Friday, 04 December 2020 00:00

ግብረ ሰዶማዊነት ክፍል ሁለት

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ

Overview

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት በሚለው ዓምዳችን ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ ክፈርል አንድን ማቅረነባችን ይታወሳል። ክፍል ሁለትን ደግሞ በአሁኑ ዕትማችን እናቀርባለን። መልካም ንባብ። ዓለም አቀፍ የማስፋፍያ መንገዶች ምንድን ናቸው? ማርሴል ከርክ እና ሀንተር ማድሰን የተሰኙ አሜሪካውያን የዚህ ድርጊት አስተባባሪዎች after the ball በተሰኘው መጽሐፋቸው ለማስፋፋት መጠቀም ያለባቸውን ዘዴ በትክክል አስፍረው ዛሬም ድረስ ተግባራዊ እየሆነ ነው። (፲፱፻፹፱) ፩. ስለ አኗኗራቸው ምንም ነገር እንዳይነሣና እንዳይወራ ማድረግ። ፪. ቃሉን ደጋግሞ ለጆሮ ማለማመድ፡- ዛሬ ቃሉ ሲነገር እንደ ነውር የምንደነግጠው ነገር ቀርቷል ይህ የእነሱ የሥራ ውጤት ነው። ሚዲያን፤ መንግሥታትን፤ ታዋቂ ሰዎችን በመግዛት ወደ ፊት እየመጡ ነው። ፫. ግብረ ሰዶማውያን በዓለም የተጎዱ የተገፉ አድርጎ ማቅረብ። የታቀደ ድብደባ እንዲደረግባቸው በማድረግ ዓለም እንዲያዝንላቸው ቁስላቸውን በማሳየት አማኝ ኅሊና መግዛት። ፬. ማኅበራዊ ፍትሕ እንደ ተነፈጋቸው አድርጎ ማቅረብ ፡- ጉዳዩን ከመብት፤ ከሰብኣዊ መብት (human right) አንጻር እንዲታይ መንግሥታትን መቃወም፤ ማሳመን፤ በአሜሪካና መሰል ሀገሮች ወንጀል መሆኑ እንዲቀር ከማድረግም ባለፈ ሰብኣዊ መብት እንደ ሆነ አድርጎ ማቅረብ። united nations ካስቀመጣቸው የሰብኣዊ መብት ውሳኔዎች (human right declaration) አንዱ ቤተ ሰብ ለኅብረተ ሰብ ዋና ምሰሶ በመሆኑ ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል የሚል አንቀጽ አለው። ሆኖም ግን ግብረ ሰዶማዊነት ይህን የሚጻረር ሆኖ እናገኘዋለን። ፭.  ዓለም አቀፍ የቱሪዝም፤ የስፓርት፤ የቱሪስት እንዲሁም ትልልቅ ኮንፈረንሶችን መጠቀም፡- ኅዳር ፳፮/ ፳፻፬ ዓ.ም. የተካሄደው ICASA በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከተላላፊ በሽታዎች ጋር በተያያዘ የተደረገ ስብሰባን ምክንያት በማድረግ ስብሰባ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። በሀገራችን ኢትዮጵያም በ፳፻፲፩ ዓ.ም.  የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ለመጎብኘት በሚል ሰበብ ለመምጣት አቅደው አልተሳካላቸውም፤ ሌሎቹንም የስፖርት ውድድሮች፤ የቱሪስት መዳረሻዎች በመጠቀም ለመስፋፋት ይጠቀሙባቸዋል።

 

፮. ታዋቂ ሰዎችን፤ የሕክምና ባለ ሙያዎችን፤ የሃይማኖት ሰዎችን በገንዘብ የዓላማቸው ማስፈጸሚያ ማድረግ ፡- በጥናት የተደገፈ፤ እውነት የሚመስል መረጃዎችን በእነዚህ ሰዎች እንዲቀርቡ በማድረግ እሱ ይህን ካደረገ እኔም ብሎ ሰውን ለማሳመኛ ይጠቀሙበታል።

