የበዓል ምንነት
በዓል፡- “አብዐለ አከበረ፣ አስከበረ፣ አበለጠገ፣ ሰውን ባዕል፣ ዕለትን በዓል አደረገ” በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው ይፈቱታል። (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ ፪፻፸፰) እርሳቸው አክለውም “በዓል፡- በቁሙ የደስታ የዕረፍት ቀን፣ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር ያለፈ ነገር የሚታሰብበት ተዝካር፣ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎትና ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘፍንበት፣ የሚዘምርበት፣ ዕልል የሚልበት፣ ሽብሸባ ጭብጨባ፣ … የሚያደርግበት፣ …” በማለት ሰፊ ማብራሪያ ይሰጡበታል። (ዝኒ ከማሁ)። ከዚህ ገለጻ የምንረዳው በዓል በደስታ የሚከበር የሚያጌጡበት፣ የሚደሰቱበት፣ የሚዘምሩበት፣ ወዘተ እንደሆነ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም በመዝሙሩ “ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት፤ በደስታ በዓልን አድርጉ” (መዝ.፻፲፯፥፳፯) በማለት እንደገለጸው በዓል ሰዎች ደስ ብሏቸው የተደረገላቸውን እያስታወሱ የሚያከብሩት ዕለት ነው።
በዓል የደስታ ዕለት በመሆኑ ምክንያት ሰዎች ለበዓሉ የሚገባውን ድግስ በማዘጋጀት ለመብላት ለመጠጣት ደስታን ለማድረግ ይሰባሰባሉ። ይህ ማለት ግን ለሥጋዊ መብልና መጠጥ ብቻ የሚጨነቁበት፣ ሥጋቸውን ብቻ ደስ የሚያሰኙበት ነው ማለት አይደለም። መንፈሳዊውን ምግብም ተመግበው መንፈሳቸውን ደስ የሚያሰኙበት፤ መሆንም ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ከላይ በርእሱ “በዓል በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን ጥራ” (ሉቃ.፲፬፥፲፫) ተብሎ እንደተገለጸው በዓል የሚያደርገው ሰው እነማንን መጥራት አለበት? እነማንንስ መጥራት የለበትም? የሚለውን ሙሉ ቃሉን በመጥቀስ ለማብራራት እንሞክራለን።
“በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፣ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፣ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና። ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፤ ዕውሮችን፣ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፪-፲፬) እንዲል። ይህ ቃል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምሳ ግብዣ ከተጠሩት አንዱን ሰው በዚህ መልኩ አስተምሮታል። ለጊዜው ለሰውየው የተሰጠው ይህ ትምህርት ሰዎች እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ሲማሩበት ይኖራል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምንባብ በተናገራቸው መሠረታዊ ነጥቦች ውስጥ ብድር መመለስ የሚችሉና የማይችሉ ሁለት አካላት ይገኛሉ።
ሀ. ብድር መመለስ የሚችሉ፡- እነዚህ አካላት በወዳጅነት፣ በቤተ ሰብነት፣ በባለጸግነት፣ በጎረቤትነት መልኩ የሚጠሩ ናቸው። እነዚህን አትጥራ ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ እነርሱ ብድር ይመልሳሉና የሚለው ነው። “ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፣ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፣ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና።” (ሉቃ.፲፬፥፲፪) እንዲል። ይህ ሐሳብ የሚያስረዳው ሰዎች ብድር የሚመልሱ ከሆነ ስጦታው ለሌላው ቀን እንዲሆን ማበደር እንጂ ስጦታ አይሆንም። ስለዚህ “ብድር የሚከፍሉህን አትጥራ” በማለት ተናገረ።
ይህ ሲባል ግን መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች እርስ በእርስ እየተጠራሩ መብላት መጠጣትን፣ በአንድነት መኖርን እየነቀፈ አይደለም። ሆኖም ይህን የተናገረው ስጦታ እንዲሆን ብድሩን ሳያስብ፣ ምን ይመልሳሉ፣ ምን አይመልሱም የሚለውን ሳያስብ በነፃ ሰጥቶ መንግሥቱን መውረስ የሚያስችል ሥራ እንዲሠራ ለማስተማር ነው።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍቅር ባስተማረበት አንቀጽም “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሏችሁና ስለሚያሳድዷችሁ መልካም አድርጉ።…የሚወዷችሁንማ ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ.፭፥፵፫-፵፯) በማለት እንዳስተማረ ክርስትናችን ከአሕዛብና ከቀራጮች የተለየና እውነተኛ ይሆን ዘንድ ብድራት ሳንጠብቅ፣ ውለታ ይመልሱልናል ሳንል በነጻ እንድናደርገው በዓል ስናከብርም ብድር የሚመልሱትን አትጥራ በማለት አስተማረ።
