆያሉ። ሥርዓት ተደንግጎለት በሱስ ለተጎዱ ጸበልተኞች በተለየ መልኩ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆን ደግሞ እጅግ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል። በልዩ ልዩ ሱስ የተጠመዱ ወንድሞችና እኅቶችን መንፈስ የሚያንጽ፣ የተጠና እና በየደብሩ/ገዳሙ የተቀናጀ የስብከተ ወንጌል፣ የውይይት፣ የንግግር ሕክምና እና የመዝሙር ክፍሎች ያሉት ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ ውጤቱ የሚለካና በየጊዜው የሚሻሻል ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን የመታደጊያ መንገድ እንዲሆን ይረዳል። እንዲህ ባለው መንገድ ታንጸው የወጡ ወጣቶች ከሱስ ከማገገማቸው በላይ ለቤተሰብ፣ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ይሆናሉ። 

መ. የጸበል ቦታዎች 

ክርስቲያኖች በየአድባራቱና በየገዳማቱ ተሰባስበው በመጠመቅ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ለማግኘት ይለምናሉ፤ ይማልላሉ። ይሁንና ጥቂት በማይባሉ ጊዜያት ይህ የሚሆነው ካላስፈላጊ ሥቃይና እንግልት ጋር ነው። ጸበልተኞቹ የአእምሮ ሕሙማን ለግርፋት እና ለሰንሰለት እስራት ይዳረጋሉ። በአስጠማቂዎች እጅ ይደበደባሉ። ብዙዎች የጸበል ስፍራዎች በቂ የውኃና የንጽሕና መጠበቂያ ቦታዎች የሏቸውም። በአንዳንዶቹ ገዳማትና አድባራት ምእመናን ከመሀል ከተማ ባልተናነሰ የቤት ኪራይ ኑሯቸው ይናጋል። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የጸበል ቦታዎች ተቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት። እግዚአብሔርን ብሎ ቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ ያለ ሕመምተኛ ተጨማሪ ሕመምና እንግልት ሊደርስበት አይገባም።

ጸበልተኞች ከመጠመቅ፣ ከጸሎትና ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተረፋቸው ጊዜ ቁጭ በሎ ከማውራት፣ ዝም በሎ ከመቆዘም ወይም ለክፉ ሐሳብ ማደሪያ ከመሆን እንደየአቅማቸው በሥራ እንዲያሳልፉ ማድረግ ለገዳማቱ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል። ለአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚኖረው በጎ ትሩፋት ባሻገር ጸበልተኞች የመዳን ሂደታቸውን እንዲያፋጥኑ፣ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሲመለሱ ለሚኖራቸው የሥራ ሕይወት ዝግጅት እንዲያደርጉ ያግዛል።

  

Read 706 times