Friday, 06 November 2020 00:00

ግብረ ሰዶማዊነት

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ

Overview

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር በማይመረመር ጥበቡ ካለመኖር ወደ መኖር በአርአያው እና በአምሳሉ ተፈጥሯል። ሠለስቱ ምዕት በሃይማኖተ አበው «ወኵሉ ሰብእ ዘበአርአያ እግዚአብሔር ወበአምሳሉ እሙንቱ ተፈጥሩ፤ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አርአያ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው።» (ሃ.አ.፲፱÷፴፫) በማለት እንደ ገለጹት። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን የሚታወቀው ከአካላዊ ተፈጥሯችን ባለፈ በለባዊት፣ በነባቢትና በሕያዊት ነፍሳችን ነው። ይኸውም በዚህ ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ከሸክላው ይልቅ ሸክላ ሠሪውን የምናደንቅበት አንዱ ምክንያት ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ነው። እንዲሁም ወንድና ሴት አድርጐ መፍጠሩም እጅግ ድንቅ  ነው። የሁለቱ ጾታ የራሱ የሆነ የወንድነት ባሕርይ ከሴትነት ተፈጥሮ ጋር ፈጽሞ መለያየት፣ እርስ በእርስ የመፈላለግ እና መሳሳብ፣ የጾታ ልዩነትን መርምረን በመረዳት ፈጣሪን ማድነቅ ይገባል።  ቅዱስ ዳዊት «ግሩም እና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች» (መዝ.፻፴፱÷፲፬) ብሎ የተናገረውም ይህን ለማስረዳት ነው። የሰው ጾታ ምንነት ዐቅድ ወይም ንድፍ ተኮር (Teleological or design focused) የሆነው በእግዚአብሔር ውሳኔ ነው። ወንድ እና ሴት የመሆን ልዩነት ማለት ወንድ በአካልም በመንፈስም የወንድነትን፣ የአባትነትን፣ የወንድምነትን የባልነትን ድርሻ ሲይዝ ከዚህ፣ በተቃራኒ ሴት የሴትነትን፣ የእኅትነትን የሚስትነትን፣ የእናትነትን ሚና ትወስዳለች። ይህ የሚወስደን «ወንድ እና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው» ይልና «እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት» የሚለው የተፈጥሮ ልዩነታቸውን የሚያስታርቀው ጋብቻ እንደ ኾነ፣ የጾታ ልዩነት ተፈጥሯችን ዘር ለመተካት፣ ከዝሙት ለመከልከል እና ለመረዳዳት እንደ ሆነ ያስረዳናል። (ዘፍ.፩፥፳፮፤ ፪፥፳-፳፭):: በጋብቻ የሚደረግ መኝታ የወንድ እና ሴት ውሕደታቸው ማሳያ ነው። ይህ ከጽንሰ ሐሳብ የዘለለ ተግባራዊ እውነት ሆኖ እያለ ግብረ ሰዶማዊነት የምዕራቡን ዓለም አሸንፎ በትምህርት ሥርዓታቸው ሳይቀር ተቀርፆ አንድ ሕፃን እስኪያድግ ድረስ ጾታውን አያውቅም ወይም ጾታ የለውም ሲያድግ እርሱ ራሱ ፆታውን ይወስናል እስከ ማለት ደርሰዋል።  ምዕራባውያኑ ይህም  ሳይበቃቸው የሀገራትን ወንዝ ተሻግረው ውቅያኖሶችን አቋርጠው የሌሎች ሀገራትን  መንግሥታት በብድርና በዕዳ ስረዛ ስም እጆቻቸውን እየጠመዘዙ ግብረ ሰዶማዊነትን በሕገ መንግሥት ደረጃ ካልተቀበላችሁ ርዳታ አንሰጥም፤ የዕዳ ስረዛ አናደርግም፤ የሚሉ ምክንያቶችን በመፍጠር እንደ መብት ሲከራከሩ ብሎም ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል። በዚህም ቤታቸው ውስጥ እያሉ በግብረ ሰዶማውያኑ የተደፈሩ ሕፃናትና ወጣቶችን ሥቃይ ሰምተናል ይሁን እንጂ ፊርማ ከማሰባሰብ በዘለለ የፈየድነው ነገር የለም።  ይህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተቆራኛቸው ኢትዮጵያውያንም የፈጸሙት አሳፋሪ ሰዶማዊ  ተግባር ይፋ ወጥቷል። እንግዲህ ስለ ችግሩ አስከፊነት ይበልጥ ለመረዳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነትን የፈረጀበትን እውነት ማወቅ የመጀመሪያው መነሻ ሐሳብ ነው። ከግብረ ገብነት (moral/ethics) አንጻር መመልከትም ተገቢ ነው። የማስፋፊያ መንገዳቸውን ተረድቶ ለመጠንቀቅ በመቀጠልም በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን መሆን አለበት? እንደ ክርስቲያን ከእኔስ  ምን ይጠበቅብኛል? የሚሉትን ጉዳዮችም አብሮ መመልከት ተገቢ ነው። በዚሀ መሠረት ግብረ ሰዶማዊነት፦   ፩. የተፈጥሮ ሕግን ይቃረናል ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያን ስለፍቺ በጠየቁት ጊዜ «ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድ እና ሴትን ፈጠረ፤ ስለዚህ ሰው አባት እና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም» ብሎ አስረግጦ ራሱ ፈጣሪ ተናግሯል።(ማር.፲፥፮-፱፤ማቴ.፲፱፥፬-፮)   አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ ወይም የዘር ሐረጎቼ (ancestors) ግብረ ሰዶማዊ ነበሩ ማለት አይችልም። ወንድ ወይም ሴት መሆን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የፈጣሪ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሴትነት እና ወንድነት ዘር በመተካት የሚመጣ የእግዚአብሔር ጸጋ ከመሆኑም ባለፈ ወንድ ወይም ሴት መሆን እፈልጋለሁ ብሎ የተወለደም የለም። ጋብቻ አዳም  ለሔዋን ሔዋን ለአዳም ከእግዚአብሔር የተሰጠ በመሆኑ ጌታችን ‹ትንሣኤ ሙታን የለም› የሚሉ ሰዱቃውያንን ጥያቄ በመለሰበት የማርቆስ ወንጌል ላይ ሰባት ወንዶች አግብታ የፈታች ሴት በመንግሥተ ሰማያት ለማን ትሆናለች የሚል ጥያቄ ሲያነሡ «ሙታን ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፣ አይጋቡምም» በማለት መልሶላቸዋል  (ማር.፲፪፥፲፰-፳፭)። እንስሳት ከተቃራኒ ጾታዎቻቸው ጋር ሆነው ድንበር አበጅተው ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩት ከእግዚአብሔር በተሰጠ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ብርሃን ካለ ጨለማ፣ ቀኝ ግራ፣ ፊት ኋላ፣ አጭር ረጅም፣ ክፋት ደግነት፣ ወንድ ሴት እነዚህ ሁሉ በተቃራኒ የሚቆሙ ናቸው። ይህ የተፈጥሮ ሕግ ያልገዛቸው ለሥጋ ፈቃድ እና ምኞት የተገዙት የሰዶም ሰዎች ምንም እንኳን ጻድቅ ሎጥ ከክፋት ድርጊታቸው እንዲመለሱ ቢለምናቸውም ባለመስማታቸው ከእግዚአብሔር ቅጣት አላመለጡም። ከሎጥ በስተቀር የእሳት ድኝ ከሰማይ ዘንቦ ስለ ኀጢአታቸው አጠፋቸው። መጽሐፍ «ወሰብአ ሰዶምሰ እኩያን፣ ወኃጥአን ጥቀ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎች እና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ» እንዲል። (ዘፍ.፲፫፥፲፫፤ዘፍ.፲፱፥፩-፲፬) አሁን ያለንበት ጊዜ ከሎጥ ጋር አልያም ከሰዶማውያን ጋር መቆማችንን የምናስተውልበት ጊዜ ነው። አንዳች ጥቅም አገኝበታለሁ ብሎ ወይም ግብረሰዶማዊ መሆን አይደለም ማሰብ በራሱ ግብረ ሰዶማዊነት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ «ኢትአምሩኑ ከመ አማፅያን ኢይሬእይዋ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወንድሞቻቸውን የሚበድሉ ሰዎች መንግሥተ ሰማይን እንዳይወርሱ አታውቁምን? ኢያስሕቱከሙ፣ ይወርሳሉ የሚሉ ሰዎች አያስቷችሁ፣ ኢዘማውያን ዘማውያንም ሆኑ ወኢእለ ያጣዕዉ ጣዖት የሚያመልኩም ሆኑ ወኢእለ ይኤብሱ በነፍስቶሙ ታንቀው የሚሞቱም ወኢእለ የሐውሩ ግብረ ሰዶም የሚሠሩ ወኢእለ የሐውርዎሙ ግብረ ሰዶም የሚሠሩባቸው….. ወኢኀያድያን የሰው ከብት የሚቀሙ ኢይወርስዋ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም» ብሏል። (፩ቆሮ.