Wednesday, 28 April 2021 00:00

መርከባችን ወደቡ ላይ እንድትደርስ ሁላችንም የቀዛፊነትን ድርሻ እንወጣ።

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን
ለዘመናት መንገደኞቿን አሳፍራ እግዚአብሔር አምላክ ወዳዘጋጀላቸውና ተስፋ ወደሚያደርጉት ወደብ ስታደርስ የኖረችው መርከብ (ቤተ ክርስቲያን)  በፈተና ውስጥ ያላለፈችበት ጊዜ ነበር ባይባልም ዛሬ ዛሬ ግን ከሌላው ጊዜ በተለየና በከፋ ሁኔታ ማዕበሉ እየናጣት ትገኛለች። እንደሚታወቀው ይቺ መርከብ ጉዞዋ በባሕር ላይ ነው። ባሕሩ ደግሞ በታላቅ ሞገድ የሚናወጽ ማዕበል ያለበት በመሆኑ ጠንካራና ባለሙያ ቀዛፊ ካልያዛት ከነተሳፋሪዎቿ ልትሰጥም ትችላለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። (ዕብ. ፲፪፥፰) በማለት እንደተናገረው ምንም እንኳን ከቅጣትና ከተጋድሎ በኋላ ዘለዓለማዊ ክብር የሚገኝ ቢሆንም ይህን የቅጣትና የተጋድሎ ማዕበል ግን በትዕግሥት ማለፍን ይጠይቃል። መርከባችን በባሕሩ ላይ ያለውን ጽኑ ማዕበል  ተቋቁማ ባሕሩን ከተሻገረች በኋላ ከገቡ የማይወጡበትን ካገኙ የማያጡትን ወደብ (መንግሥተ ሰማያት) ትወርሳለች። ይሁን እንጂ እንደዚህ ካለው ወደብ ላይ ለመድረስ በባሕሩ ውስጥ ያለውን ማዕበል ማለፍ ይጠይቃል። መርከባችን የምትናጥበት ማዕበል የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የዓለም ጠበብቶች መድኃኒት ያላገኙለት በሽታ፣ አርሶ አደሮቹ ዓመቱን ሙሉ ሲለፉበት የከረሙበትን ሰብል አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ የሚያወድም የአንበጣ መንጋ፣ ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናም የሚከሠት የጎርፍ አደጋ፣ በመርከቢቱ ውስጥ ሥር የሰደደውና መፍትሔ ያልተበጀለት የእርስ በእርስ ክፍፍል ወዘተ. ሁሉ እጅግ የመከራ ጊዜዋን እያራዘመና የመስጠም ዕድሏን እያሰፋው ይገኛል። ስለዚህ ምእመናን የተሳፈሩባት ይህቺ መርከብ ይህን ሁሉ ተግዳሮት አልፋ ተሳፋሪዎቿንም ወደ አሰቡትና ተስፋ ወደሚያደርጉት ወደብ ለማድረስ ሁሉም እንደየድርሻው መሳተፍ ይኖርበታል። 

 

ምድራዊ ባሕርን ለመሻገር መርከብ ውስጥ ለሚሳፈሩ ሰዎች ምን አልባት የተሳፋሪነት ሕጉ የተወሰነ ሊሆን ይችላል። ይህም ለቀዛፊው ዋጋ ከመክፈል ያላለፈ ሊሆን ይችላል። ወደ ማያልፈውና ወደ ዘለዓለማዊው ወደብ ታደርሳቸው ዘንድ ምእመናን የተሳፈሩባት መርከብ ግን ለሁሉም ድርሻ ሰጥታ እንደተሳፋሪ ብቻ ሳይሆን እንደቀዛፊ እንዲያስቡ፣ ከማሰብም በላይ የየድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ታስተምራለች። ድርሻቸውን የሚወጡበት አጋጣሚ ደግሞ አስቀድመው  በመርከቧ ውስጥ ገብተው ከመሳፈር የሚጀምር ሲሆን በመርከቧ ውስጥ  ያለውንና የሌለውን ለይቶ ማወቅንም የሚያጠቃልል ነው። 

ለዚች መርከብ መሻገርና ከወደቡ ላይ ለመድረስ አባቶች የአባትነት ድርሻቸውን በመወጣት ማለትም፡- ወጣቱን በመምከር፣ ፊት አይተው ሳያዳሉ ጥፋተኛውን በመገሠጽ፣ ሀገር ሰላም እንድትሆን ዕለት ዕለት ስለ ሰላም በመጸለይ፣ የውስጥ ክፍፍሉንም በምክክርም፣ በጸሎትም፣ የአበውን የችግር አፈታት ዘዴ በመጠቀም ሊፈቱት ይገባል። እንደ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለውን ክፍፍልም ቁርጠኝነት በተሞላበት መንገድ በመመልከት ምክር የሚያስፈልገውን በመምከር፣ ተግሣጽ የሚገባውን ጽኑ ማዕበል የሆነውን የትውልዱን ክፉ ሐሳብም በመገሠጽ መርከቧን ዳር የማድረስ  የራሳቸውን የቀዛፊነት ድርሻ ሊወጡ ይገባል።

