Saturday, 02 January 2021 00:00

የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን ልንጠብቅ፣ በዓላቱንም በንቃት ልናከብር ይገባል።

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አንድነት፣ ሰላም፣ እድገትና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እጅግ ብዙ አስተዋጽዖ ማድረጓን ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው። ሆኖም ባደረገችው አስተዋጽዖና በዋለችው ውለታ ልክ መከበርና መጠቀም ሲገባት በብዙ ጉዳዮች ገለል ተደርጋ፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ስትገፋ ማየቱ በተለይም ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት እየተለመደ መጥቷል። ይህ ሊሆን የቻለውም በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ በታየው መጠንን ያለፈ ትዕግሥትና ቸልተኝነት እንዲሁም በዋናነት የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየበረከቱ በመምጣታቸው ነው። የዐደባባይ በዓላትን በምሳሌነት ብንወስድ፡ በገቢ ረገድ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ተጠቃሚው መንግሥት ነው። ነገር ግን የተጠቃሚነቱን ያክል ለቤተ ክርስቲያን ሀብቶችና ለበዓሉ ድምቀት ቤተ ክርስቲያንን አግዞ ሲሠራ አይታይም። በዚህም ምክንያት ለብዙ ዐሥርት ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች የነበሩ የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች እኩይ ዓላማን ባነገቡ ሰዎች ተጽዕኖ ተነጥቀዋል፤ ምእመናን ተንገላተዋል። አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎችም የይዞታ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸውና በቀጣይ ጊዜያት ተመሳሳይ ፈተና የሚጠብቃቸው ናቸው። የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎችም ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው። ለአብነትም ለቤተ እምነት በሚሰጡ ቦታዎች ፍትሐዊነት ላይ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብባቸውና ብዙ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ ሊያስተውል ይገባል። ይህ ሲባል ግን ብዙዎቹ የይዞታ ችግሮች በመንግሥት ቸልተኝነት ብቻ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳልሆኑ በእኛ በኩልም ይህን መገንዘብ ይኖርብናል። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን አካላትም አለመቀናጀትና ዝርው አካሄድ የተነሣ የተፈጠሩ መሆናቸውንም ማስተዋል ተገቢ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ በየትኛው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር መመለስ እንደሚገባው ግልጽ አይደለም። የትኛው ኃላፊነት የየትኛው መምሪያ ድርሻ መሆኑን ለመግለጽም ያስቸግራል። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ጉዳይ ለማቀድም ሆነ የክንውን ዘገባ ለማቅረብ ስለማይቻል ባይሠራ እንኳን ተወቃሽ አካል እንዳይኖረው ያደርጋል። ስለሆነም ይህንን የአሠራር ክፍተት የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በተቻለ ፍጥነት ማስተካከል ይኖርበታል ብለን እናምናለን። እዚህ ላይ፡ የአንዳንድ አባቶች፣ ምእመናን፣ ወጣት አገልጋዮችና ማኅበራት እንቅስቃሴ ምስጋና የሚያሻው ነው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ‹ያገባኛል› በሚል መንፈስ ብዙ ርቀት ተጉዘው ጥቂቶቹን ይዞታዎችም ቢሆን አስመልሰዋል። ለወደፊቱም ቢሆን ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴና ኅብረት እጅግ አስፈላጊ ነው። በየአካባቢው ያሉ የቤተ ክርስቲያን የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ይዞታዎች ‹የእኛ ናቸው› ብሎ ዓመቱን ሙሉ ሊከታተላቸው የሚገባ አካል ሊመደብላቸው ያስፈልጋል። አንድ ጊዜ ብቅ ብሎ በዓላቱን ካከበሩ በኋላ ጉዳዩን ርግፍ አድርጎ በመተው እንደገና በዓመቱ ሲመጣ ተሰብስቦ መጯጯሁ ትርፉ ጩኸት ብቻ ነው። ሌሎች አካላትንም ‹ውሰዱልኝ› እንደ ማለት ይቆጠራል። ስለዚህ በዓሉን በአንድነት የሚያከብሩ ተጎራባች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቦታውን በአንድ መዋቅራዊ አሠራር  የሚያስከብሩበትና የሚያለሙበት መንገድ ሊቀየስ ይገባል። በአሁኑ ወቅት በክርስትና ሃይማኖታችን  በታላቅ ጉጉት ከሚጠበቁ ዐበይት በዓላት ዋዜማ ላይ እንገኛለን። እነዚህም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና ጥምቀት ናቸው። ሁለቱም በዓላት የየራሳቸው ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ የአከባበር ዘዬ ያላቸው ሲሆን፡ በምእመናንም ዘንድ በእጅጉ የሚናፈቁ ናቸው። በዓለ ልደትን ለማክበር እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ያለውን ወቅት ሁሉም አማኝ በጾም ማሳለፍ እንደሚገባው የታወቀ ነው። ከጾሙ ባለፈም ምእመናን የብርሃነ ልደቱን ደስታ ለመሳተፍ በተለያዩ መንገዶች ይዘጋጃሉ። ከእነዚህም አንዱ ነዳያንንና ዐቅመ ደካሞችን ለማስፈሰክ የሚደረግ ዝግጅት ነው። በተለይ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አስተባባሪነት በጌታችን ልደትና ትንሣኤ በዓላት እየተጠናከረ የመጣው ይህ መልካም ሥራ ዘንድሮም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለ ጥምቀትን ካለ ወጣቶች ተሳትፎ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ማሰብ አስቸጋሪ ሆኗል። በየሠፈሩ የሚታየው ይህ የወጣቶች መነቃቃት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው፤ ይህን መነቃቃት ያዩ ጥቂት አጥቢያዎችና ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ወጣቶችን ዐቅፎ በማስተማር በዓመት አንዴ ከመምጣት ዘወትር ወደ ማገልገል እንዲያድጉ አስችለዋል። ይህ መልካም ልምድ በሁሉም ቦታ ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው።  ከዚህ ባለፈም ከወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ አንጻር የበዓላቱን ፀጥታ ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሊኖሩ ይችላሉና ገና ካሁኑ ከመንግሥት አካላት ጋር በተለይም ከፖሊስ ጋር በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል። በመጨረሻም በእነዚህ የዐደባባይ በዓላት መንፈሳዊ ይዘት ላይ እጅግ ሊተኮር ይገባል። በዓላቱ ከመንፈሳዊ ይዘትነታቸው ባለፈ በተለይ በተተኪው ትውልድ እንደ አንድ ዓለማዊ ‹ፌስቲቫል› እየታዩ መምጣታቸው እጅግ አስጊ ነው። በዓላቱ በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ለሀገር ጠቃሚ ሆኖ ሳለ፡ ሚዲያዎች ሁሉ የበዓላቱን መንፈሳዊ እሴት በመዘንጋት ከቅርስነትና ከማኅበራዊ ፋይዳዎቻቸው አንጻር ብቻ መዘገባቸው እጅግ አሳሳቢና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነውና ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።
Read 705 times