Thursday, 21 January 2021 00:00

‹‹ሰላም እንዲሰፍን የቤተክርስቲያን ድርሻ››

Written by  ዳዊት ደስታ

Overview

ሰላም ምንድን ነው? ሰላም በስምምነትና በአንድነት አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች በምንኖረው ሕይወት ውስጥ እጅጉን ከሚያስፈልገን ነገር ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ ፍጥረታት እንዲኖሩ የሚያስፈልገው በሰላም ነው ያለ ሰላም ልንኖር አንችልም፡፡ ሰላም ማለት ‹‹ፍጹም፣ ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ሲለያይ የሚለው የሚናገረው ወይም የሚጽፈው›› በማለት  አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የሰላምን ፍቺ በእንዲህ መልኩ ገልጸውታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፰፻፷፰)  የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ‹‹የሰላም ግንባታ ማሠልጠኛ›› በተሰኘው ጥናታዊ መድበሉ ስለ ሰላም ምንነት እንደሚከተለው አብራርቷል፡፡ ‹‹ሰላም የሚለው የአማርኛ ቃል የተሸከመው ፅንሰ ሐሳብ ከጦርነትና ከዐመፅ ነፃ መሆን›› ከሚለው የአንዳንድ መዛግብት ቃላት ሰፋ ያለ ትርጉም ይዟል፡፡ ‹‹ሰላም›› ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታና ውድ ጸጋ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔር ሰላም ነው›› (መሳ. ፮፥፳፬) በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፡፡

 

እውነተኛ ሰላም የሚገኘው የሰው ልጅ በክርስቶስ አምኖ፣ ከኀጢአቱ ነጽቶ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታረቅ ነው፡፡ ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ››፤ ‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና›› እንዲል። (ሮሜ ፭፥፩፤ ኤፌ. ፪፥፲፬-፲፯) ሰላም የመንፈስ ፍሬ ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ከዘረዘራቸው መካከል የተጠቀሰ ነው፡፡ (ገላ. ፭፥፳፪) ‹‹ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ አንተንም ለሚወዱ ልማት ይሁን በኃይልህ ሰላም በጌጠኛ ቤትህም ልማት ይሁን›. እንዲል (መዝ. ፻፳፩፥፮-፯) በቅዱሳት መጻሕፍት ሰላም የሚለው መሠረታዊ ቃል የሚያመለክተው በሰዎች ሕይወት ውስጥ ተሟልቶ መገኘት የሚገባውን ደኅንነት፣ መላካምነት በመሆኑ ቃሉ የያዘው ፍቺ ላቅ ያለ አሳብን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰላም ማለት ሰዎች በግል ኑሯቸውም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ወቅት ሊኖራቸው የሚገባ ሁለንተናዊ ምሉእ የሆነ የሕይወት መገለጫ ነው፡፡

የጸሎታችን ሁሉ ራስ በሆነው ጸሎተ ቅደሴያችን “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ቀናች፣ የሐዋርያት ቅድስት ጉባኤ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ” እያልን እንለምናለን፡፡

ቤተ ክርቲያን በሰላም ግንባታ ያላት ሚና

ከትላንት እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያን በትንሹም በትልቁም የሰላም እና የዕርቅ ማዕከል ናት፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች የተለያዩ ዘሮች ጎሳዎች እና ስብስቦች የታረቁት እና የሚታረቁት በሃይማኖት አባቶች ነው፡፡ በሀገራት ደረጃም ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን የሃይማኖት አባቶች ሰላምን በማውረድ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ባል ከሚስት ፣ ጎረቤት ከጎረቤት ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ አንድ ሰው ከሌላው በምክንያት ቢጣላ የዕርቀ ሰላሙን ሥራ የሚሠሩት የሃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ ‹‹የሚያስታርቁ ብጹዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና›› /ማቴ ፭፡፱/ የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ካህናት ሁል ጊዜ በሰላም ግንባታ እና በዕርቀ ሰላም ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዘው ኖረዋል፣ ዛሬም  ወደ ፊትም ይህንን ተግባር የሚቀጥሉበት ነው፡፡ 