፮፥፱ አንድምታ) ግብረ ሰዶማዊነትን ለማውገዝ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃል ፈጽሞ ያወግዛቸዋል። ይህንንም ከቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት እንረዳለን። ቅዱስ ጳውሎስ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለተመለሱ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሰዶማዊነት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ጸያፍ እና የከፋ ኀጢአት እንደ ሆነ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ መስክሯል። በተለይ ለሮማውያን በፌበን እጅ በላከው ክታቡ በሰዶማዊ ኀጢአት በሥጋ ፍትወት ስለ ወደቁ ሰዎች በግልጽ «ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሰፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶች እንዲሁ  ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ እርስ በእርሳቸውም እየተመላለሱ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን  ነውር ሠሩ። ነገር ግን ፍዳቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን  ሰጣቸው» (ሮሜ ፩፥፳፮-፳፰) ብሏል። ‹የዚህ ሁሉ ምክንያት እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመፈለግ ነው› ይላል ሐዋርያው። እግዚአብሔርን ለማወቅ የጓጓ አእምሮ ቅዱስ ዳዊት  «ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» እንዳለ እንደ አብርሃም፣ እንደ ሙሴ ጸሊም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ያውቀዋል። (መዝ.፲፰፥፩) እሱን የሚያውቅ ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ አይሰጥም። ምክንያቱም ግብረ ሰዶማዊነት የሚረባ አእምሮ ያለው ሰው የሚያደርገው አይደለምና። የሚረባ አእምሮ አዳማዊ ሔዋናዊ ሕግን በአእምሮ ተመራምሮ ይደርስበታል፣ ይረዳልም። ከሐዲስ ኪዳን ዘመንም በፊት እግዚአብሔር ለሙሴ በኦሪት ዘሌዋውያን የድርጊቱን አእምሮ የለሽ አስነዋሪነት «ፀያፍ» ብሎ ነው የገለጸው «የአምላክህን ስም አታርክስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ፀያፍ ነገር ነውና» (ዘሌ.፲፰፥፳፪) እንዲል። ይህን ድርጊት ስናወግዝ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንተባበር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቅዱስ ጳውሎስ በአጽንዖት ቃል ሲገልጽ «ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተማርሁትምም» ብሏል። (ገላ. ፩፥፲፩) ድርጊቱን ማውገዝ መለኮታዊ ትእዛዝ እንጂ ሰው ስላለን ወይም መቃወም ስለ ፈለግን ብቻ አይደለም መቃወማችንም የአንድ ሰሞን ፉከራ መሆን የለበትም። ይህ ጉዳይ ፈጽሞ ከቅዱሳት መጻሕፍት ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከቅዱሳን አበው ትምህርት እና ሕይወት ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነውና።  