Saturday, 02 January 2021 00:00

የዐደባባይ በዓላት መንፈሳዊነትና ተግዳሮቶቻቸው

Written by  በዲ/ን ዶ/ር አክሊሉ ደበላ

Overview

መግቢያ እግዚአብሔር አምላካችን  ለሰው  የሚያስፈልጉ ምድራዊ ጉዳዮችን  ከሰው ልጅ መፈጠር በፊት ያዘጋጀለት ሲሆን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን አንድ ስጦታ ግን ከሰው መፈጠር በኋላ ፈጥሮለታል። ከሰው ልጅ መፈጠር በኋላ ለሰው ልጅ የተሰጠው ይህ ውዱ ስጦታ ዕለተ ሰንበት ነው። ሰውን በራሱ አምሳል ፈጥሮ የጌትነቱ ምሳሌ አድርጎ በምድር ላይ ያሰለጠነው አምላካችን ይህችን የተቀደሰችውንም ሰንበት ለዕረፍት በማድረግ አብነቱን ይከተል ዘንድ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በዚህች ቀን ከሥራው ዐረፈ።  ዓርብ የተፈጠረውን አዳም ዘላለማዊ ሕይወትና መንግሥት  የተገባው አድርጎ ሲፈጥረው የዚህን የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የዕረፍቱን ቀን  በራሱ በጌታ ዕረፍት በሰንበት ቀን አደረገው። በዚህም ከባሕርይ አምላክ የተሰጠው የጸጋ ጌትነት ታላቅ መሆኑን ገለጠው። ጌታችን በዳግም ምጽአት ለፍርድ ሲመጣ ሰማይና ምድር ሲያልፉ የሰው ልጅ ግን የማያልፍ ነው፤  ዕረፍት ያደርግባት ዘንድ የተሰጠችውም ሰንበት  ደግሞ የማታልፍ ናት።  ሰንበትን የለያት፣ የቀደሳት፣ ያከበራት፣ በዓል ትሆነን ዘንድ የሰጠን እራሱ የፈጠራት እግዚአብሔር ነው። ይህንን አስቀድሞ አርዓያ ሊሆነን በሷ  በማረፍ፣ ኋላም ትእዛዝ አድርጎ በሕገ ኦሪት አደለን። በዚህም የተቀደሰችውን በዓል ማክበር ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ያለው ዋጋ ምን ያህል ጽኑዕ እንደ ሆነ አስረዳን። አሠርቱ ትእዛዛትን በመስጠት ብቻ ሳይሆን  የኦሪቱ ሰንበት አከበባር ዝርዝር አፈጻጸም ምን መምሰል እንዳለበት ሥርዓት በመስጠትም ጭምር የተብራራ ነበር። ከዕለተ ሰንበት ባሻገር እስራኤላውያን በዓል አድርገው ማክበር ያለባቸው ጊዜያት የትኞቹ እንደ ሆኑ በሕገ ኦሪት ተደንግጎላቸዋል። ይህ ሂደት ሳይቋረጥ ወደ አዲስ ኪዳንም ተሸጋግሯል። ጌታችንም በሚያስተምርበት ወቅት በኦሪቱ ከተሰጣቸው ሕግ መንፈስ በወጣ መልኩ ሲያደርጉ የነበረውን አከባበር ነቅፎባቸዋል። ይህም የአዲስ ኪዳን በዓል አከባበር ምን መምሰል እንዳለበት ለማወቅ አንዱ ትልቅ ጉዳይ ነበር። ሌላው ደግሞ ሕግ ካልተሰጣቸው ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱ ምእመናን በበዓላት አከባበር ላይ የራሱ የሆነ ፈተና  የማምጣቱ ጉዳይ ነው።  በኋላ ላይ እንደምናየው እነዚህ ሁለቱ ፈተናዎች (ማለትም በቤተ አይሁድ የነበረ በዓል አከባበርና በቤተ አሕዛብ የነበረ በዓል አከባበር) ዛሬም ጭምር የኦርቶዶክሳዊ በዓላት አከባበር ፈተናዎች ሆነው አሉ። እነዚህ ዳራዎች ዛሬ ላይ ምን ዓይነት ችግሮች ይዘው እንደ መጡና ለነገዋ ቤተክርስቲያን የሚያስፈልጉ የመፍትሔ አሳቦችን ለመጠቆም ይረዱ ዘንድ ትናንትን ማየት አስፈላጊ በመሆኑ እስቲ እንመልከት። በተለይ በዓላት በቤተ አይሁድ ከዘመነ ኦሪት፤ የቤተ አሕዛብ ልማድ፣ በዓላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እንዴት እንደሚከበሩ፣ ዛሬ ላይ የአደባባይ በዓሎቻችን ምን እንደሚመስሉ እና መጨረሻም ላይ የነገው ምን መምሰል እንዳለበት ሐሳብ በማከል ለማቅረብ እንሞክራለን። በዓላት በቤተ አይሁድ ከሁሉ በፊት የቀዳሚት ሰንበት መከበር የብሉይ ኪዳን በዓላት ወኪልና ጥንታቸው ብትሆንም ብቸኛ በዓል ግን አልነበረችም። ከቀዳሚት ሰንበት ባሻገር ያሉት (ሰንበታት) ተብለው የተገለጡም ነበሩ። ዘሌ. ፳፫፥፴፪። ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸው መነሻ ያላቸውና የሚታወቁ በዓላትም ነበሩ። ለምሳሌ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን የሚያከብሩበት፣ የቂጣ በዓልም በመሆኑ በዓለ ናዕት እያሉ የሚጠሩት ፓሳሕ ብለው የሚጠሩት በዓለ ፋሲካ (ዘጸ.፲፪፥፩-፳፣ ዘሌ.፳፫፥፭-፰) እስራኤላውያን የአዝመራቸውን በኵራት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ቍርባን የሚያቀርቡበት በዓለ ሠዊት ወይም የመከር በዓል (ዘጸ.፴፬፥፳፪፣ ዘኁል.፳፰፥፳፮) ‹‹የዳስ በዓል›› የተባለውና አዝመራቸውን ሰብስበው ካስገቡ በኋላ ዳስ ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን በማመስገን የሚያከብሩት በዓለ መጸለት (ዘሌ.