በሀገራችን ትላንትም ሆነ ዛሬ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ጠብ እና ጦርነቶች ሲካሄዱ ኖረዋል ለምሳሌ ዘር እና ጎሳ ተኮር ጦርነቶች ከትላንት እስከ ዛሬ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ደም ሲያፋስ ነበር አሁንም እያገረሸ ሰው ከሰው እያለያየ ነው ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ መንግሥት ከሚወስደው የኃይል እርምጃ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ምእመንዋን በማስተማር ሊመጣ ካለው መዓት እና ጦርነት መታደግ እንደምትችል ብዙኃን ያምናሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት መለያየቶች እና የሰላም መደፍረስ አንዳንድ ጊዜ ጥሩ አስተዳደር ባለማግኘት ሊከሰት ይችላል፡፡ በዘመናችን ሁላችንም እንዳየነው በመገናኛ ብዙኃን እንደ ሰማነው በማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደ ተመለከትነው ቤተ ክርስቲያን ያ ሁሉ መከራ ሲደርስባት፡ መከራ አድራሾቹ ላይ ጦርነት ከመክፈት ይልቅ ለሰላም ስትጠራቸው ነበር፡፡ እየተቃጠለችም እንኳን እጇን ለሰላም ዘርግታ ነበር፡፡ ይህ ለሰላም ምን ያህል ዋጋ እንደምትከፍል እና በሀገሪቱ ለሰላም እና ዕርቅ ያላትን ከፍተኛ ሚና የሚያሳይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ግንባታ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ፸፭ በመቶዎቹ በሃይማኖት ተጽእኖ ሥር እንደ ሆኑ እና በከፍተኛ ሁኔታ ከሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ (Rahel Alene Techane. The Role of the Two Dominant Religions, EOTC and Islam in Promoting Ethiopian Unit ፤ ራሄል አለነ ሁለቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሃይማኖቶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ እና እስልምና በኢትዮጵያ ሀገር አንድነት) በሚል ርእስ ለ፪ኛ ዲግሪ ማሟያ በሠራችው ጥናት ገጽ፩) ይህ ሃይማኖት የኅብረተሰብን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተጽእኖ እንደሚያሳድርበት፣ ሃይማኖት ማኅበራዊ አንድነትን እንደሚያመጣ እና ሃይማኖት ለሰላም ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው አመላካች ነው፡፡ ሃይማኖት ለሰው ልጆች ሁሉ ጥሩ እውነተኛነት እና በጎ የሆነ እሴት ያለው ነው፡፡ ሃይማኖት ዐመፅን፣ ጦርነትን አይሰብክም ከዚህ ይልቅ ሰላምን እና ኅብረተሰቡ በሰላም አብሮ መኖር እንዲችል የሚሰብክ ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከልደቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ የሰበከው ሰላምን ነው፡፡ ሲወለድ ቅዱሳን መላእክት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ›› ብለው ነበር የዘመሩት (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡ 

ስለ ጌታችንም ከነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ሕፃን ተወልዶልናል፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፣ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል›› ብሎ ነግሮናል (ኢሳ. ፱፥፮) ጌታችንም በመዋዕለ ሥጋዌው በሕይወቱ ያሳየን በቃሉ የሰበከን ሰላምን ነው፡፡ ‹‹እኔ ሰላሜን እተውላችኋለው እኔ የምሰጣቹ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ ዓይነት አይደለም›› በማለት (ዮሐ.፲፬፥፳፯) ሲነሣም ቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ ቤት ሳሉ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ነው ያላቸው (ዮሐ. ፳፥፳)፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህንን ከጌታችን ያዩትን እና የተማሩትን አስተምረውናል ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ፲፪፥፲፰ ላይ ‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› በማለት ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር እንደሚገባን አስተምሮናል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ከነቢያት ከጌታችን ከሐዋርያት በተማረችው ትምህርት መሠረት ዘወትር ስለ ሰላም ትማልዳለች፡፡ በቅዳሴያችን በእንተ ቅድሳት የተባለው የቅዳሴ ክፍል ላይ ‹‹ስለ ሰላም እንማልዳለን›› እንላለን፣ ካህኑ በቅዳሴ ወቅት ፲፪ ጊዜ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› በማለት ሰላምን ያውጃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም ያላት ብዙ ነው፤ የተረበሸ ሁሉ ሰላም የሚያገኝባት ስፍራ ናት፡፡

