Friday, 04 December 2020 00:00

ቅጽል

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
ውድ አንባብያን በባለፈው ዕትማችን ስለ ወገን አመልካች ቅጽልና ስለ አኃዝ ቅጽል ምንነት ተመልክተናል። የቤት ሥራ መስጠታችንም ይታወሳል፤ በአግባቡ እንደሠራችሁትም ተስፋ እናደርጋለን። ለማረጋገጥ ያህል እንደሚከተለው መልሱን አስቀምጠናል። ፩. በሚከተሉት ቃላት ምዕላድን  በመጨመር በነጠላና በብዙ፣ በሴትና በወንድ ወገን አመልካች ቃላትን (ቅጽሎችን) መሥርቱ። ተ.ቁ ስም ለነጠላ ወንድ ለነጠላ ሴት ለብዙ ወንድ ለብዙ ሴት ፩ ገሊላ ገሊላዊ ገሊላዊት ገሊላውያን ገሊላውያት ፪ ቅድም ቀዳማዊ/ ይ ቀዳማዊት/ይት ቀዳማውያን ቀዳማውያት ፫ ሣልስ ሣልሳዊ/ይ ሣልሳዊት/ይት ሣልሳውያን ሣልሳውያት ፬ ሀገር ሀገራዊ ሀገራዊት ሀገራውያን ሀገራውያት ፭ ሐሳብ ሐሳባዊ ሐሳባዊት ሐሳባውያን ሐሳባውያት ፪. ውድ አንባብያን የሚከተሉትን  ቁጥሮች ለዕለታት ሲሆን እንዴት መጠቀም እንደምንችል በፊደል በመጠቀም (አኀዝ ቅጽሎችን) መሥርቱ።  ፲፮፣ ፲፯፣ ፲፰፣ ፲፱፣ ፳፣ ፳፩፣ ፳፪፣ ፳፫፣ ፳፬፣ ፳፭፣ ፳፮፣ ፳፯፣ ፳፰፣ ፳፱፣ ፴ ፲፮= ዐሥሩ ወሰዱሱ፤ ፲፯- ዐሥሩ ወሰብዑ፤ ፲፰- ዐሥሩ ወሰሙኑ፤ ፲፱- ዐሥሩ ወተሥዑ፤ ፳- እስራ፤ ፳፩-እስራ ወአሚሩ፤ ፳፪-እስራ ወሰኑዩ፤ ፳፫-እስራ ወሠሉሱ፤ ፳፬-እስራ ወረብዑ፤  ፳፭-እስራ ወሐሙሱ፤ ፳፮-እስራ ወሰዱሱ፤ ፳፯-እስራ ወሰብዑ፤ ፳፰-እስራ ወሰሙኑ፤ ፳፱-እስራ ወተሥዑ፤ ፴-ሠላሳ። ውድ አንባብያን  የቤት ሥራውን በዚህ መልኩ ሠርታችሁት ከሆነ ትክክል ናችሁ። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ለዚህ ክፍል የመጨረሻ የሆነውን ግልጠ ዘ ቅጽልን እንመለከታለን። ግልጠ ዘ ቅጽል ፡- ይህ የቅጽል ዓይነት ግልጠ ዘ የተባለው “የ” ተብለው የሚፈቱትና፣ በግስ ላይ ተጨምረው ስምን እንዲገልጽ በግስ ላይ የሚቀጸሉት  ወይም ግስን ቅጽል እንዲሆን የሚያደርጉት አገባቦች በግልጥ ስለሚታዩ ነው። ግልጠ ዘ ቅጽል የሚባሉት ዘ፣ እንተ እና እለ ናቸው። ባለፉት ዕትሞቻችን የቅጽል ዓይነቶችን ስንመለከት  መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፳ ላይ የውስጠ ዘ ዓይነቶችን  “ግልጠ ዘ እና ውስጠ ዘ”  ብለው እንደሚከፍሏቸውና በውስጠ ዘ ቅጽል ምድብ ውስጥም  የሚዘረዘሩትን ተመልክተናል። ግልጠ ዘ ቅጽሎች በሚለው ምድባቸው ደግሞ የሚዘረዝሯቸውም  ከላይ የተገለጹትን  ማለትም  “ዘ” ን፣ “እንተ” ን እና “እለ” ን ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው (ገጽ ፹፱-፺፩) በመጀመሪያ ዘርና ነባር ብለው በሁለት ከከፈሏቸው በኋላ በእያንዳንዳቸው