፯. ታዳጊ ሕፃናትን በመድፈር በዚህ ኀጢአት ማሳደግ፡- ብቸኛ የሆኑ፤ ከቤተሰብ ፍቅር ያጡ፤ የገንዘብ ችግር ያለባቸው፤ በአእምሮ ሕመም የተጠቁ (ጉዲፈቻን ጨምሮ) ሕፃናትን በመድፈርና የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ ማንነቴ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደርጓቸዋል ከዚህም ባሻገር ይህንን ዓላማቸውን በሌሎች ላይ እንዲያሰርጹ በተለያዩ ሀገሮች ያሰማሯቸዋል።

ግብረ ሰዶማዊነት ባለንበት ዘመን ተፅዕኖው ምን ያህል ነው?

የአዲሱ ዓለም ሥርዓት አራማጆች (The new age movement) ግብረ ሰዶማዊነትን ከሰው ልጅ መብት ጋር በማገናኘት ሕጋዊ ዕውቅና መስጠቱን ተያይዘውታል። ኀጢአት ነው፤ ጸያፍ ነው፤ ግብረ ገባዊ አይደለም፤ ተፈጥሮን ይጻረራል ከማለት ይልቅ ይህ የሰዎች   ግላዊ መብት እንደ ሆነ፣ ድርጊቱን የሚቃወሙትም መብትን ተጋፊዎች እንደ ሆኑ ተደርገው ይወሰዳሉ። ሳይንሱንም የራሳቸው መሣሪያ ማድረግ ጀምረዋል። በማያልቁ የውሸት መላምቶች የወጣቱን አእምሮ ለመቀየር ግብረ ሰዶማዊነትን ለማበረታታት የጾታ አተያይ (sexual orientation) ተቃራኒ ጾታን ብቻ ሳይሆን ‹ሌላ የጾታ ዓይነት አለ› ብለው ለማሳመን ጥረት ያደርጋሉ፤ ፆታቸውንም ይቀይራሉ። 

ሌላው በግሪክ እና በሮማ ሥልጣኔ ዘመን የነበረው የፍልስፍናው  ዓለም በጥቂቱም ቢሆን  ተፅዕኖው ተጠቃሽ ነው። የግሪክ ፍልስፍና አንድ ሰው ለቅዱስ ጋብቻ ስላለው አመለካከት የተለየ አስተምህሮ መኖሩ ይህን ኀጢአት ውስጥ ውስጡን ከቤተ መንግሥት ነገሥታት ጀምሮ ለማስፋፋት አስችሏል። በሩማንያ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አንቶን አዳአሙት philosophical aspect of homosexuality in ancient Greek በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው አፍላጦንም (ፕላቶም) ሆነ አርስጣጣሊስ (አሪስቶትል) ቆይተው በሐሳባቸው ቢፀፀቱበትም በጊዜው የነበረውን ማኅበረ ሰብ ያስተምሩት በነበረው ትምህርት ላይ እንዲህ ብለው ነበር የገለጹት «everything is allowed since it is natural, and what is natural goes beyond the frame of family, thus Greek love lives completely outside marriage and family - ምንም ነገር ተፈጥሮአዊ እስከ ሆነ ድረስ የተፈቀደ ነው፤ ተፈጥሮአዊ የምንለው ሐሳቡ ቤተ ሰብን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ያለፈ ነው። ይህ ማለት ፍቅር በግሪካውያን ዘንድ ከጋብቻ እና ቤተ ሰብን ሳያካትት ከዚህ ውጭ ነው» ብሏል።  (Anton ADAMUT, Philosophical aspect of Homosetuality in ancient Greek, p 11  )   ይህ ደግሞ ቅዱስ የሆነውን ጋብቻ ከመቃወሙም በተጨማሪ ለፍትወታዊነት እና መሰል እንስሳዊ ተግባራት ውስጥ ራሳችኹን ዝፈቁ እንደ ማለት ነው።