ሃይማኖታዊ ተቋማት ሃገራዊ ሰላም እና ልማት የማምጣት ሚናቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማምጣት ይቅር በማባባል የሚያደርጉት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ በሀገራችን በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በጎሳ ልዩነት ምክንያት የተፈጠሩ ግጭቶች መፍትሔዎቻቸው የኢትዮጵያን አንድነት በማምጣት ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድትኖር ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ለችግሮቻችን ምንጩ ሰላም ማጣት ነው፡፡ ሰላም ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለጎረቤታችን፣ ለመንደራችን፣ ፤ ለአካባቢያችን እንዲሁም ለሀገራችን አስፈላጊ ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት

የሃይማኖት ተቋማት የቆሙበት መሠረት ዓለማዊ አስተሳሰብ ባለ መሆኑ እንዲሁም በተቋማቱ ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን ሰላማዊውን መንገድ የሚናፍቁ በመሆናቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ የተበደሉ ወይም የበደሉ ወገኖች ካሉ በማስታረቅ፣ ያኮረፈ ወይንም የተገለለ ወገን ካለም የማስማማቱን ተግባር ይወጣሉ፡፡ የቆሙለት ዓላማም ከሀገር አልፎ በዓለም ላይ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን መጸለይና መትጋት ከሁሉም በፊት ቀድሞ የሚሠራ ነው፡፡ 

ቤተ ክርስቲያንም ሃይማኖት የሚሰበክባት ብቻ ሳትሆን ማኅበራዊ ጉዳይም የሚመለከታት ጭምር ናት፡፡ የራሷንም ሆነ የሀገሪቱን ችግር በሰላም ለመፍታት ትጥራለች፡፡ ተጠሪነትዋ ለክርስቶስ ቢሆንም የተሰየመችው ሕዝብን ልትመራ፣ ማኀበራዊ ተሳትፎ ልትፈጽም ጭምር ነው፡፡ 

ለዚህም ሰላምን በማስተማር ረገድ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሚና አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የእውነተኛ ፍቅር ቤት ናትና በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና ፍቅር እንዲሠፍን መቻቻል እንዲኖር በልዩ ልዩ መንገድ ስታስተምር የቆየች ሲሆን አሁንም በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡

ዘላቂ ሰላም እንዴት መምጣት ይችላል?

ሰላም ማኅበራዊ ዕሴት ነው ሚዛናዊ የሆነ መስተጋብርን ይፈልጋል፡፡ የደካሞች ሰላም ሲከበር በማኅበረሰቡ ውስጥ የኃያላኑም ሰላም ይከበራል፡፡ ስለ ሰላም መምከር፣ አብዝቶ መሥራት፣ የሰላም መታጣት የሚያመጣውን ችግር በግልጽ ማስረዳት፣ ከደረሱብን የሰላም እጦት ሰው እንዲማርና ከሰላም ጎን አጥብቆ እንዲቆም ማድረግ ይገባል፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ዓለምን ንቀው ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም እና ድኅነት ሲሉ እፍኝ ቆሎ እና ጥርኝ ውሃ እየቀመሱ ሌት ተቀን የሚጸልዩ አባቶች ስላሉን ወደ እነሱ ፊታችንን ልንመልስ ይገባናል፡፡ ሕዝብ ከሕዝብ ሲጋጭ ብሔራዊ መግባባት ሲጠፋ ሰላምን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነውና ምሕላን መያዝ ያስፈልገናል፡፡ 

ዘላቂ ሰላም መምጣት የሚችለው ወደ እግዚአብሔር ሰዎችን በማቅረብና ራስም በመቅረብ ነው፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠንን ሰላም ሌላ ቦታ አናገኘውም፡፡ ይህ ሰላም ፍጹም ልዩ ነው፡፡ ‹‹አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል›› እንዲል። (ፊል. ፬፥፯) የሰው ልጅ በሃይማኖት ከኖረ ያለፈ በደልን በንስሓ አስተሥርዮ ከእግዚአብሔር ስለሚገናኝ ፍጹም ሰላምን ያገኛል፡፡