፳፫፥፴፱-፵፬) መለከቶችን በመንፋት በዓል አድርገው የሚያከብሩበት ቀን (ዘኁ.፳፱፥፩፣ ዘሌ.፳፫፥፳፫-፳፭) ሊቀ ካህናቱ   በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በመግባት  የመሥዋቱን ደም በታቦቱ መክደኛ ላይ ከረጨ በኋላ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ  በሚለቀቀውና የሕዝቡን ኃጢአት በሚሸከመው ሁለተኛ ፍየል  ላይ በመጫን የደኅንነት መሥዋዕት የሚሰዋበት የማሥተሥሪያ ቀን ወይም ዕለተ አሥተሥርዮ፤ በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን በክፉው ሐማ ተንኮል ሞት ተደግሶላቸው የነበሩ እስራኤላውያን፡ መርዶክዮስ ጾምና ጸሎትን በማወጅ በየጊዜው ፉሪ የተባለውንም ዕጣ እንዲጥሉ በማወጅ፣ በጾምና ጸሎት  እስራኤላውያን እንዲተርፉ የሆነበትን ቀን በማስመልከት የሚከበር በዓል፤ በመቃብያን የተጀመረው የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ ቀን (ዮሐ.፲፥፳፪) ሰውም መሬትም በማረፍ ለድሆች መልካም በማድረግ የሚከበርበት በዓለ ኅድገት (ዘጸ.፳፭፥፩-፯) የወር መግቢያ መባቻን የሚያከብሩበት ቀን (መዝ.፳፭፥፰-፲፪) የኀምሳ ዓመት በዓልን የሚያከብሩበት ኢዩቤልዩ (ዘሌ.፳፭፥፰-፲፪) እነዚህንና የመሳሰሉትን በዓላት እንዲያከብሩ ያዘዛቸው ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም በአጠቃላይ እስራኤላውያን በታዘዙት መሠረት በዓላትን አክብረዋል ማለት ግን አይቻልም። ይልቁንም በዘሌ.፳፫፥፩-፬ ላይ ‹‹..ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፡- ቅዱሳት ጉባኤያት ብላችሁ የምትጠሩአቸው በዓላቴ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤  ለእግዚአብሔር ቅዱስ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም። በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፣ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው የተቀደሱ ጉባኤያት ናቸው።›› ብሎ በዝርዝር ከሰጣቸው የበዓላት አከባበር በተጨማሪ ራሳቸውም ያልተፈለገ ነገር በመጨመር፣ ወግ በማብዛት፣ የበዓልን ጥቅም በዘነጋና ፈቃዳቸውን ለመፈጸም በተመቸ መልኩ ያከብሩ ነበር።  እግዚአብሔር የሰጣቸው በዓል ተግባረ ሥጋን በመተው መንፈሳዊ ጉባኤን በማድረግ፣ የነፍስ ተግባራትን በመሥራት፣ ልዩ መሥዋዕትን በማቅረብ፣ በታዘዙ ጊዜያት ወደ ቤተ መቅደሱ በመውጣት፣ ምስጋናን በማቅረብና በመሳሰሉ መልኩ የሚያከብሩበት ነበር።  ሆኖም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው  ሲያስተምር ግልጽ እንደ ሆነው መምህራነ አይሁድ የተለያዩ ወጎችን በሕዝቡ ላይ በመጫን አስጨናቂ የሆኑና ከመንፈሳዊ ዓላማ አንጻር ጥቅም የሌላቸውን የበዓል አከባበር ልማዶችን ባሕል አድርገው ነበር። ለምሳሌ መጽሐፋዊውን  ትእዛዝ በመለጠጥና ሌላ ትርጉም በመስጠት ዜና አይሁድን የጻፈው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን እንደ ገለጸው በዕለተ ሰንበት ወደ ሽንት ቤት እንኳን አይሄዱም ነበር። ከዚህም ባሻገር መጽሐፋዊ ያልሆኑ ከሕጉና ሥርዓቱ የወጡ የበዓል አከባበር ልምድም ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ  ሰንበትን ማክበርና መንፈሳዊነት የሚገኘው ፈቃደ እግዚአብሔርን በመፈጸም ሳይሆን በሆነ ርቀት ክልል ውስጥ በመገኘት አድርገው  ያከብሩ የነበረበትና የሰንበት መንገድ ብለው ይጠሩት የነበረ (ሐዋ.፩፥፲፫)፣ ሰንበት አያከብርም በሚል ጌታችንን ሲከሱበት የነበረው ፈውሰ ሥጋን መቃወም፣ የሰውን ሥጋዊ ድካም ያላገናዘበ እጅግ ጥብቅ ሸክምን በሕዝቡ ላይ መጫንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።   በዓላት በቤተ አሕዛብ ሕገ ኦሪት ያልተሰጣቸው፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልተባሉቱ አሕዛብ  ደግሞ በሌላ የበዓል ትርጉምና መልክ ሲያከብሩ ነበር። የዚህኛው የበዓል አክብሮት ምንጩ አምላክ ሳይሆን  ፍጡር፣ ግቡም መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ፣ አከባበሩም ሥርዓታዊ ሳይሆን ዘፈቃዳዊ የሆነ ነበር። የአሕዛብ በዓል መነሻው የጥንት ግሪክ አማልክት ሲሆኑ ሕዝቡም ለነዚህ አማልክት ማስታወሻ በሆኑ ቀናት ያስደስታቸዋል ብሎ በሚያስብበት መልኩ በዓል ያደርጋል። አማልክቶቹም በጊዜና ዓይነት ብዙ ቢሆኑም በጣም የታወቁጽና በኦሎምፐስ ተራራ ላይ ይኖራሉ ተብለው የሚታሰቡና ኦሎምፒያንስ ተብለው የሚጠሩት፣ በቀኖናቸው  በቍጥር አሥራ ሁለት ሲሆኑ ለእነርሱ መታሰቢያነት የሚውሉ በዓላት ነበሩ። አምልኮታቸውና በዓል አከባበራቸውም መጽሐፋዊ ወይም ምሥጢራዊ ሳይሆን ከፍርሐት የመነጨ ነበር።  