በዚህ ዘመን ያለ ወጣት በዚህ መሰል ፍልስፍና እንዳይወሰድ ማስተማር የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ነው። እነዚህ አካላት የታሪክ መዛግብትን በማዛባት የራስን ታሪክ መጻፍም ተያይዘውታል በግሪክ እና ሮማ ሥልጣኔዎች ወቅት የነበሩ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ለመሰል ዓላማቸው በመጠቀም ያልነበረውን ነበረ፤ ያልሆነውን ሆነ ብሎ መጻፍም ጀምረዋል። ይህም የጥበብ አፍቃሪ የሆነው ወጣት ወደ ኋለኛው ዘመን ተመልሶ ዕውቀትን ሲፈልግ እገሌም ግብረ ሰዶማዊ ነበር፤ እከሌም እንዲህ ነበር የሚሉ መረጃዎችን በማካተታቸው በቀላሉ ግብረ ሰዶማዊነት ጽንሰ ሐሳብ ከታሪክ እና በጊዜው ከነበሩ ልሂቃን ሕይወት ጋር አስተሳስረው ዝነኞቹንና ታላላቆቹን በማድነቅ ወጣቱ ትውልድ  ሐሳቡን እንዲቀበለው ማድረግ ሌላኛው መንገዳቸው ነው። 

ለማሳያ ያህል ዘጋርዲያን በተሰኘው ጋዜጣ ጀምስ ዳቪድሰን በተባለ ግለሰብ በፈረንጆቹ ፳፻፯ ላይ በጻፈው  Mad about the boys በተሰኘ ጽሑፍ በታዋቂው የግሪክ የሥነ ጽሑፍ ሰው ሆሜር ሥራዎች ውስጥ አኪለስ (Achilles) እና ፓትረክለስ (Patroclus) የተሰኙ ገጸ ባሕርያትን ደራሲው ባላስቀመጠበት መንገድ የነበራቸውን የጠበቀ ወንድማዊ ግንኙነት እነሱ በፈለጉት መንገድ የተለየ ትርጉም ሰጥተው ማስቀመጣቸው ጥንታዊ የታሪክ ድርሰቶችን ከላይ ላነሣነው ድብቅ ዓላማ ማስፈጸሚያ ለማድረግ የታቀደ ነው።

ሌላው በዚህ ዘመን በታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ተሰሚነት ለማግኘት ወጣቶችን በዚህ ኀጢአት ለመማረክ የሆሊውድ ፊልሞች ገና ከጅምሩ በፊልሞቻቸው የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስተዋውቁት ሲሠሩበት ኖረዋል። እ.አ.አ ፲፱፻፺ ወዲህ ግን ሊገመት በማይችል ፍጥነት በየፊልሙ ውስጥ ሆነ ተብለው ተካትተዋል። እነዚህ ሁሉ ፊልሞች በዘመናት ታሪክ ውስጥ በተመልካች ዘንድ የሚፈጥሩት የአመለካከት ለውጥ ከባድ ነበር፤ አሁንም እየሠሩበት ነው። በንግድ ዕቃዎች፣ ቲሸርቶች፣ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች፣ ዘፈኖቻቸው ላይ ዓላማቸውን ያስተዋውቃሉ። የራሳቸው ቀለም የበዛበት ባንዲራ አጽድቀዋል። እንደ አሜሪካ መንግሥት ባሉ መንግሥታት ውስጥ ደግሞ በሕገ መንግሥት ደረጃ የእርስ በእርስ ጋብቻቸውን አስፈቅደዋል።

