Friday, 04 September 2020 00:00

ችግሮች የሚወገዱት፣ አውጥተን ስንነጋገርባቸው  እንጂ፣ ስንሸፋፍናቸው አይደለም!

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን
በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮአችን እያደግንና እየጠነከርን መሄድ የምንችለው፡- በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ጥፋቶችና የወደቅንባቸውን ችግሮች በትክክለኛው መንገድ በመለየት ተጸጽተን ለዘለዓለማዊ ሕይወታችን  ንስሓ ስንገባ፣ ለማኅበራዊ ችግሮቻችንም ተጠብበንና ተጨንቀን መፍትሔ የምንፈልግ ስንሆን ነው፡፡= ማኅበረሰባዊ ለሆኑ ችገሮች መፍትሔ በምንሻበት ጊዜም በተቻለን መንገድ የምንመርጣቸው ስልቶችና መንገዶች፣ ሁል ጊዜም መልካምና ለችግሩ አግባብነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚጠበቁ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ እንደየግል ግንዛቤአችን የምንሄድ ከሆነ ወደምንፈልገው ግብ የማያደርሱን ወይም በተቃራኒው ችግሩን የሚያባብሱ ወይም ችግሩን ለጊዜው የጠፋ በሚመስል መንገድ በማዳፈን፣ በኋላ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህም  ጊዜያዊ የሆነ ፋታን በመፈለግ  መሠረታዊ የሆነውን ችግር ከነምክንያቱ ለመስማት፣ ለማወቅና ለመናገር፣ ብሎም  ለመፍትሔው አቅማችን በፈቀደ መጠን ኃላፊና ባለድርሻ የመሆን ግዴታ ያለብን መሆኑን ከፍ ያለ ዋጋ ካለመስጠት ሊመጣ የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ዘመን በሀገራችን ውስጥ ሕገ ወጥና ኢ-ሰብአዊ በሆኑ ድርጊቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ በተለየ ሁኔታ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ ሰቆቃና በአምልኮ ነፃነት ላይ የሚደረግ ክልከላ፣ የንብረት ውድመትና ቃጠሎን አላየንም፤ አልሰማንም፤ በድንገት የተፈጠረ ነው፤ ወይም ጉዳቱና ጥፋቱ የተለየና ምንም አይደለም! ብለን ማለፍ የማንችለው ነው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኦርቶዶክስ ምእመናን ላይ ታቅደው እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶችን ስንመለከታቸው፡- ሰበባቸው ምንም፣ ይሁን ምን፣ ለጥቃቶቹ ዒላማ የሚደረጉት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ምእመኖቿ መሆናቸውን ለማስረዳት በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ  የቆዩ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በአስረጂነት በማቅረብ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

 

ለምሳሌም በቅርቡ፡- ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመን የሆነው አርቲስት ኃጫሉ ሁንዴሳ፣ የፖለቲካ ተልእኮ ባላቸው ሰዎች ከተገደለ  ከሰዓታት በኋላ፣ ለብዙ ወራት ዝግጅት የተደረገበት በሚመስል ሁኔታ፡- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ቦታዎች በሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማሳደድና ሰቆቃ እንዲሁም የንብረት ውድመትና ቃጠሎ፣ ከዓይነ ኅሊናችን ያልጠፋ፣ ግዙፍነት ያለው ማሳያ ነው፡፡ 

እነዚህን የሰቆቃ ሥራዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ የፈጸሙት ቡድኖችና ግለሰቦች ከተጐጂ ወገኖቻችን ጋር በአንድ አካባቢ የተወለዱ፣ያደጉና የሚኖሩ፣ በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ፣ እናትና አባት፣ የሃይማኖት መሪም ያላቸው፣ ኢትዮጵያውያን እንጂ፤ ሃይማኖትና የሃይማኖት መሪ፣ ባህልና ትውፊት የሌላቸውና ከውጭ የመጡ የሌላ ሀገር ሰዎች አልነበሩም፡፡ በእውነት እንነጋገር ከተባለ፡- የሀገራችን ሕዝብ በሃይማኖት፣ በመፈቃቀርና በመከባበር የሚኖር፣ የወላጆችና የልጆች ግንኙነት እንደ ምዕራባውያን ያልሆነ፣ ማኅበራዊ መተሳሰብን የሚያጠናክሩ ባህላዊ ሁኔታዎች ባልጠፉበትና ሕግን ለማስከበር በየደረጃው የተዋቀሩ የመንግሥት አካላት ባሏት ሀገር ውስጥ፣ ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ ለተፈጸሙት ሕጋዊነትና ሰብአዊነት ለጎደላቸው ለእነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶች፣ ስያሜ መስጠትም ሆነ መግለጽ ከባድ ነው፡፡

