ጥቂት ለማይባሉ ላለፉት ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰላም እጦት ተቸግራለች። በአንዱ በኩል የነደደው እሳት ጠፋልኝ ስትል በሌላ በኩል ይነሣል። ንብረቶች ወድመዋል፤ ዜጎች ለብዙ እንግልትና ሞት ተዳርገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ አድባራትና ገዳማት ደግሞ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሾችና ዋነኛ ዒላማዎች ሆነው ቆይተዋል። አሁንም የተሰደዱና ያልተቋቋሙ ዜጎች እጅግ ብዙ ናቸው፤ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ ከሚገኙት የሀገራችን ክፍሎች ሁሉ ‹ዳቦንና ሰላምን› የሚጠብቁ ወገኖች አያሌ ናቸው።
ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ሰምተው ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላት አሉ። ይሁንም እንጂ ከችግሩ ግዝፈትና ክብደት የተነሣ በቂ ሊሆን አልቻለም። ስለዚህ አሁንም ሰላማችንንና ዳቦአችንን የሚፈልጉ ወገኖች ብዙ ናቸው። የሰላሙንም ሆነ የምግቡን ጉዳይ ከመንግሥት ጀምሮ መልካም ነገርን ለማድረግ የማይመለከተው አካል ስለሌለ ሁሉም የቻለውን ሊያደርግ ይገባል።
መንግሥት፡- ከምንም በላይ የዜጎች ደኅንነት፣ በሰላም መኖር፣ የዕለት ምግባቸውን ማግኘት መቻል፣ በአጠቃላይ መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው መኖር መቻል ሊያሳስበውና ሊያስጨንቀው ይገባል። በመሆኑም ሰላም ማስከበር፣ ከየቤታቸው ተፈናቅለው፣ በባዶ ሜዳ ላይ ወድቀው፣ ሰላማቸውን ተገፍፈው እያዘኑና በረኃብ አለንጋ እየተገረፉ ያሉትን ዜጎቹን ማሰብ ይኖርበታል። ወንጀለኛን ለሕግ ማቅረብና ለተጎዱትም በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።
ቤተ ክርስቲያን፡- ከላይ እንደተገለጸው ምንም እንኳን የተጨነቁትን ማረጋጋት፣ የተራቡትን መመገብ፣ ለታመሙት መጸለይ፣ ለሞቱት ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ፣ ወዘተ የዕለት ተዕለት ተግባሯ ቢሆንም ከምንጊዜውም በላይ አሁን እጇን መዘርጋት አለባት። ከዚህም አንጻር የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ መምህራን፣ ዘማርያን፣ ማኅበራት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ምእመናን ሁላችን ልንጠነቀቅላቸውና ልናደርጋቸው የሚገቡን ምግባራት አሉ።
የመጀመሪያው፡- የተጎዱ ወገኖቻችንን ሥነ ልቡና መጠበቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት ክልሎችም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተከሠቱ ጦርነቶችና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ቀጥተኛ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ከአካልና ከንብረት ጉዳቱ በላይ በሥነ ልቡና ተጎድተዋል። ቤተ ሰቦቻቸውን አጥተዋል፤ የሰው ልጅን ክፋትና ጭካኔ በዓይናቸው አይተዋል፤ ወይም ከቤተሰባቸው አባላት ቢያንስ አንዱ በዚህ ችግር ውስጥ ያለፈ ነው። በነዚህ ወገኖቻችን ፊት ቆመን ስለ ፖለቲካዊ ምልከታችንና ስለ ተፈጸመው ጉዳት ፖለቲካዊ ቅርጽ መተንተንና መከራከር ሰብአዊነትን አለማስቀደም ነው። ንግግራችን ሁሉ ማጽናናት ላይ ቢያተኩርና በጸሎታችን ሁሉ ብናስባቸው እጅግ መልካም ነው። ይህ ባይሆን እንኳን ጥፋተኛ ቢሆንም ባይሆንም በጦር የተወጋን ወገን በቃል ጦር ደግመን እንዳንወጋው ዝም ማለት የተሻለ መፍትሔ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ምናልባትም ከቁሳዊው ጉዳት ይልቅ የመንፈስ ጉዳቱ ቍስሉ የሚጠገን ሳይሆን የሚያመረቅዝ ይሆናል።
ለመፈወስም ዘመናትንና ትውልድን ሊጠይቅም ይችላል። ስለዚህ ሰላምታችንን ለሚፈልጉት ሁሉ አዘውትረን ሰላምታችንን ልናቀርብላቸው ይገባል። አቅም ባይኖረን እንኳን አብረናቸው እንደ ሆንን የምናሳይባቸውን መንገዶች ማስፋት ይኖርብናል።
ሁለተኛው፡- በቻሉት አቅም ሁሉ በልተው እንዲያድሩ ማስቻል ይገባል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የተቋረጡ አገልግሎቶች፣ ከምንም በላይ ደግሞ ዕለት ዕለት የሚራቡና የሚታረዙ በሃይማኖት የሚመስሉንም የማይመስሉንም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አሉ። ችግሩ ከደረሰባቸውም ሆነ ከየአለንበት አህጉረ ስብከቶቻችን ጋር በመመካከር ለእነዚህ ወገኖቻችን ከሰላምታችን ጋር ዳቦአችንንም ልናካፍላቸው ይገባል።
ቃለ ወንጌልን አስተምህሮ ያላመኑትን ለማሳመን፣ የአመኑትን ለማስጠመቅ፣ የተጠመቁትን ለማጽናት፣ ሃይማኖት ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች ሁሉ እየተዘዋወሩ ለማስተማር፣ ሰዎች መመገብና በሰላም መኖር አለባቸው። ስለዚህ ለሰዎች ሰላምና በልቶ ማደር እጅግ አብዝተን መጨነቅ አለብን።
አባቶቻችን በሃይማኖትና በሀገር ላይ የመጣ ጠላትን ታቦት ይዘው ዘምተው በአድዋ መመከታቸውን የምንዘክርበት ወር ላይ መገኘታችን ደግሞ ለዚህ ጥሩ የማንቂያ ደወል ነው። ዛሬ በሥውር እንጂ እንደ ጥንቱ በግልጽ የሚመጣ ጠላት ላይኖር ይችላል። እኛም ግልጹን ብቻ ሳይሆን ሥውሩንም፣ ግዙፉን ብቻ ሳይሆን ረቂቁንም እየመረመርን ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር አለኝታነታችንን ማሳየት ይገባናል።
የሰላም አምላክ ሰላሙን ከእኛ አይለይብን!