አሁን፣ አሁን በመድረኮቻቸው ላይ በግልጽ ግብረ ሰዶማዊ መሆናቸውን የሚመሰክሩ የራሳቸው ማንነት እንደ ሆነ የሚቆጥሩ ታዋቂ ሰዎች መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። ይህ ነገር በይነ መረብ (Internet) ላይ ረጅም ሰዓት አፍጥጠው በሚውሉ እና ነገ በሚፈጠሩ ሕፃናት አእምሮ ውስጥ የሚፈጥረው ግራ መጋባት እንዲህ ቀላል አይደለም። ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃራኒ አእምሯቸውን ለማይረባ ነገር አሳልፈው ስለ ሰጡት ይህን መሰል ነገር ማሰባቸውን ሳይሆን ኑሮአቸው እውነት እንደ ሆነ እና ማንነታቸውን (identity) ማመናቸው ሌላው ተግዳሮት ነው። አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት አዳራሾች ግብረ ሰዶማዊነት ይሰበክባቸዋል። ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ እኛ ሀገር ውስጥ ያሉት ተከታዮቻቸው የዚህ ኀጢአት ዓላማ ማስፈጸሚያ የማይሆኑበት ምንም መተማመኛ አለመኖሩ ሀገራዊ ስጋት እንዲደቀንብን ያደርጋል። ሲያልፍም መንግሥታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ተላላኪዎቻቸውን በገንዘብ በመግዛት የሚፈጥሩት ጫና መነሻቸው በእነሱ በኩል መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

እንዴት እንከላከለው? 

አብርሃማዊ ምልጃ እና ሎጣዊ አርአያነትን በመከተል 

ሰዶማውያንን መጽሐፍ ቅዱስ «ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኀጠአተኞች ነበሩ» ብሎ ነው ሚገልጻቸው (ዘፍ. ፲፫፥፲፫)። ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የምትጸልየው ስለዚህ ሁሉ ነው። የዚህ አካል የሆነው አበ ብዙኃን አብርሃም ስለ ክፋታቸው እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው ስለ ተረዳ በበፊቱ ቁሞ «በውኑ ጻድቁን ከኀጠአተኛው ጋር ታጠፋለህን? ከተማይቱንም በእርስዋ ስለሚገኙ ኀምሳ ጻድቃን አትምርምን? » (ዘፍ. ፲፰፥፳፬) ከኀምሳ ጻድቃን ጀምሮ አሥር ደረሰ። ጻድቅ ሰው አልተገኘባትም። እንደ ሀገር፤ እንደ ቤተ ክርስቲያን ስለ እነዚህ ሰዎች ኀጢአት እንዳንጠፋ መጸለይ እነሱም በንስሓ እንዲመለሱ ወደ እግዚአብሔር በምሕላ መጮህ፤ ማልቀስ ያስፈልጋል። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ በመካከላቸው እየኖረ በድርጊትም በሐሳብም ከኀጢአት እንደ ተለየው ሎጥ ብርቱ የሆነ የክርስትና መሠረት ያስፈልገናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ «ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በአመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በአመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከታተሉ የሚመላለሱትን ጌትነቱንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል»  ብሏል። ሳናውቀው ግብረ ሰዶማዊ ሐሳብን ከሰው ልጅ መብት፤ ከፖለቲካ ትርፍ፤ ከግል ጥቅምም አንጻር የምናይ ሰዎች ማሰባችን ከሎጥ ነፍስን ማስጨነቅ በላይ አይሆንምና መለየት ያስፈልገናል። (፪ጴጥ.፪፥፯-፰)።