ለ. ብድር መመለስ የማይችሉ፡- እነዚህ አካላት፣ በድህነት፣ በችግር፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ ያሉ ድሆችና ጦም አዳሪዎች ናቸው። ድሆችና ጦም አዳሪዎች ድግሞ ብድር መመለስ አይችሉም። “ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፤ ዕውሮችን፣ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፫-፲፬) እንዲል።
ድሆችና ችግረኞች፣ ዕውሮች፣ እጅና እግርም የሌላቸው ወዘተ ተብለው የተዘረዘሩት አንዳንዶቹ ሊለምኑ ያፈሩ፣ ሊሠሩ የተቸገሩ የሕይወት መንገዱ የጠፋባቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ ሁነው መሥራት የማይችሉ ሕይወታቸውን በልመና ብቻ እንመራለን ብለው የሚያስቡ ናቸው። ስለዚህ ለእነዚህ ወገኖቻችን ቋሚ የሆነ መተዳደሪያ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ባይቻል እንኳን በበዓል ወቅት የምሳ ወይም የራት ግብዣ በሚዘጋጅበት ጊዜ ቅድሚያ ለእነዚህ አካላት መስጠት አስፈላጊ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብድር የሚከፍሉትን ሳይሆን ብድር መክፈል የማይችሉትን ጥራ በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው።
ሰው ምጽዋት ሲሰጥ ብድሩን ከእግዚአብሔር አገኘዋለሁ ብሎ መስጠት እንዳለበት ያስተምረናል። በመጨረሻም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው “ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፬) የሚለውን ነው። ዋጋውን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰዎች አይደለም። ወይም ካበላቸውና ካጠጣቸው፣ በወቅቱ ምሳ ወይም ራት ከጋበዛቸው የሚያገኘው የእራት ወይም የምሳ ግብዣ አይደለም። ስለዚህ “እንዲህ ማድረግ የማይችሉትን ጥራ” በማለት አስተማረ።
መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ እንደ ስጦታውም መልሶ ይከፍለዋል” (ምሳ.፲፱፥፲፯) በማለት እንደተናገረው ሰዎች ድሆችን በችግራቸው ሁሉ ሲረዱ ተበዳሪው እግዚአብሔር መሆኑን ልናስተውል ይገባል። በትምህርተ ኅቡአት “ዘየአሢ ተወካፊ፤ የሚሰጥ ተቀባይ” ተብሎ እንደተገለጸ በባለጸጋዎች ላይ አድሮ ይሰጣል፤ በድሆች ላይ አድሮ ይቀበላል። ስለዚህ የቸርነት ሥራ የሚሠራ ሰው ለእግዚአብሔር እንዳደረገ ተበዳሪውም እግዚአብሔር እንደሆነ ቆጥሮ ላላቸው ሳይሆን ለሌላቸው መርዳት አለበት።
መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል “ሀብታችሁን ሸጣችሁ ምጽዋት ስጡ፤ ሌባ በማያገኝበት ነቀዝም በማያበላሽበት የማያረጅ ከረጢት የማያልቅም መዝገብ በሰማያት ለእናንተ አድርጉ” (ሉቃ.፲፪፥፴፫) በማለት ያስተማረው ዋጋው ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነ ሲያስረዳን ነው። ሰማያዊው ዋጋ ደግሞ አያልቅም፤ አያረጅም፤ ሌባ ወንበዴ የሚያገኘው አይደለም። ይህ የማያልቀው፣ የማያረጀው፣ ሌባ ወይም ወንበዴ የማይወስደው ሰማያዊ ዋጋ ደግሞ የሚገኘው ለባለጸጎችና ለቤተ ዘመድ በማብላትና በማጠጣት ሳይሆን ለድሆችና ለአካል ጉዳተኞች ወይም ለጦም አዳሪዎች በማብላትና በማጠጣት ነው።
ቆርነሌዎስ የተባለው የመቶ አለቃም ምጽዋት የሚያደርግ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር። በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሁኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል” (ሐዋ.፲፥፬) በማለት ያደረገውን ምጽዋትና ጸሎት እግዚአብሔር እንደተቀበለለት፣ መልካም ዋጋውንም እንደሚያገኝ አስረዳው። እንግዲህ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሁኖ ወደ እግዚአብሔር አዐርጓል” ማለት ዋጋው በሰማይ ታላቅ ሆኖ እግዚአብሔርም ተቀብሎለት መልካምና ሰማያዊ ዋጋን ልታገኝበት እግዚአብሔር ፈቅዷል ማለት ነው።
ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል?