ዘላቂውን ሰላም ሰጪ ወደ ሆነው ልንቀርብ ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እርሱ ሰላማችን ነው›› (ኤፌ. ፪፥፲፬) እንዲል፡፡ ሰላም ሲጠፋ ተስፋ ሲጨልም ልብ ይታወካል፡፡ ነፍሳችን ሁሌ የምታርፍበት ወደብ ጌታችን ነው፡፡ አምላካችን የሚጠራን ለሰላም ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ለሰላም ጠርቶናል›› (፩ቆሮ. ፯፥፲፭) በሰላም ተኝተን እንድናንቀላፋ ሰላምን ወደሚሰጠን አምላክ ሰላምን እንለምን፤ ‹‹በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁ አቤቱ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛል›› እንዲል (መዝ.፬፥፰)፡፡ የዛሬውንም ሆነ የነገውን ተስፋችንን ልናረጋግጥ የምንችለው ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡

ለሰላም መታጣት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ማንኛውም ዜጋ የሚፈልገውን አሳብ ለማራመድ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ከክርስትና እምነት አንጻር ሰላም ከእግዚአብሔር የመነጨና ከሰዎች ችሎታና ግንዛቤ በላይ የሆነ ጥሪ ነው፡፡  በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ ለዚህ ተልእኮ ይኖሩ ዘንድ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሰላም የሚታጣው የሰላምን ጥቅም ካለመረዳት፣ በሥጋዊ አስተሳሰብ መጠመድ፣ ነገን መርሳት፣ ፍቅር አልባነት፣ ጊዜያዊ ጥቅም፣ ድህነት፣ ሥራ ፈትነት እና መሰል ተግባራት ሲበዙ ነው፡፡

በማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አንዳንዴም ተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ያልተጣጣሙ ፍላጎቶች የተነሣ የፖለቲካ ትግል ይፈጠራል፡፡ በዚህ ዓይነት የተፈጠረው የፖለቲካ ትግል የሚካሄደው ደግሞ አልፎ አልፎ ሕጋዊና ሞራላዊ በሆነ መልኩ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የማኅበረሰቡን ባሕል፣ ሕግ፣ እምነትና ግብረ ገብነትን በተቃረነ መንገድ ይሆናል፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያን ተግባርና ጉዳይ የልጆቿ አንድነት በሰላምና በኅብረት ተጠብቆ እንዲኖርና ከሁሉም ማኅበረሰብ ጋር ተስማምታ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን ምእመናን አባላት የጋራ ጥረቶች ላይ ማሳተፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም ታስተምራለች፡፡ ሰላም እንዲሆን ሰላም እንዲሠፍን ጥሪ ታቀርባለች፣ የምትሰብከው መጽሐፍ ቅዱሷም ቢሆን ሰላምን አጥብቆ ይሻል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ከሁሉ በላይ የምትፈልገው ደግሞ ውስጣችን በእምነትና በፍቅር አንድ እንዲሆን ነው፡፡ ይህን የውስጥ ወይም የመንፈስ አንድነትን የሚያጠናክር ትምህርቷም እንዲህ ይገለጻል፡፡ ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› ይላል። (፩ቆሮ. ፩፥፲)፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ትልቁ ዕሴቷ (ኤፌ. ፩፥፳፫) ከላይ እንደተገለጸው ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ ከአምላኳ ከክርስቶስ ጋር ያላት አንድነት ነው፡፡ ሰብአዊ የሆነ ፍጡር ዘለዓለማዊ ድኅነትን ለማግኘት ሊመካበት የሚገባው ነገር ይህ ነው፡፡ ተለያዩ ሰዎች በፖለቲካ ልዩነትም ወይንም በሌሎች ጉዳዮች የተነሣ ቅራኔና በፖለቲካ ትግል ውስጥ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ልዩ ልዩ ፍላጎትና አመለካከት ያላቸው ሕዝቦች ወደ ሰላምና ትብብር እንዲመጡ ትሰብካለች ወይም ታስተምራለች፡፡ 

ሰላምን መረዳት አለብን

የሰው ልጅ ሰላምን መረዳት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከምንም በላይ የሀገር ሰላምና የሕዝቦች ደኅንነት ስለሚያሳስባት የጥላቻን ዘር በመዝራት የሚፈጸመውን አክራሪነት ለሀገር ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ መሆኑን ተረድታ ሰላምን ትሰብካለች፡፡ እንዲሁም የአክራሪነት አካሄድ ከሰው አልፎ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስለሌለው ታወግዛለች፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም ተነሥታ በዓለም የተስፋፋችው በጦር ኃይል ሳይሆን እውነተኛ በሆነው በወንጌል ትእዛዝ በመመራት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሲልካቸው አስገድዳችሁ ስበኩ አላለም፡፡ ሐዋርያትም ሆኑ ሊቃውንት ወደ ዓለም ሲሰማሩ ከአምላካቸው የተቀበሉትን የሰላም ወንጌል በመተግበር ነው፡፡ 