ሕፃናትን በመጠበቅና በማስተማር 

ሕፃናት አሁን ባሉበት የዕውቀት ደረጃ እና ከእኛ በተሻለ ዓለምን የሚረዱበት መንገድ ከእነሱ ጋር ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚያሰችል አይደለም። በሚያዩት ፊልም በሚሰሙት ሙዚቃ አእምሯቸው ተቀይሯል። ይህም በጓደኞቻቸውና በአካባቢያቸው ተጽእኖ የመጣ ስለ ሆነ ይህ የቱንም ያህል ጊዜ ይፍጅ የእነሱን ዓለም መረዳት ያስፈልጋል። ከመናገር በፊት እናዳምጣቸው። የቀን ውሏቸውን መገምገምና ከእነርሱ ጋር በነፃነት መወያየት ያስፈልጋል። የቅድመ ጥንቃቄ ሕጎችን በተገቢው ሁኔታ እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ነው። ችግር ቢደርስባቸው እንኳን የድረሱልኝ ጥሪ እንዲያሰሙ የቤተ ሰቦቻቸውን እና የፀጥታ አካላትን ስልክ ቁጥር በቃላቸው እንዲይዙ ማድረግም አንዱ የመፍትሔ አማራጭ ነው። ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ብናበረታታቸው የሚባሉትን ሁሉ በፀጋ ከመቀበል ይልቅ ለምን የሚሉበትን አቅም ይፈጥርላቸዋል ። ዝም በል ዝም በይ ማለት ግን መፍትሔ አይሆንም ። በዋናነት ደግሞ ምንም ከባድ ቢሆንም ከሁሉ በላይ ግን ግብረ ሰዶማዊነት ምን እንደ ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጠቀስን በቀላል ቋንቋ ልናስረዳቸው፣ መሰል አመለካከት ያለውን ሰው የሚለዩበትንም መንገድ ልናሳያቸው ይገባል ። በተለይ ሕጻናትን ለትምህርት ውጭ ሀገራት ልኮ ማስተማር ልጆቹ ጠንካራ ሥነ ልቡና እና ግንዛቤ እስከ ሌላቸው ድረስ በዚህ መሰል ኀጢአት የመጎዳት አቅማቸው የከፋ ነውና ልናስብበት ይገባል።

በጉድፈቻም ሆነ በሌሎችም ምክንያቶች ከሀገር የሚያስወጡ አካላት ዝነኞች ስለ ሆኑ፤ አቅሙ ስላላቸው አሳልፎ መስጠት እየተለመደ መጥቷል። ነገ ከነገ ወድያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለታቸውና ሕዝብና ሀገርን ያሳደገች ቤተ ክርስትያንን ማሰደባቸው የማይቀር ነው። ልጆቻቸውን ከቤተ ክርስትያን ሳያስቀሩ በግብረ ገብ ትምህርት አልፎም ተርፎም ለዲቁና ከዚያም ከፍ ለሚል የክህነት አገልግሎት ለአገልጋይነት ያበቁ ዲያስፓራ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ሁሉ አደራቸውን ያልተወጡትን ደግሞ ቤት ይቁጠራቸው። አንድ ሕንዳዊ ወጣት ከሀገሩ ሲወጣ የሀገሩን ባሕልና ወግ ይዞ እንደ ሄደ ሁሉ ሲመለስም ይዞት ይመጣል። ይህ የወላጆቹ ተጽእኖ ነው። በእኛ ሀገር ይህ የማይታሰብ እስኪመስል ድረስ ቦላሌውን ጥሎ የሰው ቀሚስ አድርጎ ሻሹን ግጥም አድርጎ አስሮ ምኑም ሳይገባው ሰንሰለትና ጆሮ ጌጥ ማድረግ ሥልጣኔ ይመስለዋል። እኛም አይተን ዝም፤ ነገም ዝም ካልን ነውር የሆነ ነገርን የሚከለክለውን ኢትዮጵያዊ ባሕል አክብረን ማስተማር ካልቻልን ችግሩ ይከፋል።

የወንጀል ሕጎቻችን እንዲጠበቁ ግፊት ማድረግ 

በጥንት አቴናውያን ሕግ በዚህ ኀጢአት የወደቀ፤ የተያዘ ሰው የመምረጥ የመመረጥ፤ በፍርድ ቤት ስለ ራሱ የመከላከል መብት የለውም። ( Douglas M.MacDowell, Athenian laws about homosexuality ,university of Glasgow ,p 23) ይህ ማለት በሕግ ደረጃ ዓለም አቀፋዊ ወንጀል ወይም ነውር ነው ማለት ነው። በሀገራችን ፲፱፻፺፮ በወጣውና ፲፱፻፺፯ በታተመው የወንጀል ሕግ አንቀጽ ፮ ጠቅላላ ድንጋጌው ላይ ክፍል ፪ ግብረ ሰዶምና ለንጽሕና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ሌሎች ድርጊቶች በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር በዝርዝር ወንጀል መሆኑን እና የሚያስከትለውን ቅጣት ከ፲፰ ዓመት በታችና ከ፲፰ ዓመት በላይ ለሆነ ዕድሜ አስቀምጧል።

በማኅበረ ሰቡ ዘንድ ኢ-ግብረ ገባዊ (ኢ- ሞራላዊ) መሆንን ከግምት ውስጥ አስቀምጦ ወንጀለኛው ለፈጸመው አስነዋሪ ተግባር ቅጣቱን የሚያከብዱ ጠቅላላ ሁኔታዎችን ለምሳሌ የተጎጅን የገንዘብ ችግር፤ የኅሊና ኃዘን፤ አሠሪው፤ ሞግዚቱ ከሆነ፤ ወይም ሥልጣኑን ተጠቅሞ አስነዋሪ ግብረ ሰዶማዊነት ከፈጸመበት ከ፩ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም ከ ፲ ዓመት በማይበልጥ ጽኑዕ እሥራት ይቀጣል። ሕጉ «በቀላል እሥራት ይቀጣል» የሚለው ሐረግ ቅጣቱ ቀላል ከሆነ ለወንጀለኛ የሕግ መከራከሪያ ክፍተት ያገኛል፤  ድርጊቱንም አቅልሎ ለማየት አጋጣሚ ያገኛል። በተለይ አንቀጽ ፮ ቁጥር ፴፩ ላይ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች እና ፲፰ ዓመት ባልሞላቸው ላይ ለሚፈጸም ግብረ ሰዶማዊነት ቅጣቱ ከ ፲፭ አመት እስከ ፳፭ ዓመት የሚያስቀጣ ነው ይላል። 

ሕጎችን ባጠበቅናቸው ቁጥር ወንጀለኞች  ቅጣቱን በመፍራት ሕጉን የማክበር አዝማማሚያ ከፍ ያለ ነው። ከላይ ያየናቸው ቅጣቶች ከግብረ ሰዶማዊነት የወንጀል ክብደት አንጻር ቅጣቱ ያንሳል እንጂ አይበዛም። 

አሁን ባለው  የግብረ ሰዶማውያን የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከላይ የተቀመጠው  ሕግ  «በቀላል እሥራት ይቀጣል» የሚለውን ዓረፍተ ነገር ጨምሮ በቀላል እሥራት መባሉ በራሱ ለድርጊቱ ፈጻሚዎች የልብ ልብ መስጠት ነው።  በሕጉ ላይ የሰፈሩት ቅጣቱን የሚያከብዱ ጠቅላላ ሁኑታዎች የሰፈሩት ጉዳዮች ጠንካራ ቢሆኑም እርሱን ተከትሎ ግን ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት የሚለው ሐረግ ቅጣቱን የሚያከብዱ ጠቅላላ ሁኔታዎች አንጻር ቅጣቱ  የማይመጣጠን  ሆኖ እናገኘዋለን። በተለይ አካለ መጠን ባልደረሱ ሕጻናት ላይ ለሚፈጸም ወንጀል የተቀመጠው ቅጣት ከወንጀሉ ክብደት አንጻር ትንሽ ነው። ዕድሜ ልክ የማይጠፋ መጥፎ ጠባሳ በሕፃት ላይ ያደረሰ አካል ዕድሜ ልክ የማይቀጣበት ምንም ምክንያት የለም። እነዚህ ሕጎች እንዲጠብቁ፤ እንዲሻሻሉ  መንግሥት ካላደረገ፤ የሚመለከታቸው አካላት ካሁኑ ካልጮሁ ግብረ ሰዶማውያን የሕጉን ቅለት ተጠቅመው ሕጋዊ ሰውነት ይዘው  ነገ ከነገ ወድያ ፍርድ ቤቶችን እንደ ሌሎች ቀላል ወንጀሎች ቆመው የማይከራከሩበት ሕጋዊ ድጋፍ የማያገኙበት ምንም  ምክንያት አይኖርም። 