ዛሬ ዛሬ የበዓል አከባበር ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ሰዎች በዓል ያደርጋሉ፣ ይደግሳሉ፣ ሰውም ይጠራሉ። ይሁን እንጂ የሚጠሩት ዘመዶቻቸውን እየፈለጉ፤ ምን አልባትም እነርሱ በዓል ከማድረጋቸው በፊትም ሆነ በኋላ እየጠሩ ያበሏቸውና ያጠጧቸውን ይጠራሉ እንጂ ድሆችን እየፈለጉ አይጠሩም። ከዚህም እልፍ ሲል በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጁ ነገሮች ከበዓሉ ምንነት ጋር የማይሄዱ ናቸው። ለምሳሌ የምሽት ክበቦች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የዳንስና የጭፈራ ዝግጅቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ እየተባሉ ማስታወቂያ የሚነገርላቸው ለእንደነዚህ ያሉት ተግባራት ነው። ይህ ደግሞ ሰው በዓሉን ምክንያት በማድረግ ወደቤተ ክርስቲያን ልሂድ ሳይሆን ወደተዘጋጀው ጭፈራ ቤትና ዝሙት ወደሚስፋፋበት ቦታ ልሂድ እንዲል ያደርገዋል።
በዓል በመጣ ቍጥር ሰዎች ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሳይሆን ለሥጋዊ ደስታቸው እንዲጨነቁ ለድኅነተ ነፍሳችን ስለሚሠዋው አማናዊ መሥዋዕት ሳይሆን ለሥጋዊው ድግስ እንዲጨነቁ ያውም ከዘመድ ዘመድ አማርጠው ለመጥራት፣ ታላቅ የሚሉት ሰው ቤታቸውን ስላላየላቸው የሚያስቡበት ሁኔታ እንደ ሥርዐት ወይም እንደባህል እየተቆጠረ ሲመጣ ይስተዋላል።
በበዓል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን የተወሰደው ምግብም ቢሆን በመጀመሪያ ታላላቅ የተባሉ ሰዎች ተመግበው ሲተርፍ ችግረኞች ሊታሰቡ ይችላሉ። ምን አልባትም ሲተርፍ ይሰጣችኋል ሲባሉ ቆይተው አልተርፍ ብሎ አለቀ የሚባሉበትና ምንም ነገር ሳይቀምሱ እንደለመደባቸው ረኀባቸውን መጠጊያ አድርገው የሚመለሱበት ጊዜም ይስተዋላል። የሚበላውና የሚጠጣው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ አይተው ረኀባችንን እናስታግሣለን ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ግን ከቤታቸው የሚበሉትና የሚጠጡት ያልጎደለባቸው ሰዎች በልተውትና ጠጥተውት ያልቅና ምንም ሳይቀምሱ ይመለሳሉ።
መፍትሔው ምን መሆን አለበት?
ከላይም እንደተገለጸው ሰዎች ባንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን እያመሰግኑ የተገኘውን ቢበሉና ቢጠጡ ጥፋት ነው ማለት አይደለም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው።” (መዝ.፻፴፪፥፩) በማለት እንደገለጸው በአንድነት ተሰባስበው የእግዚአብሔርን ስም የእመቤታችንን ስም፣ የቅዱሳንን ስም፣ ወዘተ እየጠሩ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የተገኘውን እየበሉና እየጠጡ ቢኖሩ ጥፋት አይደለም።
ዋናው ትኩረት መሰጠት ያለበት ጉዳይ በሚሰበሰቡበት ጊዜ የተዘጋጀው ምግብ ከማለቁ አስቀድሞ ለድሆች መታደል ይኖርበታል። ምክንያቱ ደግሞ ባለጸጎች ከቤታቸውም ሄደው የሚበሉትና የሚጠጡት ስለ አላቸው ነው። ስለዚህ ቅድሚያ ለድሆችና ለችግረኞች ሊሰጥ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንን መጠጊያ አድርገው እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የተጠለሉት ችግረኞች ቢያንስ በዚህ ጊዜ መመገብ አለባቸው።
በዓለ ልደት ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን የሰው ልጆች አንድ ላይ የዘመሩበት ነው። ባለጸጎች ቤት አናስገባም ሲሏቸው እንስሳት ትንፋሻቸውን ገብረው የተወለደውን ሕፃን ያሟሟቁበት በዓል ነው። ስለዚህ ዛሬም በዓለ ልደትን ማክበር ያለብን ልዑላኑ መላእክት ከትሑታኑ እረኞች ጋር አብረው እንደዘመሩ ሁሉ ባለጸጎችና ድሆች አብረው የሚያከብሩት በዓል መሆን አለበት። በዓለ ልደትን ያላቸው ባለጸጎች ደግሰው የሚያበሉት የሚያጠጡት ድሆች ደግሞ በክብር ተጠርተው አብረው ከባለ ጸጎች ጋር ተቀምጠው መብላት መጠጣት የሚችሉበት መሆን አለበት።
