Thursday, 21 January 2021 00:00

በዓለ ጥምቀትን ሁሉም አካል ሊጠብቀው አማኞችም ከምሥጢሩ ሊሳተፉ ይገባል።

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን
የጌታችን ዐበይት በዓላት የቤተ ክርስቲያናችን ዐበይት በዓላት ናቸው፡፡ ሌሎች የቅዱሳን ጻድቃንና የቅዱሳን መላእክት በዓላት ትርጕም ኖሯቸው ሊከበሩ የቻሉት በጌታችን በዓላት የሚታሰቡ ምሥጢራት በመኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የቅዱሳን በዓለ ልደት እንደ በዓል የሚከበረው ጌታችን በልደቱ ልደተ ሰብእን በመቀደሱ ነው፡፡ ሰማዕታት የተሠዉበት ቀንም ልዩ ተደርጎ የሚከበረው ጌታችን በሞቱ ሞታቸውን ስለ ቀደሰው ነው፡፡ እርሱ ተወልዶ ልደታችንን ባይቀድስልን የቅዱሳን ልደት የሚያስደስት፣ ሞቶም ሞታችን ዕረፍት እንዲሆን ባይባርክልን የሰማዕታት መሠዋትም ከንቱ በሆነ ነበር፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን የጌታ በዓላት በልዩ ትኩረትና ድምቀት ይከበራሉ፡፡ ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል ደግሞ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ስቅለቱና ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ ዳግም ምጽአቱ፣ ወዘተ. በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ከሌሎችም ይልቅ እጅግ ደምቀው የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በዓለ ጥምቀት ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ በተለየ ሁኔታ በዐደባባይ የሚከበር በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የበዓሉ ባሕርይ ከሌሎች በዓላት ይልቅ ብዙ የኅብረተሰብ አካላት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚጋብዝና፡ ብዙዎችን በአከባበሩ ለማካተትም የተመቸ ነው፡፡

 

ከቤታቸው ተቀምጠው መንቀሳቀስ የማይችሉ ዐቅመ ደካሞችና አረጋውያን፣ በተለያዩ አደጋዎችና ሕመሞች ጤናቸው ታውኮ በየጓዳውና በየጤና ተቋማቱ የተኙ ታካሚዎች፣ በየጎዳናው ወድቀው የሚያነሣቸውን ያጡ ምንዱባን፣ በሕይወተ ሥጋ ለመቆየት በተሰማሩበት ክፉ ሥራ የተነሣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው ለመሳተፍ ሥነ ልቡናቸው ተቃውሶ በሩቅ ያሉ ምስኪኖች፣ በዓለም ሩጫ ተይዘው ቤተ ክርስቲያንን ለዘነጉ ብኩን ክርስቲያኖች፣ በአሠሪዎቻቸው ጫና ቤተ ክርስቲያንን መሳለም ብርቅ የሆነባቸውና ቤት ተዘግቶባቸው ያሉ የቤት ሠራተኞች፣ ከሃይማኖት መንገድ ወጥተው የሳቱ የጠፉ ልጆች፣ በተለያየ ምክንያት ከመቅደሱና ከታቦቱ ርቀው የተለዩ ሰዎች ሁሉ በረከተ ቤተ ክርቲያንን በቅርበት የሚያገኙበት ተናፋቂ በዓል ነው፡፡

ከእነዚህ መካከል ለአንዳንዶቹ የመጥሪያ ደወልም ነው፡፡ ታቦተ ሕጉ በየበሩና በየሠፈሩ ዞሮ መባረኩ ‹‹ልጄ ሆይ አንተ በተለያየ ሰበብ ብትርቅና ብትረሳኝም፡ እኔ ግን አስብሃለሁና ወደ ቤትህ ተመለስ›› የሚል የአምላክ የፍቅር ድምፅ ያለበት የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ነው፡፡ ልባቸው በመቅደሱ ሆኖ አካላቸው በመድከሙና በመታመሙ በአካል ብቻ ለራቁትም ‹‹ልጄ ሆይ ምንም እንኳን በአካል ብትርቀኝም በመንፈስህ ከእኔ ጋር እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ልትመጣ ወድደህና ፈቅደህ ሳለ መድከምና መታመም አግኝቶህ ወይም ሰው በማጣት በአካል ባለመምጣትህ አትዘን፤ እኔ ወደ አንተ እመጣለሁና፤ አንተም ዘወትር ከእኔ ጋር ነህና›› የሚል የጌታችንን አስደናቂ የማጽናኛ ቃልን ያዘለ ተልእኮም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ማገልገላቸው ምሥጢሩና ትርጓሜው ረቂቅ መሆኑን ሊገነዘቡትና ሊጠነቀቁለት ይገባል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ወጣቶች የበዓሉ አካላት መሆናቸው ከላይ የገለጽነው የበዓሉ አሳታፊነት ውጤት ነው፡፡ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች መመሥረት ወዲህ በሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ዝማሬ መታጀብ የጀመረው የበዓሉ ሒደት፣ ከግቢ ጉበኤያት ምሥረታ በኋላም ብዙ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎችን በዝማሬ እንዲያገለግሉ ዕድሉን መክፈቱ የታወቀ ነው፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤትና በግቢ ጉባኤያት ያልታቀፉ የየአካባቢው ወጣቶች ደግሞ አካባቢን በማጽዳት፣ ለታቦተ ሕጉ ማለፊያ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ የጉዞ ሥርዓትን በማስከበር፣ መድረኮችን በመገንባትና በመሳሰሉት የየድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡

በዓሉ የሚያመጣውን ይህን ሁሉ አንድነትና ኅብረት ግን ከበዓሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀምበት አይስተዋልም፡፡ ይህ ሁሉ የሰው ኃይል በአስደናቂ ጥምረት በካህናትና በቤተ ክርስቲያን መምህራን እየተመራ በዓሉን በአንድነት ካከበረ በኋላ መበተኑ እጅግ ሊያሳስብ የሚገባ ነው፡፡ ቢያንስ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ዓመቱን ሙሉ ስለ መጠቀም በአንድነት ሊነጋገርና መርሐ ግብር በማውጣትም በተግባሩ ሊተባበር ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለችና ምእመናን እየተሠዉና እየተሰደዱ፣ ቤት ንብረታቸውም እየወደመ ባለበት ወቅት ይህ ግዙፍ የሰው ኃይል የመጨረሻ ዓላማው በዓለ ጥምቀትን ማክበር ብቻ መሆን የለበትም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤያት ይህንን በአጽንዖት ሊያቅዱበት ይገባል፡፡ ወጣቶችን ሰብስበው የማስተማር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው የየአድባራቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ይህንን ጉዳይ ከማንም በላይ ሊጨነቁበት ይገባል፡፡ በየአካባቢው የሚገኙ የጽዋ ማኅበራት ከእስከዛሬው በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር ሊመክሩበት ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ በዓለ ጥምቀት ከመንፈሳዊ ትርጓሜው በዘለለ፡ የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ልዩ ዕሴት፤ ከሀገርም በዘለለ የዓለምም ቅርስ እንደ መሆኑ የአማኙ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀብት መሆኑን በማሰብ የሚመለከተው ሁሉ በዓሉንና የበዓሉን ዕሴቶች በመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል እንላለን።

የረድኤትና የበረከት በዓል ያድርግልን!

 

Read 421 times