ስለዚህ የወንጀሉን ክብደት በሚመጥን መልኩ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ። ኅብረተሰቡ የሕጉን መጥበቅ ተከትሎ   ወንጀለኛን ማጋለጥ፤ ለፍርድ ማቅረብ የሚቻልበትን አቅም እንገነባለታለን።  ይህ ካልሆነ ምንም እንኳ በዚህ ርኩሰት የተጠቃ አካል ወንጀሉ ቢፈጸምበትም ነገ የሚደርስበትን መገለል በመፍራት አደባባይ ወጥቶ እንደዚህ ተደረገብኝ ማለት ይከብደዋል። ነገር ግን በዚህም ምክንያት ሕጉ የሰጠውን ከለላ በመጠራጠሩ ልጄ ወይም ጎረቤቴ እንደዚህ ሆነ ብሎ ደፍሮ ስለማይናገር ወንጀለኛው በቀላል እሥራት ሊታለፍ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። በግልጽ ወንጀለኛነቱ እየታወቀ እገሌ እኮ እንደዚህ ነው እንደዛ ነው እየተባለ በሹክሹክታ ከማውራት ውጭ በአደባባይ እገሌ ይህን ፈጽሟል ማለት ከብዷል። ምክንያቱ ደግሞ በአንድ በኩል አጸያፊነቱን አስበን ዘግንኖን  በሌላ መልኩ ግን ሕግ ባለበት ሀገር ፈርተን ነው ከማለት ውጭ ምን ልንል እንችላለን።  

መፍትሔው በየጎዳናው ይህን ያደረጉ ወንጀለኞችን በተባበረ ክንድ ማጋለጥ፤ ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህንን ማድረግ አለመቻል ከሚመጣው ትውልድ ከመወቀስ አያድነንም። ሳይቃጠል በቅጠል የምንልበት ጊዜ አልፏል  አሁን እንደሰደድ እሳት  ሳያቃጥለን ድርሻችንን  መወጣት ግዴታችን ነው። ኅሊና ያለው የትኛውም ሰው  እንዲህ ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ዝም ብሎ አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ወንጀለኛን ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል። እንደ ማኅበረሰብ እንደ ምእመን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለጥቃት የተሰናዱ ቦታዎችን በማጋለጥ  ለሕግ አቤት ማለት ይገባል።   

በአጠቃላይ በሰው ዘር ማንነት ላይ የተቃጣው ይህ ርኵሰት ውስጥ ውስጡን እንደ ሰደድ እሳት ሲቀጣጠል እግዚአብሔርን የሚፈራ እና የሚያፍር ምእመን ባለባት ቅድስት ሀገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከመተኛት ግንዛቤያችንን በማስፋት ልጆቻችንን፣  አካባቢያችንና ቤተ ክርስትያንን መጠበቅ ክርስትያናዊ ግዴታችን ነው። ዛሬ በጅምሩ መከላከል ካልቻልን ችግሩ ከገዘፈና ከአቅም በላይ ከሆነ በኋላ ማስቆም ይሳነናል። የምዕራቡ ዓለም ዓላማውና ግቡም የእግዚአብሔር ሀገር፣ የክርስትና ደሴት የምትባለዋን ኢትዮጵያን ከሃይማኖቷ አስወጥቶ፣ የማይገባ ምግባር አሠርቶና ከእግዚአብሔር አጣልቶ እንዳልነበረች ማድረግ ነውና ከወዲሁ የከፋ ተልእኮውን አስቀድመን ልንረዳውና ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል።

 

Read 142 times