በዚቺ መርከብ ውስጥ የተሳፈሩት አባቶች ብቻ አይደሉም። መንፈሳዊ ማኅበራትም ይገኙባታል። እነዚህ ማኅበራት የዚች መርከብ በባሕር ውስጥ መስጠም የሚያደርሰው አደጋ እነርሱንም አብረው እንዲሰጥሙ የሚያደርግ ነውና እንዳትሰጥም ለማድረግ ከአባቶቻቸው ጋር በመሆን አብሮ መታገል ይኖርባቸዋል። ከእግራቸውም ሥር ሆነው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ መሠረት ያደረገ ምክራቸውን ከልብ በማዳመጥ ምእመናን የተሳፈሩባትን መርከብ ከስጥመት ሊታደጓት ይገባል።

መንግሥትም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን የተሳፈሩባት መርከብ ከሰጠመች እርሱም አብሮ የሚሰጥም መሆኑን ከወዲሁ ሊገነዘብ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ ምእመናን በሃይማኖታቸው (በክርስትናቸው) የክርስቶስ ዜጎች ቢሆኑም እንደ ሀገር ሲታዩ ኢትዮጵያውያን ናቸውና። ሕዝቡ ከመርከብ ጋር አብረው ከሰጠሙ የሚመራው ሕዝብ የሌለው መንግሥት ወይም ሕዝብ አልባ መንግሥት ሊሆን ስለሚችል ነው። 

ምእመናን የተሳፈሩባትን መርከብ ከስጥመት ከመታደግ አኳያ ድርሻ ካላቸው አካላት መካከል ወጣቱ ይገኝበታል።  ሀገር በሰላማዊ መንገድ እንጂ በጦርነት አትገነባም፤ ወደ ጦርነት የገቡ ሀገራት ሲፈርሱና ሲበታተኑ እንጂ ሲያድጉ፣ ሲገነቡ፣ ሲበለጽጉ አልታዩምና ከጊዜያዊ ስሜት ወጣ ብሎ በሰላማዊ መንገድ መወያየትና የሚቀርበውን ጥያቄም በአግባቡ ማቅረብ ያስፈልጋል። ወደ ፊት እየታሰበ ያለውን ሀገራዊ ምርጫም በሰላማዊ መንገድ ማከናወን ያስፈልጋል። ሊነሡ የሚችሉ ጥያቄዎችም ካሉ ከዚያ በኋላ ማንሣት የሚገባ መሆኑን ልብ ሊለው ይገባል። ለቤተ ክርስቲያንም ብሎም ለሀገር የሚገባውን ጉዳይ በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ሆኖ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መታገል ግድ ይላል።

በብሔር፣ በዘር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖት ወዘተ ሳንከፋፈል ምእመናን የተሳፈሩባትን መርከብ ከስጥመት ልንታደጋት ይገባል። የአንዱ ጉዳት ለሌላው ሊታየው፣ የአንዱ ሕመም ሌላውንም ሊያመው ይገባል። ምክንያቱም በጎረቤት የሚነድ እሳት የጎረቤቴን ቤት ነው የሚያቃጥለውና ችግር የለውም ብለን ዝም የምንል ከሆነ ወደ እኛ ቤት መድረሱ አይቀርም። ስለዚህ ችግሩን የሁላችንም አድርገነው በመረባረብ ልንታደጋት ይገባል እንጂ ጉዳት የደረሰበት የአንድ ወገን ቤተ እምነት፣ ብሔር፣ ጎሣ ወዘተ. ብቻ መጮህ የለበትም። 

ለመስማትም፣ ለማየትም በሚከብድ ጽኑ ማዕበል እየተናጠች ያለችው  ነገር ግን በርካታ ተሳፋሪዎችን ያሳፈረችው መርከብ ካለባት ተግዳሮት ወጥታ ወደሰላማዊው ወደብ ትደርስ ዘንድ በውስጧ ከተሳፈሩት መንገደኞቿ ባሻገር ከውጭ ሆነው የሚመለከቷትም ለደኅንነቷ ሊረባረቡ ይገባል። ቀዛፊዋም እንደዚሁ መርከቢቱና መንገደኞቿ በባሕር ሰጥመው እንዳይቀሩ የራሱን የቀዛፊነት ድርሻ በንቃት ሊወጣና ተሳፋሪዎችን  ሊደርሱ ካሰቡበት ወደብ ሊያደርሳቸው ይገባል። ተሳፋሪዎችም እንዲህ ያለውን የቀዛፊነት ድርሻ ሊረባረቡበት እንደሚገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በዚህ ትብብርና የአንድነት ጉዞ ውስጥ  ደግሞ ጎልቶ የሚታይ ድርሻ ካለው አካል ጀምሮ ሁሉም ድርሻ እንዳለው መዘንጋት የለበትም። ስለዚህ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከማኅበራት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ከወጣቱ ትውልድ፣ ከፖለቲከኞች፣ ወዘተ ጀምሮ ሁሉም ድርሻቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል።

 

Read 496 times