ውድ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን የመስም ቅጽልና የመድበል ቅጽልን ምንነት ተምረናል። የቤት ሥራም መስጠታችን ይታወሳል። እናንተም እንደሠራችሁት ተስፋ እናደርጋለን።
ለማረጋገጥ በሚከተለው መንገድ መልሱን እናስቀምጣለን።
ተ.ቁ
ግስ
መስም ሳድስ ቅጽል
መስም ሣልስ ቅጽል
መድበል ቅጽል
፩
ከሠተ
መክሥት
ከሠት
፪
ተለወ
መትልው
ተለውት
፫
ተንበለ
መተንብል
ተንበልት
፬
ነበረ
መንብር
ነበርት
፭
ሜጠ
መመይጥ
መየጥ
፮
ሰፈነ
መስፍን
መስፈኒ
ሰፈንት
፯
ነገደ
መንግድ
ነገድ
ውድ አንባብያን መልሱን በዚህ መልክ ከሠራችሁት ጥሩ ሠርታችኋል። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ስለ ወገን ቅጽልና ስለ አኀዝ ቅጽል እንመለከታለን።ማስታወሻ አንዳንድ ግሶች መስም ሳድስ ቅጽል እንጅ መስም ሣልስ ቅጽል ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ የቀተለ መስም ሳድስ ቅጽሉ መቅትል መስም ሣልስ ቅጽሉ መቅተሊ ይሆናል። ጠበ የሚለው ግስ መስም ሳድስ ቅጽሉ መጥብብ ሲሆን መስም ሣልስ ቅጽሉ ደግሞ መጥበቢ ይሆናል። የጸንዐ ደግሞ መስም ሣልስ ቅጽሉ መጽንዒ ይሆናል። ስለዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ግሶች መስም ሣልስ ቅጽል ያልተጻፈላቸው በመጽሐፍ የማይገኝላቸው ስለሆነ ነው።
ወገን ቅጽል
ይህ የቅጽል ዓይነት ወገንነትን፣ ዝምድናን የሚያመለክት ሲሆን በሀገር ስም ላይ ለተባዕታይ ጾታ ዊ/ ይ እና ለአንስታይ ጾታ ደግሞ ዊት/ ይት በመጨመር ይመሠረታል። ይህን በተመለከተ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፸ ላይ “ወገን ቅጽል ማለት አባትነትን፣ ወገንነትን፣ ጎሳነትን የሚያሳይ ሲሆን የሀገርና የትውልድ ስሞች መድረሻ ፊደላቸውን ራብዕ እያደረገ ምዕላድ ፊደላት “ዊ”፣ ”ዊት”፣ “ይ” ፣ “ይት” ን በመጨመር የሚቀጸል ነው” በማለት ያስረዳሉ።
መምህር አስበ ድንግል ደግሞ ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፴፫ ላይ ጾታ ቅጽል በማለት ይጠሩትና ሲያብራሩት ግን “ጾታ ቅጽል ማለት ወገን ቅጽል ማለት ነው። በስም ላይ አርፎ ወገንነትን የሚገልጽ ነው በመድረሻው ላይ፡- ለነጠላ ወንድ “ዊ”፣ ለነጠላ ሴት “ዊት”፣ ለብዙ ወንድ “ውያን”፣ ለብዙ ሴት “ውያት” በቅጽልነት የሚገኝበት ነው። በማለት ጾታ ቅጽል ብለው የጠሩት ወገን ቅጽል ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የሁለቱም መምህራን ከስያሜ ያለፈ ልዩነት የለውም። በዚህም ወገን ቅጽል ማለት በስሞች ላይ “ዊ/ይ”፣ “ዊት/ ይት” የሚሉ ምዕላዶችን በመቀጠል ዝምድናን የሚያስረዳ የቅጽል ዓይነት ነው። የተሻለ ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ እንመልከተው።
ተ.ቁ
ስም
መስም ሳድስ ቅጽል
መስም ሣልስ ቅጽል
መድበል ቅጽል
አንስታይ ብዙ
፩
ሰማይ
ሰማያዊ
ሰማያዊት
ሰማያውያን
ሰማያውያት
፪
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያዊ
ኢትዮጵያዊት
ኢትዮጵያውያን
ኢትዮጵያውያት
፫
ድኅር
ደኃራዊ/ይ
ደኃራዊት/ይት
ደኃራውያን/ ይያን
ደኃራውያት/ይያት
፬
ምድር
ምድራዊ
ምድራዊት
ምድራውያን
ምድራውያት
፭
ግብፅ
ግብፃዊ
ግብፃዊት
ግብፃውያን
ግብፃውያት
አኀዝ ቅጽል
አኀዝ ቅጽል የሚባለው ቁጥር ሲሆን የነገሮችንና የስሞችን መጠን ወይም ብዛት ለመለካት የሚያገለግል ነው። ይህ ቅጽል ለነገር፣ ለሰው ስሞች ሲሆን እና ለዕለታት ሲሆን የተለያየ ቅርጽ አለው።
ለምሳሌ፡- ለሰው ወይም ለነገር ሲሆን አሐዱ፣ ክልኤቱ፣ ሠለስቱ፣ ዐርባዕቱ፣ ኀመስቱ፣ ስድስቱ፣ ሰብዓቱ፣ ሰመንቱ፣ ተስዓቱ፣ ዐሠርቱ
ዐሠርቱ ወአሐዱ፣ ዐሠርቱ ወክልኤቱ፣ ዐሠርቱ ወሠለስቱ፣ ዐሠርቱ ወዐርባዕቱ፣ ዐሠርቱ ወኀመስቱ፣… እያለ ይገለጻል።
ለዕለታት ሲሆን፡- አሚሩ፣ ሰኑዩ፣ ሠሉሱ፣ ረብዑ፣ ሐሙሱ፣ ሰዱሱ፣ ሰብዑኡ፣ ሰሙኑ፣ ተስዑ፣ ዐሥሩ
ዐሥሩ ወአሚሩ፣ ዐሥሩ ወሰኑዩ፣ ዐሥሩ፣ ወሠሉሱ፣ ዐሥሩ ወረብዑ፣ ዐሥሩ ወሐሙሱ፣ … እያለ ይቀጥላል።
በአጠቃላይ አኀዝ ቅጽል በነገሮች ስም፣ በሰዎች ስም፣ በዕለታት ላይ ወዘተ እየተጨመረ ብዛትን የሚያመለክት የቅጽል ዓይነት ነው።
ውድን አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ ከሆነ የቤት ሠራ እንስጣችሁ።
፩. ውድ አንባብያን በሚከተሉት ቃላት ወገን አመልካች ምዕላድን በመጨመር በነጠላና በብዙ፣ በሴትና በወንድ ወገን አመልካች ቃላትን መሥርቱ።
ተ.ቁ
ስም
መስም ሳድስ ቅጽል
መስም ሣልስ ቅጽል
መድበል ቅጽል
አንስታይ ብዙ
፩
ገሊላ
፪
ቅድም
፫
ሣልስ
፬
ሀገር
፭
ሐሳብ
፪. ውድ አንባብያን የሚከተሉትን ቁጥሮች ለዕለታት ሲሆን እንዴት መጠቀም እንደምንችል በፊደል በመጠቀም (አኀዝ ቅጽሎችን) መሥርቱ።
፲፮፣ ፲፯፣ ፲፰፣ ፲፱፣ ፳፣ ፳፩፣ ፳፪፣ ፳፫፣ ፳፬፣ ፳፭፣ ፳፮፣ ፳፯፣ ፳፰፣ ፳፱፣ ፴