ሰላማዊ መሆን

ክርስቲያኖች የተጠሩት ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው፡፡ ሰላማዊነት የመንፈሳዊ ሰው አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ሰላማዊ ሰው በማንኛውም በሚፈጸሙ ተግባራት ፈጽሞ ልቡ አይርድም፡፡ የቱንም ያህል ችግር ቢደርስበት ሰላሙን አያጣም ነቢዩ ዳዊት ‹‹ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም ሰልፍም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ›› (መዝ. ፳፯፥፫) እንዲል፡፡ አንድ ሰው ውስጣዊ ሰላሙን ካጣ ሁሉም ነገር በእርሱ እይታ የሚረብሸው፤ ትንሹም ነገር ውስብስብ ሊመስለው ይችላል፡፡ የልብ ሰላም ሲኖረን አእምሮአችንም ሰላም ይሰፍንበታል፡፡

ማጠቃለያ 

ሰላም ስንል የተሟላ ሕይወት እንደ ሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎችን ማክበር በሰውነታቸውና በማንነታቸው ብቻ መቀበል፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ጦርነቶች አለመኖር፣ ፍትሐዊ የሆነ የሥልጣንና ሀብት ክፍፍል መኖርን፣ መቻቻልና ማኅበራዊነትን ይጠይቃል፡፡ በእንተ ቅድሳት በሚባለው የምልጃ ጸሎታችን ቀድመን የምንለምነው ልመናም ከሁሉ አስቀድሞ በክርስቶስ ሥጋ እና ደም ስለሚጸናው መንፈሳዊ አንድነት ሰላም መሆን ልመናን እናቀርባለን፡፡ “አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር በይቅርታው አንድ ያደርገን ዘንድ ሰላምን እንማልዳለን” ይላል፡፡ የቅድስት ማኅበር አባላት ስለ ሆኑት ስለ ሐዋርያት፣ ስለ ሰማዕታት፣ ስለ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ስለ ሊቀ ጳጳሱ፣ ስለ ቀሳውስት… እያልን ከመጸለያችን በፊት ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እግዚአብሔርን እንለምነዋለን፡፡

የእግዚአብሔር መንገድ ጽድቅ፣ ፍቅር፣ ሰላም በአጠቃላይ በጎ ሥራን ሁሉ መሥራት ነው፡፡ የቅድስና ሕይወት ማለት በቅድስና መመላለስ ማለት ነው፡፡ የቅድስና ሕይወት የሰላምን ሕይወት በሚመሩ መካከል ያለ ሀብት ነው፡፡ 

ሰላምን መከተል ተግባራዊ የሆነ የቅድስናን ኑሮ በክርስቶስ ሆኖ ከመምራት ውጭ ምን ሆኖ ሊታሰብ ይችላል? እርሱ ሰውን ወዳጅና የሰላም ንጉሥ ነው፡፡ ዓለም ቢሸሹት ይከተላል፡፡ ቢከተሉት ገደል ይሰዳል፡፡ በዓለም ውስጥ ስንኖር አኗኗራችን እንደ ዓሣ ምግብ በብልሃት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የዓለም ክፋት ትዝ እያለን ወደ ዓለም የምንመለስ ከሆነ በኀጢአቷ ታጠምደናለች በዓለም ውስጥ እየኖርን ግን ዓለምን ስንርቅ በቅድስና ሕይወት መኖር ይቻለናል፡፡ አበው ‹‹በእባብ ማሳት ምክንያት በበደልን ጊዜ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ራቅን ደስታ ካለባት ከገነትም ወጣን አንተ ግን ለዘለዓለሙ አልጣልኸንም፤ በቅዱሳን ነቢያትህ ጎበኘኸን እንጂ በኋላ ዘመንም በጨለማና በሞት ጥላ ለምንኖር ለእኛ ታየህልን  የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን በእጅ ላይ አበራህ፡፡›› (ቅዳሴ ዘባስልዮስ) እያሉ አጥተነው የነበረውን የቅድስና ሕይወት እንዴት እንደተመለሰልን ይገልጻሉ፡፡

 

Read 1741 times