ደግሞ ሌሎች ንኡሳን ክፍሎች እንደሚዘረዝሩ ጠቁመናል። ነባር ቅጽሎች ብለው ከሚዘረዝሯቸው መካከል ግልጠ ዘ የሚባሉት ቅጽሎች ይገኛሉ። እነዚህ ግልጠ ዘ የሚባሉት “ዘ” ፣ “እንተ” እና “እለ” እንደሆኑ ይዘረዝራሉ። መምህር ኀይለ ኢየሱስ መንግሥት የልሳነ ግእዝ መማሪያ ብለው ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ግልጠ ዘን ግልጠ (የ) ብለው ይሰይሙትና ሲገልጹትም  “ዝንቱ ዘመደ ቅጽል እንዘ ይወድቅ መልዕልተ ግስ ይከሥትዎ ለስም። (ስሞችን የሚገልጽ ማለት ነው።) ብለው ያስረዱና በዝርዝር ሲያስቀምጧቸውም “ግልጠ (የ) ቅጽላት ዘይትበሀሉ “እንተ” ፣ “ዘ” ወ “እለ” ውእቶሙ።”  (ገጽ ፺፭) በማለት ይጠቅሷቸዋል። ከላይ መምህራኑ በገለጹት መሠረት ግልጠ ዘ የሚባሉት “እንተ”፣ “ዘ” እና “እለ” ናቸው። ግልጠ ዘ የተባሉበት ምክንያት አንድ ግስ ቅጽል እንዲሆን የሚያደርጉት እነዚህ አገባቦች ወይም ቃላት በአካል ግሱ ላይ ተጨምረው ስለሚታዩ ነው። በአገልግሎት ደረጃ የተወሰነ ልዩነት ስላላቸው ልዩነታቸውን አንድ በአንድ እንመለከታለን። “ዘ” ይህ ቅጽል ለአንድ ለብዙ ለሴት ለወንድ ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለአንድና ለብዙ፣ ለሴትና ለወንድ መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡- - ዘተንሥአ እሙታን አምላክ ውእቱ። - ዘነሥአት ዕፍረተ ብእሲት ተመይጠት መንገለ ቤታ። - ዘነበቡ ትንቢተ ነቢያት ውእቶሙ። - ዘይቀድሓ ማየ አንስት ወረዳ መንገለ ቀላይ። “እንተ”  ይህ ቅጽል ከቍጥር አንጻር ለአንድ  ብቻ ሲሆን ከጾታ አንጻር ግን ለሴትና ለወንድ ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለአንድ (ለነጠላ ቁጥር) ብቻ ሆኖ ለሴት ለወንድ መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡- - ዝ ውእቱ ሕፃን እንተ ያፈቅሮ አቡሁ። -ዛቲ ይእቲ መርዓት እንተ ታፈቅር ብእሴሃ። “እለ” ይህ ቅጽል ከቍጥር አንጻር ለብዙ  ብቻ ሲሆን ከጾታ አንጻር ግን ለሴቶችም ለወንዶችም ይቀጸላል። ወይም ይህ አገባብ የተጨመረበት ግስ ለብዙ ቁጥር ብቻ ሆኖ ለሴቶች ለወንዶች መቀጸል ይችላል። ምሳሌ፡- -ቡሩካን ውእቶሙ አበው እለ ሠርዑ ለነ ሥርዐተ። -አንስት እለ ነሥኣ መኃትዊሆን ተሰብሓ በፈጣሪሆን። ውድ አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። ከላይ የቀረበውን ትምህርት መሠረት አድርጋችሁ ግልጠ ዘ ብለን በዘረዘርናቸው ቅጽሎች በእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን ሥሩባቸው። “ዘ” “እንተ” “እለ”
Read 635 times