እግዚአብሔር ለወንድ እና ለሴት በከበረ ጋብቻ አንድ  ሥጋ እንዲኾኑ በፍቅርና በመተሳሰብ በአንድነትም እንዲኖሩ ተፈጥሯዊ ዝንባሌን ሰጥቷቸዋል። በተፈጥሮ የተሰጠንን ትክክለኛ ስሜት አለማግኘታችንን በእሱ አለመደሰት መቻላችን በውስጣችን እንስሳዊ ስሜትን መግራት አለመቻል እና የሰውነት ስሜታችን በልጦብን የመንፈስ ልዕልናችን ለማሳደግ አለመፈለጋችን በከፋ ኀጢአት እንድን ወድቅ ሆነናል። በራሳችን ላይ ጦርነት አውጀናል። ሰው ጨካኝ እና የተፈጥሮን ሕግ የሚጥስ ብሎም ተፈጥሮን የሚያጠፋ ከንቱ ፍጡር ሆኗል። እንስሳት እንኳን  የማያደርጉትን ነገር መድፈር አሁን፣ አሁን የተለመደ ነገር ሆኗል። ኀጢአት የውስጥ ሰላማችንን ስለሚያዛባው መረጋጋት እና ሰላም ማግኘት አልቻልንም። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ሳይሆን በራሳችን የምንኮራ፣ ተሳዳቢዎች፣ ለፀብ እና ክርክር የተመቸን አድርጎናል።  «ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ ፤ይህን የሚያደርግ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና»።  ዘዳ ፳፪፥፭። ከዚህ በተፃራሪ ዘመኑ የደረሰበትን የሕክምና ጥበብ ተጠቅሞ ወንድ ልጅ፡ ሴት ሆኖ፤ ቀሚስ አድርጎ እንደ ሴት እያወራ እየተራመደ፤ ኩል ተቀብቶ ሲመጣ ማየትን ኅሊና እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ይህ ማለት በሰው ዘር ማንነት (ተፈጥሮ ) ላይ የተነሣ ፀረ-ሰብእ ድርጊት ነው። እነዚህን ሁሉ የኀጢአት ዓይነቶች ስናስብ የሰው ልጅ ምን ያህል በፈቃዱ ያለ ማንም አስገዳጅነት የሕይወት ምንጭ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ማመፁን እንረዳለን። እያንዳንዱ ኀጢአት ሌላ ኀጢአት ይወልዳል። ግብረ ሰዶማዊነትም በባሕርዩ ከአንድ ኀጢአት ወደ ሌላ ኀጢአት የመሸጋገርና  ለከፋ ኀጢአት የሚያጋለጥ ነው።  ፪. ግብረ ሰዶማዊነት በእግዚአብሔር ሕግ ላይ ማመፅ ነው የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ በተደጋጋሚ ዐምጿል፤ ይህኛው የፈጠረውን አምላኩን ከተቃወመበት የስሕተት መንገድ በጣም የከፋው ነው። «ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ… ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ...» (፩ቆሮ.፮፥፱-፲) ብሎ ነው ያስቀመጠው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ንስሓ ቢገቡ እና ቢመለሱ ይቅርታው ሰፊ ነው። «ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን» (ሮሜ፰፥፲፯) ብሏልና። ነገር ግን ንስሓ ለመግባት ፈቃደኛ ካልሆኑ መንግሥቱን እንደማይወርሱ ሐዋርያው በሁለት ወሳኝ ሐሳቦች አሳስቧል። የመጀመሪያው የእግዚአብሔርን መንግሥት ማጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወደ ገሃነመ እሳት መግባት ናቸው። ፫.ግብረ ሰዶማዊነት ግብረ ገባዊነትን (morality) ይፃረራል ግብረ ገብነት (morality) በሕግና በኅሊና ሚዛን እውነት ወይም ሐሰት ለማለት የሚያስችለን ከቤተ ሰቦቻችን ፤ ከአካባቢያችን የምንማረው ነው። ሁሉም ሰው የሚስማማባቸው ግብረ ገባዊ ሕግጋት (moral laws) አሉ። ሰውን መግደልን እና ሌሎች መሠል ድርጊቶች ኅሊና አይቀበላቸውም ። ከዚህ አንጸር  ግብረ ሰዶማዊነትም በግብረ ገባዊ ሕግ ሚዛን ሲታይ ተቀባይነትም የለውም።  