Friday, 16 October 2020 00:00

መከራ መስቀሉን መሸከም ሰማዕትነትን በተግባር መፈጸም ነውና መሳቀቅ አይገባም።

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

በ፳፻፲፫ ዓ.ም በዓለ መስቀል ተከብሮ የዋለው በተከታታይ በተፈጸሙ  ጥቃቶች ምክንያት  ሰማዕትነትን የተቀበሉ ምእመናን በእንዴት ዓይነት መከራ እንዳለፉ በተግባር ባየንበት ሁኔታ ነው። መከራ መስቀሉ የሚታሰበው በልቅሶ፣ በመከራ፣ በኀዘን፣ በመሳደድ  መሆኑን በዐይናችን አይተናል፤ በጆሯችን ሰምተናል። መንግሥት ባለበት ሀገር ክርስቲያኖች በዓለ መስቀልን በኀዘን እንዲያሳልፉ  ማድረግ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ” የተባለውን በተግባር ተተግብሮ አይተነዋል። ይህ ድርጊት የቤተ ክርስቲያንን ክብር የበለጠ የሚገልጥ ቢሆንም ሃይማኖትን ተገን አድርገው ግፍ ለሚፈጽሙ ግን በአባቶቻችን ዘመን የዓላውያን ነገሥታትና መኳንንትን የግፍ አገዳደል ዳግም እያሳየን ነው።  በክርስቲያኖች ላይ ገሀድ የወጣ አድልዎ ተፈጽሞባቸው ሲያለቅሱ መዋላቸው መንግሥትን ትዝብት ላይ የሚጥል ሲሆን በሌላ በኩል ዘመን ሰጠን ብለው ከልክ የሚያልፉ አካላት ከማይችሉት አምላክ ጋር እየተገዳደሩ፣ ሞታቸውን እያፋጠኑ መሆኑን እንድንረዳ የሚያደርግ እኩይ ድርጊት ነው። ቤተ ክርስቲያንን ምክንያት እየፈለጉ መግፋት  ለ፳፻ ዘመናት የዘለቀ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሀገራችን ተከሥቶ ማየታችን እጅግ የሚያሳዝን ነው። በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን መከራ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ከመማጸን በተጨማሪ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅን ተግባር መፈጸም ይገባል። በሃይማኖታችን ምክንያት መንግሥታዊ ጥቃት ሲፈጸምብን ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ተግባራትን መፈጸም ነው።  የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያናችን “የሰማዕትነትን ክብር ይሰጠን ዘንድ ስለ ሰማዕታት እንማልዳለን” በማለት ዕለት ዕለት የምትጸልየውን ሰምቶ  ለክብር እንዲያበቃን አምላካችንን መማጸን ነው። ሁለተኛው እጃችንን አጣጥፈን፣ አንድ ቦታ ተቀምጠን እስከምናልቅ ከመጠበቅ በክርስትና ሃይማኖታችን የሚተኩትን እግዚአብሔር እንዲያበዛቸው ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን ማጠናከር ነው። ይህም በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ የሮማ ክርስቲያኖች ከሞት የተረፉበትን መንፈሳዊ ጥበብ መተግበርን ያካትታል። የሮማ ክርስቲያኖች ከሞት የተረፉት ከብረት የጠነከረ አንድነት የነበራቸው በመሆኑ ጭምር እንደነበር መረዳት ይገባል። እርስ በርስ እየተተቻቸንና መልካም ሥራ ለሚሠሩት የማሰናከያ ድንጋይ እየሆንን ይህንን የመከራ ዘመን እንደማናልፈው መረዳት ይኖርብናል። በመለያየትና በመተቻቸታችን ለጠላት የተመቸን እንሆናለን እንጂ ለራሳችንም ለቤተ ክርስቲያንም ስለማንጠቅም የመጥፊያ መንገዳችንን እንዳናዘጋጅ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ላለፉት አርባና ኀምሳ ዓመታት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ከኢትዮጵያ አጥፍቶ ታሪክ ለማድረግ በዕቅድ ሲሠራበት የኖረውን እኩይ ድርጊት በማልቀስና በማኅበራዊ ሚዲያ  በመንጫጫት ብቻ ማስቆም እንደማንችልም መረዳት ያስፈልጋል። የቅዝምዝሙን አመጣጥ አይቶ ጎንበስ ብሎ ለማሳለፍ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ክርስቲያናዊ ፈሊጦችን በመጠቀም ዘመኑን መዋጀት የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች የቤት ሥራ መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል። በመናገርና ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳወቅ ብቻም በዕቅድ የሚፈጸመውን የጠላትን ጥቃት ማስቆም አይቻልም። ክርስቲያኖችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እኩይ ዓላማ ይዞ እያሠለጠነ ለሚያስፈጀን አካል ጥያቄ ማቅረብ ንብረታችንን ከሰረቀ ሰው ጋር ፍለጋ መውጣት ነው።   በዚህ ዘመን በሌሎች መሥዋዕትነት ለክርስቲያኖች መልካም ዘመን ይመጣላቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት በመሆኑም ከስሜታዊነት ርቀን በአስተዋይነት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ መሥራት ይኖርብናል። ከአባቶቻችን የተቀበልናት መክሊት (ክርስትናችን) በእኛ ዘመን እንዳትቀበር እግዚአብሔርን ይዘን የምንችለውን ሁሉ ለመፈጸም መዘጋጀት ታላቅነት ነው። ዘመኑ ክፉ በመሆኑ  ወደ ፊትም በዓለ  መስቀልን ስናከብር እንደዚህ ዓይነቱ መከራ እንደሚጠብቀን እያሰብን መዘጋጀት እንጂ በክፉ ወሬ መፈታት ተሸናፊነት ነው። ፀረ ኦርቶዶክስ የሆኑ የዞንና የከተማ ባለሥልጣናት ኦርቶዶክሳውያን መስቀልንና ጥምቀትን እንዳያከብሩ ሲከለክሉ ቆይተዋል። ዘንድሮም በዓሉ ሳምንት ሲቀረው ልማደኞቹ የሆሣዕና ባለሥልጣናት ወገኖቻችን በዓለ መስቀልን እንዳያከብሩ ከልክለዋል።  አንድ ቦታ እየከለከሉ ሌላ ቦታ እየፈቀዱ ያሉትን ባለሥልጣናት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እኩል ማገልገል እስከምትጀምሩ ሰላማዊ ትግላችንን አናቋርጥም ልንላቸው ይገባል።  እነዚህ ሰዎች መደበቂያቸው ሃይማኖት ወይም ጎሳ ነው። ዓላማቸው ባይሳካ እንኳ ሕዝብ ጎራ ለይቶ ደም ሲፋሰስ በሰው ኀዘን የሚደሰቱ ብዙ ከንቱ ሰዎች ስላሉ እነርሱ በሄዱበት መንገድ መጓዝ ሽንፈት መሆኑን ዐውቀን በመንፈስ ልዕልና ላይ በመቆም ማሸነፍ ይገባል።  ሀገርን በሥራ ከመለወጥ ይልቅ ተንኮል በመሸረብ ውለው የሚያድሩ ሰዎች ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው እንዳይጠየቁ በማዘናጋት ችግር እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ባለሥልጣናቱ ይህን የሚፈጽሙት ሕዝብን ሁሉ እኩል ሊያገለግሉ የተቀበሉትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የእኛ ለሚሉት ሃይማኖት በማድላት ነው። የሆሣዕና ከተማ ክርስቲያኖች ፍትሕ ማጣት የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ፍትሕ ማጣት መሆኑን መረዳት ነበረባቸው። እነዚህ ባለሥልጣናት  ራሳቸውን ከሕግ በላይ ማድረጋቸው በመላ ሀገሪቱ የምንገኝ ኦርቶዶክሳውያን እንድንተባበር ያደርገናል እንጂ አያለያየንም።    መፍትሔውም  መንግሥት  የሕግ የበላይነትን አስከብሮ ጉዳት ደርሶባቸው ሜዳ ላይ ተበትነው የሚገኙትን፣ በየቤተ ክርስቲያኑና በየግለሰቦች ቤት ተጠልለው ያሉትን ክርስቲያኖች ሰብስቦ ወደቀያቸው መመለስ በቀደመው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲኖሩ ማድረግ፣ በቀጣይም እንዲህ ያለ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከልና መጠበቅ ይገባል። ይህንም ሁሉ መከራ ለመከላከል ሰላማዊና ቤተ ክርስቲያን በምትፈቅደው መሠረት እየታገሉ በትዕግሥት ማለፍንም የዕለት ተለት ተግባራችን ማድረግ ይኖርብናል። በሃይማኖት ጸንተን የምንቀበለው መከራ መስቀልም ሰማዕትነትን በተግባር መፈጸም ነውና መሳቀቅ የለብንም።   
Read 706 times