አማልክቶቻቸውም በፍርሐት በተሞላ ምናባቸው የተፈጠሩ ናቸው። በዓሎቻቸውም አስጨናቂ ሁኔታ ሲገጥም፣ የተፈጥሮ ክስተት ሲዛባ፣ በአካባቢያቸው አንድን ለውጥ ሲያዩ መሥዋዕት በማቅረብ የሚያከብሩት ነበር።    ለምሳሌ፡-   √ የፀሐይ ሙቀት ሲያይል የፀሐይና ትንቢት፣ እንዲሁም የሳይንስና ሕክምና አምላክ አድርገው የሚያስቡት አጵሎስ ‹‹ተቈጥቶ ነው›› ብለው ያስባሉ፤ √ ባሕር ስትታወክ ‹‹በባሕርና አየር ላይ ይተነፍሳል›› ብለው የሚያመልኩት  የባሕር አምላክ ፖሲደን  ‹‹ተቈጥቶ ነው››። √ የሽብር አምላክ (Deimos), የፍቅር አምላክ Cupid (Eros)፣ የጦርነት አምላክ  የተባለው ማርስ (Ares)፣ የጥበብና ጦር አምላክ የሆነቸው Athena፣ የጉልበት አምላክ የሆነው  Kratos እና ወዘተ... እነዚህ አማልክት የሚታሰቡበት ቀን ቢኖራቸውም በዓላቸው መሥዋትን በማቅረብ የተወሰነ፣ ሥጋዊ ተድላ ደስታን መሠረት ያደረገ ነበር። ይልቁንም ሥራን የሚከለክል አልነበረም። በአብዛኛው  ልማደ አሕዛብን በማድረግ፣ ለወንጌልም ሆነ ለኦሪት ትእዛዝ የማይመች ድርጊትን በመፈጸም የሚከበር በዓል ነበር።  ምንም ልማድ ቢፈጽሙ፣ ምንም ሥራ ቢሠሩ የሚከለክልና ስሕተት እንደ ሠሩ የሚቈጥርባቸው ሥርዓት ስላልነበራቸው ክርስትና ተሰብኮ ወደ ክርስትና በተመለሱበት ጊዜ የራሱ ችግር ይዞ መምጣቱ አልቀረም።  በርግጥ እነዚህ ሁለቱም ወገኖች፡- አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ወደ ክርስትና በሚመለሱበት ጊዜ ወግና ልማዶቻቸውን ትተው ለወንጌል በሚመች መንገድ ለመሄድ ችግር ገጥሞአቸዋል።  በተለይ ክርስቲያናዊ ሥርዓትን ወጥ በሆነ መልኩ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ እንዲከናወን ለማድረግ የቀድሞ ልማዶቻቸው ፈተና መሆናቸው አልቀረም። ለምሳሌ፡- ቅዳሜን እንደ ሰንበት ያከብሩት ለነበረ ቤተ አይሁድ የጌታ ዕለት የተባለችውን እሑድን ለመቀበል፣ ግዝረትን በጥምቀት ለመተካት ተቸግረው ነበር። በቤተ አሕዛብም በወንጌል የታዘዙትን ይፈጽሙ ዘንድ፣  በኃጢአትና ጽድቅ፣ በሥርዓታዊና ኢ-ሥርዓታዊነት መካከል ያለውን ድንበር ያልተለማመደው  ሕይወታቸውና  ኢክርስትያናዊ  ልማዳቸው ብዙ አስቸግሯቸዋል። የኦሪትን ትእዛዝና ሥርዓት ለመፈጸምም ተቸግረዋል። እነዚህ የኋላ ምንጫቸው የግሪክ አማልክትን ማምለክና በዚህ ሂደት ውስጥ የተለመዱ አሕዛባዊ ልማዶች የሆኑ በሥልጣኔ ሽግግር የምዕራቡን ዓለም አስታክከው እየተላለፉ መሄዳቸው አልቀረም። በዓላት በክርስትና  ለዓለም የተሰበከችው  ወንጌል  ሕዝብና አሕዛብን አስታርቃ ለአንዲት መንግሥተ እግዚአብሔር የምታበቃ ናት። ይህን መንፈሳዊ ዕርቅ ለመፈጸም የሕዝብና አሕዛብን ልማድ ማስታረቅ፣ የሁለቱን መንፈሳዊ ዝንባሌ ፍጹም መንፈሳዊ ወደ ሆነው ክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት ማስገዛት የወንጌል ትምህርት ኃላፊነት ነበር። በመሆኑም የቀድሞ በዓሎቻቸው መንፈሳዊ በሆኑ ክርስቲያናዊ  በዓላት ተተክተዋል። ለምሳሌ ከቤተ አይሁድ ብንወስድ በበዓለ መጥቅዕ - ቅዱስ ዮሐንስ፣  በሠርቀ ወርኅ - ልደተ ክርስቶስ፣ በበዓለ መጸለት - በዓለ ጥምቀት፣  በበዓለ ፍስሐ - ስቅለተ ክርስቶስ፣ በበዓለ ፋሲካ - በዓለ ትንሳኤ፣ በበዓለ ሠዊት -  በዓለ ጰራቅሊጦስ፣  በጾመ አስቴር - ጾመ ረቡዕ፣ በጾመ ዮዲት - ጾመ ዓርብ፣ በጾመ ሙሴ -ጾመ እግዚእ ተተክተዋል።   ከክርስትና በፊት በነበራቸው ልማድ አሕዛብ ብዙ አማልክቶቻቸውን ያስቡ በነበረው ልማድ እንዳይቀጥሉ፣ የበዓል ምኞቶቻቸው አሕዛባዊ ሆነው እንዳይቀሩ፣ የሕዝቡን የረዥም ዘመን ፍቅረ ጣዖት ለማስተው በነዚያ ዕለታት በጣዖታት ስም ተሰይመው ይከበሩ የነበሩ ዕለታትን  ቀደምት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ስም እየለወጡ እንዲያከብሩ አድርገዋል። ለምሳሌ፡-  የባሕር አምላክ ፖሲዶንን ያከብሩ የነበረበትን ዕለት ወደ ክርስትና ከተመለሱ በኋላ ኒኮላዎስ  የተባለውን ቅዱስ በየዓመቱ ሲያከብሩበት፣ የጦር አምላክ የሚሉትን ኦሪስን በሚያከብሩበት ዕለት ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተክተው ያከብሩበታል።     እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባ ነጥብ በዓል የማክበር አስፈላጊነት በብሉይ ኪዳን የነበረና በሐዲስ ኪዳንም የቀጠለ፣ ራሱ ጌታችን የሰንበትን አከባበር በተመለከተ አይሁዳውያን ሲፈጽሙ የነበረውን ስሕተት አርሞ ክርስቲያናዊውን አከባበር ምንነት ከመንፈሳዊ ዓላማው ጋር እንዴት መዛመድ እንደሚገባው አስረድቶ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ቀናውን መንገድ ማሳየቱን ነው። ሆኖም የሰንበት አስፈላጊነት ላይ ለእስራኤል ዘሥጋ የሰጠውን ትእዛዝ ለእስራኤል ዘነፍስም አጽንቷል። ከሱ የተማሩ ሐዋርያትም፣ ኋላ የተነሡ አባቶችም ይህን አምላካዊ ትእዛዝ ፈጽመዋል። አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም ወደ ፊት ለሚመጣ የክርስትናው ዓለም የሚበጀውን ቀኖና ቀንነው፣ ሥርዓት ሠርተው፣ በቍጥር ሰፍረው፣ በጊዜ መጥነው ሰጥተውናል። ለምሳሌ፡- የዕለተ ሰንበት አስፈላጊነት፣ የክርስቲያኖች የሰንበት አከባበር መልክ፣ የትንሣኤና የመሳሰሉትን መቼና እንዴት ሊከበሩ እንደሚገባ ከጥንት  ከአንደኛ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሊቃውንት ብዙ አስተምረውበታል። ይልቁንም ሠለስቱ ምዕትና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ላይ የተገኙ ሊቃውንት በዓላትን  አስመልክቶ  የክርስትና ዓለም መከተል የሚገባውን መንፈሳዊ መርሕ አብራርተው አስቀምጠዋል። ለምሳሌ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ሰንበተ ክርስቲያን ያስተማረውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ክርስትና ወደ ዓለም ሲስፋፋም ይህን ትምህርተ አበው መሠረት አድርጎ የሄደ በመሆኑ በተለይም ደግሞ በኦርቶዶክሱ ዓለም የበዓላት አከባበር ወጥነቱን ሳይለቅ፣ በሚከበሩበትም ወቅት የሥርዓት ልዩነት ሳይጎላባቸው ብዙ ቆይቷል። ለምሳሌ በሁሉም አኀት አብያተ ክርስቲያናት  የልደተ እግዚእ እና በዓለ ጥምቀት  እስከ አራተኛ መ/ክ/ዘመን ድረስ በአንድነት ይከበሩ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአደባባይ በዓላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ቀኖና የራሱ የሆነ መልክ አለው።  ለምሳሌ ቅዳሜና እሑድን እንደ አንድ ቀን አድርጋ ስታከብር  አከባበሩም እንደ አይሁድ ሰውን እንዳይጫን ሥራም እንዳይፈቱ፣ ይልቁንም እንደ ክርስቲያን  መንፈሳዊ ሥራን እንዲሠሩ ታስተምራለች። እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሰንበት፡- ዕረፍት የሚደረግባት፣ የሚገባ መንፈሳዊ ሥራ የሚሠራባት፣ በቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ  የታመመውን በመጠየቅ፣ የተቸገረውን በመርዳት በመማማርና የመሳሰሉትን በማድረግ ከአይሁድ ልዩ በሆነ መልኩ የሚከበርባት ናት።   የበዓላቱም አከፋፈል √ ሳምንታዊ - በየሳምንቱ ይታሰቡ ዘንድ በሕግና ቀኖና የተደነገጉ ቀዳሚት ሰንበትና እሑድ፣ √ ወርኀዊ በዓላት - የጌታችንን በዓል ሥጋዌውን መሠረት በማድረግ፣ ጽንሰቱንና ልደቱ በማሰብ ወር በገባ በሃያ ዘጠነኛው ቀን፣ ከፍጡራን ሁሉ በላይ የሆነችውን  የእመቤታችን ዕረፍቷንና የመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤቷን መክበር በማሰብ በየወሩ በሃያ አንደኛ ቀን፣ በማዕረግ ከመላእክት ሁሉ የሚልቅ የቅዱስ ሚካኤልን  ገቢረ ተዓምር በማሰብ ወር በገባ በአሥራ ሁለተኛው ቀን  ይታሰባሉ። √ ዓመታዊ በዓላት - ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚታሰቡ፣ ልዩ መታሰቢያ የሚደረግባቸው በዓላት ናቸው። እነዚህም በኢይዓርግና ኢይወርድ ተወስነው በየዓመቱ በተለያየ ቀንና ወር የሚውሉት እንደ ስቅለት፣ ሕማማት፣ ትንሳኤ፣ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ዕርገትና ጰራቅሊጦስን የመሳሰሉ ዓዋድያት በዓላት እና ሁል ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ ባለው የታወቀ ቀን ላይ የሚውሉ ትስብእትን፣ ልደትን፣ ጥምቀትን፣ መስቀልን፣ በዓላተ ቅዱሳን፣ ደብረ ታቦርን የመሰሉ ዓዋድያት ያልሆኑ በዓላት ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ።  በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ለጌታችን በዓላት ልዩ ትኩረት ሰጥታ ታከብራለች። እነዚህም ዓበይትና ንዑሳን በዓላት ተብለው ይከፈላሉ። ዓበይት  በዓላት የሚባሉት፡- መጋቢት ፳፱ የሚከበረው በዓለ ትስብእት (ጽንሰት)፣ ታኅሣሥ ፳፱ የሚከበረው በዓለ ልደት፣ ጥር ፲፩ የሚከበረው በዓለ ጥምቀት፣ ነሐሴ ፲፫ የሚከበረው በዓለ ደብረ ታቦር፣ በዓለ ሆሣዕና፣ በዓለ ስቅለት፣ በዓለ ትንሣኤ፣  በዓለ ዕርገትና በዓለ ጰራቅሊጦስ ናቸው። ንዑሳት በዓላት የሚባሉት ደግሞ፡- ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ በዓለ ጌና (ታኅሣሥ ፳፰)፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ዘይትና መስቀል ናቸው። ከዓበይት በዓላት  ውስጥ ደብረ ታቦርና ጥምቀት፣ እንዲሁም በንዑሳት በዓላት ውስጥ ደግሞ በዓለ ጌና፣ ቃና ዘገሊላ እና መስቀል በአደባባይ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚከበሩ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑት ብሔራዊ በዓላት ሆነው ሀገራዊ ዕረፍት ታውጆ የሚከበሩ ናቸው። በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ በዓላት ያልሆኑ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትና የአደባባይ በዓላት ያልሆኑ የጌታ በዓላት ከድምቀታቸው የተነሣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመንገዱ ሞልቶ፣ በከተማው ጎልቶ የሚታይባቸው በዓላት ብዙ ናቸው። ከዚህም ባሻገር እንደ ሀገርም እንደ ቤተ ክርስቲያንም የአከባበር ድምቀታቸው የታወቀው፣ ባላቸው የከበረ ቃል ኪዳንና መንፈሳዊ ዋጋ ብዙ  ሕዝበ ክርስቲያን  ከመላ ሀገሪቱና ባሕር ማዶ በየዓመቱ ሄዶ የሚያከብራቸው ቅዱሳት መካናት፡- ገዳማትና አድባራት እንደ አክሱም ጽዮን፣ ቁልቢ ገብርኤል፣ ግሸን ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ደብረ ሊባኖስ ወዘተ የመሳሰሉ አሉ። የአደባባይ በዓላት ተግዳሮቶች በመሠረታዊነት የአደባባይ በዓላት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊቷ ተግባራዊ ማስተማሪያ መንገዶች ናቸው።  የያዙት መንፈሳዊ ዓላማ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ሠርጾ ፍሬውም በእጅ የሚዳሰስ፣ በዓይን የሚታይ፣ በጆሮ የሚሰማ፣ የሚቀመስ፣ የሚሸት፣ ከምንም በላይ በሕይወት የሚታይ መሆኑ የሚገለጽበት መንገድ ነው። ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን ከሚሉ ቤተ እምነቶች በተለየ መልኩ ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር አምስቱንም የስሜት ሕዋሳትን የምትጠቀም ቤተ ክርስቲያን ይህችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመሆኑ ማሳያው በክርስትና ትምህርት ያበቡ በዓላቶቿ ናቸው።  እነዚህ በዓላት በዘመናት ውስጥ የታዩና ተለዋዋጭነትን ያሸነፉ፣ መንፈሳዊ ማኅቀፋቸው በትክክል የሚታወቅ፣ በሁሉም ሕዝብ ውስጥ በጊዜና በአከባበር ሁኔታ ግልጽና የጋራ አረዳድ የፈጠሩ፣ ትውልድን የቀረጹ፣ ላለፈው ትውልድ ታሪክ፣ ለሚመጣ ትውልድ ተስፋ ሆነው ያገለገሉ፣ ወንጌል ሆነው የሰበኩ፣ መጽሐፍ ሆነው የተነበቡ፣ ቅርስ ሆነው የታዩ ናቸው። እነዚህ የአደባባይ በዓላት ከኢትዮጵያ ምድር የቅዱስ ያሬድ ጥዑም ዜማዎች ወደ ሰማይ ያረገባቸው የማዕጠንቱ አደባባዮች፣ ዓለም ኢትዮጵያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኘበት ገጾች፣ ኢትዮጵያም ለዓለም ወንጌልን የምታስተምርባቸው አትሮኖሶች ናቸው።  በነዚህ በዓላት የተነሣ ብዙ ሺህ ወንድሞቻችን ወደ ክርስትና ተመልሰው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል፣ ብዙዎች ወደ እምነቱ ባይመጡም በኦርቶዶክሳዊ ማንነት ቀንተው በአክብሮት  ቆመዋል፣ መልካም ልብስነታቸው ከቤተ ክርስቲያን ተርፎ  ለሀገርም መድመቂያና የክብርና የሞራል ብርድ የማያስመታ ሆኖ ዘልቋል። ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ጭምር የቤተ ክርስቲያናችን የአደባባይ በዓላት ምትክ የሌላቸው የሀገሪቱ ደማቅ በዓላት፣ ኩራትና እሴቶች ናቸው። በሕዝበ ክርስቲያኑም ዘንድ ያላቸው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው። መንፈሳዊ አገልግሎታቸውም የላቀ ነው። ሆኖም ዘመኑ የራሱ የሆነ ፈተናንም ደቅኖባቸዋል። በተለይ ዓለማችን፣ ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ካሉበት ወቅታዊ ቁመና አንጻር ስንመለከት የችግሮቹን ክብደት አጉልቶ ስሚያሳየን የመፍትሔዎቹን አስፈላጊነት እንረዳለን። የአደባባይ በዓላት  መንፈሳዊ ይዘት ፈተናዎች እንደ አጠቃላይ እየወደቀ ከመጣው የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ባብዛኛው የተያያዘ ቢሆንም ሌሎች ተጨማሪ ግፊቶችም አሉበት። እንደ አጠቃላይ ግን ከላይ የገለጽናቸው ሐዋርያት ወንጌልን በሰበኩበት ጊዜ የነበሩ ሁለቱ ፈተናዎች ዛሬም ጭምር መልካቸውን ለውጠው ያሉ ይመስላሉ።  ለምሳሌ፡- በቤተ አይሁዳዊ  ጠባያቸው ለበዓላት አከባበር ችግር እየፈጠሩ ያሉት ልማዶች በበዓል ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ ያለ መሥራት ዝንባሌዎች፣ በሰንበት የተቀዳ ውሃ የተወቀጠ ቡና የማይጠጡ፣ ወንዝ የማይሻገሩ፣ መጽሐፍ የማይጽፉ የማይደጉሱ፣ ልብስ የማያጥቡ ...ወዘተ አሉ። ሰንበት ነው ብሎ እነዚህን አለማድረግ ግን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አይደለም፣ ልምዱም የቤተ አይሁድ ልማድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወር ውስጥ ካሉት ቀናት ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ ሁሉም ክርስቲያን ሥጋዊ ሥራውን አቁሞ እንዲያከብራቸው የምታዝዘው ሁለቱን ሳምንታዊና ሦስቱን ወርኃዊ በዓላትን ብቻ ነው። ሌሎቹ ቀናት በየአጥቢያ ምእመናን የሚከበሩ ናቸው። በሁሉም ቀናት ሥራ ፈትቶ መዋልን ቤተ ክርስቲያን አላስተማረችም። በቤተ አሕዛባዊ ገጽታው ደግሞ ያለንበት ወቅት የበዓል አከባበር ችግሮች እጅግ የበዙ ናቸው። ዛሬ ላይ የአሕዛባዊ ልማዶች መግቢያ መንገዶች ብዙ ናቸው። ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓትና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት ውጭ ዘመኑን ተገን በማድረግ እየወረስናቸው ያሉ  ልማዶች በርካታ ናቸው። የመገናኛ ብዙኃን፣ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ ፊልሞችና የስፖርት መዝናኛ አማራጮች፣ ሥርዓተ ትምህርትና የንባብ ምንጮቻችን ባሳደሩብን ተጽዕኖ የተነሣ ከኦርቶዶክሳዊነት በወጣ መልኩ የምናሳልፍበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በመንፈሳዊነት ታሽተው የመጡልን ክብረ በዓሎቻችን  የመንግሥት ፖለቲካዊ ፍላጎት እሾህ ሆኖ ሲወጋቸው ይታያሉ። የነፍስን ፍሥሐ ሲያመጡልን የኖሩትን በዓላት በመጠጥና ስካር፣  ለፍትወት ቀጠሮነት ያዋልናቸው  ብዙዎች ነን።  ከጊዜ ጊዜ ግልጽ እየሆነ ያለው ሥልጣንን ተገን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቷን እየበደሉ ያሉ አሉ። ይኸውም ይዞታዋቿ የሆኑ ባሕረ ጥምቀትና ሌሎችን የአደባባይ ማክበሪያ ቦታዎቿን በመንጠቅና ለሌሎች አብያተ እምነቶች መስጠት በብዙ የሀገሪቷ ክልሎች እንደ ወረርሽኝ የተዛመተ በሽታ ሆኗል። ይዞታዎቿን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚነጥቁበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ አስቂኝና  በሞራል ሚዛን ሲለካ አሳዛኝ ነው። አብዛኞቹ የተነጠቁት ይዞታዎች የማይመለሱ ቢሆንም በስንት የሕዝብ ጩኸት የሚመለሱትም ታሪካዊ ውለታ እንደ ተፈጸመላት አድርገው ብዙ ማስታወቂያ ይሠሩበታል። ቢሆን ቢሆን እስከዚያ ድረስ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ላባከኑበት ጊዜና ጉልበት ላደረሱበት የሥነ ልቦና ስብራት ይቅርታ ጠይቀው መሆን ነበረበት። ይዞታዎቿን ሲቀሙ ቦታውን ቢመልሱም ባይመልሱም የሕዝቡን አእምሮና ትኩረት ይዞታው ላይ በመትከል በዓላቱን ሊያከብራቸው የሚገባበትን መንፈሳዊ ይዘቶች ላይ ትኩረት እንዳያደርግ፣ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን በደሎች ላይ ጊዜ ወስዶ እንዳያስብባቸው፣ ከቦታ ውጭ ያሉ ትላልቅ ጉዳዮችን እንዳያነሣ፣ የሥነ ልቦና ውጊያ አካልም ናቸው። ሌላው ችግር ቤተ ክርስቲያናችን በዋናነት ለመንፈሳዊ ዓላማ የምታከብራቸውን ቅዱሳት በዓላትን ዋና ትኩረቱን ቱሪዝም የማስመሰል ድባብ አለ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቋ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ ናት። ይሁንና ቤተ ክርስቲያን እነዚህን በዓላት የምታከብረው የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ እንጂ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ብላ አይደለም። ሕዝቡም የሚወጣው የቱሪዝምን በዓል ለማክበር ሳይሆን መንፈሳዊ በዓልን ለማክበር ነው። ስለዚህ  ከመንፈሳዊነት በጎላ መልኩ ቀዳሚ ጉዳይ መስሎ በብዙ ሚዲያዎች የሚሰማው ቅኝት  አንዱ አስተዛዛቢ ጉዳይ ነው። ቱሪዝሙ ከበዓሉ መንፈሳዊ ትርጓሜ በኋላ የሚመጣ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ አለበት። ሚዲያዎች በአንድ ጎኑ የቱሪዝም እሴትነቱን ብዙ እያስተጋቡ የቀረውን ጉዳይ ደግሞ  አርቲስቶችን፣ ዘፋኞችን፣ ታዋቂ ናቸው ብለው የሚያስቡትን ሰዎች የሚጋብዙበት፣ ቀኑን በሙሉ ስለ እነርሱ ሕይወት ታሪክና ሙዚቃቸውን የምንሰማበት ያደርጉታል።  በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ ምድራዊ ዘፋኞችን ብሔራዊ ጣቢያዎች ላይ እየሰማን ውለን በዓል እንዳከበርን ይታለፋል። የመርሐ ግብር ይዘቶቹም ከበዓላቱ መንፈሳዊ ተልእኮ የወጡ ሥጋዊ መዝናኛና ፌዝ የተሞሉ፣ መብላትና መጠጣትን፣ ጭፈራን እንደ ድምቀቱ መመዘኛ የሚመለከቱ፣ በልደትና ትንሣኤ ፍጹም ሰማያዊ በዓላት ላይ የክርስትና ተቃራኒ በሆኑት የዘፈን ኮንሠርቶች ማስታወቂያ የሚያጨናንቁ፣ በዓላቱን አስታክከው ንግድን ለሚያጧጡፉ ተቋማት የሚያስተዋውቁትን ያህል የቤተ ክርሰቲያኒቷን እሴቶችና ትምህርቶች ለማስተዋወቅ ያልተሠለፉ የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች በዝተዋል። ሌላው የሚዲያዎቹ ችግር የበዓላቱን ማኅበራዊና ባሕላዊ ጎኑን እያጎሉ ነገረ ሃይማኖታዊ ጭብጦቹ ተዳፍነው የሚታለፉበት አጋጣሚ ብዙ ናቸው። ወጣቶቹ እንዴት  እንደሚጨፍሩ፣ እናቶች በዓላቱን የሚያስታውሱ ምግቦችን እንዴት እንደሚያዘጋጁ፣ ጎልማሶቹ ምን  ምን ባሕላዊ ትውፊትን እንደሚከውኑ ወዘተ.. የበዓላቱ ዋና ጭብጥ ሆነው ያልፋሉ። ከምንም በላይ በዓላቱ ሃይማኖታዊ መሆናቸው ተረስቶ ታስቦባቸውም ይሁን በመዘንጋት ተግባራዊ ትኩረት አጥተው ይታለፋሉ። ይህም በመሆኑ ሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወቱን ስለ ማሻሻል፣ ከበዓላቱ በረከትን ስለ ማግኘት ሳይሆን እንዴት ተደስቶ ማሳለፍ እንዳለበት ጥረት እንዲያደርግ ያለማምዳሉ። በርግጥ ውስጣዊ ድክመቱ በዋናነት የራሱ የሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ ዝንባሌ ድክመት ነው። ለጥምቀት ሄዶ  ባሕረ ጥምቀቱ ጋር ተገኝቶ፡  ነገር ግን ጥምቀትን ሳያከብር የሚመለሰው ብዙ ሰው ነው። ጀበና ሲሰብር፣ ሎሚ ሲወረውር፣ ሥጋውን የሚያስደስት ጨዋታዎች ሲጫወት ውሎ ከጥምቀት የሚገኘውን መንፈሳዊ እርካታ ያገኘ መስሎት ይመለሳል። ሳያውቀው ከቤተ ክርስቲያንና ከኦርቶዶክሳዊ ማንነት ተቃራኒ ቆሞ ይገኛል። ይህም እንደ ምእመንም እንደ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለ ይጠቁማል።  በአጠቃላይ የአደባባይ  በዓሎቻችን በአሁኑ ጊዜ ውጫዊ ተጽዕኖና ውስጣዊ  ድክመት ተዳምረው መንፈሳዊ ድምቀታቸው ላይ ትልቅ ፈተና ደቅነውባቸዋል። ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን ችግሮች አስቀድማ ተረድታ ልጆቿን ለመፍትሔ ማሰለፍ ላይ ጊዜውን የሚመጥን ዝግጅት ያደረገች አይመስልም። ችግሮቹም ከጊዜ ጊዜ እየበዙ እንጂ እየቀነሱ፣ እየሰፉ እንጂ እየጠበቡ አይደለም። ይህም በመሆኑ የነገው ትውልድ ላይ የሚኖረው አደጋ  ከፍተኛ ነውና ዛሬውኑ መፍትሔ ያሻዋል። የማጠቃለያ አሳቦች ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነው። የምታደርጋቸው አገልግሎቶችም ይህን ሰማያዊ ተልእኮዋን መሠረት ያደረጉ ናቸው። የሰማያዊ ቤት አንባሳደር ሆና ፍጥረቱን በምታገለግልበት በዚህ ምድር፡ ሕይወቷ የሚመስለው  የወከለችውን  ሰማያዊ  ዓለም እንጂ የቆመችበትን ምድራዊ ዓለም አይደለም።  የሷ ገንዘብ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ይህንን ማንነቷን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።  