ግብረ ገባዊነትን በሚፃረር ሁኔታ  በራስ አስተሳሰብ ለራሳችን በምንፈልገው መንገድ መቀየር ከጀመርን ሰነባብተናል። ለምሳሌ “ግብረ ሰዶማዊነት ኀጢአት አይደለም” ብሎ እንደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በሕገ መንግሥት ደረጃ ተቀብሎ ማርቀቅ ለአድራጊዎቹ ለጊዜው ትክክል ቢመስላቸው ሕጉን ስለቀየርነው በእውነታዊው ዓለም ያለው ግብረ ገባዊ የኅሊና ሕግ  ትክክል ነው ማለት አይደለም። መሠረታዊ የግብረ ገብ ዕውቀቶች እኛ ስንቀየር እነሱ አይቀየሩም። እኛ ተቀይረናል ማለት መሬት ላይ ያለው ግብረ ገባዊ (moralilty) እውነት ተቀይሯል ማለትም አይደለም። ጥንቱንም ሕፃናትን መድፈር፣ ሰውን መግደል፣ መስረቅ አስነዋሪ ኀጢአት ነው ዛሬም ያው ነው። የሚቀየረው በእነሱ ላይ ያለን አመለካከት ነው። ይህን አመለካከት በጊዜ ሂደት ባለንበት የሕይወት ደረጃ ልክ እንመዝነዋለን።  ኀጢአትን ቀን ተቀን ልምምዱ እያደረገ ያለ ሰው ስለዚህ ነገር ማውራት በራሱ ትርጉም አይሰጠውም። ነገር ግን ሥነ ምግባሩ አይቀየርም። ለምሳሌ ስለ ፍቅር ያለን አመለካከት ላለፉት ጊዜያት ሊቀየር ይችላል፤ ነገር ግን እኛ ልንቀየር ብንችል እንኳን ፍቅር አልተቀየረም። ይህም ግብረ ሰዶማዊነት መብት አይደለም ወደሚል መደምደምያ ይወስደናል። ይህን ድርጊት መፈጸም ከግብረ ገብነት (morality)  አኳያ ትክክል ካልሆነ ትክክል ያልሆነ ነገርን የሚፈቅድ መብት የለም ማለት ነው። እንደ መብት ለመከራከር ጉዳዩ ትክክል መሆን ያሻዋል። የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ሕጎችም መሠረት የሚያደርጓቸው ዐሥርቱ የሙሴ ሕግጋትንና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን የማኅበረ ሰብን ቅቡል የሆኑ ግብረ ገባዊ ሕጎችን በመጠበቅ ላይ ነው። ግብረ ሰዶማዊነትም ከግብረ ገብነት አኳያ ስሕተት ስለ ሆነ ተቀባይነት የለውም። ይህን የምንቀበል ከሆነ ሕፃናትን የደፈሩ፣ የሰው ነፍስ ያጠፉ፣ በሕግ ደረጃ ትክክል ናችሁ ብለን እነሱንም መቀበል አለብን ማለት ነው። በግብረ ገብም፣ በፍትሐ ብሔርም ሕግ በእግዚአብሔር ሕግም ተቀባይነት ስለሌለው፡ ቤተ ክርስቲያንም አትቀበለውም።  ፬. እንስሳዊ አፈንጋጭ ባሕርያት በሰው ዘንድ ቅቡል (normative) አይደሉም ግብረ ሰዶማዊነት እንስሳዊ ባሕርይ ነው። (moral)፣ አመዛዛኝ አሳቢ (rational) አይደሉም። በተሰጠው ነፃ ፈቃድ ሠናይ ወይም እኩይ ተግባራትን እንዲመርጥ የተፈጠረ ፍጡር ከሰውነት ወደእንስሳነት ከወረደ እንስሳ እንጂ ሰው ሊባል አይችልም።     ፭. ሳይንሳዊ መሠረትነት የለውም  ሌላኛው በሳይንሱ ዓለም ወንድ ከ፵፮ ሃብለ በራሂ (chromosom) ሴትም ከ፵፮ ሃብለ በራሂ (chromosom) እንደ ተፈጠሩ ያትታል። ዕፅዋት የወንዴ እና ሴቴ ዘር በመጣመር ይራባሉ። አበቦች የሚራቡት በእንስሳት ወይም ነፋስ ተሸካሚነት የወንዴ ጽጌ ከሴቴ ጽጌ ጋር ሲገናኝ ብቻ ነው። ግብረ ሰዶማዊነት ከዚህ የተፈጥሮ ሕግ የተለየ ነው።  ፮. በጤና ረገድ ገዳይ ነው ተፈጥሮን ያልተከተለ በመሆኑ በጤንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። HIV virusን ጨምሮ ለአንጀት ካንሰር እና መሰል በሽታ ተጋልጠዋል። በስተመጨረሻም ከሕክምና የመቆጣጠር ደረጃ በላይ ሆኖ ከሰውነት ደረጃ ወጥተው ለመኖር ይገደዳሉ። በተለይ በመደፈር ተጎጂ የሆኑ ከሆኑ እኛም ቀርበን ሕክምና እንዲከታተሉ ከመግፋት ይልቅ ስለምናገላቸው ለከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫና ይጋለጣሉ፤ መማር፤ መሥራት ስለማይችሉ ራሳቸውን ለማጥፋት ሊገደዱ ይችላሉ። 
Read 141 times