ሃይ ባይ በሌለበት፣ በጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች አማካኝነት አሏህ ወአክበር! በማለት በምእመናን ላይ የተፈጸመውን ይህን ተግባር ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ያሉ የእስልምና አባቶችና እናቶች ያወገዙት ሲሆን፤ መንግሥትም በጥቃት ፈጻሚዎቹና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የአመራር አካላትና አባላት ላይ ርምጃ ለመውሰድ በማጣራት ላይ የሚገኝበት ሁኔታ፣ ችግሩ በሕግ የተፈቀደ እስከሚመስል ዝም ተብሎ ከታየና ከቆየ በኋላ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ያለው የክትትል ሁኔታ የሚበረታታ ነው፡፡ ጥፋት ፈጻሚ የሆኑት ጥቂት ቡድኖች ፣ የወንጀል ድርጊታቸውን ሲፈጽሙ፣ በተወሰነ ደረጃ ከአንዳንድ የእስልምና አማኞችና አዛውንት ከሆኑ አባቶች  ሰብአዊ ተግባር ውጪ፣ ለተወሰኑ ሰዓታት የገደባቸውና የተከላከላቸው የማኅበረሰብም ሆነ የመንግሥት ኃይል  አልነበረም። ስለዚህ ድርጊቱ ሃይማኖትና ዘርን ሳይለይ ሁሉንም ያሳዘነ ከመሆኑ አንፃር፣ የጥፋት ዘመቻው ይህን ያህል ጉዳት በታቀደና በተደራጀ ሁኔታ አንድ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ  ማድረስ ስለቻለበት ዓላማ፣ ግብ፣ ዐቅም፣ ዝግጅትና ምቹ ሁኔታ ጭምር እንጂ፣ የጥፋቱ መገለጫና ውጤት የሆነውን የሕመም ስሜት(ጉዳት) በማከም ላይ ብቻ የተገደበ እንዳይሆን መታየት አለበት፡፡  

ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፡- የሀገራቸው ሰላም መሆን የሚገዳቸውና  የሚያስጨንቃቸው፣ እንደማንኛውም ዜጋ ለልማቷና ለልዕልናዋ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ እንዳስፈላጊነቱም ሰማዕትነት መክፈል የሚጠበቅባቸው እና ሀገራቸው ያለችበትን ሁኔታም የሚረዱ መሆኑ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ የሀገሪቱን ሰላም መሆን የማይፈልጉ ቡድኖች በአሁኑ ሰዓት ከሌላው ነጥለው ኦርቶዶክሳውያንን በተለየና ተደጋጋሚነት ባለው መንገድ እያጠቁ ያሉበትን ሁኔታ በአግባቡ አለመገንዘብ፣  ጥቃቱ በማንኛውም ዜጋ ላይ እየተፈጸመ ያለ ነው ማለትና  ተራና ቀላል አድርጎ መመልከት፤ እንዲሁም በቀጣይ የሚመጣው ችግር ማን ላይና ምን ሊሆን ይችላል? ብሎ አለማሰብና  አለመዘጋጀት፤ ሞኝነት ነው፡፡ 

ስለሆነም የጥፋት ተልእኮ ባነገቡ ጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሕይወት፣ ሥነ አእምሮ፣ አካልና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በምንም መልኩ ሙሉ ለሙሉ መካስ የማይቻል ቢሆንም፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደነበሩበት ለመመለስ፣ በሁሉም በኩል ጥረት ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተደጋጋሚነት እየተከሠተ ያለውን ይህን ጥፋትና ችግር ለማስቆም፡- ሁላችንም የጥፋት ድርጊቱን ዓላማ፣ ግብና ዕቅድ መገንዘብ፣ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። በዚህ መሠረት ፖለቲካን ሽፋን በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ እንደ ፋሲካ በግ ለእርድ  በሚቀርቡበት ሴራ፣ ውስጥ ፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ እየተሳተፉ ያሉ አካላት እነማን እንደሆኑ በመለየት፣  የጥፋት ተልእኮውና ሴራው ዘላቂነት ባለው መንገድ እንዲቆም፣ ትኩረት ሰጥተን  በየድርሻችን ለመሥራት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ከተፈጸሙት የጥፋት ድርጊቶች በኋላ ሁኔታውን ያወገዙ አካላት ይህን ክፉ ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ፣ ከጥፋት ድርጊቱ በስተጀርባ ያለውን ድብቅ ሴራ ፈልፍሎ በማውጣት ጥፋተኞችን ለሕግ ማጋለጥ ከዚህ በተጨማሪም ካለፈው ማለትም ማድረግ ይገባቸው ከነበረውና ካልነበረው ተምረው፣ የሚመጣውን ጊዜ በመዋጀት፣ በየድርሻቸው ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት ይገባቸዋል፡፡

 

ባጠቃላይ ችግሩ በመወገዝ ብቻ ያልቆመና ላለፈው ብንዘገይም የሚመጣውን ለመቅደም ማሰብ ያለብን ስለሆነ፣ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ ለመስጠት፡- በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ሥራዎችን (ክትትሎችን፣ ጥናትና ምርምሮችን እንዲሁም ውይይትና ምክክሮችን) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በየጊዜው ውይይት ማድረግ ወሳኝነት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥፋቶችና ችግሮች የሚወገዱት  በሚገባው ደረጃ አውጥተን ስንነጋገርባቸው  እንጂ ስንሸፋፍናቸው አይደለም። ስለሆነም በጉዳዩ ላይ ዘላቂነትና ተጨባጭነት ያላቸውን ሥራዎች በየድርሻችን እየሠራን፣አፈጻጸማቸውንም በየጊዜው በመገምገም፣ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ብሎም ሀገርን ከአጥፊዎች እንጠብቅ፡፡ አጥፊዎችም ርምጃ እንዲወሰድባቸውና ከዚህ መሰል ድርጊታቸው  እንዲታቀቡ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Read 757 times