ከዚህ የተነሣ በዓላቷም የዚህ ተልእኮዋ አካል ናቸው።  ታቦታቱን ይዛ ወደ አደባባይ ስትወጣ፣ መስቀሉን ይዛ ሕዝብ ጋር ስትሄድ፣ ከበሮና ጸናጽሉን፣ ልብሰ ተክህኖና ነጠላውን ይዛ  በየጥምቀተ ባሕሩ ስትገኝ የቆመችለትን ወንጌል ለመስበክ ነው። ከሰው ፊት ይዛ የምትቆምባቸው እሴቶቿ ሁሉ እሷን የሚሰብኩ፣ እሷን የሚገልጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የአደባባይ በዓላቱም መድመቅና መደብዘዝ፣ ሥጋትና ተስፋ መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ከምንም በላይ መሥራት ያለባት መንፈሳዊ ይዘቱ ላይ እየላላ ያለውን የሕዝቡ ሕይወት ላይ ነው።  በርግጥ የምታከናውነውም ሥርዓት  ሁሌም መንፈሳዊ ይዘቱ የተጠበቀ ነው። ይሁንና በዓሏን ለማክበር የሚመጣ ማንኛውም ሰው የእርሷን መመዘኛ እንዲጠብቅ የማድረግ ኃላፊነቱ የእርሷው ነው። ወደ ሰርግ ቤት የሚሄድ ሰው ለሙሽራና ለሰርጉ የሚያስፈልገውን አለባበስ የመልበስ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓላት የሚታደሙ ሰዎች ሁሉ ለእርሷ የሚገባውን ሥርዓት ጠብቀው የመሄድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። በአለባበስ፣ በአዘማመር፣ በአካሄድ፣ በሌላ ማንኛውም ተሳትፎ ቤተ ክርስቲያን የምታዘውን ብቻ አድርገው እንዲጓዙ ለማድረጉ መብቱ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት።  በተለይ ደግሞ ምእመኗ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ሌላው ጉዳይ ይዞታዎቿን በተመለከተ የሕዝበ ክርስቲያኑን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም እንዲቆም ማድረግ፣ ማነቃቃት ያስፈልጋል። ይህንም በማንኛውም ቦታ ላለው ችግር ሁሉ  ኦርቶዶክሳዊ ተቆርቋሪነት እንዲኖረው ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። በዚህም ታላቅነቷን፣ ተደማጭነቷን፣ የራሷን መፍትሔ  በራሷ መከተል የምትችል መሆኗን ማሳየት ይኖርባታል። ሕዝቡ ላይ ከተሠራ በኋላ ከመንግሥትና ሌሎችም አካላት ጋር ሕጋዊ መንገድን ተከትላ የተወሰዱባት ሀብቶቿን ማስመለስ፣ ማስከበር ያስፈልጋል። ለዚህም ደግሞ የተደራጁ የሕግ ባለ ሙያዎች፣ የሚዲያ ባለ ሙያዎችና መሰል የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ማሰባሰብና ማመካከር ያስፈልጋል። የበዓላቱን አካባበር አስመልክቶ ሚዲያዎች የሚሰጡትን ሽፋን ይዘት ቤተ ክርስቲያናችን ትኩረት ሰጥታ ማየት ይኖርባታል። መገናኛ ብዙኃን ስለ በዓላቱ ሲዘግቡና በቀጥታ ሲያስተላልፉ፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲተላለፍላት በምትፈልገው መልኩና ሃይማኖታዊ ተልእኮዋን ባገናዘበ መልኩ መሆን ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነና  ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ተቃራኒ የሚቆም ሚዲያም ካለ በሚዲያዎች ላይ አቋም መያዝ ትችላለች። በዓላቱን መቅረጽ፣ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ በቦታው ተገኝቶ መዘገብ እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ይሁንታ ያሻል። ይህን ለማስተካከልም በዓላትን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የምትከተለውን መርሕ በመመሪያም ጭምር አዘጋጅታ ይፋ ማድረግ፣ ከሚመለከታቸው አካላትም ጋር ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ከበዓላት በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ፕሬስ ኮንፍረንሶችን እያዘጋጀት ስለ በዓሉ አከባበር፣ ምን እንዲዘገብላት እንደምትፈልግና ጋዜጠኞች መከተል ስላለባቸው ሥርዓት መግለጫ ብትሰጥ መልካም ነው። ከዚህ ባለፈም በየሚዲያው ላሉ ጋዜጠኞች በየተወሰነ ጊዜ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ብትሰጥ ከሚድያዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጥበቁም በላይ፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማያውቁትም ማሳወቅ ይሆናል። ከበዓላቱ ረድዔትና በረከት ያሳትፈን!
Read 1707 times