የሀገሪቱ መንግሥት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና የምእመናንን ደኅንነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት የሃማኖት አባቶች ጥሪ አቀርቡ፡፡
በቅርቡ ማለትም ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ኪረሙ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥረ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች አሸባሪው ፀረ ሰላም ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ጥቃት ቁጥራቸው የማይናቅ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ለሞትና ለስደት መዳረጋቸውን የሃማኖት አባቶቹ አንስተው በተጨማሪም በከፍተኛ ወጭ የተገነቡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በዝርፊያና በቃጠሎ መውደማቸውን አስረድተዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ አያይዘውም “ወቅታዊ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያን ችግር ውስጥ እንድትወድቅ የሚፈልጉ የአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ድርጊት ተዳምሮ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥሏታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የምእመናንና የአብያተ ክርስቲያናትን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ ለችግር የተጋለጡ አብያተ ክርስቲያናትንንና ምእመናንን ለመጎብኘት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የደኅንነት ድጋፍ እንዲያደርግልን ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘንም” ሲሉም የሃይማኖት አባቶቹ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በክልሉ መንግሥት በኩል አልፎ አልፎ ከሚገባው የድጋፍ ቃል ውጭ ተጨባጭ መፍትሔ ማምጣት እንዳልተቻለም አክለዋል፡፡
የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት አካባቢ የጦርነት ቀጠና በመሆኑ በዚህ የተነሣ በፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ወረዳው ሀገረ ስብከቱ አጣሪ ልዑክ መላክ አልቻለም ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ ይሁን እንጂ ወረዳ ቤተ ክህነቱ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቁን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ “በአካባቢው ያገለግሉ የነበሩ ካህናት በመሞታቸውና በመፍለሳቸው የተነሣ ከዚህ ቀደም የነበረው አገልግሎት ተዳክሞና አብያተ ክርስቲያናትም ተዘግተው ይገኛሉ ካሉ በኋላ የሀገረ ስብከቱ የሃማኖት አባቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው የግል ጉዳያቸውን የሚያራምዱና ቤተ ክርስቲያንን እያስጠቁ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም መክረዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ አክለውም “የቤተ ክርስቲያንን ውድቀት የሚመኙ በርካታ አካላት መኖራቸውን በመረዳት ለእነዚህ ፀረ- ኦርቶዶክስ ኃይላት ክፍተት መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር እጅግ ውስብስብና አሳሳቢ መሆኑን መንግሥት ተረድቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባና ቤተ ክህነትም ከመንግሥት ጋር ተነጋግሮ የአካባቢው ፀጥታ እንዲከበር ጥረት ቢያደርግ መልካም ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ ኮማንደር ታሪኩ ስልክ የደወልንላቸው ቢሆንም ስልክ ባለማንሣታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