በዓል ስናከብር ድሆችን መጠየቅ እንዳለብን የሚያስረዳን ተጨማሪ መረጃ እንጥቀስ። በድርሳነ ሚካኤል “በዚህ በዓል ብቻውን የሚበላ የሚጠጣ ደስ የሚለው እየራባቸው እየጠማቸው ድሆችን ጦም አዳሪዎችን ቸል የሚላቸው አይፈለግምና። በዚህ በዓል ደሀው ከሜዳ ወድቆ በብርድ እየተሠቃየ በክብር ልብስ የሚያጌጥ አይፈለግም። ይህ በዓል ደሀው በሜዳ ወድቆ ባጌጡ ቤቶች የሚቀመጡለትን ሰዎች አይፈልግም። ይህ በዓል ደሀው በእስር ቤት እየተጨነቀ በተድላ በደስታ ያለ ልክ የሚበላ የሚጠጣ ሰውን አይፈቅድም። ይህ በዓል ደሀው ታሞ የሚረዳው የሚጎበኘው አጥቶ ሲጨነቅ ብቻውን ራት ወይም ምሳ የሚያደርገውን አይሻም። በወንጌል የተጻፉት ትእዛዛት የሚሉት ይህ ነው” (ድርሳነ ሚካኤል ዘወርኃ መጋቢት ገጽ ፪፻፵፭-፪፻፵፯) እንዲል።
ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ድሆችን መጎብኘት የግድ እንደሆነ ይህ ካልሆነ ግን የበዓሉ ሥርዓት ድሆችን የማይጎበኘውን፣ የማያበላውን፣ የማያጠጣውን፣ የማያልብሰውን እንደማይፈልግ ያስረዳናል። ስለዚህ ከላይ በርእሳችን እንደተገለጸው ከባለጸጎች ይልቅ ድሆችን፣ ከዘመዶቻችን ይልቅ የማያውቁንን፣ ጉልበት ካላቸው ይልቅ አካል ጉዳተኞችን መርዳት ይኖርብናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ብድር ሊከፍሉ የሚችሉትን ሳይሆን ብድር መክፈል የማይችሉትን እንድንረዳም ያስተምረናል።
ይህ ተግባር ዋጋው በሰማይ እንደሆነና ለዚህም በትጋት መሥራት እንዳለብን ሲያስረዳ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔም እላችኋለሁ፤ ባለቀባችሁ ጊዜ እነርሱ በዘለዓለም ቤታቸው ይቀበሏችሁ ዘንድ በዐመፃ ገንዘብ ለእናንተ ወዳጆች አድርጉበት” (ሉቃ.፲፮፥፱) በማለት እኛ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የምናደርገው ድሆችንና ችግረኞችን የመጎብኘት ሥራ እነርሱ ደግሞ በዘለዓለም ቤታቸው ይቀበሉናል። እኛ ዛሬ እነርሱን ማብላታችን እነርሱ ደግሞ በሰማያዊው ቤታቸው ያበሉናል፤ ያጠጡናልም።
ባለጸጎችንና ጎረቤቶቻችንን ብንቀበል፣ ብናበላና ብናጠጣ እነርሱም በተራቸው የሚቀበሉን፣ የሚያበሉንና የሚያጠጡን በዚህ ዓለም ነው። ድሆችና ችግረኞች ግን የሚቀበሉን፣ የሚያበሉንና የሚያጠጡን በሰማያዊ ቤታቸው ነው። ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል በምናደርግ ጊዜ በዚህ ዓለም ብድር የሚከፍሉትን ሳይሆን በዚህ ዓለም ብድር መክፈል የማይችሉትን መጥራት እንዳለብን አስተማረን።
ባጠቃላይ በዓል የደስታ ዕለት ያለፈን ነገር እያስታወስን የምንደሰትበትና የተደረገልንን ነገር እያስታወስን እግዚአብሔርን የምናመሰግንምበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለትም መብል መጠጥ ይዘጋጃል። ሰዎች ይሰበሰባሉ፣ በእግዚአብሔር ስም፣ በእመቤታችን በቅድሰት ድንግል ማርያም ስም፣ በቅዱሳን ስም እየተሰበሰቡ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይበላሉ ይጠጣሉ። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልም እንዲሁ ሰዎች እየተጠራሩ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ዘመድ ከዘመድ ይጠያየቃሉ። ይሁን እንጂ የዘመድ መጠያየቂያ ከመሆን ባሻገር ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን ብድር መመለስ የማይችሉትን እንዳንዘነጋ መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ብድር መመለስ ከሚችሉት ከዘመዶቻችንና ከባለጸጎች ይልቅ ቅድሚያ ሰጥተን እንድናበላቸውና እንድናጠጣቸው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል። በተማርነው ትምህርት ተጠቅመን፣ ከባለጸጎችና ከዘመዶቻችን ይልቅ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን አስበናቸው የተቻለንንም አድርገንላቸው የበዓሉን በረከት እንዲያድለን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን።