Wednesday, 07 April 2021 00:00

ከሰላም እንጂ ከግጭት የምናተርፈው ነገር የለምና ሁላችንም ለሰላም እንትጋ!

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ  የሰላም እጦት እንደ ውኃ ጥም እያንገበገባት ትገኛለች። ምክንያቱን በተመለከተ እንኳንስ ችግሩ በቀጥታ የደረሰበት አካል ችግሩን ያደረሰውም ቢሆን ጉዳዩን ወደ ሌላ አካል መግፋት እንጂ የራሱ ችግር እንደሆነ አምኖ አይቀበልም። ይባስ ብሎም ቀድሞ በመጮኽ የተበደለና የተገፋ አድርጎ ለዓለም ያውጃል። ዓለም ደግሞ ቀድሞ የሚሰማውና ባይችልም መፍትሔ አመጣለሁ ብሎ የሚሞክረው ቀድሞ ለጮኸለት አካል ነው። ይህ ደግሞ እንደምንመለከተው ችግሩን የሚያባብስ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም።  በዋናነት ግን ሀገራችን እየተከተለችው ያለው የፖለቲካ ርእዮትና፣ ዓለማቀፋዊው የተሳሳተ ትርክት ሲሆን ከዚህም ባሻገር ሀገር በቀሎቹ እኩያን ወይም ጡት ነካሾች በሀገራችን ለሠላሳና ለአርባ ዓመታት የጥላቻ ንግግርና የሐሰት ትርክት፣ እንክርዳድን በትውልድ አእምሮ ላይ ሲዘሩ ኖረዋል። እኩያኑ የዘሩትን ራሳቸው ቢያጭዱት መልካም ነበር። የሚያሳዝነው እኩያኑ የዘሩትን ንጹሐኑ ያንኑ ማጨዳቸው ነው። ይህ ደግሞ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲመለከተው እያደረገ ወደ እርስ በእርስ ግድያና እልቂት አስገብቶናል። ለችግሩም መሠረታዊና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማምጣት ከማንችልበት ሁኔታ ላይ እንድንገኝ አድርጎናል። 

 

በትግራይ፣ በማይካድራ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ ሰሞኑን ደግሞ በአጣየ አካባቢ የተከሠተው ችግር ሀገርንም ቤተ ክርስቲያንንም የሚጎዳት ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ቁርሾ (ዘላቂ ጠባሳ) ጥሎ የሚያልፍ እንጂ ማንም ቢሆን አንዳች ነገር የሚያተርፍበት ድርጊት አይደለም። ምን አልባት የሚያተርፍ አካል አለ ከተባለም የሰውን ሰላም የማይወደው፣ ሰይጣንና የግብር አበሮቹ ብቻ ናቸው። እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ  ከአንድ አካል ብቻ የሚጠበቅ ነገር አይደለምና ሁሉም በየድርሻው ሊታገለው ይገባል። 

እንግዲህ  ከላይ  በዝርዝር የተጠቀሱትን የግጭት መንሥኤዎችና የሰላም ተግዳሮቶች በዘላቂነት በመፍታት የየራሳቸው የተለየ ድርሻ ካላቸው አካላት መካከል የመጀመሪያው መንግሥት ነው። ስለሆነም መንግሥት አሁን እየተከተለው ያለውን የፖለቲካ አካሄድ ቆም ብሎ በማጤን ችግሩን በአግባቡ ሊፈታ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይኖርበታል። ችግር በተፈጠረ ቍጥር የርዳታ ቡድን እያቋቋሙ ለጊዜያዊ መፍትሔ መሯሯጡ ይህን ያህል የጎላ ጠቀሜታ የለውም። ነገሩ “ለሰጪም አያንሰው ለበይም አይደርሰው” ስለሚሆን መንግሥት በደከመውና በሮጠው ልክ ተጎጂዎችን መርዳት ሳይችል ይቀራል። ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ብዙ ቢደክም የተጎጂዎችን ችግር ስለማይፈታ መልሶ ከትችትና ከወቀሳ ላይ ይጥለዋል። ይህ ማለት ግን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ጊዜያዊ ርዳታም  ቢሆን አያስፈልግም ማለት አይደለም። ነገር ግን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው ቆም ብሎ ከልብ ማሰብና የግጭት ምንጩን የሚያደርቅ ሥራ መሥራት ነው። አዳንዴ የጥፋት ቡድኖች የሚይዙት የጦር መሣሪያ፣ ያላቸው ቅንጅት፣ መረጃውን በፍጥነት ለሕዝብ ለማድረስና ግጭቱን ለማባባስ የሚንቀሳቀሱበት ፍጥነት ምን አልባትም በመንግሥት ውስጥ ያሉ አካላት ድጋፍ አለበት ብለን እስክንጠራጠር ድረስ የሚያደርሰን ሆኗል።

ወደ ፊት እየታሰበ ያለውን ሀገራዊ ምርጫም በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ሰላም መቅደም አለበት። ሰው የህልውና ስጋት እያስጨነቀው ምረጡኝ ብሎ መቀስቀስም እንዲያው ለይስሙላ መንቀሳቀስ አልያም እኔ ከኖርኩ ምን ቸገረኝ የማለት ያህል ይመስላል። በእርግጥ “ዳሩ ሲፈታ መሀሉ ዳር ይሆናል” እንዲሉ አባቶች በሩቅ የምናየው የሚመስለን ችግር በአጭሩ ካልተፈታ ነገ ከነገ ወዲያ መሀል ላይ የማይመጣበት ምክንያት የለም።  ደግሞም መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ነውና በዚህ ላይ ጠንከር ብሎ ካልሠራ “ካልጠበቅሽው በላሽው” እንደሚባለው መንግሥት የሕዝብን ሰላም ካላስጠበቀ ሰላሜን ተነጥቄያለሁ ብሎ መንግሥት ላይ መጮኹ አይቀርም። ይህም ሁኔታ ከአጥፊዎች ባልተናነሰ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል።

እነዚህን ሀገራዊ ችግሮች በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ሌላኛዋ ባለ ድርሻ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ናት። እንደሚታወቀው ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት በቅዳሴዋ፣ በማሕሌቷ፣ በሥርዐተ አምልኮዋ ሁሉ ስለ ሰላም ያልጸለየችበት ጊዜ የለም። ይሁን እንጂ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ማመልከቱ እንዳለ ሆኖ በሰው ሰውኛውም ከሚመለከተው አካል ጋር መሠረታዊ የሆነ ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መሥራት ይኖርባታል። እንደ ሀገረ ስብከት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ያሉ ቢሆንም ከችግሮቹ ስፋት አኳያ አጥጋቢ ናቸው ማለት አይቻልም። ሀገራዊ የሆነ ውይይት፣ በሲኖዶስም ሆነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ መደረግ ይኖርበታል። ችግር በተፈጠረ ቍጥር መግለጫ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጋርም በየደረጃው ጥልቅ ውይይት ማድረግና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል።

ሁል ጊዜ ችግር በተፈጠረ ቍጥር ሌላው አይጠቃም ባይባልም የመጀመሪያዋ ተጠቂ ቤተ ክርስቲያን ናት። አባቶች ደግሞ ለቅዱስ ጴጥሮስ “በጎቼን ጠብቅ” ተብሎ የተሰጠው ኃላፊነት የእነርሱም ነው። ምንም እንኳን የአባቶቻችን መንጋን የመጠበቅ ኃላፊነት በቀዳሚነት ምእመናንን ከኃጢአትና ከክሕደት በመጠበቅ የጽድቅ ሥራን እንዲሠሩ በማድረግ መንግሥቱን እንዲወርሱ ማስቻል ቢሆንም ነፍስ የጽድቅ ሥራን የምትሠራው በሥጋ ህልውና ላይ ቆማ ስለሆነ ምእመናን በግፈኞች ሲገደሉ፣ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቍጥር ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል ዝም ብሎ ማየት ከተጠያቂነት አያድንምና እንደቀደሙ አባቶች ሳያፍሩና ሳይፈሩ መንግሥትን ድኃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ተመለስ ሊሉት ይገባል። 

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ የራሳቸው የሆነ ድርሻ ያላቸው ብዙ ሕዝብ የሚከተላቸውና ሐሳባቸውን የሚጋራቸው  ፖለቲከኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ፖለቲከኞች ዛሬ የሆነውንም ያልሆነውንም ወሬ በሕዝቡ አእምሮ ላይ እየነዙ ሰውን እርስ በእርስ አጋጭተን የፖለቲካ ጥቅም እናገኛለን የሚሉ ፖለቲከኞችን እየተመለከትን ነውና እነዚህ ፖለቲከኞች ይህ ዓይነት ድርጊታቸው ሊያጎድላቸው እንጂ ሊያተርፋቸው እንደማይችል መረዳት ይኖርባቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚያችም ምድር ክፉ የተናገሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሰፍት ሞቱ” (ዘኍ.፲፬፥፴፯) ተብሎ እንደተጻፈ ክፉ ወሬ ለማንም አይጠቅምምና ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። ይልቁንስ ሕዝቡን እርስ በእርሱ እንዲተሳሰብ፣ ተከባብሮና ተዋድዶ እንዲኖር፣ በኢትዮጵያዊና በሰብአዊነት መንፈስ እንዲኖር ማስቻል ይገባል።

በመጨረሻም ሕዝቡ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው በሚያስቡትና በሚያወሩት ክፉ ወሬ እየተሰናከለ የማይጠፋ ጠባሳ ጥሎ ከመሄድ መቆጠብ ይኖርበታል። አንዳንዴ የሚነገር ሁሉ እውነት አይደለምና  “ወሬያችሁን ለራሳችሁ አድርጉት” ሊላቸውም ይገባል። አብሮ ተሳስቦ የኖረ ሕዝብ፣ በኀዘኑም ሆነ  በደስታው ጊዜ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ልዩነት ሳይፈጥር አንድ ላይ የኖረ ሕዝብ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚለቀቅ የጥፋትና የሐሰት ትርክት (ወሬ) ጉዳዩን ማባባስ አይገባምና ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። ደግሞም “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባለው የመጣውን ወሬ ሁሉ እየተከተሉ ሀገርን ከማፍረስ መታቀብ ታላቅ ዋጋ አለው ። “ሀገራችንን ለወሬኞች፣ ለጠላት አሳልፈን አንሰጥም” ሊልም ይገባዋል።

ይህን ክፉ ወሬ ለወሬኞቹ በመተው ከየቦታቸው ተፈናቅለው፣ በብርድ ፣ በረኃብ፣ በጥም፣ ወዘተ. እየተሠቃዩ ያሉትን በኢትዮጵያዊነትና በሰብአዊነት መንፈስ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጎሣ፣ ቀለም ወዘተ ሳንለይ ልንደርስላቸው ይገባል። በዚህም ሁሉ ተሳስበን በከንቱ ወሬ ሀገራችንን ከማፍረስ ተቆጥበን ክፉ ጠባሳን ሳይሆን መልካም ስምና መልካም ታሪክ ለመጪው ትውልድ ልናስተላልፍለት ይገባል። 

 

Read 582 times